አዊ ዞን በአማራ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ሲሆን፣ በስሩም 12 ወረዳዎች አሉ። ዞኑ ሶስቱንም የአየር ጸባይ ያካተተ እንደመሆኑ የትኛውም አካባቢ ይበቅላል የተባለውን ሁሉ ሊያበቅል የሚችል ነው። በተለይ አማራ ክልል ቡና አይበቅልም የሚለውን አባባል ዞኑ ፉርሽ የሚያደርገው ሲሆን፣ ለቡና ተክል ምቹ መሆኑም በጥናት ከመረጋገጡም በላይ በተግባር እየታየ ይገኛል። በዞኑ ስላለው የጸጥታና ሰላም ሁኔታ፣ ስለተፈናቃዮች እንዲሁም ግብርናውን በተመለከተ አዲስ ዘመን ከአዊ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአዊ ዞን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እንደመኖራቸውና ከዚህ ቀደም በአዋሳኝ ወረዳዎች ችግር እንደመፈጠሩ ከቀናት በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ ከጸጥታው አኳያ የተፈጠረ ችግር ካለና የወሰዳችሁት እርምጃ ምን እንደሚመስል ቢገልጹልን?
አቶ ባይነሳኝ፡- በዞኑ የተካሄደው ምርጫ ግምገማችን እንደሚያመለክተው ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን መስራት አለብን በሚል መንገድ በእቅድ ተይዞ በጣም ሰፋፊ ሥራዎችን ነው የሰራነው። ከእነዚህ ስራዎች አንጻር በቅድሚያ በዚህ ዓመት ከምናደርገው ምርጫ አንጻር ከአመራር፣ ከጸጥታ ኃይሉ እንዲሁም ከህብረተሰቡ የሚጠበቁ ነገሮች ምንድን ናቸው የሚለውን ህብረተሰቡ በዝርዝር እንዲያውቀው በማድረግ ጉልህ ስራ ተሰርቷል።
በአገራችን ባለፉት ዓመታት ውስጥ በተለይ የዴሞክራሲን ምህዳር ከማስፋት አኳያ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ በመታመኑ እንደመንግስትም እንደብልጽግናም ጭምር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ተደርጎ ስለተወሰደ በእሱ አካባቢ ጠንካራ ሥራ መሥራት አለብን በሚል ነው እያከናወንን የመጣነው። ከዚህ አንጻር ከላይ እስከታች ያለ አመራርና የሚመለከታቸው ከምርጫው ሥነምግባር ሕግ ጋር በተያያዘ መንገድ ምንድን ነው አድርግ አታድርግ የሚለን? መውሰድስ የተገባን ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው? የሚለውን ለሚመለከታቸው አካላት ከላይ እስከ ታች የተለያዩ ስልጠናዎች ጭምር የሰጠንበት ሁኔታ ነበር።
ይህን መሰረት በማድረግ ወደምርጫው ሲገባ የተደረሰው ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ የየራሳቸውን ማኒፌስቶ እንዲያስተዋውቁ የማድረግ መብት አላቸው የሚል ግንዛቤ ላይ ነው። ይህን ሊያሳልጥ የሚችል በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መቋቋም ነበረበት። የፖለቲካ ድርጅቶቹ የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም በየጊዜው የሚታዩ ግድፈቶችን እንዴት እናሻሽል? ጥሩ ነገሮችን ደግሞ እንዴት እናስቀጥል? በሚል በየጊዜው እየተገመገመ ለመሄድ ጥረት አድርገናል። በዚህ ረገድ የተሰራው ሥራ በጣም ጥሩ ነበር።
እነዚህን ሥራዎች አከናውነን ወደምርጫው ስንመጣ እንደሚታወቀው አካባቢው ትልቅ ስጋት የነበረበት ነው፤ ምክንያቱም ተፈናቃዩ አለ፤ እሱም ብቻ ሳይሆን ከተፈናቃዩ ጋር በተያያዘ በአካባቢው ሌሎች ኃይሎችም የሚንቀሳቀሱ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እኛም በትኩረት ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ስንሰራ ነው የቆየነው። በዚህም ህብረተሰቡ ራሱ አካባቢውን ለመጠበቅ ተነሳስቶ ሰንብቷል።
