
- የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጅት መጠናቀቁም ተገለጸ
ቻግኒ፦ ምርጫው በቻግኒ ከተማ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የከተማው አስተዳደር የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ አጋዢ አስታወቀ።
አቶ ተሰማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች እንዳስታወቁት፣ በቻግኒ ምርጫ ክልል ባሉ 19 ምርጫ ጣቢያች የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ነዋሪውን ባሳተፈ መልኩ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
በተለይም ወጣቱን በማደራጀት ሰላሙንና የከተማዋን ሰላም እንዲጠብቅ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወቁት አቶ ተሰማ ፣ ሌላውም የከተማዋ ነዋሪ በጸጥታው ዙሪያ ሰላሙ እንዲጠበቅ የራሱን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የጸጥታ ኃይሉ፣ ሚሊሻው፣ ፖሊሱና ሁሉም በትብብር ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የየቡካላቸውን እየተወጡም ናቸው። በምርጫ ጣቢያው አካባቢ ምንም ዓይነት እንከን እንዳይኖር ሚቻለው ሁሉ እየተደረገ ነው። ከምርጫም በኋላ ከተማው ሰላማዊነቱ የተጠበቀእንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዜና በቻግኒ ምርጫ ክልል ስር ከሚገኙ 72 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል በቻግኒ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ ድምፅ ለሚሰጠው ህዝብ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ መሰናዳታቸው ተገለጸ።
ስድስተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመዘገብ በስፍራ የሚገኙ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች በቻግኒ ከተማ ተንቀሳቅሰው ምልከታ ባደረጉበት ወቅት፤ በምርጫ ጣቢያ 03 ቀበሌ፤ የአምስቱ ምርጫ ጣቢዎች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ወንድሜነህ ቻላቸው እንደገለጹላቸው፤ በምርጫ ጣቢያዎቹ ለመራጮች በሚመች ሁኔታ አስፈላጊ ዝግጅቶች ተካሂደዋል።
በየምርጫ ጣቢያዎቹ ክረምቱን ተከትሎ ዝናብ ምርጫውን እንዳያስተጓጉል ድንኳንም በመትከል ጭምር ለመራጩ ህብረተሰብ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ተጥሯል። ለምርጫ አስፈጻሚዎችም ሆነ ምርጫ ታዛቢም ጭምር አስፈላጊው ሁሉ መሟላቱን አስታውቀዋል።
የድምፅ አሰጣጡ ከተጠናቀቀ ከምሽቱ 12 ሠዓት በኋላ ለሚደረገው የድምፅ ቆጠራ ችግር እንዳይኖር ምናልባት መብራት ቢጠፋ እንኳን በየጣቢያው ጄኔሬተር ተዘጋጅቷል። ከዚህ ቢያልፍ ደግሞ ፈጣን የሆነ በጸሐይ የሚሠራ ብርሃን ሊሰጥ የሚችል መብራትም ተዘጋጅቷል። መራጩ ህዝብ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መንገድ ይመርጥ ዘንድ ርቀቱን ሊጠብቅ በሚያስችለው መልኩ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013