
የአገሪቱ ትላልቅ ሁነቶች ማስተናገጃው መስቀል አደባባይ ንጋቱን በጀመረው ጭጋጋማ አየር ተሸፍኗል። እዚያ ቦታ ጥቁር ክናቴራ የለበሱ፣ ፊታቸው ላይ ኀዘን ያጠላ፣ ዓይኖቻቸው እምባ ያቀረሩ ሰዎች ጥቁር ካባ ደርበው ተሰባስበዋል፡፡ በግፍ ህይወታቸውን የተነጠቁ ለአገርና ለህዝብ ብለው ውድ ህይወታቸውን የከፈሉ ሰዎች ለማሰብ አንድ ላይ ቆመዋል፡፡
አካባቢው የሞላው የኀዘን ድባብ ተሰብሳቢው ላይ ተጋብቷል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በግፈኞች የተነጠቁ ወዳጆቻቸውን በሴረኞች በአሰቃቂ ሁኔታ ያጡ ተበዳዮች ስለተገደሉት በቁጭት ያወራሉ፡፡ የሞቱት ሰዎች በጎ ዓላማና የገዳዮቹን ዕኩይ ተግባር ኀዘን ባጠላበት ድምፀት ያስረዳሉ፡፡ የሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች ስለተገደሉት ንፁሐን የምስክርነት ቃል ይሰጣሉ፡፡ ሀምሌ 24/2013 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በአሸባሪው ህወሓት የተገደሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት በሻማ ማብራት ለማሰብ ተሰባስበዋል፡፡
በግፋ የተገደሉት አባላቱ ህዝቡን በማስተባብር ዕርዳታ እንዲደርስና መሰረተ ልማት መልሶ እንዲገነባ በማድረግ፣ የመንግሥት አገልግሎት መልሶ እንዲጀመርና ህዝባቸውን በማረጋጋት ወደሰላሙ እንዲመለስ በማድረጋቸው በህወሓት በግፍ መገደላቸውን የሻማ ማብራት የሥነ ሥርዓቱ አስተባባሪ የነበሩት ጋዜጠኛ ዓርዓያ ተስፋማርያም ጠቁሟል፡፡ እነዚህን ንፁሐን የገደሉና ያስገደለው አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት መሆኑን ሁሉም ማህበረሰብ ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል፤ ያሉት ጋዜጠኛ ዓርአያ ተስፋማርያም መንግሥትም በዚህ ሽብርተኛ ቡድን ላይ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብረሃም በላይ በበኩላቸው ህዝብና አገርን ለማገልገል ሲሉ በግፈኛው ህወሓት የተገደሉት እነዚህ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ለአገራቸው ሲሉ የተሰው ጀግኖች መሆናቸውን ገልጸዋል። በአመራሮቹ ላይ የተፈፀመው ግድያ አሸባሪው ህወሓት ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ፈፅሞ እንደማያቆምና ሁሉንም ማህበረሰብ በቁጭት እንደሚያነሳሳ በዚህ የተጀመሩ ጥረቶች ሁሉ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
የትዴፖ ሊቀመንበርና የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ማስተባባሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አረጋዊ በርኼ በስነ- ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የእነዚህ ህዝብን ለማገልገል የቆረጡ ሰላማዊ ሰዎች ግደያ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሽብር ቡድን ህዝብ ላይ ስቃይና ሰቆቃ ለማብዛት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ ህዝብ በአንድነት ቆሞ ሊታገለውና ከእኩይ ተግባሩ ሊያስቆመው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የትዴፓ ሥራ አስፈፃሚ አባልና ዋና ፀሐፊ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የውሃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ጊደና መድህን በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት የአገር ነቀርሳ በመሆኑ ተመንግሎ መጣል ይኖርበታል፡፡ አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን አሁን እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ እየገለጸ ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው ፣ የትግራይ ህዝብ አሸባሪው ህዋሓትን ሊታገል ይገባል ብለዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑን የገለጹት አቶ ጊደና፣ ህወሓት የተሰኘው የጥፋት ቡድን ህዝቡን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመነጠል የሚያደርገውን እኩይ ተግባር ማስቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል በህወሓት አማካኝነት በተከሰተው ቀውስ ምክንያት ህዝብ እንዳይጎዳና መሰረታዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻልና ክልሉ የገጠመውን ፈተና ለማርገብ እንዲያስችሉ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በኃላፊነት ተመድበው ሲሠሩ የነበሩና የህዝቡን ባህልና ሃይማኖት በተፃረረ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የስነ ስርዓቱ አስተባባሪ ጋዜጠኛ ዓርዓያ ተስፋማርያም ገልጸዋል፡፡
በአሸባሪው ህወሓት የተገደሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላትን የሚዘክር የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት በመስቀል አደባባይ በተካሄደበት ወቅት የስነ ስርዓቱ አስተባባሪ የሆኑት ጋዜጠኛ ተስፋ ማርያም እንደገለጸው በአሻባሪው ህወሓት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የተገደሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላትን ለመዘከር ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ሠርታችኋል፤ ተባብራችኋል በሚል በሀገረ ሰላም የተገደለችውን ነፍሰጡር አመራር ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎችን በአደባባይ በግፍ መግደሉንም በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጹዋል። በዚህ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ላይ የጊዜያዊ አስተዳድሩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አብርሃን ጨምሮ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የተለያዩ ፓርቲ አመራሮች እና የትግራይ ተወላጆች ተገኝተዋል፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም