
አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ የሚታዘቡ ከ15 ሺ በላይ ሴቶች ማሰማራቱን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ። ከአራት ነጥብ ሦስት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የመራጮች ትምህርት መስጠቱን ገለጸ።
የኢትጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሂደት አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ታዛቢዎች በሚሰማሩባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የተቀመጠውን ህግና ደንብ ተከትለው እንዲሠሩ ለማድረግ አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቷል።
ሁሉም ታዛቢዎች የተጣለባቸው አገራዊ ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ ያመለከቱት ገነት ስዩም፣ የኃላፊነቱን ክብደት በአግባቡ በመገንዘብ በአግባቡ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሲቪል ማህበራት የምርጫው ሂደት አካታችነት፣መቆየቱን ጠቁመዋል። እንደ አጠቃላይ ያለው የሲቪል ማህበራት ተሳትፎ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዚህም ለአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሴቶች የመራጮች ትምህርት ለመስጠት አቅዶ አራት ነጥብ ሦስት ለሚሆኑ ሴቶች ተደራሽ አድርጓል። የምርጫውን ሂደት ለመታዘብም 15 ሺህ 778 ሴቶችን አሰልጥኖ ማሰማራቱን ገልጸዋል።
ሴቶች ተመዝግበው ለመምረጥ የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲወስዱ ለማድረግ ቤት ለቤት ቅስቀሳ በማድረግ ስድስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሴቶችን መድረስ መቻሉንም ፌዴሬሽኑ ባለው መረጃ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እስከአሁን ከተደረጉ ምርጫዎች የተሻለ የሴቶች ተሳትፎ የታየበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከስምንት ሚሊየን በላይ ሴቶችን እና 50 የሴት ማህበራትን በስሩ ያቀፈ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013