
አዲስ አበባ ፦ ከሳማንታ ፓወር የነበረን ውይይት ግራ የሚያጋቡ ወይም የሚያወዛግቡ ጉዳዮችን ለማጥራት የሚያስችል እድል የፈጠረ ነው ብለን እናምናለን ሲሉ የሠላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ ።
ወ/ሮ ሙፈሪያት ከትናንት በስቲያ ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤይድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር የነበራቸውን ውይይት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት ፣ ሃላፊዋ በአካል መገኘታቸው ጥቅም እንዳለው ተገንዝበናል። ያላወቋቸው፤ ያልነበሯቸውን መረጃዎች ለመስጠት አስችሎናል። ግራ የሚያጋቡ ወይም የሚያወዛግቡ ጉዳዮችን ለማጥራት የሚያስችል እድልም የፈጠረ ውይይት ነበር ብለን እናምናለን።
በውይይታቸው ከእርዳታ መጓተት ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን ፣ ሂደቱን ማሳለጥ የሚያስፈልግበት አግባብ መኖሩን ፣ የጀመርናቸው የእርዳታና የሰብአዊ ስራዎች በሁለንተናዊ መልኩ አጠናክሮ የመቀጠል አስፈላጊነታቸውን መነሳታቸውን አመልክተዋል።
በመንግስት በኩል እንደ መንግስት ያለውን ዝግጁነት፣ የትግራይ ህዝብ ህዝባችን ነው ፤ መንግስት የትግራይ ህዝብና አሸባሪውን ህውሓት መቼም ቢሆን አንድ አድርጎ ተመልክቶ እንደማያውቅ ፤መንግስት ፖለቲካ እና ሰብአዊነትን መለየት የሚችል እንደሆነ ፤ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ተዋንያኑን ለመያዝ የተደረጉ ጥረቶች ዙሪያም ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ለአሜሪካ አስፈላጊ አጋር ሀገር ነች የሚለው መልዕክት የተንጸባረቀበት ውይይት እንደነበር ያስታወቁት ወ/ሮ ሙፈሪያት ፣ ሰብአዊነትን ማዕከል ያደረገ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን በተመለከተ እሱን ተከትሎ የተሰሩ ስራዎች ፣ የእርዳታ አቅርቦቶችን በአየር ትራንስፖርት እስከ ማቅረብ የተኬደበትን ርቀት እና በተቀመጡ የአሰራር ሥርዓቶች ምን እንደሚመስሉ ግንዛቤ ለማስጨበት እንደተሞከረ አስታውቀዋል።
በቅርቡ የእርዳታ አቅርቦት ይዘው የቆሙት መኪኖች አሸባሪው ህውሓት የአፋር ህዝብ ላይ በወሰደው ማጥቃት ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ፤ ቡድኑ ሥርዓት መያዝ ሲችል በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የትግራይን ህዝብ ለመታደግ የሚያስችል ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት እንዳለ እንደተነገራቸው አመልክተዋል።
በውይይታቸው በትግራይ ክልል እተካሄዱ ያሉ የሰብአዊ እርዳታዎችን በተጨማሪ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እየተጓዘች ያለችበትን የለውጥ ሂደት ፣ ባህሪ ፣ የተገኙ ውጤቶች እና ያጋጠሙ ውጤቶችን በተመለከቱ ገለጻ አድርገንላቸዋል ብለዋል።
እሳቸውም የኢትዮጵያን ለውጥ በቅርበት እንደሚከታተሉት፣ ሲያደንቁትም እንደቆዩ፣ በርካታ ውጤቶች የተገኙ መሆናቸውን፣ ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ በኢኮኖሚው በሰብአዊ መብት አያያዝ እነዚህ ውጤቶች በጣም አበረታች ተምሳሌት የሆኑ ውጤቶች መሆናቸውን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መልካም ምኞታቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለአሜሪካ መንግስት በቀጠናው ጉዳይ ላይ ያላትን አስፈላጊነትና ተፈላጊነት ከግምት እንደሚያስገቡ አሁን ያጋጠመን ተግዳሮት በተለይም የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ መንግስት ለምን ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ በቂ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም አስታውቀዋል።
ጦርነቱን ፈልገነው የመጣ ሳይሆን በአሸባሪው ቡድን ህውሓት ውሳኔና ምርጫ የመጣ ፤የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተዳፈረ ተግባር ከመሆኑ አኳያ እነሱን እንደዚህ አይነት ክስተት ቢያጋጥማቸው ምን እንደሚያደርጉ ጥያቄም አንስተንላቸው ነበር። ያደረግነው የህልውና ፣ የሀገርን ሉአላዊነት የማስጠበቅ ጉዳይ ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሆነ በዚህ መልኩ አስረድተናል ብለዋል።
ችግሩ ተገደን የገባንበት ከመሆኑ አንጻር የሰብአዊ እርዳታና አገልግሎቱ በተሳለጠ ሁኔታ እንዴት መሄድ እንዳለበት ፤ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት ስንሰራ እንደቆየን በቅርቡም ያደረግነው ሰብአዊነትን ማዕከል ያደረገ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ዓላማው ምን እንደሆነ ፤ይሄንኑ ተከትሎ የተፈጠሩ አደረጃጀቶች፣አሰራሮችን ለመግለጽ ሞክረናል። በእነርሱ በኩል ባይሆኑ እና ቢሆኑ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው መወያየታቸውን ገልጸዋል።
የእርዳታ አቅርቦቶችን ለማድረስ በትግራይም በኩል ያሉ የየብስ አማራጮች አስተማማኝ መሆናቸው ችግሩ የአሸባሪ የህውሓት ጠብ አጫሪነት እና ህብረተሰቡን የማጥቃት ፍላጎት መሆኑን አሳውቀናቸዋል ፣ እነሱም እውነታው በደንብ የገባቸው ይመስለኛል ብለዋል።
እርዳታው ሁለንተናዊ መሆን አለበት የሚለው ላይም ሃሳብ ተለዋውጠናል። አማራ ክልል ከ100 ሺ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉን አፋር ላይም በተመሳሳይ ብዙ ሺህ ዜጎች አሉን የእርዳታ አቅርቦቱ እነሱንም ታሳቢ እንዲያደርግ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል።
ደጋግመን የነገርናቸውም እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ከተፈለገ ይሄንን ባህሪውን እንዲያቆም በግልጽ መንገር። አሽሞንሙኖ የሚመለከታቸው አካላት ማለት ሳይሆን በስም ጠርቶ የመንገር አስፈላጊነት ወሳኝ እንደሆነ ማስገንዘባቸውን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም