ዓለማችንን በአንድ ድምጽ ሊያግባቡ ከሚችሉት ጥቂት ነገሮች መካከል ዋናው ሙዚቃ መሆኑ ይታመናል:: ሙዚቃ የዓለም ሕዝቦች መግባቢያ ቋንቋ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው:: በተለያየ ቋንቋ የሚወጡ ዘፈኖች ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚነጋገሩና የማይደማመጡ ሰዎችን በአንድ ድምጽ ሊያግባባቸው ይችላል:: የሕይወትን ለዛና ቃና በማጣፈጥም ትልቅ ድርሻ አለው:: በትንሽ ደቂቃ አያሌ ነገሮችን የመግለፅ እምቅ አቅምም አለው:: አንዳንዶች ሕይወት በራሷ ያለሙዚቃ መዓዛ፣ ለዛና ቃና የላትም ይላሉ ::
ቴዎድሮስ ነጋሽ የፍሉት ሙዚቃ (የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ )ተጫዋች ነው:: በብሔራዊ ቲያትር የሚሠራው ቴዎድሮስ ነጋሽ በብዛት በሚጫወተው የሙዚቃ መሣሪያ ሰዎች ቴዲ ፍሉት በሚል ቅጽል ስያሜ ይጠሩታል::
ቴዎድሮስ ነጋሽ ውልደቱና ዕድገቱ በአዲስ ከተማ አካባቢ ነው:: ታዳጊ እያለ ታላቅ ወንድሙ ባለው የሙዚቃ ፍቅር የሙዚቃ መሣሪያዎችን ይጫወት ስለነበር የቴዎድሮስንም የሙዚቃ ፍቅር አቀጣጠለው:: ይህም ለዛሬ ሕይወቱ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው::
ታላቅ ወንድሙ ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መመረቁ ፤በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የሚዘጋጁ ኮንሰርቶችን የሙዚቃ መሣሪያ ቅንብር ጨዋታዎችን እያደነ እንዲከታተል ረዳው:: ይህ ወንድሙ በሞት ሲለይም ቴዎድሮስ ለአፍታም ቢሆን ከሙዚቃው አለም አልወጣም፤ ይልቁኑም እንደዱላ ቅብብል የሩጫ ውድድር ሙያውን ተቀብሎ በስኬት አስቀጥሎታል::
በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ በሚዲያ ክበብ ይሳተፍ እንደነበርም ቴዲ ያስታውሳል:: ይህም ወደ መዝናኛው ዓለም ሥነጽሑፍ ክበብ እንዲጠጋ ረዳው:: ግጥም የመጻፍ ክህሎቱን ያጎለበተለት ወደ ሙዚቃው ክበብ ይበልጥ እንዲጠጋ የረዳውም ሆነ:: በምታልፈዋ በእያንዳንዷ ቀን የልብ ትርታውን እያዳመጠ የፍሉት ሙዚቃ መሣሪያን ከማፍቀር አልፎ መሞከርና መጫወት ጀመረ::
በከዋክብት የሥነጽሑፍና የሙዚቃ ክበብ መግባቱም ለእርሱና ለሌሎች ሙዚቃና ሥነጽሁፍ ለሚወዱ ሰዎች በር የከፈተ ነበር:: ቴዎድሮስ በከዋክብት ክበብ በመታቀፌ ሙዚቃ እንኳን ደህና መጣህ ብላ በሩን በርግዳ የተቀበለችኝ ያህል ይሰማኛል ሲል ይገልጻል:: በዚያም ሆኖ የሙዚቃውና የሥነጽሁፍ ሥራውን ቀጠለ:: የዕለት እንጀራውን አበሰለ፤ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን መስራት ውስጥ ገባ ::
ቴዲ ሙዚቃ ውስጥ እያለም የቀለም ትምህርት መከታተል አላቆመም:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን አጠናቆ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) ተማሪ ሆነ ፤ሁለት ዓመት እንደተማረ ባጋጠሙት ማኅበራዊ መሰናክሎች በወቅቱ በነበረው ባልተረጋጋ ፖለቲካ እና ለሙዚቃ በነበረው ፍቅር ትምህርቱ አቋረጠ::
ሕይወቱ ስትናፍቀው የነበረችውን የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት አምስት ዓመታት ተከታተለ:: በዚህም ፍሉት ዋና ኮርስ ፒያኖ ንዑስ ኮርስ ተምሮ በዲግሪ ተመረቀ :: የቀለም ትምህርቱን በቃ ብሎ ጨርሶ አላቆመውም :: ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ሁለት ዓመት ተምሮ ያቋረጠውን ትምህርት ቀጥሎ በንግድ ሥራ አመራር በዲግሪ ተመረቀ :: ጠንክሮ በመማሩም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እና በሙዚቃ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁለት ዲግሪ አግኝቷል::
በሙዚቃ ሥራው በጣም የሚወደውና የማይዘነጋው የመድረክ ሥራ እንዳለውም ቴዎድሮስ ይጠቅሳል :: ይህም በጣሊያን የባህል ማዕከል በ2008 ከሙዚቃ መሣሪያ አቀናባሪና ከፒያኖው ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ ጋር የተጫወተው ኮንሰርት ነው :: ታዳሚው ሙዚቃውን እየሰማ ሲያደንቅና ሲያጨበጭብ ወደ ሙያው የበለጠ እንዲዘልቅ አበረታታው:: በፍሉት ሙዚቃም የበለጠ እንዲገፋ፣ የፍሉት ሙዚቃ አድናቂዎችን ለማነሳሳት ብዙ ርቀት ለመሄድ እና በተጨማሪም የበለጠ የፍሉት ሙዚቃ አድናቂ ትውልድ ለመፍጠር እንዲወስን ረዳው :: በፍሉት የሙዚቃ መሣሪያ ተጫውቶ በዩቲዩብ የለቀቃቸውና በቴሌቪዥንም የሚለቀቁ በፍሉት የሙዚቃ መሣሪያ የተጫወታቸው ሙዚቃዎች አሉት::
ቴዎድሮስ በሙዚቃው ብቻ ሳይሆን በሥነጽሁፍም ይንቀሳቀሳል ፤ ሁለት የግጥም መጽሐፎችን አሳትሟል:: መጻሕፍቱ ስሞት ዝም አትበይኝና ስካርና ፍቅር የሚሉ ናቸው:: ዘግይቶም ቴዲ ፍሉት ሁለቱን የግጥም መጻሕፍት በአንድ ጥራዝ አሳትሞ 12ሺ ኮፒ ሸጧል:: ስለ ሙዚቃ እያወራን ስለሆነ የነብስ ሙዚቃ በሚል ርዕስ ከጻፈው ግጥሞ ቀንጭቤ ላስነብባችሁ አሻሁ::
እስቲ ጸጥበሉ ሙዚቃ ይሰማኛል
ከቅርብም አይደለ ከሩቅ ይስበኛል
ጫዋታው ይቆየን እንደርስበታለን
ሀሳቤ ከዛ ነው አጥቻለሁ ቀልቤን ፤
ከተራራው ጋራ ከዋክብት ካሉበት
ከጨረቃው ግርጌ ውበት ከሞላበት
ሾፐን ሀይድን ሞዛርትም መሰለኝ
ረቂቅ ሙዚቃን ከፍቶ የሚያሰማኝ፤
አይደለም አይደለም የማንም አይደለም
መላዕክት መሰሉኝ ሰምቼው አላውቅም
ልዩ ነው ሙዚቃው ነብስ የሚያለመልም፤……
ከነዚህም ውስጥ 18ቱን ግጥሞቹን በንባብና በሙዚቃ በማጀብ “ግጥም በሙዚቃ” ከሙዚቃ አቀናባሪው ብሩክ አሰፋ ጋር በመሆን በዩቲዩብ የኩሽ ሙዚቃና አርት ቻናል ሥራ ዎቹንለቋቸዋል::
ቴዎድሮስ ለታዳጊዎችና ወጣቶችም ምክር ይለግሳል:: ታዳጊዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ለሙዚቃ ጥበብ ፍላጎቱ ካላቸው የልብ ትርታቸውን አድምጠው መደበኛ ትምህርታቸውን እየተማሩ ጎን ለጎን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ጥረት ማድረግ አለባቸው ይላል:: ሰዎች ስኬት እጃቸው ላይ የሚገባው ሲፍጨረጨሩ እና ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ወጣቶች ጋር በየጊዜው ሲገናኙ ሲመካከሩና ያሰቡትን ለመተግበር ሲሞክሩ መሆኑን ቴዎድሮስ ነጋሽ ይናገራል ::
ዓላማ ካላቸው ግባቸውን ለማሳካት መጣርን ሊዘነጉት አይገባም፤ድምፃዊም ሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች የአሰበበት ቦታ የሚደርሰው ጥረት ሲያደርግ ነው ሲል ያብራራል::
ያደግኩት መሀል መርካቶ አካባቢ ቢሆንም አስካሪ መጠጥ ሲጃራ ጫት በመሳሰሉ ደባል ሱሶች ተዘፍቄ አልወድቅኩም ያለው ቴዲ፣ በአዲስ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያሉ ወጣቶች በሙሉ ዓላማቸውን ለማሳካት ከሱሰኝነት መራቅ ይጠበቅባቸዋል ሲል ይመክራል::
አንዳንድ አስተዋይ ወጣቶች የጠቀስናቸው ሱሶች ቢኖሩባቸውም ራሳቸውን ተቆጣጥረው ለስኬት ሲደርሱ ይስተዋላል:: እኔ ለታዳጊ ወጣቶች የምመክረው ፊልም ቲያትርን ድራማን ሙዚቃን ከማየትና ከማድነቅ ባለፈ ተምረው የሚተውኑበትን የሚጫወቱበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው ነው:: ለዚህ ደግሞ በትምህርት ቤትም በመኖሪያ አካባቢም ጥበብ አፍቃሪ ሰው አክባሪ ዜጋ ወዳጅ ማድረግ የተሻለ ነው ሲል ቴዎድሮስ ነጋሽ ይናገራል::
ቴዎድሮስ ነጋሽ ሥራዎቹ በኢትዮጵያ ሚዲያና በዩቲዩብ ተመልካቾች መለቀቃቸው ዕውቅናን አስገኝቶለታል:: በአሁኑ ወቅት የኩሽ አኩስቲክ ባንድ ከጓደኞቹ ጋር መሥርቶ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በየሳምንቱ አርብና ማክሰኞ ምሽት በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ይጫወታል:: በተጨማሪም ሥራዎቹን በዩቲዩብ የኩሽ ሙዚቃና አርት በሚል ይለቃል:: የሙዚቃ መሣሪያዎች መጫወት የሚፈልጉ ሰዎችንም በማሠልጠን ተተኪ የሥነጥበቡን ባለሙያዎች ለማፍራት ጥረት እያደረገ ነው::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2013