እውነት ለመናገር የሰራነውን ውጤት ነው ያገኘነው ብዬ አምናለሁ። በዚህ ረገድ ሥራዎቻችንን የጨረስነው ቀድመን ነው ማለት ይቻላል። ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት በምርጫው ዕለት የተፎካካሪ ድርጅቶች ታዛቢዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ሁሉንም በግልጽ ያስኬድንበት ሆኖ ነው የቆየው። ከዚህም የተነሳ ምርጫው መጠናቀቅ የቻለው ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ ነው። በተጨማሪም እንደ እኔ የማምነው ተዓማኒነት ያለው ምርጫ አካሂደናል ብዬነው። በዚህ ረገድ በዞናችን ያጋጠመ ምንም አይነት ችግር የለም።
በዚህ አጋጣሚ የዞኑን ህብረተሰብ ማመስገን ይገባል። ምናልባትም የነበረው ችግር ትንሽ መጉላላት ነው። የተሞክሮ ችግር በመኖሩም ምክንያት ጭምር ነው ይህ ሊፈጠር የቻለው። ፍጥነት ላይ ጉድለት ነበር። በተለይ ከተሞች አካባቢ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ ሰልፎች ነበሩ። በዛ መንገድ ህብረተሰቡም ምርጫውን በሰከነ መንገድ አከናውኗል። በጥቅሉ ለመምረጥ የነበረው ተነሳሽነት ሰፊ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የነበረው ሰልፍ በጣም ረዣዥምና አሰልቺ ከመሆኑ ባሻገር ሌላ ምንም አይነት ችግር አልተስተዋልም።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምርጫው ዋዜማ እንዳሉት ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ዴሞክራሲንም ችግኝንም እንተክላለን የሚል ነበር፤ እንደ አዊ ዞን ከዚህ አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ባይነሳኝ፡– ወደ ችግኝ ስንመጣ ችግኝ እንደ አዊ ዞን የሚታየው እያንዳንዱ ህብረተሰብ አንድ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የራሱ ተግባር እንደሆነ ሁሉ በችግኝ ላይም ያለው ግንዛቤ የዚያን ያህል ነው፤ በመሆኑም ትኩረቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ እንደ አገር የደን ሽፋናችን 15 በመቶ አካባቢ ላይ ነው። እንደ አዊ ዞን ግን በመቶኛ ሲሰላ 38 አካባቢ ነው። እንደ አዊ ዞን ካለው 38 በመቶ የደን ሽፋን ውስጥ 25 በመቶው የተፈጥሮው ደን ሲሆን፣ 13 በመቶው ደግሞ ሰው ሰራሽ ደን ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመትም ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኝ ያፈላን ሲሆን፣ የተከላውንም ሥራ ጎን ለጎን የማከናወን ተግባር መሰራት አለበት በሚል በመንቀሳቀስ ላይ ነን። ነገር ግን በእስካሁኑ ሂደት በሚፈለገው ደረጃ እየተጓዘ ነው ማለት አይቻልም። ለዚህም ምክንያቱ አብዛኛው ሰው ትኩረቱ ምርጫ ላይ በመሆኑ ነው። እንዲያም ሆኖ የተቀመጠ መርሐግብር አለ፤ በዚያ መርሐግብር በስፋት እንሄድበታለን።
በተለይ በዚህ ዓመት ደግሞ ከሌሎች ዓመታት በተለየ አዋጭነቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት አትክልትና ፍራፍሬን የሚመለከት ደግሞ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ችግኝ ያፈላን ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ቡና ተጠቃሽ ነው። ወደውጭ ጭምር ኤክስፖርት የሚደረግ የማንጎ አይነትንም ያካተተ ነው። በመሆኑም የተከላ ስራው በስፋት የሚከናወን ነው የሚሆነው። ስለዚህም በቅርቡ ዞን አቀፍ የሆነ የተደራጀ መርሐግብር ይኖረናል። ትኩረት ሰጥተንም የምንሰራው ስራ ይሆናል።
