
አዲስ አበባ፡- የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ሴራ ለማስቆም እና የቡድኑን አባላት ለፍርድ ለማቅረብ የትግራይ ህዝብ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የደቡብ ምስራቅ ዞን የሀገረ ሰላም ከተማ ሚሊሻ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ገ/መስቀል ወ/ሚካኤል አስታወቁ ።
ኮማንደር ገ/መስቀል ወ/ሚካኤል በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ ኢትዮጵያ እንድትበታተን ያለአንዳች እረፍት ሲተጋ የኖረው አሸባሪው ህወሓት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና የቡድኑን አባላትም ለፍርድ ለማቅረብ መላው የትግራይ ህዝብ ከፌዴራል መንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ዛሬም ሀገሩን የሚወድ፤ ለሀገሩ አንድነትም ዋጋ እየከፈለ ያለ ህዝብ ነው ያሉት ኮማንደር ገ/መስቀል ፣ አሸባሪው ህወሓት ከምዕራባውያን ጋር በመመሳጠር በቀመረው የፖለቲካ ቅስቀሳና ከፋፋይ ፖለቲካ ህዝብን ላልተገባ የፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀመበት ይገኛል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ እጉያው ውስጥ ሆኖ ‹‹ጀግና ነህ›› እያለ እያታለለና በእሱ ደም እየነገደ፤ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሳ ኃይል መሆኑን ያስታወቁት ኮማንደር ገ/መስቀል፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ማንነት ጠንቅቆ አውቋል፤ የትግራይ ህዝብ የቡድኑን እውነተኛ ባህሪ አውቆ ሊነቃ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ህዝብ ለሞተ ሰው የሚቆረቆር ነበር ያሉት ኮማንደር ገ/መስቀል፤ ታዲያ አሁን እንዴት ነው አሸባሪው ህወሓት ብልፅግናን ደግፈሃል እያለ የገዛ ልጆቹን ሲገድል እያየ ዝም የሚለው ሲሉም ጠይቀዋል ፡፡
እንደ ኮማንደር ገ/መስቀል ገለፃ፤ አሸባሪው ህወሓት አማራን ዋነኛ ጠላቱ አድርጎ የትግራይ ህዝብ እንዲያስብ ተፅዕኖ ሲፈጥርበትና ሲያስፈራራው ነው የኖረው፡፡ መሰሪ ስለሆነም ህዝቡንም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሳይቀር በማጭበርበርና በፖለቲካ በማፈን የሱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል አድርጓል፡፡
“ከዚህ ቀደም ለህዝብ እርዳታ ሲላክ በቀጥታ ለጁንታው ይሄድ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ህዝቡን ውስጥ ውስጡን በስውር ሲያደራጅ ነው የቆየው፡፡ በመሰረቱ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የሚተባበሩ ሰዎች የነሱ ታናሽ ወንድሞች እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች መረጃ በመስጠት ፣ እህል በማቀበል ጁንታውን ነበር ሲተባበሩ የነበሩት” ብለዋል ፡፡
የጊዜአዊ አስተዳደሩ ውስጥም ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ሲሰሩ የነበሩ አካላት አሉ ያሉት ኮማንደር ገ/መስቀል፤ በዚህ የተነሳ የጊዜያዊ አስተዳደር አካል በነበሩ ሰዎች የተገደሉ የጊዜያዊ አስተዳደር ሰራተኞች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ውስጡን በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡
እንደ ኮንማደር ገ/መስቀል ገለጻ፤ ጁንታው ሀገሪቱ እድሜዋን ሙሉ የማትወጣው እዳ ነው ጭኖባት የሄደው፡፡ በእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ለምዕራባውያን ሀገር ሽጧል፡፡ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመደራደር የዘመናት ቁጭታችን ውጤት የሆነውን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለመሸጥ ተስማምቶ የነበረ ቡድን ነው፡፡
በመላው ዓለም ያሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማተራመስ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ በአንድ ልብ በመሆን መቃወም እና ለሀገራቸው መታገል እንደሚገባቸውም ኮማንደር ገ/መስቀል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም