የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በይቀበሉ ይሸለሙ በሚለው መርሀ ግብሩ ከሁለት ቢልዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን አስታወቀ።
የባንኩ የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሪክተር አቶ በልሁ ታከለ ዛሬ በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በወጣው የባንኩ የእጣ ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ በማበረታቻ ፕሮግራሞች በመታገዝ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት በውጭ ሃዋላ አማካኝነት ከተለያዩ አገራት ከሚኖሩ ወገኖች ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰብ ችሏል።
15ኛው ዙር የባንኩ የይቀበሉ ይሸለሙ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ ፕሮግራም በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አደራሽ እጣው የወጣ ሲሆን፤ ለእድለኞቹም ዘመናዊ አውቶ ሞቢል፣ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ፣ 16 ላፕቶፐ ኮምፒውተሮች፣ 64 ስማርት ሞባይል ቀፎዎችን ለሽልማት አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ እየተነቀሳቀሰ መሆኑንም የባንኩ የህዝብ ግኑኙነት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሌን ሃይሉ ገልፀዋል።
ባንኩ በሃገራዊ ልማት ስራዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ በመጠናከር በተለይ በሀብት ማሰባሰብ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ነው የህዝብ ግኑኙነት ስራ አስኪያጅዋ የጠቀሱት።
የይቀበሉ ይሸለሙ መርሀ ግብር ማዘጋጀቱ በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እንደሚያግዝና ህብረተሰቡ ህጋዊ ያልሆነ መንገድ ሂዶ እንዳይዘረዝር እንደሚጠቅም ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል።
ማዕረግ ገ/እግዚአብሔር