ዞኑ በመስኖ ስራም የሚታወቅ ነው። በዞኑ ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈሱ በርካታ ወንዞች አሉ። ይህም የወንዝ ፍሰት ከደን ጋር ተያይዞ የመጣ ውጤት ነው ብለን ነው የወስደነው። ህብረተሰቡም የደንን ጥቅም ይበልጥ እየተረዳ በመምጣቱ ለደን ያለው ግምት በአሁኑ ወቅት በጣም ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም ለአዊ ዞን የደን ተከላ ሂደት አስቸጋሪ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ በተለይ ጓንጓ ወረዳ ያገኘናቸው አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለዳጉሳና ለኑግ በማረስ እያዘጋጁት እንደሆነ ገልጸውልናል፤ በዞኑ ላሉ አርሶ አደሮች እየተደረገ ያለ ድጋፍ እና ግብርናን ለማዘመን እየተከናወነ ያለ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ባይነሳኝ፡- በዚህም ዓመት በጣም ትኩረት ከሰጠናቸው ጉዳዮች ዋነኛው ግብርና ነው። እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት ከኮሮና ጋር ተያይዞ እንደ አገር ግብርናው ላይ የራሱን ተጽዕኖ በማሳረፉ ወደመስኖው ማተኮር ተገቢነት እንዳለው መጠቀሱ ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞናችን ደረጃ የሰራናቸው ሥራዎች አሉ። በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ለመስኖ ስራ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን በማለት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። ይህን የሚመራ ቡድን ከምርጫው ሥራ ነጻ ሆኖ ትኩረቱን በዚህ ጉዳይ በማድረግ ተቋቁሟል።
በዚህ ረገድ እስካሁን ባለን መረጃ በተለይ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሚፈለገው በላይ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃም ምርጥ ዘሩ መትረፍ ችሏል። ከዚህ የተነሳም የአርሶ አደሩን ፍላጎት አሟልተን በቀጣይም ለመስኖ ብሎም ሌሎች ጉድለት ላለባቸውም አካባቢዎች የማሰራጨት ስራ የሰራን ሲሆን፣ ለምሳሌ ወደምዕራብ ጎጃም የተሰጠበት ሁኔታ ነው ያለው። በጥቅሉ ሲታይ ከየትኛውም ዓመት በተሻለ መንገድ የምርጥ ዘር አቅርቦት በዚህ ዓመት የተሻለ ነው ማለት ይቻላል።በተለይ በቆሎን ወስደን ስንመለከት ‹‹ሊሙ›› የሚባለው ዝርያ ተፈላጊነቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ከአሁን በፊት አርሶ አደሩ ከፍተኛ ምሬት ነበረው። በዚህ ዓመት የሚፈለገውን ያህል አቅርበናል። በዚህ ረገድ መሰረታዊ ችግር ተቀርፏል።
ከማዳበሪያ ጋር በተያያዘ አቅርቦቱ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፤ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ አሁን ላይ እጥረት አጋጥሞናል። ዩሪያን በተመለከተ ወደ ቆላማው ክፍተት አለ። እሱም የመዘግየቱ ምስጢር ከጅቡቲ ሲመጣ ቶሎ ያለመድረስ ችግር በመኖሩ ነውና በተቻለን አቅም እንዲፈጥንልን ጥረት በማድረግ ላይ ነን። ከክልሉም ጋር በተነጋገርነው መሰረት ተጭነው በመንገድ ላይ እንዳሉ በማወቃችን ወደቆላማው አካባቢ ፈጥኖ ለማድረስ ዝግጁዎች ነን። ከዚህ ውጭ ያለው ነገር እንደእኛ ግምት በጣም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት እንችላለን።
በተለይ በገበያ ላይ ተፈላጊነት ያላቸውን ምርቶች እንደ አኩሪ አተር ያሉትን በተለየ መንገድ ምርጥ ዘር ላይ ተመስርተን ሥራ መስራት እንዳለብን በማመን ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው። የዘር አቅርቦቱም በመንግሥት ደረጃ እየቀረበ ነው።
ከዚህ ውጭ ዞኑ አብዛኛው ደጋማ ስለሆነ የመሬቱ አሲዳማነት አንዱ ችግር ነው። ይህን ችግር ለመቀነስ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ላይ ነን። በዚህ ረገድ በጣም ጥሩ የሚባል ርቀት ተጉዘናል። ይሁን እንጂ እሱንም ስንገመግም ካስቀመጥነው እቅድ አንጻር በተወሰነ ደረጃ ክፍተት እንዳለ ማስተዋል ችለናል። በመሆኑም በተወሰነ ደረጃ ድጋፍ የሚጠይቅ ነገር አለው። በመሆኑም የተቋቋመው ቡድን ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
በምርጫ ስራችን ያገኘነው መልካም ነገር ወደሌሎቹ ሥራዎቻችን እንዴት እናስፋ በሚልም ነው በጉዳዩ ዙሪያ ስንወያይበት የነበረው። ምክንያቱም ምርጫው ስኬታማ ይሆን ዘንድ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፤ ከዚህም የተነሳ በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል። ስለዚህም ይህን በምርጫው በኩል ያገኘነውን ተሞክሮ ወደሌላውም ለማስፋት ነው እየሰራን ያለነው። የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተን በመንቀሳቀስ ያለነው የግብርና ሥራ ነውና በዚህ ላይ አጠናክረን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- የዞኑ አርሶ አደር እንደ ችግር የሚያነሳው ነገር ምንድን ነው? አርሶአደሮች ጥያቄው ካላቸው ምን ዓይነት መፍትሔ ሰጣችኋቸው?
አቶ ባይነሳኝ፡– ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ የዩሪያ ማዳበሪያ አቅርቦት ነው። ይህን ፍላጎት ለማሳካትም ክልሉም ጨረታ አውጥቶ የዩሪያ ማዳበሪያውን ለማቅረብ እየሰራ ሲሆን፣ ዞኑም ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት በመነጋገር ላይ ይገኛል። እሱም ፈጥኖ እንዲመጣ የማድረግ ሥራ እየሰራን ነው።
ሌላው የአርሶ አደሩ ጥያቄ መሬቱ አሲዳማ እንደመሆኑ የኖራ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ነው። በዚህ ዙሪያ ያለውንም ችግር ለመቅረፍ በተመሳሳይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን አቅርቦት ላይም ፍላጎት ላይም ያለውን ክፍተት ግንዛቤ በመፍጠር በመስራት ላይ እንገኛለን። እንደ ግብርና ክፍተቶች ናቸው ብለን የለየናቸው አሁን በጠቀስኳቸው አካባቢዎች ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ከሌላ ክልል የመጡ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፤ ለእነዚህ ተፈናቃዮች የተለያየ አካል የተቻለውን ድጋፍ ሊያደርግ ቢችልም እንደዞን በብዙ ሺህ የሚገመት ተፈናቃይ መኖሩ ቀላል የሚባል አይደለምና እያጋጠማችሁ ያለው ችግር እንዴት ይገለጻል? በምን አግባብስ እየተፈታ ነው?
