አዲስ አበባ፡- የታክስ ሥርዓት ማሻሻያውን በታሰበው ልክ ውጤታማ ለማድረግ ማሻሻያውን በሙያ የሚደግፍ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተከፈተ፡፡
“የግብር ፍትሃዊነት ትብብር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት” በሚል ስያሜ ዋና ተጠሪነቱን ለገቢዎች ሚኒስቴር ሆኖ በትናንትናው ዕለት በይፋ የተከፈተው ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በዘርፉ የተጀመረውን ማሻሻያ ውጤታማ ለማድረግና በግብር ስርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አቅም ይፈጥራል ተብሏል፡፡
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ተገዢነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ፣ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ወደ ግብር ሥርዓቱ ያልገቡ የንግዱ ተሳታፊ አካላትን ወደ ግብር ስርዓቱ ለማስገባት ዕገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“አገሪቱ ማግኘት ከሚገባት ከሠላሳ እስከ አርባ በመቶ የሚሆነውን ገቢ ታጣለች” ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ለገቢው መታጣት ዋነኛው ምክንያት በህቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ ከታክስና ቀረጥ ክፍያ ጋር የማይተዋወቁ ወይም መክፈል በሚገባቸው መጠን የማይከፍሉ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ከዚህ ቀደም በግብር ከፋዩና በግብር ሰብሳቢው መካከል የነበረውን አለመተማመን ለማስቀረትና የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን ፍትሃዊ ለማድረግ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ የንግዱ ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትር ዲኤታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ገብሬ ዘብሬ በበኩላቸው፤ ለፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ መቋቋም ዋነኛው ምክንያት በግብር ሥርዓቱ ውስጥ በሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሳቢያ በሀገሪቱ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር የሚመጣጠን ግብር እየተሰበሰበ አለመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ከሃገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ በግብር ሥርኣቱ ውስጥ ያሉትንም ችግሮች ለመቅረፍና ሃገሪቱ የምትፈልገውን ሁለንተናዊ ለውጥ ዕውን ለማድረግ ከግብር የሚገኘው ገቢ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ አስፈላጊውን ማሻሻያ ለማድረግ ተወስኗል፡፡ ከዚህ አኳያ ማሻሻያው በታሰበው ልክና በሚፈለገው መጠን ውጤታማ እንዲሆን ሥራውን በሙያ ለመደገፍ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡ ይህም ማሻሻያው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ግብዓት በተደራጀና በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብና በግብር ስርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አቅም ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በመሆኑም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት በትብብር የሚሰራ ይሆናል፡፡ ለዚህም ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተውጣጡ ከሰባ አምስት በላይ ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን በአባልነት እንዲሁም አስራ ሁለት አባላት ያሉት የገቢዎች ሚኒስቴር የአመራር ኮሚቴን በአመራር ሰጭነት አቅፏል፡፡ ከዚህም በአሻገር ከሁለት መቶ በላይ የሆኑ ከአስሩም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተመልምለው ስልጠና ያገኙ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳካት ከጽህፈት ቤቱ ጎን ተሰልፈዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ለአንድ ዓመት ያህል በአዲስ አበባ ከተማ በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ውጤታማነቱ እየታየ በቀጣይ በሌሎች ክልሎች ላይም ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ይበል ካሳ