
አዲስ አበባ፡- የተጋረጡ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በመቀልበስ በጽኑ አለት ላይ የቆመውን አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊነታችንን ማስቀጠል እንደሚገባ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ አስታወቁ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትናንት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ባስመረቀበት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳስታወቁት፤ የተጋረጡ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በመቀልበስ በጽኑ አለት ላይ የቆመውን አንድነታችንንና ኢትዮጵያዊነታችንን ማስቀጠል ይገባል። ከስኬታችንና ከህልውናችን በስተጀርባ ያለው እውነት ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ህልውናችንን የሚፈታተኑ ችግሮችን በአንድነት መቀልበስ ያስፈልጋል።
ታሪክ ብቻ ስንተርክ ቆይተን የበይ ተመልካች ሆነናል፣ ሌሎች ሀገሮች ግን ታሪካቸውን ለውጠዋል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤ በሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት ስኬት ማግስት ብርሃን አመንጭተን የፍሬው ተቋዳሽ ለመሆን በር ላይ ቆመናል ብለዋል።
በውጭና በውስጥ ጠላቶች የተሸረበውን ሴራ ያመከነው ህዝባችን በእልህ፣ በቁጭት፣ በጽናትና በአንድነት መቆም በመቻሉ ነው፣ በዲፕሎማሲ፣ በግድቡ ግንባታ፣ በሚዲያ ጦርነትና በሀብት ማሰባሰብ የተገኘ ፍሬ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን በአንድነት እንዳንቆም ያሴሩት ሴራ በሀገሩ በማይደራደርው ኢትዮጵያዊ መክኗል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ ፣ በዓድዋ የታየው ኢትዮጵያዊ ጽናት በህዳሴው ግድብም ተደግሟል። ይህም ወዳጆቻችንን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችንን ጭምር አስደምሟል ብለዋል።
ስድተኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ሲጠናቀቅ በአንድ አይቆሙም፣ እንዲያውም ይፈራርሳሉ ብለው ከውስጥና ከውጭ የሚገኙ ጠላቶች አሟርተው ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከሟርተኞች በተቃራኒው ሆኖ በነቂስ ወጥቶ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ይበጀኛል ያለውን መሪ መርጧል። በዚህም ህዝቡ በድጋሜ ጠላቶቻችንን ማሳፈሩን አስታውቀዋል።

ተመራቂዎች በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ሆነው ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ ፤ ህዝባችን ላሉበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ በመፈለግ ልትሠሩ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይንም፤ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳስመረቀ ገልጸዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ ውስጥ አራት ሺህ 153 ወንዶች፣ ሁለት ሺህ 421 ሴቶች ሲሆኑ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ እና በ3ኛ ዲግሪ እንዲሁም በስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች ስልጠናቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች አስቸጋሪ የነበረውን ጊዜ ተቋቁመው ለመመረቅ የበቁ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ተመራቂ ተማሪዎች ቀጣይ የሚገጥማቸውን ችግር በመቋቋም ለድል እንደሚሠሩ ያሳየ ነው ብለዋል። የዚህ ዓመት ተመራቂዎች በርካታ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ችግሮችንና ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዚህ የበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ሥራዎችን በትጋት እየሠራ ነው ያሉት ዶክተር አጸደወይን፤ ዩኒቨርሲቲው በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የህዳሴውን ግድብ በማስመልከት ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከሱዳን የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዕለቱም ዩኒቨርሲቲው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም