አዲስ አበባ:- በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽነሩ አቶ መኮንን ሌንጂሳ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ስራው በተለይ በየደረጃው በተዋቀረ ኮሚቴ አመካኝነት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በሁለት ወር ውስጥም ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል።
ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረትና ሰፊ ሥራ ተሰርቷል ያሉት ኮሚሽነር መኮንን ይህም በህዝብ፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ እየተከናወነ መሆኑን፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በአይነት እርዳታ በማቅረብ በኩል ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቦ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ዞኖችና ወረዳዎች እንደየተግባራቸው በጀት ተልኮላቸው ስራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ቤት መስራት፣ መብራት ማስገባት፣ የሥራ እድል መፍጠርና የመሳሰሉት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ሙሉ ለሙሉ የበጀቱ ምንጭም ህዝብ፣ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ እስካሁን ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ብር 600 ሚሊዮን 774 ሺህ 987.21 (44 በመቶ) በዞኖችና ወረዳዎች በየሂሳብ ደብተራቸው ገብቶላቸው ስራቸውን ሌት ተቀን በመስራት ላይ ይገኛሉ። ከሶማሌ የተፈናቀሉ 41ሺህ 53 ዜጎችን በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ 11 ከተሞች በማስፈር እንዲጠለሉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን 506ሺህ 485 የድንበር አካባቢ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት መመለስ ተችሏል። የቤንሻንጉል ተፈናቃዮችን በተመለከተ የመለየትና የሚሰፍሩበትን የተሻሉ አካባቢዎች የመምረጥ ስራዎች ተሰርተው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።
ኮሚሽነር መኮንን አሁን ያለውን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንደሌለና ከሚመለከታቸው ተቋማትና ከመከላከያ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት በአካባቢዎቹ እየሰራ ነው በማለት አስረድተዋል። አያይዘውም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡ ከመንግሥት ጋር ያለማቋረጥ እየሰራ መሆኑንና ህዝብና ህዝብን በማጋጨት ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ወገኖችን ከመንግሥት ጎን በመሆን እየታገላቸው መሆኑን፣ የመጨረሻው የሰላም ምንጭም ህዝቡ እንደሆነ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 14/2011
ግርማ መንግሥቴ