
አዲስ አበባ፡- አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ጥቅማቸውን የሚያስከብርላቸው መንግሥት እንዲመጣ ከመፈለግ የመነጨ እንደሆነ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ሰለሞን ተፈራ አስታወቁ።
አቶ ሰለሞን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አንዳንድ ሀገራት ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተጣሱ በሚል በሀገሪቱ ሉአላዊ ጉዳዮች ጣልቃ የመግባት ሙከራ ይስተዋላል። ይህ የኢትዮጵያን እድገት ካለመፈለግ የሚመነጭ፣ አገርን የማዳከም ዘመቻ ነው።
በሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ሰበብ የርዕዮት ዓለም ጦርነት የሚያካሂዱበት ሁኔታ አለ። ለአብነትም ሊቢያና የመን ማሳያ ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ አሜሪካ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጉዳይ የሚያስጨንቃት ቢሆን ኖሮ በህወሓት ኢህአዴግ ሲፈፀም የነበረው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ያሳስባት ነበር ብለዋል።
ዘመቻው በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫና የግድቡ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት በሚከናወንበት ዋዜማ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ በሰብዓዊ መብት ሰበብ በሀገሪቱ ላይ ጫና በመፍጠር ተላላኪ መንግሥት በመፍጠር የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ከሚያደርጉት ሩጫ የመነጨ ነው ብለዋል።
አሜሪካ ማንኛውም መንግሥት የራሷን ጥቅምና ፍላጎት ካስከበረላት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ አያሳስባትም። ጥቅሟ ካሳሰባት ሰብዓዊ መብት ተጣሰ በሚል ዘመቻ እስከ መንግሥት ግልበጣ ድረስ ጣልቃ ትገባለች ብለዋል።
ጣልቃ ገብነቱ የራሷን ጥቅምና ፍላጎት ለማራመድ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ እንደፈለገ የምታዘውና የምታሽከረክረው መንግስት እንዲኖር ካላት ፍላጎት የመነጨ መሆኑንም አመልክተዋል።
በምርጫው በህዝብ የተመረጠና ቅቡልነት ያለው መንግሥት ከተመሰረተ ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽምላቸው ተላላኪ መንግሥት አያገኙም። ስለዚህ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ካለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በሰብዓዊነት ሽፋን ፍላጎታቸውን የሚያሟላ መንግሥት እንዲኖር ለማድረግ እየተሯሯጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህዝብ የሚካሄደውን ምርጫ እውቅና የሚሰጡት አሜሪካ፣ እንግሊዝ ወይም ሌሎች ሀገሮች አይደሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው። ምን አልባትም የኢትዮጵያ መንግሥትም እውቅና መስጠት እንደማይችል አመልክተዋል።
የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን አለመግባባትና ክፍፍል መሰረት ያደረገ ነው። ይህን ለመቋቋም ሁሉም በሀገር አንድነት ላይ አንድ አቋም ሊኖረው ይገባል ። ኢትዮጵያውያን አንድ ፍላጎት አለን። እሱም የበለጸገች፣ አንድነቷ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው ብለዋል።
የውጭ ሀገራት ጫናና የእጅ አዙር ጦርነት የሚያደርጉት የእኛ ድክመት እስከ ቀጠለ ድረስ ነው። ከዚህ ውጭ የኢትዮጵያውን አንድነትና ጥንካሬ እስከኖረ ድረስ የሚገቡበት ቀዳዳ አያገኙም። ጫናውንና የእጅ አዙር ጦርነቱን ለመመከት አንድነትን ማጠናከረ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ሞገስ ተስፋ