
አዲስ አበባ፦ 6ተኛው አገራዊ ምርጫ በተለይም ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ከተሳታፊነት ባለፈ ንቁና ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ አካታችነት ክፍል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መድሃኒት ለገሰ አስታወቁ።
ወይዘሮ መድሃኒት በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ቦርዱ በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ከተሳታፊነት ባለፈ ንቁና ብቁ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች ሰጥቷል ።ሥልጠናዎቹ የተመራጭነት አቅማቸውን ከማጎልበት ባለፈ የወደፊቱ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ያሳድጋል።
በቦርዱ በኩል ተፈጻሚ የሚሆኑ ደንቦችና ድንጋጌዎች የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል እስከ አሁን ድረስ ከነበሩት የምርጫ ህጎችና ድንጋጌዎች በተሻለ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የአካታችነት መስፈርቶችን ያሟሉ ለማድረግም ከፍተኛ ሥራ ተሰርቶ ውጤት መታየቱን ገልጸዋል።
የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን እንዲያካትት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩልም በፕሮግራማቸው በምርጫ ዘመቻቸው በጠቅላላው አሠራራቸውና በሚያስተላልፉት መልዕክት ሁሉ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ በምክክር መድረኮች በማወያየት ለውጦች መታየታቸውን ጠቁመዋል።
በምርጫ ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን ከሚያከናውኑ የሲቪክ ማህበራት ጋር በአካታችነት ዙሪያ በርካታ ስራዎችን መስራታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ መድሃኒት፣ ማህበራቱ ከስርዓተ ትምህርት ዝግጅታቸው ጀምሮ ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ጭምር አካታች ማድረግና ተደራሽነቱ ላይም በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው የሚያስገነዝቡ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል ብለዋል።
የቦርዱ የምርጫ ማስፈጸሚያ ሰነዶች ማለትም ከተለያዩ ክፍሎች የሚወጡት የሴቶችና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ወይ የሚለው እየተፈተሸ እንዲሄድና ክፍሉም የራሱን ግብዓት እንዲያካትት የሚያስችለው አሰራር ተፈጥሮ በዛም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በምርጫ ተሳታፊነት ላይ በዚህ ደረጃ ስልጠና አግኝተው አያውቁም ያሉት ወይዘሮ መድሃኒት፣ ሁሉም እጩዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉ የሥልጠናው ርዕስ አግባብነት ያለው መሆኑ ለምርጫ ሂደቱ መሳለጥ ብሎም ተደራሽነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
እንደ ወይዘሮ መድሃኒት ገለጻ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴትና አካል ጉዳተኛ እጩዎችን አቅርቡ እያልን በተለያየ መድረክ ላይ ስናማክር ነበር ይህ ግን ብቻውን በቂ ካለመሆኑም በላይ እጩ ሆነው የሚቀርቡት ሴቶችም ሆኑ አካል ጉዳተኞች የሚፎካከሩት ከዚህ ቀደም የተወዳዳሪነት ልምዱ ካላቸው በትምህርት ዝግጁነትም የማይመጣጠኗቸው ጋር ስለሆነ ይህ መሰሉ ስልጠና ራሳቸውን በማብቃት ብቁ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ በምርጫው ቢያሸንፉም ባያሸንፉም ለቀጣይ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ትልቅ መሰረት የሚጥል እውቀት ያገኘበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ወቅቱ የምርጫ ሥራ የሚበዛበት በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ እጩ የሆኑ ሴቶች በሥልጠናው ተሳታፊ የመሆን ጉዳይ አሳስቦን ነበር ያሉት ወይዘሮ መድሃኒት፣ ነገር ግን በከፍተኛ ተነሳሽነት ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል። ከተሳታፊዎቹ የተገኘው ግብረ መልስም አበረታች መሆኑን ገልጸዋል ።
ሥልጠናዎቹ በአዳማ፣ ባህርዳር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ አፋር፣ ሐዋሳ እንዲሁም ድሬዳዋ መሰጠታቸውን ፣ ከ1 ሺ3 መቶ በላይ ተሳታፊዎችም እንደነበሩም አስታውቀዋል ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም