
ጎንደር፡- የድንበርና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለኢትጵያና ሱዳን ህዝቦች የትብብርና አብሮ የመልማት እንጂ የግጭት መነሻ መሆን እንደሌለበት የሱዳን ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ፕሮፌሰር አብዱ ኡስማን አመለከቱ።
ፕሮፌሰር አብዱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የዳበረ የአንድነት መንፈስ ያላቸው፤ በሁለት ሀገር የሚኖሩ አንድ ህዝቦች ናቸው። አሁን የሚታየው ውዝግብ የሁለቱን ሀገሮች አንድነት የማይመጥን ነው።
የድንበርና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለሁለቱ ህዝቦች የትብብርና አብሮ የመልማት እንጂ የግጭት መነሻ መሆን እንደሌለበት የጠቆሙት ፕሮፌሰር አብዱ፤ በሀገራቱ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ችግሮችን በውይይት ለመፍታ ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ኮሚቴ በማዋቀር እንደሚሠሩ ያመለከቱት ፕሮፌሰር አብዱ ፣ በውዝግብና በግጭት የሚፈታ ችግር እንደሌለም አመልክተዋል።
የጐንደር ዩኒቨርሲቲ የሱዳን ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሮፌሰር አብዱ ፤ ይህ ልምድ በቀጣይ በሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚተገበር ጠቁመዋል።
‹‹ጐንደር የመጣንበት ዋና ዓላማ የተማሪዎችን ምረቃ ለመታደምና ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጋር ለመምከር ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማጠናከር የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው ብለዋል። በኢትዮጵያና በሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተጀመረው ግንኙነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሌላኛው የልዑካን ቡድኑ አባል የዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ኡመር ኡላማን በበኩላቸው ፤ የኢትዮጵያና የሱዳን ህዝቦች ተጋብተውና ተዋልደው በጠበቀ ትስስር የሚኖሩ ህዝቦች እንደመሆናቸው ጥቃቅን ችግሮቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሁለንተናዊ ለውጥ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች በሱዳን፤ የሱዳን ሙዚቀኞች በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃዎቻቸውን በማቅረብ አንድነታቸውን ሲያጠናክሩ እንደቆዩ ያስታወሱት ዶክተር ኡመር ፤ ኢትዮጵያ ስንመጣ ወደ ሁለተኛ ቤታችን እንደመጣን እንጂ ወደ ጐረቤት ሀገር በእንግድነት የመጣን ዓይነት ስሜት አይሰማንም ብለዋል።
በህዝቡ ውስጥ የሰረጸው ስሜት የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የሚጐዳ ሳይሆን የሚያስቀጥል ሊሆን ይገባል ያሉት ዶክተር ኡመር ፣የሀገራቱን ግንኙነት በተሻለ መልክ ለማስቀጠል ከሁለቱም ሀገራት ምሁራን ብዙ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ትስስር ለማጠናከር ምሁራን፤ በባህል፣ በታሪክ፣ በግብርናና በመሰል ጉዳዮች ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ ያስፈልጋል፣ የሱዳን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠሩ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዝብ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በኪነጥበብ ረጅም ዕድሜ የዘለቀ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው። በቀጣይም አርቲስቶችና ምሁራን ልዩነቶችን የሚፈታና አንድነታቸውን የሚያጠናክር ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
ሁለቱ ህዝቦች የማይነጣጠሉ በመሆናቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት የሚጐዳው ህዝቦቹን በመሆኑ የሁለቱ ሀገራት ምሁራን በፖለቲከኞች መካከል ያለውን አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች ከጐንደርና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት አለው። ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት፣ በምርምር፣ በግብርና እና መሰል ጉዳዮች በጋራ እየሠሩ ነው ፤ በተለይም በድንበርና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባት በውይይትና በድርድር ለመፍታት እንዲቻል እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በቀጣይም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመፍጠር አንድ የሆኑ ህዝቦች አንድ ሆነው እንዲኖሩ ለማስቻል እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም