
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባለት እና የተለያዩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራዎች) ባደረጉት የተቀናጀ ንቁ ተሳትፎና ዘመቻ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ተመስርታ በምክር ቤቷ በማቅረብ ልታስወስነው የነበረውን የ”ኤችአር 445” ረቂቅ ማዘግየቷ ታውቋል።
የኢትዮጵያዊያን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት እንዳስታወቁት ፣ በተቀናጀ መልኩ ከአሜሪካ የኮንግረስ አባልዋ ካረን ባስ ጋር ባደረጉት ውይይት እውነታውን ማስረዳት ችለዋል። በዚህም የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች ኢትዮጵያን በውሸት በማጠልሸት ተጨማሪ ጫና ለማሳደር የሄዱበትን እኩይ ተግባር አክሽፈዋል።
የአሸባሪው ድርጅት አባላት የህወሓት ታጣቂዎችና ካድሬዎች በዜጎች ላይ እየፈጸሟቸው ያሉ አስነዋሪ ድርጊቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈጸማቸው በማስመሰል ለአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ሲያቀርቡ መቆየቱን አመልክተው፤ በዚህም ምክንያት ለአሜሪካ ኮንግረንስ ሊቀርብ የነበረውና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው ኤችአር 445 (HR 445) የተሰኘው ሰነድ ከመጽደቁ በፊት እውነታውን ኢትዮጵያ ተገኝተው ለማጣራት የኮንግረስ አባልዋ ካረን ባስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።
በአሸባሪው ህወሓት እና በርዝራዦቹ እየተፈጸሙ የሚገኙ ወንጀሎችን በተለይም ሕፃናትን ለውትድርና እየተጠቀሙ መሆናቸውን፣ ግድያና ዝርፊያዎችን በስፋት እየፈጸሙ ስለመሆናቸውና መጠነ ሰፊ ግፍ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የአሜሪካ መንግሥት ይህን ድርጊት ማውገዝ ቀርቶ አንዲት ነገር ማንሳት አለመቻሉ ለምንድን ነው ሲሉም የኮንግረንስ አባሏን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጠይቀዋል።
የአሸባሪው ቡድን አባላት በንጹሐን የአማራ ተወላጆች እና በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በየአካባቢው የተፈጸሙ ግልጽ የሆኑ የንጹሐን ግድያዎች እና ተያያዥ ችግሮችን አሜሪካ ለምን አላወገዘችም? ሲሉም ጠይቀዋቸዋል።
ከዚህ አልፎ አሸባሪው ቡድን በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ተግባር ለምን በቸልተኝነት ይታያል? መንግሥት ሕግ ለማስከበር የወሰዳቸው ተገቢ የሆኑ ዕርምጃዎች ስለምን እውቅና ተነፈጋቸው? የፌዴራል መንግሥት የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፎችን ለማድረስ ያደረጋቸው ከፍተኛ ጥረቶች አሜሪካ ለምን በአዎንታዊ መመልከት ተሳናት? የሚሉ ጉዳዮችንም የፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት ለካረን ባስ አንስተው ጠይቀዋቸዋል።
ካረን ባስም ይህንን ግልጽ የሆነ ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት እውነታውን ለመረዳት የፊታችን መስከረም ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ እስከዚያው ድረስም የተባለውን የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ እንደማያቀርቡት አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም