(ክፍል ሁለት)
እንደምን አደራችሁ ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ በትላንትናው የወቅታዊ አምድ ዝግጅታችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ በ2014 ረቂቅ በጀትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ ክፍል አንድ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው የወቅታዊ አምድ ዝግጅታችንም የዚህን ቀጣይ ክፍልና በተለይ በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ወቅታዊ ሁኔታን በሚመለከት ለእናንተ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ያህል ቢሆንም ትንሽ መለስ ብሎ ሁኔታዎች እንዴት ተፈጠሩ? ፣ለምን ተፈጠሩ?፣ሳይፈጠሩ ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? ከተፈጠሩ በኋላ ምን ተደረገ የሚለውን ነገር በመጠኑ ማሳየት ጠቃሚ ነው። እኛ በአለን አቋም ኢትዮጵያ ላይ ግልፅ አደጋ፣ በቅርብ የሚታይ አደጋ፣ እስካልመጣ ድረስ ከማንም ኃይል ጋር ውጊያና ግጭት አንፈልግም። በሰላም በትብብር መልማትና ማደግ እንፈልጋለን። ይህን ነገር ከዓለም አንጻር በሁለት መንገድ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ሰላም እናስቀድማለን፤ ለሰላም የሚከፈል ክፍያ የትኛውም ነገር እንከፍላለን።
ማደግ ስለምንፈልግና ሰላም መፈልግ ክብራችን ሰላም መፈለግ ህልውናችን የሚነካ ከሆነ ግን ተገደን ሰላምን ለማምጣት የምንገባባቸው ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ህወሓትን በሚመለከት ከብዙ ምክንያቶች አራት ወሳኝ ምክንያቶች ግልጽ አደጋ አገራችን ላይ ደቅኖ ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች አሁን ወደ አለበት ነገር እንዲመጣ አድርገዋል።
አንደኛው በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ከነበረው በተለየ መንገድ ከመከላከያ የሚስተካከል ተቋም ለመገንባት የፌደራል መንግሥት ከዚህም ከዚያም የሚሰጠውን በጀትና ቀድሞ ያከማቸውን ሀብት ወታደር ለማዘጋጀት ሰፊ ሥራ ሰርቷል። ግድየለም ወታደር እያዘጋጁ አገርን አደጋ ውስጥ ካላስገቡ ሌላውን ካልነኩ እንለፋቸው እንዳንል እዚያ መገንባት ብቻ ሳይሆን እዚህ መጎርጎር አለ። ቀድሞ የተሰገሰገና የተከማቸ ኃይል ስላለ ግማሹ እየወጣ ይህንን የማዳከም ያን የማጠናከር ሥራ በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል፤በሁሉም መንገድ። ይህ ነገር አደጋ ነው፤ ሄዶ ሄዶ የአገር ህልውና ችግር ውስጥ ያስገባል። ተቋም እያፈረሱ ተቋም መገንባት፤ ያኛው የእኔ ተቋም አይደለም፤ በሚል ሌላ ተቋም የመገንባት ጉዳይ ምን ፈልገው ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳና እንደስጋት እንዲታይ ያደርገዋል።
ሁለተኛው ግልጽና የቅርብ አደጋ የቅጥረኝነትና ቅጥረኞችን የማስፋት ባህል ነው። በአፋር ቅጥረኞች አሉ። የአፋር ህዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዳይገባ ምንዳ የሚከፈለው ሥራ የሚሰጣቸው፣ትጥቅና ስልጠና የሚሰጣቸው ቅጥረኞች አሉ። በኦሮሚያ ትጠቅና ስልጠና ገንዘብ የሚሰጣቸው ቅጥረኞች አሉ። በአማራም፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በደቡብም ቅጥረኞች አሉ። በየቦታው ቅጥረኞች እያደራጁ ገንዘብ እየሰጡ እያስታጠቁ አጀንዳ እየሰጡ ያሰማራሉ። የራስ ኃይል ማደራጀት ሳይሆን እዚህኛው አካባቢም ሰላም መኖር የለበትም የሚል በግልጽና በዕቅድ የሚመራ ሙከራዎች አሉ። በእርግጥ ከዚህ ሁኔታ እኛ መማር ያለብን እሳት ለኩሶ እሳት እየሞቁ ሌሎችን ማቃጠል እንደማይቻል አሁን ያለው ሁኔታ ለሌሎቻችንም ትምህርት ይሰጣል ብዬ አስባለሁ።
ኦሮሚያ ውስጥ ያለ አማራ፣አማራ ውስጥ ያለ ሌላ ብሄር 30 ፣ 40 እና 50 ዓመት ኖሮ ተወልዶ እያለ ተጨባጭ አዲስ ነገር ሳይፈጠር ከሚኖርበት ቦታ ይፈናቀላል። እነዚህ ሰዎች በቅጥረኞቻቸው ማፈናቀላቸው ብቻ አይደለም፤ ቀድሞ የተዘጋጀ የፕሮፖጋንዳ ቡድን ስላላቸው መፈናቀሉን ቀድሞ የምንሰማው ከእነሱ ነው። አፈናቅለው ዜናውን የሚነግሩን እነሱ ናቸው። እናም ተነስ አማራ ተነስ ኦሮሞ ጠፍተሃል ይላሉ፤ ኦሮሞና አማራም ከየዋህነት ብዛት በዛው መንገድና ቦይ ይከተላሉ።
ማነው ያፈናቀለው? ለምን አፈናቀለ ?ለምን ታስቦ ነው? ቆም ብሎ ስሜትን ገታ አድርጎ ለማሰብ ሰው ይቸገራል። ይሄ ያሳለፍንበትን ሁኔታ እናንተ እንኳን ምን ያህል እንደተፈተናችሁበት ታውቁታላችሁ። ቅጥረኞች እያበራከቱ እዚህ እያመሱ እዛ ማደራጀትና ያለመነካት ሁኔታ ነበር። የስላቃቸው ክፋቱ ደግሞ ሰላማዊ ክልል እኛ ብቻ ነን ማለታቸው ነው።
እኛ አንድ የተፈናቀሉ እሱን ስናሰፍር ሌላ የተጋጨ እሱን ስናስታርቅ ነበር ያሳለፍነው። ይህን እናንተ በቅርበት የምታውቁት ነገር ነው። በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ስብሰባዎች በሰዎች ግድያና መፈናቀል ምን ያህል የሚሳለቁ ሰዎች ብዙዎች ነበሩ። እኛ ነን የምንሻለው፤ እኛ እያለን አትበጣበጡም። እኛ እንምጣልህ አይነት እምብዛም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሩ ያልሆነ ግብዣ ለመጋበዝ ተሞክሯል።
ሁለተኛ ፈታኙ ነገር ተቋም እየገነባህ ተቋም ማፍረስ ብቻ ሳይሆን ቅጥረኞች እያበራከትክ ግጭትና መፈናቀልን ማብዛት በኢትዮጵያ ሕዝብ መተማመንን መቀነስ ተሞክሯል። ሶስተኛውና አደገኛው ነገር የትግራይ ሕዝብ ብዙ ችግር አለበት። እንደምታውቁት በሥልጣን ላይ ባሉበት ዘመንም የሰሯቸው ሥራዎች የትግራይን ሕዝብ ከድህነትና ከመታገዝ ሊያወጣ የሚችል አልነበረም። ነገር ግን ያንን ትተው ሕዝቡን ለጦርነት ይቀሰቅሱ ነበር። ግራና ቀኙን ለጦርነት ሲቀሰቅሱ ሰፊ ሥራ ሰርተዋል። ይህ ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የከፋው ነገር ግን ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ነው። ሰሜን ዕዝ ማለት ወታደር ብቻ አይደለም፤ የትግራይን ሕዝብ ጋሻና መከታ ሆኖ ለ20 ዓመት የጠበቀ ነው።
እኔ ሶስት አራት ዓመት ልጅነቴን፣ትምህርቴን ጥዬ ለመጠበቅ የኖርኩበትም ነው። የወንድሜ በጣም ትንሽ ልጅ የሞተበት ነው። ብዙዎችን ወስደን የገበርንበት ማለት ነው። ያ ሰራዊት ለሰራው ውለታ እንኳን ሲባል ቢያንስ ቢያንስ ጡት እስከመቁረጥ መሄድ አልነበረባቸውም። የአርሶ አደር ማሳ እንደሚሰበስብ፣ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት እንደሚሰራ እናንተ ታውቃላችሁ። ደግሞ የድሃ ልጅ ነው። የተለየ ማህበረሰብ የወለደው አይደለም። በነሱም ዘመን አብሮ የነበረ ነው። እናም መከላከያውን ለማዋረድ የተሄደበት ርቀት በጣም አስደጋጭና ሰቅጣጭም ነው። ማጥቃት ብቻ ሲባል ዝም ብሎ ወጊያ ብቻ አድርገን አናስበው። ብዙዎች በእግራቸው እንዲሄዱ፣በታንክ እንዲደፈጠጡና አሳዛኝ በሆነ መንገድ ህይወታቸው ፣ክብራቸውና ስብዕናቸውን እንዲያጡ አድርገዋል።
በዚህም የተወሰነ አይደለም። ሰሜን ዕዝን አጥቅቶ መቀመጥ አይደለም። ሰሜን ዕዝን አጥቅቶ ወንበር መያዝና ማስፋት ነው ፍላጎቱ። እናም እነዚህ ግልጽ አራት አደጋዎች የፌደራል መንግሥት ሳይፈልግ በግድ አገሩን እንዲከላከል፣የተቀማውን የአገር ሀብትና ትጥቅ እንዲያስመልስ ተገዶ ወደ ግጭት ገብቷል። ያው ግጭቱ መደበኛ በነበረበት ጊዜ እንደምታውቁት አጠር ያለ ጊዜ ነው የወሰደው። የገለጸኳቸውም ሆነ ያልገለጽኳቸው ችግሮች በርካታ ናቸው። ችግሩን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት በብዙ ሽምግልና ለምነናል። ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች ፣ፖለቲከኞችና የዚያን አካባቢ ባለሀብቶች ስከኑ፣ረጋ በሉ ጦርነት ከተፈጠረ ይበልጥ ትግራይን ይጎዳል። ጦርነት ለኩሶ በሰላም መኖር አይቻልም። እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ አፍሪካ ውስጥ ግጭት ፈጥረን እኛ ኢትዮጵያውያን በሰላም መኖር አንችልም። እንኳን ሌላ አገር የመንና ሶሪያ የተፈጠረው ግጭት ለእኛም ተርፎ ስደተኞች አምጥቶብናል። አይጠቅምም፤ አገር ያፈርሳል፤ አሁን የሚጮኸው ሁሉ ምንም አያደርግም እንዲያውም ብዙ አገራት ፈርሰው አይተናል። የሚቸገረው ያገሬው ዜጋ ነው፤ ይቅር በሚል ብዙ ተለምነዋል። ከልመናውም ብዛት የነበረውን የእብሪት ልክ ታውቃላችሁ። አንቻልም፣ አንደፈርምና አንነካም አይነት እሪብትና ራስን በትክክል አለመመዘን እብሪቶች በስፋት ነበሩ።
ይህ ሲሆን የመጀመሪያ የመንግሥት ሥራ ጦርነቱን እዚያው ማቀብ ነው። ሌላ ቦታ ሄዶ በአገር ደረጃ መናጋት እንዳያመጣ እዚያው ለማቀብ ተሞክሯል። ከዚህ አንጻር የተሳካ ስራ ተሰርቷል። ሁለተኛው ልክ ውጊያው ሲከፈት በሌሎች አገራትም በአገር ውስጥ ያሉ ቅጥረኞችም በአንድ ጊዜ ተነስተው ለማመስ ነበር ዓላማቸው። በየቦታው እንዲቀጥል ነው ፍላጎቱ። ሕዝቡ በየቦታው ሲፈናቀልና ችግር ሲፈጠር እኛ እንከፋፈላለን። ይህም እንዳይሳካ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል። በግጭት ውስጥ ጥፋተኛው ጁንታ ያልነው ኃይል ላይ ብቻ ለማነጣጠር ተሞክሯል። አጥፍተዋልና አላልንም። ለምሳሌ ከተሞች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል። ውጊያው ከተሞች ውስጥ እንዳይገባ የተሞከረው ሙከራ በታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትና መንግሥት በጉልህ የሞራል ልዕልና የሚያስቀምጣቸው ነው።
ማይካድራ ላይ የተጨፈጨፈው ሕዝብ ወንድምና እህት ሕዝብ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ለማካሄድ ሳይሆን ሥነ ምግባር በተላበሰ መልኩ የሰራበት መንገድ መቼም ቢሆን ታሪክ ያደንቀዋል። አሁን በውሸት ሊሸፈን ቢሞከርም ግን አይሳካም። ምክንያቱም ታሪክ የሚያደንቀው ሥራ ነው። እኛ ጁንታና ጥፋተኛ ያልነውን ሰው ስንይዝና ወደ ሕግ ስናቀርብ በዚያው ልክ በጀግንነት እየተዋጋም ቢሆን መርምረንና ጠይቀን የሙያውን ሥነ ምግባር ባላከበረ መልኩ ወደ ሌላ ተግባር ተላልፏል ያልነውን ማንኛውንም ወታደር ለሕግ እያቀረብን ነው። የእኛ ስለሆነ ስለተዋጋ ወንጀል ቢሰራ ችግር የለውም አላልንም።
በነገራችን ላይ ጁንታ ያልነውና ይህን ሁሉ ጣጣና ኪሳራ ያመጣብን ያሰርንነው ኃይል የተከበረው ምክር ቤት ሄዶ ማየት ይችላል እጅግ ዘመናዊ፣ዲሞክራሲያዊ በሚባል አገር ልክ በነጻነት ነው እየቀለብን ያለነው እንጂ አስረናልና እንግረፍ አላልንም። በሕግ ነው እንዲታይ ያደረግነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ትግራይ በአጭር ጊዜ የነበረው ሁኔታ ከተቀየረ በኋላ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር፣ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዳይሸራረፍበት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የነበረው ሂደት በሙሉ የሚያሳየው እሱን ነው። በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ዕርዳታ በስፋት እንዲቀርብ፣ይህ ድሃና ችግር የበዛበት አገር ያለ የሌለ ሀብቱን አፍስሶ ከማንም አገር በላይ ዕርዳታ አቅርቧል።
እናግዛለን ያሉ አገራትም አንዳንዴ ከመስመር እየወጡም ቢሆን እስካገዙን ድረስ በሚል ለማመቻቸት ሙከራ ተደርጓል። የመንግሥት አገልግሎት ባጠረ ጊዜ እንዲጀመር አድርገናል። አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይ በዚያ ፍጥነት የተሰራው ለማለት በሚያስቸግር ልክ ተሰርቷል። ለምሳሌ ቴሌኮሙኒኬሽንን ለማስጀመር 30 ያህል ሰዎች ተሰውተዋል። ዝም ብሎ አይደለም የተቀጠለው፤ ሰው እየተገደለ ነው የተቀጠለው። መብራትም እየቀጠለ ሰው እየተገደለ ነው። መሰረተ ልማት ዘርግተን ችግር እንፍታ ስንል በገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሰው መስዋዕትነትም እየተከፈለ ነው።
ግብርናን ዘንድሮ ለመጀመር ምርጥ ዘር ገዝተን ብቻ ሳይሆን ክልሎች ለምነንም ጭምር ነው ያቀረብነው። ማዳበሪያ፣ በሬዎች ተጎድተዋል ሲባል ትራክተርም በስፋት ለማስገባትና አርሶ አደሩ ወደ ስራ እንዲገባ ሰፊ ጥረት ተደርጓል። የጤናና፣የትምህርት ተቋማት፣የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ስራቸውን እንዲጀምሩ ጥረት ተደርጓል። ኦፕሬሽን ከጨረሰን በኋላ እነዚህን መሰረተ ልማቶች ገንብተን መውጣት በቂ ስላልሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩን አሰልጥነን ተጨማሪ ሀብት ሰጥተን፣ፖሊሲ ያስፈልገኛል ሲል ፌዴራል፣መከላከያ ካለው ሰብስበን ፖሊስ አሰልጥነን በየዞኑና ወረዳው ድረስ መድበናል። ራሳቸውን ችለው ራሳቸው በራሳቸው በሰላማዊ መንገድ እንዲያስተዳድሩ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገናል።
ይህን ለማድረግ ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ሕዝብና ክልሎች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ አፍስሰዋል። እንግዲህ 100 ቢሊዮን ብር ሌላ ችግር ላይ ብናውለው ስንት ችግር ይቀርፍ ነበር። ነገር ግን ቅድሚያ የነበረውን ቀውስ ማርገብ ይሻላል በሚል የተሄደ ሙከራ ነው። ከዚህ አንጻር የተገኙ ውጤቶች ምንድናቸው? ምንድነው ያሳካነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ ለችግሩ ግንባር ቀደም ተጠያቂዎችና አመንጪዎች ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ለሕግ ቀርበዋል። የተቀሩትም ዳግም እንዲህ አይነት ጥፋት እንዳያጠፉ ሆነዋል። ይህ በቀላል የሚታይ አይደለም። ሰሜን ዕዝ ነጻ ወጥቷል ተመልሷል። ጎንደር፣ ባህርዳርና አስመራ የሚተኮስበት ሚሳኤል ተመልሷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በብድር የተገዛው ሚሳኤል መልሶ ኢትዮጵያን ከማጥፋት እንዲቆም ተደርጓል። ሰሜን ዕዝን ቀምተን ትጥቃችንን አዳብረን እንደፈለግን እናደርጋለን የሚለው ሀሳብ የማይሳካ መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል።
ከሁሉም በላይ መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊ ቁመና ይዞ ጠንካራ ሆኖ እንዲገነባ በምንም መንገድ የማይገኝ መልካም እድልና ልምድ ተገኝቷል። ይህ መልካም እድል ነው። ከዚያ በፊት በነበረው ሁኔታ እኮ ብታቅድ ምንም ነገር ብታስብ የጥፋት ኃይሉ እኩል ስለሚሰማ ምንም ሥራ መስራት አይቻልም። የሚያጠፋውም የሚያለማውም አንድ ነው። ሲፈናቀል የምታሰማራው ኃይል ግማሹ እያየ አላየሁም የሚል ነው። ይህም የእቅዱ አካል ነው። በዚህ ምክንያት መከላከያን ለማደራጀትና ለማጠናከር እድል ተገኝቷል።
ሁለተኛውና አስፈላጊው ነገር ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል ፤ ግጭት ለመፍጠር ፤ ለመለያየት የነበረው ፍላጎት ዜሮ ሆነ ባልልም በከፍተኛ ደረጃ የተለየ ውጤት አምጥቷል። ኢትዮጵያውያን ከምንግዜውም በላይ የሚደማመጡ የሚተጋገዙ የሚደጋገፉ ሆነዋል፤ ይሄን በተግባር አይተነዋል። ይህን ማጠናከር ያስፈልጋል ግን ለመለያየት የነበረው መሻት እና ፍላጎት እምብዛም የተሳካ እንዳይሆን አድርገናል። በነዚህ ሁሉ ጥረቶች ያገኘናቸው ምላሾች ምንድናቸው? ሲባል እንግዲህ ገንዘብ ፣ጊዜ ፣ ሰው ሰውተናል። ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ ብዙ ድካም ደክመናል። በደከምነው ልክ 40 ዓመት የተዘራውን የዘረኝነት መርዝ ልናጸዳ አልቻልንም። የዘረኝነት መርዙ ሌሎች ተጨማሪ ጊዜዎችንና ሁኔታን ይፈልጋል። የነበሩን መልካም ሙከራዎች ይህን ከመቀነስ አንጻር በቂ ነበሩ፤ ጠቃሚ ውጤት ተገኝቶባቸዋል ሊባል የሚያስችል አይደለም። ዘረኝነት ካንሰር መሆኑ ፤ ዘረኝነት አንዴ ከገባ ለብዙ ጥፋት የሚዳርግ መሆኑ፤ ትምህርት ተገኝቶበት እንደሆን እንጂ መርዙ ግን አልነጠፈም።
ሁለተኛው በዝግጅት የተሰራ ቢሆንም በውሸት ፕሮፖጋንዳ የተካኑ ሰዎች በአገር ውስጥ እና በውጭ ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ሀብት ብዙ ሚዲያዎችን በመግዛት የነበረው ቅስቀሳ ቀላል አይደለም። በእርግጥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መገንዘብ ያለበት በፕሮፖጋንዳ ዘመቻው ይህ የጥፋት ኃይል ብቻውን አልነበረም የሰራው። የእርሱን ሃሳብ የሚደግፉና ከጀርባው ያሉ የተላኩ ኃይሎችም በስፋት ተሳትፈውበታል ፤ ገንዘባቸውን አባክነዋል፤ በብዙ አስጽፈዋል ፤ በብዙ አስነግረዋል። የአገር መከላከያ ሚኒስትርም የከፈለው ዘርፈ ብዙ መስዋዕትነት ባጎረስኩ ተነከስኩ ሆኗል መልሱ። ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም ጁንታው ንጹሃንን መሳሪያ ለማድረግ ያደረገውን ጥረት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። የጁንታው አንዱ ስልት እርሱ ሲገድል ጀግና ሰራዊት ነው፤ እርሱ ሲሞት ደግሞ ሲቪል ነው። ቀጣዩ ስራ ይሰራ የነበረው በዚህ በኩል ያለው ኃይል ከሲቪል ጋር አልጋጭም እያለ እንዲተው እርሱ ግን በጣም አስከፊ፤ አስቀያሚ ነገሮች ማድረግ እንዲችል እድል ለመፍጠር ተሞክሯል። መከላከያውም እየተነካካ ኦቨር ሪአክት እንዲያደርግም በጣም ጥረት ተደርጓል። የታጠቀ ኃይል በህልውናው ሲመጣበት እና ሲነካካ የከፋ ርምጃ ሊወስድ ይችላል። ያም ሙከራ ተደርጓል።
ሌላው የምናጠፋቸውን ስህተቶች ለማግነን ተሞክሯል። አንድ ኦፕሬሽን ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል ችግር ነው የሚል እሳቤ ሳይሆን ለማግነን ተሞክሯዋል። ይሄው ሰራዊት ከኤርትራ ጋር በነበረው ውጊያ፤ ይሄው ሰራዊት ከሶማሌ ጋር በነበረው ውጊያ፤ የሚፈጥራቸው ስህተቶች አንዳንዴም ከዚያ ያነሰ ስህተት ሁሉ ተጋኖ እንዲታይ ተሞክሯል። ከዚህ ተነስተን እየሆነ ያለውን ቁጭ ብለን እናጥና አልን። እናውቃለን ከኢትዮጵያውያን ስሜት አንጻር ምን አይነት ምልከታ እንዳለ፤ ለመገንዘብ አንቸገርም፤ ግን እናጥና አልን። የዓለምን እናጥና፤ የእኛን ታሪክ እናጥና፤ ያለንበትን እናጥና፤ የሚሻለንን ነገር እንይ አልን።
አንደኛ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ 30 ዓመት ተዋጉ፤ መቼም ኢትዮጵያና ኤርትራ 30 ዓመት ሲዋጉ ሁሉ ሀሳብ፣ ሁሉ ፍላጎት፣ ሁሉ ትጥቅ፣ ሁሉ በጀት የእነርሱ ነበር ብለን እራሳችንን አንሸውድም። ከጀርባዎቻቸው ከፍተኛ ኃይሎች ነበሩ። በደንብ ያባሉን፤ በመባላት ሂደት ውስጥ አስፈላጊውን ቅመሞች እየጨመሩ ነገሩ እንዳይቆም የሰሩ ኃይሎች ነበሩ። ምን አገኙ የደከመች፤ የደቀቀች ኤርትራ የደቀቀች ፤ የደከመች ኢትዮጵያን ፈጠሩ። ብዙ ሰው ረገፈ ፤ብዙ ሃብት ረገፈ። መጨረሻ ያገኘነው ግን ሁለት የደቀቀ አገር ነው። ተባብሮ እንኳን ችግር መፍታት ወደማይችልበት ደረጃ የደረሰ ማለት ነው። አሁን ያለውን የትግራይ ሁኔታ ስንመለከት በእኔ ግምት ግጭቱ እንዲቆም የሚፈልግ ኃይል ብዙ አይደለም። እንዲሁ እየተጋጨን፤ እየተጋጋጥን ፤ የደቀቀች ትግራይ፤ የደቀቀች ኢትዮጵያን ማየት ወይም ደግሞ አማራ እና አሮሚያ እያሉ የደቀቀ ኦሮሚያን የደቀቀ አማራን ማየት ፍላጎት ያለበት ነው የሚል ምልከታዎች አይተናል። አደገኛ ልምምዶችን አይተናል። ለዚህ አንዱ ለምሳሌ ሀዋሳ ከሚባል ከተማ ሁለት ሰዎች መንግሥት ጋር ይመጣሉ። እናንተ ምን ታደርጉ ጁንታው ተኩስ ከፍቶባችሁ፤ እንዲህ አስቸግሯችሁ እንዲህ አድርጓችሁ ፤ ሕግ ማስከበርማ የመንግሥት ስራ አኮ ነው። እኛም ሀዋሳ አካባቢ እኮ እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞናል። ሁለት ሌላ ሰዎች ደግሞ ከሀዋሳ አካባቢ ጁንታው ጋር ሄደው ሲያሟሙቁ ፤ ሲጽፉ፤ ሲያሻሽሉ ሀሳብ ሲሰጡ ይታያሉ። እነዚህ የሀዋሳ ሰዎች ከፋፍለው ያጫውቱን እንጂ ተመልሰው ይወያያሉ። ያው የሞኝ ነገር ብለው ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ላይ የነበረው ውርጅብኝና ሁኔታ ‹‹ለቅሶው ከፍየሏም በላይ ነው›› ከሚባለውም በላይ ነው። አንዳንዴ ግራ ያጋባል። በጣም ግራ የሚገባኝ ግን ትግራይ አካባቢ ስለተፈጠረው ችግር መፈናቀል ምናምን የሚያነሱ ሰዎች ለኢትዮጵያ አስበው ነው፤ ማድመጥ አለብን ብለን እንኳን እንዳንከተላቸው ተሳስተው ቤኒሻንጉል አይደሉም። ቤኒሻንጉል የሚፈናቀለው ትርጉም የለውም። እርሱ ሰው አይደለም? ሌላ ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያጋጥመውን ችግር አንድም ሰው አያነሳውም። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሁላችንም እኩል ነን ፤የተለየ ነገር የለም፤ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ናቸው። ብዙ ነገር አይተን ከታሪካችን ተምረን ይሄ ነገር ወጣ ባለመንገድ ማየት ያስፈልጋል ፤ በተቀደደልን ቦይ እንጓዝ ብለን እንድናስብ አደረገን።
ወጣ ብለን ለማየትም ሞከርን። ዩኩሬንን አየን። አሁን ዩክሬን ላይ ያለው ነገር ምንድነው? ምንድነው እየሆነ ያለው? ምስራቅ ዩክሬንና አሁን በእኛ አገር በሰሜኑ ክፍል እየሆነ ያለው ይመሳሰላል። ምንድነው ከኋላው ያለው ነገር? ከኋላው ያሉ አክተሮች ምን ይመስላሉ? ዩክሬን ላይ የሚወሰነው ውሳኔ ሪአክት የሚደረግበትና ኢትዮጵያ ሲወሰን ሪአክት የሚደረግበት አራምባ እና ቆቦ ነው። በአንድ አይነት ሁኔታ ማለት ነው። በአርመኒያ እና አዘርባጃን ያለውን ግጭት ለማየት ሞከርን ፤ አፍጋኒስታን፣ሲሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን የገጠመውን ለማየት ሞከርን። ገፋ አደረግንና ጃፓን እና ኮሪያ የገጠመውን ለማየት ሞከርን፤ ያን ግጭት ያን ጦርነት ምን አመጣው? ምን አይነት ውሳኔ እንደሕዝብ ወስነው ነው ለውጥ ያመጡት? እነዚህን ሁሉ ካጠናን በኋላ በአገሬ አባባል ‹‹ለዶሮ በሽታ በሬ አናርድም›› የሚለው ነገር አስገዳጅ ሆኖ አግጦ መጣ። የታመመው ዶሮ ነው፤ በሬ የሚታረድበት ምንም ምክንያት የለም፤ ተገደን ነው የገባነው፤ ባሻን ሰዓት ማቆም ስለምንችል ማቆም ያስፈልጋል፤ ጥሞና ያስፈልጋል፤ ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ከበሽታው ልክ በላይ ድካምና ጊዜ ማባከን ተገቢ አይደለም። በሚል የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋል አልን። የጥሞና ጊዜ እኛንም ያስተምራል ፤ ሌላውንም ኃይል ያስተምራል፤ የዓለም ሕዝብንም ያስተምራል፤ ሌሎች አገራትም በቅንነት ከጉዳዩ መማር ከፈለጉ በተለይ ምስኪን የአፍሪካ አገሮች ለመማር እድል ያገኛሉ። እና ጥሞና ያስፈልጋል ቀስ ብለን እንየው አልን። ይሄን ስናደርግ ግን በርካታ ውይይቶችን አድርገናል።
እኔ እራሴ ከትግራይ አካባቢ ብቻ ከባለ ሀብቶች ፤ከአድሚኒስትሬሽኑ ፣ ከምሁራን ጋር በርካታ ውይይት አካሂጃለሁ። ከመሪዎች፣ ከወታደራዊ አመራሮች ሰፋፊ ውይይቶችን አደረግን። አንዳንዶች ግጭቱን ማስቀጠል ስላልተፈለገ ነው የሚል አይነት ነገርም ይናገራሉ።
የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ የምፈልገው ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ አስር ዓመት ሃያ ዓመት ውጊያ ማስቀጠል ይቻላል፤ ምንም ችግር የለም። ክላሽም አለ ፤ጥይትም አለ፤ ሰውም አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ የማይቻለው በአምስት ዓመትና በአስር ዓመት እድገት ማምጣት ነው። ያልተለማመድነው ነገር እርሱ ነው። ለምሳሌ ከሁለት ሶስት ክልሎች ብቻ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ 100 ሺህ ልዩ ኃይል የሰለጠነ፤ የታጠቀ፤ የተደራጀ ማውጣት ይቻላል። አይ ልዩ ኃይል አይበቃም ሚሊሻም ያስፈልጋል ከተባለ በአንድ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ሚሊሻ ከሞላ ጎደል የታጠቀ፤ ከሞላ ጎደል መተኮስ የሚችል፤ ማውጣት ይቻላል። እንደምታውቁት 100 ሚሊዮን ሕዝብ ያለበት ሀገር ስለሆነ 1 ሚሊዮን ወጣት ቀስቅሶ አሰልጥኖ ማሰማራት ይቻላል። ባለፉት ሰባት ስምንት ወራት በነበረው ውጊያ የኢትዮጵያ መንግስት ክተት አላወጀም ታውቃላችሁ። ግጭቱን ማስቀጠል ይቻላል። ትርፉ ግን መግደል፤ መሞት ከሁለቱም ወገን ዶላር እየተኮስን በአንድ በኩል ደግሞ ረሃብ አለ እያልን ሰው እየጨረስን ድል ልናመጣ አንችልም። የእኛ ድል በመግደል ላይ የሚቆም አይደለም። አይጠቅመንም ብለን ከተግባባን በኋላ የጥሞና ጊዜውን ከማወጃችን በፊት የሚሰሩ ስራዎች ነበሩ።
በነገራችን ላይ የሰራዊት ማውጣትን በሚመለከት ያው ከዚህ ቀደም ሃሳቡን መግለጹ ከወታደራዊ ዲሲፒሊንና ምስጢር አንጻር የራሱ የሆነ አሰራር ስላለ አልተገለጸም። ግን አሁን ግልጽ ለማድረግ እኛ ወታደር ያወጣነው ትናንትና ከመቀሌ ወጣ ሲባል ስትሰሙ አይደለም። ከአንድ ወር በላይ የፈጀ ፕሮሰስ ነው። በአራት ግንባር ከፍለን እያወጣን ነበር። በአንደኛው ግንባር ትጥቆቻችንንና ወታደሮቻችንን ስናወጣ እናንተም አልጠረጠራችሁም፤ ጁንታውም አልጠረጠረም፤ ብዙ ሰው አላወቀም። ሁለተኛውን ዙር ስናወጣ ለምሳሌ ከምርጫ 15 ቀን በፊት ሰፊ ኃይል አውጥተናል። ብዙ ችግር አልነበረም። ሶስተኛውን ኃይል ስናወጣ ነው ጥርጣሬ የመጣው። በርከት ያለ ኃይል፤ በርከት ያለ ኮምቮይ፤ ታጥቆ ፣ተጭኖ፣ ከመሐል አካባቢ ፤ከተንቤን አካባቢ ሲወጣ በዚህ ግዜ ሰፋ ያለ ሕዝብ በማሰማራት ትጥቅ እየወጣ ነው፤ ሰራዊት እየወጣ ነው ፤ በሚል እና በሌላም በሌላም ምክንያት በየቦታው መንገድ መዝጋት ተጀመረ፤ አሁን እንደምነግራችሁ አይደለም፤ በአንድ ጊዜ 2 ሺ 3 ሺ መኪና በሚንቀሳቀስበት ሰዓት ጉዞው በኪሎ ሜትሮች ነው፤ እና በዚህ መሐል መንገድ እየዘጉ ግጭት ለመፍጠር ፣ጎማ ማስተንፈስ መኪና የማቃጠል አይነት ሙከራዎች ተደርገዋል። ግን ከዚያ በፊት የሠራናቸው ሥራዎች ብዙ አልታወቁም። ወይም ሶስተኛው ተጠርጥሮ ይሆናል። ሶስተኛው ኃይል ከመሐል አካባቢ ከተለያየ ሰፈር ተበትኖ የነበረው ተሰብስቦ ሲወጣ እንደዚያ አይነት ጥቃት ለማድረስ ተሞክሯል። አራተኛው ከመቀሌ ያወጣነው ኃይል፤ መቀሌ አካባቢ ጠንከር ያለ ኃይል በሺ የሚቆጠሩ መኪኖችን አሰልፎ የወጣ ኃይል አመቺ ቦታ ላይ በመሆኑ ጥቃት ሳይደርስበት ወጥቷል። አለመጠቃቱ ብቻ ሳይሆን፤ መቀሌ በኃይል ተይዟል ለምትሉ ከመቀሌ መከላከያ ከወጣ በኋላ ጁንታው እዛ አካባቢ ቢያንስ ለሁለት ቀን አልመጣም። እዛ አካባቢ የነበረው ርዝራዥ ደንሶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኃይሉ የገባው አርሚው እንደወጣ አይደለም። ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ሺህ መኪና ሲግተለተል እንዴት ዝም ብሎ ይለቀቃል። የተወሰነ ነገር ይሞከር ነበር። እውነታው እርሱ አይደለም። እውነታው ጥሞና ያስፈልጋል። አርሶ አደሩ በእኛ ምክንያት አላረሰም አይባል፤ በእኛ ምክንያት ሰብዓዊ መብት ተጣሰ አይባል። እኛ እየሞከርን ያለነው መገንባት ነው። ይሄንን ደግሞ ስናደርግ አስተዳደር አሰልጥነን፤ ፖሊስ አሰልጥነን አስታጥቀን ከሞላ ጎደል መንግሥት የሚመስል ነገር ፈጥረናል።
መከላከያ የከተማ ፖሊስ አይደለም፤ ራሱን ለተለያዩ ተልዕኮዎች የሚያዘጋጅ መሆን አለበት። መከላከያን ዝም ብለን አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ (ፋቲግ) ውስጥ መክተት የለብንም ብለን ወስነናል። እንግዲህ ይህ ውሳኔ ምን ጥቅም እና ምን ጉዳት አለው ለሚለው ጠላትም ወዳጅም ቀስ ብለው ጊዜ ወስደው ማሰብ አለባቸው። እኛ ግን ሳንወስን ለወራት ቁጭ ብለን ተወያይተናል። ውሳኔው እስከ አሁን ባለን ግምገማ ትክክል ነው። ለዶሮዋ ህመም በሬ አርደን አናበላሽም ብለናል። ውጤቱን በጋራ እናያለን።
ለእዚህ ውሳኔ አንደኛው የገፋፋን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ። የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስ እንፈልጋለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና አለ፤ ኦክሲጅን እና ቬንትሌተር ችግር አለ፤ እነርሱን ብዙ እንፈልጋለን። ሁላችሁም በጉጉት የምትጠብቋቸው ፕሮጀክቶች አሉ። እነርሱን ክፍት አስቀምጠን ዝም ብለን ገንዘብ ልናባክን አይገባም። ከስደት ተመላሽ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሉ። እነርሱ ላይ መስራት ያስፈልጋል። የግብርና ጊዜው እዚህም እዚያም አስፈላጊ ነው፤ እርሻ ያስፈልጋል። ስንዴ ለማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የአገልግሎት አቅርቦት መኪና በሙሉ ጅቡቲ መሰለፍ አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መኪና ጅቡቲ ማሰለፍ ትተን፤ ከየቀጠናው ሚሊሻ እያዋጣን የምንልክ ከሆነ መኪናውን ሁለት ጊዜ መጠቀም አንችልም። ሎጀስቲክ አቅማችን ወይ ሚሊሻውን ወይም ደግሞ ስንዴውን እንድንመርጥ ያስገድደናል።
ስለዚህ የዋጋ ንረትን ለማስተካከል ገንዘብና ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሎጀስቲክስም በጣም ስለሚወስነን፤ ያንን ማድረግ ይሻላል። እንደበቀደሙ ሚሳኤል ይተኮስብናል እናዳንል ሚሳኤሉ ወጥቷል። እና የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋል። ሕዝቡም ይየው ብለን ወስነናል። እኛ ከወጣን በኋላ ብዙ ዜና ይሰማል። ሰዎች በሃይማኖታቸው ይገደላሉ፤ በሰፈራቸውም ይገደላሉ። መቼም የኢትዮጵያ መንግሥት ተብሎ እንደማይሳበብ ተስፋ አደርጋለሁ። ስንኖርም እኛ፤ ወጥተንም እኛ ከተባልን ትንሽ ፍትሐዊ አይሆንም።
እኛ እያልን ያለነው፤ ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የተቀመጡ ሰዎች በከተማ ውስጥ ወሮበሎች ያለአግባብ እየተገደሉ እና እየታሰሩ ነው ስንል ማንም ሰው በዛ ደረጃ ሊያራግብልን አይፈልግም። ነገር ግን ባለፉት ጊዜያት እዛ አካባቢ በጣም ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ምንም አይነት የሚዲያ ጩኸት አልታየም። ሰሞኑን ግን ይህን ሁለት ቀን ዓለም አቀፍ ሚዲያው እያስተጋባ ያለበት መንገድ በጣም ያስገርማል። ኢትዮጵያውያን መንቃት እንዳለብን ያመላክታል። እንደዛ አይነት አፍ የሚያስከድን ምርጫን ለመዘገብ የተቸገረው ሚዲያ ከየት መጥቶ ነው አሁን ድግስ ያሞቀው ብሎ ማሰብ ይጠይቃል። ዋናው ጉዳይ ግን እኛ በተቀደደልን ቦይ አንሔድም።
መንግሥት መቀየር አለበት፤ አሁን ያለው መንግሥት አይመችም የሚሉ ሙከራ የሚያደርጉ አገራት መኖራቸውን እናውቃለን። ለእነዚህ አገራት ያለን መልዕክት ኢትዮጵያ እስከ ፀናች እና እስከ ቆመች ድረስ እዚህ ያሉት ግለሰቦች ሥልጣን ላይ መቆም ሁለተኛ ጉዳይ ነው። ተላላኪ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም የሚሸጥ መንግሥት ከመሆን ደግሞ አንድ ጊዜ አይደለም፤ 100 ጊዜ ለውጥ ቢደረግ ይሻላል። ምክንያቱም ጥቅም ስለሌለው። ግን አያዋጣም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሪፈረንደም ምን እንደሚፈልግ አሳይቷል። ከእኛ ጋር ተከባብሮ መኖር ጥሩ ነው። ካለበለዚያ ጠቃሚ አይደለም።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን የሚቀደድልን ቦዮች አሉ ፤ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ይሄም ኃይል ከፍተኛ የሆነ የግምገማ ችግር አለበት። ከዕድሜ ጋርም ሊሆን ይችላል። ችግር አለ። ጥቂቶቹን ላንሳ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን መታፈን እና ጫናውን እየጠላ ሲመጣ፤ ጫናውን በማላላት ይቅርታ በመጠየቅ መቆየት ሲቻል፤ በየከተማው ወጣት በመግደል አፈናው ቀጠለ፤ ሕዝቡ በበኩሉ አልቆመም ይህ የግምገማ ስህተት ነው።
ሁለተኛው ስህተት ከለውጥ በኋላ ይቅርታ ተጠይቆ ሕዝቡም ይቅርታ አድርጎ ነበር። ይሄ ኃይል እንደነበር ብልፅግና ውስጥ ቢቆይ ኖሮ ቢያንስ የያዘውን ይዞ ሥልጣኑንም እንደያዘ ይቆይ ነበር፤ አያጣም ነበር። ከብልፅግና የወጣበት ግምገማ ከፍተኛ ስህተት ነበር። ቀድሞ ማየት እንጂ ወደ ኋላ ማየት ብዙ አይከብድም ማስታወስ ይቻላል። በስልጣን በሃብት በመደበኛ እና በኢመደበኛ የሃብት ክምችት መንግሥት የመሆንን ነገር ዝቅ ያደረገ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ትግራይ ከተሄደ በኋላ ዝም ብሎ መረበሽ ሳያስፈልግ የክልሉ መንግሥት ሆኖ መቀመጥ ይቻል ነበር። እኛ የመዋጋት ፍላጎት አልነበረንም። እዛ ጋርም የግምገማ ስህተት ነው። ሚሳኤልን፣ ትጥቅን ከቀማሁ እንደፈለግኩ እሆናለሁ የሚል ሃሳብ ነበር። የሚደርሰውን ኪሳራ የእያንዳንዱ የትግራይ እናት ትመዝነዋለች። የደረሰባቸውን ነገር እነርሱ ያውቁታል።
አሁንም ቆም ብሎ ማየት የሚያስፈልገው እንደዚህ ዓይነት በጣም የተጋነነ ግምገማ የሚያስከትለውን አደጋ ነው። ልክ የእስራኤል ሕዝብ የሚያልፍበትን መከራ ሁሉ አልፎ ከግብፅ በወጣበት ጊዜ እስከ ቀይ ባህር ድረስ የተከተለውን የፈርኦንን መንግስት የሚያስታውስ ነው። አርፎ ካይሮ መቀመጥ ሲገባው ቀይ ባህር ድረስ መጥቶ እንደተዋጠው ማለት ነው። የእስራኤል ሕዝቦች ሲያቋርጡ የፈርኦን መንግሥት አርፎ እዛው ቢቀመጥ ኖሮ ችግር አልነበረም። ጣጣ ያመጣው ተከትሎ መሄዱ ነው። አሁንም ቆም ብሎ ማየት ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም። ቆም ብሎ ማየት ለሁሉም ኃይሎች ይጠቅማል። በዚሁ አግባብ እየሄድን ነው።
የተከበረው ምክር ቤት በብዙ ድካም በብዙ ችግር ውስጥ መንግስት በሆነ ቁመና እንዲሰራ ያደረገ ምክር ቤት ነው። ይህን ለመገንዘብ ይቸገራል ብዬ አላስብም። የወሰንነው ውሳኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለኢትዮጵያ ብልፅግና ጉዞ ይጠቅማል። በራሳችን ዕቅድ፣ መንገድ እና ፍላጎት ለመጓዝ ይጠቅማል፤ ዝም ብሎ መከተል ጥሩ አይደለም። ፈረስ ዝም ብሎ ጋሪን የሚያስከትለው ጋሪ ማሰብ ስለማይችል ብቻ ሳይሆን ፈረስ ራሱ ግራ ቀኝ ማየት እንዳይችል አይኑ ተሸፍኗል። እኛ ዝም ብለን አንከተል ብለን አይተናል። በእርግጠኝነት የተሻለ ውጤት ያመጣል። ቢያንስ ለእኛ ልንሰራ ያሰብናቸውን ሥራዎች ለመስራት ይግዘናል ብለን እናስባለን። በተረፈ ግን ኢትዮጵያ ተዳክማለች እና እንደዚህ ሆናለች የሚሉ ፍላጎቶች ብዙ አይጠቅሙም። የኢትዮጵያ ጉዳት የሁሉም ጉዳት ስለሆነ፤ ብዙ አይጠቅምም። የኢትዮጵያ ዕድገት ሌሎችንም ይጠቅማል። ስለዚህ ሌሎችም ኃይሎች ቆም ብለው እንዲያስቡ እመክራለሁ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መከላከያን በሚመለከት በጀቱ ቢሰፋ ቢበዛ ለተባለው ሃሳብ የምናወጣው ወጪ ከጂዲፒ አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው። ብዙ አገራት በቅርብ ርቀት ያሉ አገራት ከኛ የተሻለ ይመድባሉ። ጥቂት አገራት ደግሞ ለመከላከያ ሳይሆን አጠቃላይ የያዝነውን በጀት ለመከላከያ ይመድባሉ። ዋናዎቹን አይደለም በቅርብ ርቀት ያሉ አገራት ለኢትዮጵያ የተመደበውን በጀት ያክል የሚመድቡ አገራት አሉ። መልካም፤ በቂ ብር ነው የመደብነው ብዬ ልላችሁ አልችልም ማለት ነው። ነገር ግን ለሎው ኢንፎርስመንት ኤጀንሲ ድሮ ከነበረው ሪሶርስ በጣም ከፍ ያለ ተመድቦላቸዋል። ከፍ ያለ ሀብት ተመድቦላቸዋል። ይህ ተስፋ በኢትዮጵያ ኃይልና በመከላከያ ኃይል ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤፍ 22 የታጠቀ የኢንፎርሜሽን ዋርፊየር ከምድር ብቻ ሳይሆን ከሰማይ ማወቅ የሚችል፤ በራዳር በጂፒኤስ የሚዋጋ፤ ከአየር ወደ ምድር የሚዋጋ ፤ወይም ሱ 35 የታጠቀ፣ወይ ደግሞ ራፋኤል የታጠቀ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች የያዘ ሚሳኤሎች የታጠቀ፣ ኒውክለር ቦንብ ያለው፣ ማንም ቢመጣ የሚመልስ ብዬ ልመጻደቅ አልችልም። ውስንነት አለበት ፣ ነገር ግን በእርግጠኝነት መናገር የምችለው አንድ ነገር አለ። የኢትዮጵያ ወታደር ያለው ልብ ማንም የለውም። ይሄን ስላየሁት በደንብ እናገራለሁ።
በቀን ሀያ አምስት፣ ሰላሳ ሰላሳ አምስት፣አርባ ኪሎሜትር በእግሩ እየተጓዘ ታውቃላችሁ መቼስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አይከፈለውም። ጀግና ነው፣ ተራራን ይወጣል፣ ይወርዳል፤ በዝናብ በጸሐይ ይጓዛል። ለአገሩ ክብር ይሞታል፣ለአገሩ ክብር የሚሞት አስደማሚ ሴትና ወንድ ያሉት አገር ነው። ከማንም ጋር በሰላም ብንኖርም የእኛ ዘመናዊ ትጥቅ ግን ልባችን ነው። ይሄ የማይታበል በተግባር የታየ ወደፊትም የሚታይ፣ በታሪካችን የታየ ነገር ነው። አዲስ ነገር አይደለም። እና በትጥቅ አይደለም ውጊያ፣በትጥቅ ቢሆንማ! በሶስት ሳምንት እኮ ጁንታውን መበተን እኮ አይቻልም። እነሱም እንደሚሉት ትጥቁ እነሱ ጋር ነበር። እና መከላከያ ብዙ ሀብት የለውም። ብዙ ልብ አለው፣ ብዙ ህልም አለው፤ አገሩን ይወዳል። እሱን የሚጠናከርበት ስራ እየተሰራ ነው።
ደግሞ ሕዝቡም እናንተን ጨምሮ መከላከያ ማለት አገር እንደሆነ ገብቶት በሞራል የሚደግፈው ሕዝብ ነው። አላያችሁም እንዴ ሰሞኑን እኮ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በሄደበት ሁሉ በየመንገዱ የሚቀልበው ሕዝብ ነው ያለው። የሕዝቡ ፍቅርና ሞራል ይጠብቀዋል። አሁንም በሞራል አሁንም በሰው ኃይል፣በትጥቅ፣ በስንቅ፣ በአመለካከት ልናጠናክረው ይገባል። ጥያቄ የለውም ይሄ። ማጠናከር አለብን። በርካታ ወጣቶች ኢትዮጵያን መታደግ የሚቻለው ጠንካራ ሰራዊት ስንገነባ መሆኑን አውቀው አዋጅ ሳይጠብቁ በከፍተኛ ቁጥር መቀላቀል አለባቸው። የእኛ መከላከያ ደግነቱ ሥራ ከሌለው ማረስም ስለሚችል፣ ማረምም ስለሚችል ኪሳራ አይደለም። ይሄ ሁሉ እንደጠበቀ ሆኖ አሁን የበጀትነው በጀት የምንፈልገውን ስራ ያሰራናል የሚል ተስፋ አለ። ከዛ በላይ ዲማንድ የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ መልሰን ለእናንተ ለማቅረብ የሚያስችል ዕድል አለ።
እኛ መንገድ የምንሰራው ኢትዮጵያ ካለች ነው። ሌላ ግንባታ የምንገነባው ኢትዮጵያ ካለች ነው። ኢትዮጵያ ከሌለች ቅድሚያ የሚሰጠው ለዚሁ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሰላምና ልማት ማስቀደም ስላስፈለገ በዚህ አግባብ ቀርቧል። ከእናንተ ጋር የምስማማው በቂ ገንዘብ አይደለም፣ ግን ደግሞ ቀላል ገንዘብ አይደለም። ‹‹ገንዘቡና ልቡ ሲደመሩ ኢትዮጵያን በደንብ መከላከል ይችላሉ›› የሚል ዕምነት ነው በእኛ በኩል ያለው።
ዲፕሎማሲን በሚመለከት ተቋሙን ማደስ ተቋሙን በከፍተኛ ሪፎርም መቀየር ያስፈልጋል። የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ የምፈልገው ነገር ቅድም የተነገረው ቁጥር ስልሳ ምናምን የሚጠጋ ኤምባሲና ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ያስፈልጋታል ወይ ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል። አሁን እኛ አያስፈልገንም እንዲህ አይነት ነገር። እኛ ዶላር በየቦታው ከምንበትን ለጊዜውም ቢሆን ለስድስት ወርም ለዓመትም ቢሆን አሁን ካሉ ኤምባሲዎች ቢያንስ ቢያንስ፣ ሰላሳው መዘጋት አለበት። ቢያንስ ተዘግቶ አምባሳደሩ እዚሁ ሆኖ ምክንያቱም አምባሳደሮች ለምሳሌ እኔ በኬንያ ያለኝ አምባሳደር እዛ ያለው የውጭ ጉዳይ ወይም መሪ የሚያገኘው በአመት በሁለት አመት አንዴ ሊሆን ይችላል። አሁን እዚህ መጥቶ የኬንያን ጉዳይ እዚያም ቢሆን ጋዜጣ ነው የሚያነበው እዚህም ቢሆን ጋዜጣ ነው የሚያነበው ፤እዚህ ሆኖ ከተከታተለ በኋላ ቀጠሮ ሲያዝለት ሊሄድ ይችላል። ብዙ አገራት ኮሮናን አያይዘው ቀንሰዋል እኛ አሁን ባለንበትን ሁኔታ ያንን የሚያክል ኤምባሲ በየቦታው መጠፍጠፍ አስፈላጊ አይደለም። ውጪ ጉዳይ ይቀይረዋል ብዬ አስባለሁ።
በሚቀጥለው መስከረም የሚመሰረተው መንግሥት አሁን ያለውን የኤምባሲ ቁጥር ብንፈልግም ይቀበለዋል ብዬ አላስብም። አላስፈላጊ ስለሆነ። ይሄን ማስተካከል ይኖርብናል። እዛ ውስጥ የሚታረሙ በጣም በርካታ ጉዳዮች ስላሉ። ነገር ግን ከማን ጋር ነው የምታወዳድሩት ዲፕሎማሲውን ?ኢትዮጵያ እና ማን እያላችሁ ነው ?ብዙ ነው እኮ ኃይሉ። ብዙ ገንዘብ ነው የሚፈሰው ፤አሁን ያለው ጉዳይ መደበኛ ሁኔታ እንዳለው አይደለም የሚታየው፤ ያን ትንሽ ማስተዋል ያስፈልጋል። በርካታ ወጣቶች ሰልጥነው ወደ ውጭ ጉዳይ ተቀላቅለዋል ገና ቢሆንም በሂደት ተቋሙ ይጠናከራል የሚል ግምት አለ። ከኤምባሲዎች ያልተናነሰ በጣም የሚያስገርሙ ኢትዮጵያውያን አሉ ፤ በአውሮፓና በአሜሪካ። አንድ ብር ሳይከፈላቸው ከአምባሳደር ልቀው ተሽለው የሚተጉ ፣የሚሰሩ። እኔ ውጭ ጉዳይን ብሆን የማደርገው ምንድነው /ብሆን ነው ያልኩት/ ሎስአንጀለስ ላይ ቆንስላ አያስፈልገኝም ፣ሎስአንጀለስ ላይ አገሩን የሚወድ ሳይከፈለው የሚተጋ ዜጋ አለ ፤እሱን ዲያስፖራ አስተባብር ተብሎ ሌላውን ሰብሰብ ማድረግ ያስፈልጋል። አውሮፓ ላይ አገር የሚያውቁ ቋንቋ የሚያውቁ ወዘተ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ እነሱን እየመረጡ ሌላውን ሰብሰብ ማድረግ ያስፈልጋል። ውጭ ጉዳይ ያደርገዋል፣ በውጭ ሀገር የምትገኙ ኢትዮጵያውያን መዘጋጀት አለባችሁ። ከዚህ በላይ ኢትዮጵያ መሸከም አትችልም። የግል የሥራ ጉዳይ መሆን የለበትም ፤አብዛኛው ይቀየራል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አለም ላይ አሁን ባለው ተለዋዋጭ ባህሪ እና ጂኦፖለቲክስ የኛ ፖለቲካል እይታም ትንሽ መፈተሽ ያስፈልጋል። እግረ መንገድ ለማንሳት ብዙ ሰዎች አርቲክል ያነቡና ከዚያ መጥተው መንግሥትን መጥተው ያማከራሉ። እንዲህ ፣እንዲህ እየተባለ ነው በማለት። አርቲክል የሚዘጋጀው ዝም ተብሎ አይደለም ፣አርቲክል እንዲጻፍ፣ እንዲዘጋጅ እንዲታተም ሥራ ተሰርቶ ሰዎች የሚፈልጉትን ሀሳብ ገበያ ላይ አቅርበው እኛ ምንም ሳናሰላስል እሱኑ ገዝተን ፣እሱኑ የመንግሥት ፖሊሲ አድርገን በዛ ወጥመድ ውስጥ መግባት ነው። ከምናነበው ከምናየው ከምንሰማው ባሻገር ከኛ ሁኔታ አንጻር መፈተሽ የሚያስፈልግ ማሰላሰል የሚያስፈልጉ ጉዳዮች አሉ። ዝም ብሎ ዲፕሎማሲ የሚባል ነገር የለም። ማሰብ ያስፈልጋል። ያነበብነው ፣የሰማነው ሁሉ ትክክል አይደለም፤ እኛ በምናውቀው ነገር የዋሸን ሚዲያ ስለማናውቀው ነገር ልናምን አንችልም። ዓለም ላይ የምናየው ሚዲያ እንደሚቀጥፍ በምናውቀው ነገር አይተነዋል። ስለዚህ በማናውቀው ብዙ ነገር ያው የባሰነው ማለት ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ድህነት ብርቃችን አይመስለኝ፤ ኖረንበታል ፣ ነጻነት ብርቃችን አይመስለኝም ፤በአባቶቻችን ነጻ ሆነን ኖረናል፣ ዲፕሎማሲም ብርቃችን አይመስለኝም ዩኤንንም ኤዩንም የፈጠርን አገር ነን። ለኛ ብርቅ ብልጽግና ነው፣ ለኛ ብርቅ ልማት ነው። በምናውቀው ነገር ላይ ጊዜን ከሚያባክኑብን ሰዎች፤ በማናወቀው ነገር ላይ ቢያግዙን ጥሩ ነው። ለምሳሌ እዳ ያለአግባብ ተጭኖብናል በሚረባው በማይረባው እንከፍላለን ግን አስተካክሉልን? ስንል ለመመለስ የሚፈልግ አገር በጣም ጥቂት ነው። እውነተኛ ወዳጅ ከሆነ ልማት ላይ ማገዝ ፣ኢንቨስትመንት ላይ ማገዝ ይቻላል። ያ ካልሆነ ግን በምናውቀው ነገር ላይ ከሆነ ብዙ ለውጥ የለውም።
