
አዲስ አበባ፡- በውጭና በውስጥ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎችን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ጥምረት እና የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማህበር አስታወቁ፡፡
ማህበራቱ ትናንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበራት ጥምረት ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ሶስና ወጋየሁ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ችግሮች ለመቅረፍ ዳያስፖራዎች ከመንግሥት ጎን በመሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ናቸው፡፡
እንደ ወይዘሮ ሶስና ገለጻ፤ ኢትዮጵያን እንደሌሎች የፈረሱ አገራት ለማድረግ የሚደረገውን የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፍላጎት እንዳይሳካ ለማድረግ ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባል።
ዳያስፖራው ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ሀገሩን መጠበቅና ማስከበር አለበት ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ለማድረግና የውጭ ጫናዎችን ለመመከት ዳያስፖራዎች በተቀናጀ መልኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ጸሐፊ አቶ ሙሳ ሼኮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት እንድትገባና ግጭቱ እንዲራዘም የሚሹ ኃይሎች አሉ፤ አሁን የሚስተዋለው ግጭትና አለመረጋጋትም አላማው የህዳሴው ግድብን የማፍረስ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡
የዳያስፖራው ማህበረሰብ በተናጠል ከመንቀሳቀስ ወጥቶ በጋራ በመሆን በልማቱና በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ሥራ የኢትዮጵያን ገጽታ በትክክል እያስተዋወቀ ይገኛል ያሉት አቶ ሙሳ፤ በተለይ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ፤ እነዚህ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋና ከኢትዮጵያ አጎራባች ሀገሮች ጋር ሰላም እንዳይኖር የእለት ተዕለት ሥራቸው አድርገው እየሰሩ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ምንም አይነት የገንዘብ እርዳታ እንዳይገኝ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ግጭት የተነሳ ሀገሮች ተዳክመዋል፣ ፈርሰዋል፣ ወደ ኋላ ቀርተዋል ያሉት አቶ ሙሳ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰላም እንዲሰፍን መስራት ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጫናዎችን በማሳደር ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟ እንዲናጋ የሚሰሩ አካላትን መፋለም እንደሚገባም አቶ ሙሳ ጠቁመዋል፡፡
ዳያስፖራዎች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየቀረቡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ስለ ህዳሴ ግድቡ ሀቁን በማረጋገጥ ማስረዳት እንዳለባቸው የተናገሩት ጸሐፊው፤ ሞጋች በመሆን ከግብጽና ከአጋሮቿ የሚመጣውን ፕሮፓጋንዳ ትክክል እንዳልሆነ በማስረዳት የጀመሩትን ተግባር ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሳ ገለጻ፤ ግብጾች ከ200 በላይ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በርካታ ድረ ገጽና የህትመት ሚዲያዎችን ተጠቅመው የዓለምን ማህበረሰብ እያሳሳቱ ይገኛሉ፣ በኢትዮጵያ ጫናዎች እንዲበረቱና የውስጥ አንድነት እንዲሸረሸርም እየሰሩ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎችም ይህንን በመገንዘብ በዚህ ልክ ሊሰሩ ይገባል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም