
አዲስ አበባ፡- መጪው ምርጫ አገርን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ሁነቱ ህጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ አሸናፊ እንድትሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውንም በከፍተኛ ጥንቃቄ መወጣት እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ።
መጪው ምርጫ ሰላማዊ በማድረግ ረገድ የባድርሻ አካላትን ሚና በሚመለከት በተለይ ለአዲስ ዘመን ያነጋገራቸው በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አብዱ መህመድ አሊ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዓመታት ነጻ ፍትሃዊ እና ተአማኒ ምርጫ ሲናፍቅ ቆይቷል።
ይህንን የህዝብ መሻት ትርጉም ባለው መልኩ ለመመለስ በተለይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ወቅቱ ለህዝብ መቆማቸውን የሚያሳዩበት ታሪካ አጋጣሚ እንደሆነ አመልክተዋል።
በምርጫው ሰላማዊ አውዱን ጠብቆ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ገዢውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እስካሁን በምርጫው ሰላማዊ መንገድ እየተከተሉ መሆኑን ያመለከቱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በምርጫው እለትም ሆነ ማግስት ይህን ማስቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ግንዛቤ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይሁንና ‹‹ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ከቆጠራ አስቀድሞ እዚህ ቦታ ላይ አሸንፋለሁ በማለት ህዝብን ወደ አልተፈለገ መንገድ ከመምራት መቆጠብ አለባቸው›› ብለዋል።፡
የምርጫው ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ እንደሚወስን የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ምርጫው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዴሞክራሲያዊ እና ዘመናዊ አገር ውስጥ መግባታችንን ያሳየናል ብለዋል።
ሁሉም ባለድርሻዎች ምርጫው ህጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ ቢችሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናት የዴሞክራሲ ሥርዓት ትግል እና ምኞት እውን እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ አይናቸውን አፍጥጠው የሚገኙ አገራት ቆም ብለው እንዲያስቡና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገነባን መሆኑን እንዲያረጋግጡ ያእንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ኤባ በበኩላቸው፣ ‹‹መጪው ምርጫን የተለመደው ቀልድ አይደለም። አገርን የማስቀጠል እና ያለማስቀጠል ጉዳይ ነው ብለዋል።
ምርጫው ህጋዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መራጩ ህዝብም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለራስ ይልቅ አገርን ማስቀደም አለባቸው። ሁለት አገር እንደሌላቸውና ከሁሉ በላይ አገር ስትኖር ብቻ ምርጫ እንደሚካሄድ ማወቅ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያ እንድታሸንፍም ህግና ሥርዓትን በአግባቡ ማክበርና ማስከበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2013