አቶ ባይነሳኝ፡– ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ እውነት ለመናገር በዚህ ዓመት ከፈተኑን ሥራዎች አንዱ ነው። እንደሚታወቀው እንደ አገር ባለፈው ዓመት የነበረው ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ከባድ መሆኑን አሁን ላይ መጥቀስ አልፈልግም።
ይህ ከሚኖርበት አካባቢ ተፈናቅሎ በዞኑ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል ብዙ በደል የደረሰበት ነው። ቤተሰቡን፣ አለኝ የሚለውን፣ የቅርቡን ያጣ ነው። የከፋ አገዳደልንም ሳይወድ በግዱ የተመለከተ ነው። ከዚህም የተነሳ የሥነልቦና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባው የህብረተሰብ ክፍል ነው እየተንከባከብን ያለነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረው ሁኔታ ባላሰብነው መንገድ የመጣብን መሆኑም አንዱ ፈታኝ ከሆኑ ነገሮች መካከል የሚመደብ ነው።
እርዳታውን አሰባስቦ ፈጥኖ በመድረስ በኩል ከፍተኛ ችግሮች ገጥመውን ነበር። ነገር ግን እውነት ለመናገር በአካባቢው ያለ ሰው በጣም መልካም የሆነ እና ተባባሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ልብስ ለሌለው ልብስ፣ እህልም በማቅረብ እና በሌሎችም ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ነው በተለይ ጓንጓና ቻግኒ አካባቢ ሲያደርግ የነበረው።
በተለይ ከመንግስት የሚመጣ አቅርቦት እስከሚፋጠን ድረስ ያለውን በመሸፈን በኩል የሕዝቡ ርብርብ ከፍተኛ ነው። ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረገው ርብርብ መቼም ቢሆን ታይቶ የማይታወቅ ነው። ከአገር ውስጥ፣ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተደረገው ርብርብ መልካም የሚባል ነው። የነበረው ችግር ምንድን ነው ቢባል ይህን ድጋፍ በአግባቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ በማድረግ በኩል ክፍተቶች መኖራቸው ነው። በተደጋጋሚ ለማረም ጥረት ተደርጓል። እሱ ብቻም ሳይሆን ችግር በፈጠሩ አካላት ላይም ርምጃ እስከመውሰድ ደርሰናል።
በዚህ ረገድ ወጣ ገባ የሆኑ ችግሮች ነበሩ፤ በዋናነት ግን ሁኔታው ከታወቀ በሁሉም አካላት ርብርብ ከጀመሩ በኋላ የዚያን ያህል ክፍተት አልነበረም። ክፍተቱ የነበረው የተፈናቃዩ ቁጥር በጣም ከፍ ያለ ከመሆኑ ጋር በወቅቱ በአግባቡ ከማስተናገድ ጋር በተያያዘ ነበር። ይህም ቢሆን ከጊዜ ወደጊዜ በተደረገው ጥረት እየተሻሻለ ነው የመጣው።
በዚህ መንገድ ማስቀጠሉ ፋይዳ ስለሌለው ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ምንድን በሚል የሁለቱም ክልል አመራሮችና በተለይ አዋሳኝ ቦታ ላይ ያለን የአዊና የመተከል ዞን አመራሮች በቅርበት በመነጋገር እነዚህ ተፈናቃዮች መመለስ አለባቸው በሚለው ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘን ወደነበሩበት አካባቢ ለመመለስ አካባቢው ምቹ ነው ወይስ አይደለም? ምን ዋስትናስ አላቸው? ዋስትናስ እንዲኖራቸው መደረግ ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ያለውስ ጥበቃ ምን ይመስላል የሚለውን በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል።
በአካባቢው ሁላችንም እንደምናውቀው አማጽያን ነበሩ። እነዛ አማጽያን እጃቸውን ሰጥተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሐድሶ ወስደው ወደአካባቢያቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተደርጓል። ያም ሆኖ ግን አሁን ወጣ ገባ የሆነ ችግርና ስጋት አለ። ከዚያ ውጭ የተጠናከረ የመከላከያ ኃይል እንቅስቃሴ አለ። ልዩ ኃይልም በተመሳሳይ እንዲሁ። ከዚህ ውጭ ደግሞ በራሱ በህብረተሰቡ የሰለጠነ የሚሊሻ ኃይል እንዲኖረው በማድረግ በኩል የተሰራ ሥራ አለ። ይህን ካደረግን በኋላ እንደከዚህ ቀደሙ በየቦታው መበተን ሳይሆን አንድ አካባቢ ላይ ራሱን አደራጅቶ መከላከል በሚያስችለው መንገድ መስፈር አለበት በሚል የጋራ መግባባት ላይ ተደረሰ። የት የት አካባቢ ይስፈሩ የሚለውም ጉዳይ የጋራ ተደረገ። መስፈሪያ ቦታቸው ለብቻው፤ እንዲሁም የእርሻ ቦታቸውም ለብቻው በተቀራራቢ ሁኔታ መመቻት አለበት የሚለውን የጋራ በማድረግ በአሁኑ ሰዓት ወደየመጡበት መንቀሳቀስ ጀምረዋል። በተለይ ማንዱራን በቅርቡ አንቀሳቅሰናል።
ተፈናቃዩን በእኛ ትራንስፖርት ካንቀሳቀስነው በላይ በራሱ አማራጭ መንገድ ተጠቅሞ የገባ ማህበረሰብ አለ። እየገባም ጭምር ነው። በእርግጥ እኛም ህብረተሰቡም የፈለገው በቀጣይ ክረምት ውስጥ ገብቶ አምርቶ ለሚቀጥለው ዓመት ራሱን በምግብ የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው። ይህ ካልሆነ ግን እዛም ተመልሶ የሚደገፍ ኃይል መሆን የለበትም።
የተፈናቃዮችን መመለስ የጉሙዝ ብሄረሰብ አካላትም ይፈልጉታል። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ እርሻውንም የሚያርሱት በጋራ በመሆኑ ነው። እርሻውን እየተላመዱ የመጡት ከዚህ ከተፈናቀለው የህብረተሰብ ክፍል ነው። በመሆኑም መመለሳቸውን ይፈልጉታል። ነገር ግን ከበስተጀርባ ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ናቸው እንጂ የሚበጠብጡት ከህብረተሰቡ ጋር ምንም አይነት መሰረታዊ ችግር የለም። ለዚህም ነው አሁን ተፈናቃዩ ወደኋላ መመለስ የጀመሩት።
በዚህ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ታላላቅ ባለሀብቶች ጭምር ተፈናቃዩን ለማቋቋም በተለይ ደግሞ ለቤት መሥሪያ የሚሆን ቆርቆሮ በማዘጋጀት፣ ማሳው በትራክተር እንዲታረስ በማድረግና መሰል ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው የሚገኙት። ይህን በማድረግ ረገድም በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውም ጭምር ጥሩ የሚባል ውጤት በመታየት ላይ ነው።
እንዲያም ሆኖ አሁንም ጥበቃ ያስፈልጋል፤ ይህን ቁርጠኝነት ደግሞ መከላከያ ወስዷል። ከአሁን በኋላ እኛ እየሞትንም ቢሆን እናንተን የማዳን ኃላፊነት አለብን፤ ከዚህ በላይ እድል አንሰጥም። በመሆኑም በዚህ ላይ ቁርጠኝነቱ አለንና እመኑን በሚል ህብረተሰቡን አወያይተዋል። በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ ወደእዛ በመመለስ ላይ ይገኛል። ስለዚህም እየሰራነው ያለው ነገር ተስፋ የሚሰጥ ነገር አለው። ዞሮ ዞሮ ግን ጥንቃቄ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ተፈናቃዮች ናቸው ያሉት? ካለው ቁጥርስ ገሚሱ ተመልሷል ማለት ይቻላል?
አቶ ባይነሳኝ፡– ቻግኒ ብቻ የነበረው ተፈናቃይ ወደ 45 ሺህ አካባቢ ነው፤ ከዛ ውጭ በየወረዳው ያለው ከ90 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ይሆናል። ይህ ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር ጫናውም የዚያ ያህል ከባድ ነው የነበረው። በነገራችን ላይ የከበደን በየአካባቢው ያለው ሳይሆን አንድ አካባቢ ቻግኒ አካባቢና መንትዋ አካባቢ ያስቀመጥነው ኃይል ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመኖሪያነትም ምቹ ስላልነበረ ጫናው ከፍተኛ ነበር።
ከዚህ ከ90 ሺህ ተፈናቃይ ውስጥ እየተመለሰ ያለ ኃይል አለ፤ አሁን በቅርቡ እንኳ ወደ 15 ሺህ አካባቢ እንደተመለሰ መረጃው አለኝ። ሌላው ግን የሚመለስበት ስፍራ ምቹነቱን ካረጋገጥንለት እኛንም ሳይጠብቅ በራሱ ጊዜ የሚሄድ አለ፤ እየሄደም ጭምር ነው። ወደመጣበት ለመመለስ ደግሞ በጣም ትልቅ ፍላጎት አላቸው።
በዚህ ውስጥ ግን ሌላም ፈተና ገጥሞናል። በጭራሽ መሄድ የለብንም የሚሉ ጥቂት ሰዎች ገጥመውናል። ጉዳዩን ለማጥናት በሞከርንበት ጊዜ አንዳንዶቹ የራሳቸው ተልዕኮ ያላቸው ሆነው ነው ያገኘናቸው። ከተማ ውስጥ ሆነው መኖሪያ ቤት ያላቸው፤ እርሻ ያላቸው፤ ግን ተፈናቃይ ነን በሚል ብቻ ከህብረተሰቡ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የመሄድ ፍላጎት አላሳደሩም ነበር፤ መጨረሻ ላይ ግን ሰዎቹን በመለየትና ራሱን የቻለ ውይይት በማድረግ እንዲረግቡ ከማድረጋችንም በተጨማሪ ወደየመጡበት እየሄዱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወሳኝ የሆኑ ትልልቅ ማሽነሪዎች በዚህ ዞን አቋርጦ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞና ዞኑ ካለውም ቅርበት አኳያ ለህዳሴ ግድቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ባይነሳኝ፡– ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ መንገድ በአመራሩም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ነው። ህዳሴ ግድብን እንዲሁ እንደተራ ነገር የምናየው አይደለም። ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነትና ከዛ በመለስ ያሉ ነጻ በሚወጡበት ወቅት ነጻ ያወጡት ራሳቸውን ብቻ አይደለም። አፍሪካውያኑንና ሌሎቹንም ጥቁር ሕዝቦች ጭምር ነው።
ከእነዚህ ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ቅኝ አዙር አገዛዝ አሁንም አልወጣንም። ሲፈልጉ በአይ.ኤም.ኤፍ ሲፈልጉ በዓለም ባንክ ሲፈልጉ ደግሞ በሌላ መንገድ ኃያላኑ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው ያሉት። ህዳሴ ግድብ በዚህ መንገድ መጠናቀቅ ለእኛ ሌላኛው ድል ነው ። በተለይ ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካውያንና ለመላ ጥቁሮች። ከዚህ በኋላ በኢኮኖሚውም ጉዳይ ዝም ብሎ የሚቀመጥ አገር ይኖራል ብለን አናስብም። ከዚህ አንጻር ግድቡ ለኢትዮጵያ ሌላ ታሪክ ነው። አመራሩ የሚገነዘበው በዚህ ደረጃ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ ነው፣ በተጨማሪም አገርን ከአገር ጋር የማስተሳሰር አቅሙ ከፍ ያለ ነው።
በተለይ ደግሞ ለአዊ ሕዝብ አካባቢው በዚህ መንገድ ከለማ በኢትዮጵያ ውስጥ የቱሪስት መስህቡና ሌሎችንም ጥቅማጥቅሞች ከማምጣት አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። በአካባቢው የቱሪስት ምልልሱ በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምር ነው የሚሆነው። ከዚህ አንጻር ለአዊ ሕዝብ ልዩ ስጦታ ነው።
አሁን አሁን የሰው ግንዛቤ እያደገ መጥቷል፤ ግድቡ በጎርፍ ከተሞላ የደለል አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችልና ከዚህ አንጻር ደንን በማልማት ችግሩን ለማስወገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በጣም ከፍተኛ ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን በዚህ አካባቢ እንዳየሁት ለግድቡ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችም ሆነ ሌሎች እቃዎች ይጓጓዛሉ። ሕዝቡ ይህን እቃ ባለቤት ሆኖ ነው የሚጠብቀው። ሌላው ቀርቶ በአካባቢው እቃ የያዙ ተሽከርካሪዎች መጥተው ነዳጅ አጥተው ቆመዋል ከተባለ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የሚደረገው። በአገራችን ላይ በግድቡ በሚመጣ ጫና ሕዝቡን አንድ እያደረገ ነው። ህዳሴ ግድብ ልዩነትን እያጠፋ ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ዞኑ ኢንቨስተሮችን ሊስብ የሚያስችለው ምን ምቹ ሁኔታ አለው ይላሉ?
አቶ ባይነሳኝ፡– አዊ እውነት ለመናገር በብዙ ረገድ የታደለ ዞን ነው። በማዕድኑ ዘርፍ ቢመጣ ወርቅ፣ እምነበረድ፣ የኖራ ድንጋይና ሌሎችም አሉ። በተለይ ወደዚገምና ሌሎችም አካባቢዎች በጣም ከፍ ያለ ክምችት አለ። በአካባቢው ጥቁር ድንጋይ(ግራናይት) ጭምር አለ። ብዙ ባለሀብቶችም ስራዎችን እየሰሩ ናቸው።
ከዚህ ውጭ በግብርናው መስክም ጃዊ የሚባለው ሰፊ ወረዳ ሲሆን፣ በሰሊጥና በአኩሪ አተር አምራችነቱ የሚታወቅ ነው። እነዚህ ምርቶች ደግሞ ወደውጭ ለመላክም ሆነ ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ፍጆታ በጣም ተፈላጊ የሆኑ ናቸው። ከዚህ አንጻር በሁለቱም ላይ በስፋት እየተሰራ ነው። ስለሆነም ባለሀብቶች ወደዞኑ መጥተው ፋብሪካ መክፈት ቢችሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው።
ሌላው የደን ውጤት ነው። አዊ በቀርከሃ ምርቱ በጣም ይታወቃል። በቀርከሃ ቻይና ብንመለከት በጣም በርካታ ስራዎች የሚሰሩበት አገር ነው። በመሆኑም ባለሀብቶች ቢመጡ በከፍተኛ ደረጃ አቅርቦቱ ስላለ አዋጭነት ይኖረዋል እንላለን። እኛ ዘንድ ያለው ቀርከሃ ሁለት አይነት ነው፤ የደጋ ቀርከሃና በተለምዶ ሽመል የምንለው አይነት የበረሃ ቀርከሃ ወደመንትዋ፣ ጃዊ አካባቢ በስፋት አለ። እንደ ዞን የደን ሸፋኑ 38 በመቶ እንደመሆኑ የወረቀት ፋብሪካዎችን ከመክፈት አንጻር እድሉ አለ። በመሆኑም የትኛውም አካል ፍላጎት የሚኖረው ከሆነ ሁኔታዎች ምቹ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ አዲስ የተከፈተ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ለአካባቢው ህብረተሰብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል?
አቶ ባይነሳኝ፡– የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ አዲስ እንደምንለው አይነት አይደለም። በጣም በጥሩ አቋም ላይ ያለ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ከሚሰጡት አገልግሎት መካከል አንዱ ጥናትና ምርምር ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ቢሆንም ጥሩ ነገር በመስራት ላይ ይገኛል። በዞናችን ሶስቱም የአየር ጸባይ ሁኔታ ነው ያለው። በእነዚህ አካባቢዎች ዩኒቨርስቲው የሚያስፈልገውን መሬት በመውሰድ የምርምር ስራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች የጀማመራቸው ስራዎች ሲኖሩ ዋሽራ፣ ዳንግሌ የሚባል የበግ ዝርያን ከሌሎች ጋር በማዳቀል እንዳይጠፋ ስራ በመስራት ላይ ነው። ከዚህ ውጭ የተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። እነዛን የማህበረሰብ ክፍሎች ፕሮጀክት በመቅረጽ በዶሮ ርባታ፣ በእንስሳት ሀብት ልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እየሰራ ነው። በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት በኩል በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው። ለሆስፒታሎችም የአልጋና የመሳሪያዎች አቅርቦት በማድረጉ የሚያስመሰግን ስራ ሰርቷል። አዲስ እየተመሰረተ ላለውም የዚገም ሆስፒታል ላይ ስራዎችን ከወዲሁ ለመስራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ባይነሳኝ፡– እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2013