በነገራችን ላይ ድህነት የምንኮራበት የምናወድሰው ጉዳይ ባይሆንም እኔና ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ተመልሰን መደብ ላይ ለመተኛት ችግር ያለብን አይመስለኝም። በዚህ ሰው ሊያስፈራራን አይችልም !አብዛኛው የኖርንበት መደብ የሆነ ዓመታት ኖረን ስለረሳነው ትመለሳለህ ብሎ ሰው ስላስፈራራን አንቀበለውም። አንፈልገውም መቀየር እንፈልጋለን ፤በክብር በነጻነት ከመጣ ግን ብዙ ከባድ አይደለም። እና አገራት ላይ ያለው ጨዋታና ቁማር ቀስ ብሎ ያስፈልጋል። እኛም ደግሞ የበለጠ ለማን ታማኝ መሆን እንደምንፈልግ ፣ማን የበለጠ በኛ ስራ መታመን መደሰት እንዳለበት እንደምናስብ ቆም ብሎ ማየት ይፈልጋል፤ እኛም ጋር ችግር ስላለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሺህ ሆኖ ከሚጮህብን የሆነ አካባቢ አንድ ሰው ሲናገር እንደነግጣለን ፤እናም ትኩረቱ እዚህ መሆን አለበት። የኢትዮጵያን ልማት፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፣ኢትዮጵያ ሰላም ፣ኢትዮጵያ አንድነት፤ በግንባር ቀደምነት የሚረጋገጠው በኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፤ ሌላው አጃቢ ነው። ስለዚህ ትኩረቱ ወደዚህ ቢሆን ዲፕሎማሲው መከላከያው ሰላሙ ይረጋገጣል። ነገር ግን ሰላም ምንም ቢከፈልላት ዋጋ ታጣለች፤ ታደርጋለች። በመታገስ ፣ፈጥነን ባለመወሰን፣ ሸብረክ በማለት የአንድ ቀን ሰላም ካገኘን ፈጥነን ፕሮጀክቶችን እንጨርሳለን። ለሰላም የሚከፈል ዋጋን ለጦርነት ከሚከፈል ዋጋ ጋር አንድ አድርጎ ማየት ጥሩ አይደለም ፤ አብዝተን ለሰላም የምንሰራ አብዝተን ሰላምን የምንሻ መሆን አለብን፤ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላም ካለ ብቻ ነው። ከሰላም ጋር ሁሉም ተያይዞ ይመጣል ፤ዋናው መልማት ነው።
ጤናን በሚመለከት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ ሰፋፊ ስራዎች ተጀምረዋል። ጤና ጣቢያዎችን እያስፋፋን ነው፤ የጤና ኬላ ግንባታዎች ተደርገዋል፣ሙያተኞች እንዳይበተኑ መኖሪያ ቤት እየገነባን ነው ፣በነባር ጤና ኬላዎችና ጤና ኬላዎች ሶላር ኢነርጂና ንጹህ ውሃ እያስፋፋን ነው። እንደተባለው እናቶች እንዳይቸገሩ ከሁለት ሺህ በላይ ለእናቶች ለወሊድ ጊዜ ማቆያዎች ተሰርተዋል፣ ሆስፒታል ግንባታዎችም እየተካሄዱ ነው፣ ከክልል ጋር በመሆን በሺህ የሚቆጠሩ አምቡላንሶች አስፋፍተናል፤ በጀትም እንዳያችሁት እጥፍ ነው። ግን ይሄም መጠናከር አለበት። በተለይ የግል ዘርፍ ሊሰራበት የሚገባው አንዱ አካባቢ ጤና ነው፤ የግል ሴክተሩን በስፋት ማስገባት ይኖርብናል።
መከላከል ላይ የተነሳው በማይተላለፍ በሽታዎች ላይ የተነሳው ሀሳብ ሁሉ ትክክል ነው። በእርግጥ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ያሏቸው ትላልቅ ሆስፒታሎች በካንሰር፣ በኩላሊት እና በልብ ህክምና ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ዲፓርትመንቶች እየከፈቱ ነው ፤ኢንቨስትም እያደረግን ነው። በጊዜ ብዛት ውጤታማ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ። መታገዝ ያለባቸው የግል ሴክተሮችም አሉ፤ በልብ ህክምና ኢትዮጵያዊ የሆኑ አንድ ሐኪም ከዚህ ቀደም በእስር ላይ የነበሩ ከለውጡ በኋላ የተፈቱ በጣም አነስተኛ በሚባል ቦታ የብዙ ሰዎችን ችግር እየፈቱ ይገኛሉ። እንደነዚህ አይነት ሰዎች መታገዝ አለባቸው።
ቀደም ሲል እንዳነሳሁት በብዙ ልብና መሻት እያገለገሉ ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ ሊሰሩ የሚችሉ። እነሱን ማገዝ ያስፈልጋል። ችግራችንንም ስለሚቀርፍ ከሰለጠነው አለም የሚመጣ አቅም ካለ መጠቀም ጥሩ ነው። አልኮል፣ ትንባሆ ፣ሀሺሽ ጭፈራ ቤት እንዲቀንስ ማድረግ ፣ማስ ስፖርት እንዲበራከት ማድረግ ያስፈልጋል። እነዚህ አጓጉል ባህሪዎች ትውልድን የሚያበላሹትን ቀነስ እያደረጉ ፤ የበለጠ ስፖርት ላይ ፣ ችግኝ መትከል ላይ የእግር ጉዞ ላይ ማስፋት ፤ አዲስ አበባ ውስጥ የምታዩት አብዛኛው ዎክ ዌይ ማስፋፋት ስራ ከዚህ ጋር ይያያዛል። ሰው ታክሲ እየቀነሰ በእግሩ እንዲሄድ ፤በእግር መሄድ ጤና ነው በእግር መሄድ በጣም ብዙ ችግሮችን ይፈታል ገንዘብን ብቻ አይደለም።ነገር ግን ብዙ ዎክዌይ የለም፤ እሱን እያሰፋን ጤናችንን የምናሳድግበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። ሆስፒታሎችን እናስፋፋለን ፤ በጀቱ አሁንም ቢያድግም በቂ አይደለም። የግሉ ሴክተር እየገባ የሚያሻሽል ቢሆን ጥሩ ነው።
በጎዳና ላይ ያሉት ዜጎች በሚመለከት ያላችሁት ሁሉ ትክክል ነው። ግን አሁንም ኢትዮጵያውያን ከተደመርን ቀላል ነው። 100 ሺህ ኢትዮጵያዊ ከወሰነ ጎዳና ላይ አንድም ሰው አይኖርም ፤አንዳንድ ሰው ለመውሰድ ከወሰነ ማለት ነው። 100 ሺህ ዲያስፖራ ከወሰነ ጎዳና ላይ ህጻን እንዳይኖር ማድረግ ይቻላል ፤ አንድ ሰው አሳድጋለሁ ብሎ ከወሰነ። ነገር ግን ጎዳና ላይ ያለው ችግር ኢኮኖሚ ብቻ አይደለም። አንደኛው ኢኮኖሚ ነው፣ ሁለተኛው ወላጅ አልባ መሆን ነው፣ ሶስተኛው ልጆች በአልባሌ ሱስ መያዝና በቤተሰብም በሚያግዙም ሰዎች ስር መቀመጥ አለመፈለግ ነው፤ የሚያግዝ እያለ ፣ካምፕ እያለም የማይፈልጉ ልጆች አሉ ፤አዳዲስ ሱሶች ከመለማመድ ጋር ተያይዞ። ያም ሆኖ ከግል ሴክተር ጋር በመሆን ካምፖች የገነባናቸው አሉ፤ በባለፉት አመት፣ አመት ተኩል።
አሁንም በቅርቡ ከውጭ ሀገር ሰዎች ጋር እንዲሁ ስምምነት አድርገናል። እንገነባለን ለመያዝ እንሞክራለን። ባስወጣነው ቁጥር የሚፈስ ከሆነ ዋጋ የለውም፤ ያለው እንዳይወጣ የወጣው ደግሞ እንዳይመለስ እያደረግን በጊዜ ብዛት ችግሩ ይፈታል የሚል ተስፋ አለኝ። አሁን ግን እንዳላችሁት እየተባባሰ መጥቷል ፤ይሄ ደግሞ በጎዳና ላይ አዳዲስ ባህሪ አዳዲስ ዘረፋን ስለሚያስከትል አስቦ መስራት ያስፈልጋል።
በመጨረሻም ምርጫን በሚመለከት በርካታ ሀሳብ አንስታችኃል ፤ያው ምርጫችን ለሁሉም ነው። ኢትዮጵያን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንን ያስደመመ ነበር። እኛም ተምረንበታል። አለምም ተምሮበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ምርጥ አስተማሪ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ቀደም ሲል እናንተን ለማመስገን የፈለኩት በእኔም ውስጥ ያለው ደስታ በእናንተም ውስጥ ያለው ደስታ ተመርጫለሁ አልተመረጥኩም የሚል ሳይሆን ኢትዮጵያ አሸንፋለች የሚል ስለሆነ ነው።
አብዛኛው የፓርላማ አባል በዚህ ምርጫ ያልተወዳደረ ቢሆንም በብዙዎቻችሁ ያየሁት በምርጫው ላይ ያላችሁ እይታና ምልከታ የሚያሳየው ግን የኢትዮጵያ አሸናፊነት የብዙዎቻችን ፍላጎት መሆኑን ያመለክታል። ይሄ እጅግ ደስ የሚል ነገር ነው። ምርጫ ቦርድ ያደረገው ሙከራ መደነቅ ያለበት ነው ፤ ማጠናከር ቢገባንም። ፍርድ ቤት ያደረገው ሙከራ መጠናከር ያለበት ቢሆንም በእርግጥ ፍርድ ቤት ላይ ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል። አሁንም አንዱ የሌብነት ችግር ያለው እዛ አካባቢ ነው፤ ተቋሙ አልጠራም ፣አልተስተካከለም። ወደፊት ብዙ ሥራዎችና ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ። ነገር ግን እሱም ቢሆን ሙከራው መደነቅ አለበት። ሚዲያዎች ያደረጉት ነገር መደነቅ አለበት ፤ተፎካካሪ ፖርቲዎች ያደረጉት ነገር መደነቅ አለበት። ተፎካካሪ ፖርቲዎች በተቻለ መጠን የተሻለ ምርጫ እንዲደረግ ጥረት አድርገዋል።
እንግዲህ ማሸነፍና መሸነፍ እንኳን ለኛ ለኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ከኛ ወዲያ የሚሉትም ሲቸገሩ አይተናል። መሸነፍ የሚዋጥ ነገር አይደለም ፤ይከብዳል።ያ የሚያመጣው አዳዲስ ባህሪዎች በሆደ ሰፊነት ማየት ይፈልጋል። በነበረው ሂደት ግን አርባ ምናምን ፓርቲዎች አስደናቂ ነገር አድርገዋል፤ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። ይሄ መደነቅ አለበት። እኔ የሚያስፈራኝ እና ይሄ ምክር ቤት በተለይ የማትወዳደሩ የምክር ቤት አባላት በጣም እድለኛ ናችሁ ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ የሕዝቡ ነገር ነው። እስከ ሰባት ሰዓት የመረጠንን ሕዝብ ምን አድርገን ነው የምናገለግለው ?ምን ብናደርግ ነው ድህነት የሚቀንሰው ?ምን ብናደርግ ነው ከደሳሳ ጎጆ የምናወጣው ?ይሄ ሕዝብ እኛ እንኳን የምንመረጥ ሰዎች የማናደርገውን እስከ ሰባት ስምንት ዘጠኝ ሰዓት ቆሞ ፣ሌሊት አልገባም ብሎ መርጦን ነገ በሙስና የምንሰርቀው ከሆነ ሞት ይሻላል። አደገኛው ነገር ይሄ ነው። የወጣችሁ በጣም እድለኛ ናችሁ። በእናንተ ጊዜ የነበረው ምርጫ እንደዚህ አልነበረም፤ታውቃላችሁ?። አሁን የሚመጣው ፓርላማ እናንተ ከነበራችሁ ጥረትና ትጋት አምስት አስር እጥፍ ማደግ አለበት። በእርግጥ ይህ ፓርላማ ባለፉት ዓመታት ያለፈበት መከራ ብዙ ነው። ይሄ ፓርላማ እንደ ኖርማል ፓርላማ የሚታይ አይደለም። ትልቅ ኃላፊነት የተሰማው ለብዙ ፖለቲከኞች አስተማሪ የሆነ ነገር ያየንበት ፓርላማ ነው። ይሄንን ፓርላማ ስትወጣ የምትከፍለው ታክስ ላይ መጨቃጨቅ ፣ቤት ላይ መጨቃጨቅ ተገቢ አይደለም። በነጻ ያገለገለ ነው፤ ክብር ይገባዋል ፤ ተከብሮ መሄድ አለበት። ክብር የሚገባው ስብስብ ስለሆነ ብቻ ደግሞ አየደለም ልምድ አለው። ቢያንስ ቢያንስ የሌብነት ልምምዱ የቀነሰ ነው።
ይኼንን እያንዳንዱ ቀበሌ፣ ወረዳ ዞን፣ ክልል መጠቀም አለበት። ለራሱ ሲል። ይሄ ፓርላማ እንደዚህ የሚመሰገን ከሆነ አሁን የሚመጣው ደግሞ ሸክሙ በጣም ብዙ ነው። እኛ አገር ፓርላማ ደመወዝ አይከፈለውም። እኛ አገር ፓርላማ ጥቅማጥቅም የለውም። እዚህ ኬንያ፣ ኡጋንዳ ብንሄድ ፓርላማ የተለየ ነገር ነው። በነጻ ነው በአገር ፍቅር ስሜት የሚሰራው። ነገር ግን ዘንድሮ የተመረጥን ሰዎች ከዛ በላይ ኃላፊነት ተሰምቶን ካልሄድን የሕዝቡ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ባንሰርቀው፤ ቢያንስ ሰዓት ባንቆጥር፤ ቢያንስ እሱ መደብ ላይ እየተኛ በሚያፈስ ቤት ውስጥ እየሆነ እኛ ከዛ ያለፈ ነገር ባንፈልግ፤ እና ብናስተባብረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መምረጥ ብቻ ሳይሆን መስራትም ይችላል። ይኸው በችግኝ እኮ እያየን ነው። ካመነ ይሰራል። ቀርበን ተባብረን ሰርተን ኢትዮጵያን የሚያሻግር ነገር ማድረግ ይኖርብናል። እዚህ ያለው ምክር ቤት ባለው ልምድ ረጅም ጊዜ ያገለገላችሁ ሰዎች አላችሁ፤ በየደረጃው ያለውን መስተዳድር በማገዝ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የሰለጠነ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደረግ፣ ሰዎች በነጻ መናገር ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት የሚሰማቸው ማድረግ ከእናንተም ከእኛም ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ።
በኛ በኩል ምርጫውን ካሸነፍን፤ ምርጫ ቦርድ አሸንፋችኋል ካለ ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይነት መንግስት ኢትዮጵያ ደግማ እንድትፈጥር አንፈልግም። እኛ የምንፈልገው ከየፓርቲው ያሉ ሻል ሻል ያሉ ሰዎች አንድም ይሁን ሁለት ካቢኔ ውስጥ፤ አንድም ይሁን ሁለት በየኤጀንሲው በየክልሉ እየገባ አገሩን የሚያግዝ ፖለቲካ ሲመጣ የሚጨቃጨቅ፣ ልማት ሲመጣ አብሮ የሚሰራ ነው እንጂ የምንፈልገው ተቃዋሚ የሆነ ሁሉ ከወደቀ ወድቀሃል፣ አምስት አመት ጠብቅ አንልም።
በእርግጥ ይሄ ምርጫ በጣም ተሸውደው በወዳጆቻቸው የግምገማ ስህተት ምክንያት ተሳስተው ያጡ ሰዎች አምስት አመት መጠበቅ ሊገደዱ ይችላሉ። ከዛ ውጭ ግምገማ ሳያሳስተው ጸንቶ ቆሞ በውድድር ውስጥ ያለፈው ግን በየደረጃው በአስፈጻሚው ውስጥ በተለያየ አካላት ተሳትፎ ጠንካራ መንግሥት አገር የሚያሻግር መንግስት ማድረግ አለብን። ይሄን የምናደርገው ኢትዮጵያ ታሸንፍ፣ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ካልን ብልጽግና አሸንፏል ከሚለው ጋር በጣም ይራራቃል። ኢትዮጵያ የምታሸንፈው ልጆቿ ሁሉ በጋራ ሲቆሙላት ስለሆነ በኛ በኩል የምንፈልገው በየትኛውም ደረጃ ቢሆን አገሩን በነጻነት ማገልገል የሚፈልግ ሰው ከኛ ጋር ሆኖ እንዲያገለግል እንፈልጋለን። እኛ ፍላጎታችን የኢትዮጵያ ቀጣይነት የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና ብቻ ነው። ይሄን የሚያስቡ ሰዎች ሁሉ አብረውን ቢሰሩ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለን እናስባለን። በዚህ ውስጥ የሚጎዳ ፓርቲ የለም። አምስት አመት ሲደርስ ደግሞ እንጨቃጨቃለን፣ ችግር የለውም። ያኔ ደግሞ እንደገና ምርጫ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም አሁን ባደረገው ሪፈረንደም (ሪፈረንደም ነው ያደረገው “ባይ ዘዌይ”) የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመዘገበው፤ ከተመዘገበው የመረጠው በፐርሰንቴጅ ብታወዳድሩት በዓለም ላይ አደግኩ የሚል አገርም (አሜሪካን ጨምሮ) ሊመርጥ ከሚችል ዜጋ የመረጠው ቁጥር የኢትዮጵያ በጣም ብዙ ይበልጣል፤ ይሻላል። መርጧል ወጥቶ። ነግሮናል፤ ለኛም ለሌላውም። የምፈልገው ሠላም ነው፣ ጠንካራ መንግስት ነው። ዝም ብላችሁ የሚላላክ ነገር አታምጡብን ብሏል። አሁን ይሄን ለማፍረስ ደግሞ አዳዲስ ቋንቋዎች ይፈጠራሉ። አንሰማም። የኢትዮጵያን ህዝብ ሪፈረንደም እናከብራለን። የኢትዮጵያን ሕዝብ ሪፈረንደም ግን “ሜሴጁ” አንድ ፓርቲ ይለፍ ሳይሆን ኢትዮጵያ ታሸንፍ እንደሆነም በደንብ እንገነዘባለን። ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነን የተሻለ መንግሥት የተሻለ ሥርዓት እንፈጥራለን። ብልጽግናችንን እናረጋግጣለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ አትሸነፍም፤ አትወድቅም። ያለፍንበት ፈተና ሁሉ የሚያሳየው ችግሮችን መቋቋም በቀላሉ የሚችል “ሪዚሊየንት” ሕዝብና አገር መሆናችንን ነው። በቀላሉ የማንፈርስ መሆናችንን ነው። ይሄን ለጠላትም ለወዳጅም አሳይቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀጥላል። ምናልባት የተለመደ ጉዳይ ባይሆንም አሁን ደግሜ የማረጋግጥላችሁ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይወዳል፣ ይደግፋል፤ ያሻግራል። ይሄን አይተናል። በዚሁ መንፈስ በአንድ ልብ በተባበረ ክንድ ቀጣዩን ዘመን የተሻለ እናደርጋለን።
ይህ ምክር ቤት ባለፉት ስድስት ዓመታት ለሰራቸው ገድሎች ታሪክ ያወሳዋል። በቅርበት ባየሁት ልምምዴ ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት ለእናንተ አለኝ። በተለየ ካፓሲቲ በጋራ አገር ለማበልጸግ እንደምንሰራ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013