
ጎንደር ፦በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ትላልቅ ምርምሮችን ለመስራት 20 አዳዲስ የምርምር ቡድኖች መዋቀሩን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበራዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢኒያም ተክሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ምርምሮችን ለመስራት 20 አዳዲስ የምርምር ቡድኖች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተዋቅረዋል ። ቡድኖች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ችለው ምርምሮችን እንዲያደርጉ ታሳቢ ተደርገው የተዋቀሩ ናቸው።
የምርምር ቡድኖቹ በ2014 ዓ.ም ወደ ተግባር እንደሚገቡ ያስገነዘቡት ዶክተር ቢኒያም፣ ይሄም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ትላልቅ የምርምር ስራዎችን መስራት ያስችለዋል ብለዋል ።
እንደ ዶክተር ቢኒያም ገለፃም፣ በትግበራው የምርምር ውጤቶችን ብቻ አይጠበቁም ። የሚሰሩ ምርምሮች የሚፈለገውን ጥራትና ደረጃ እንዲያሟሉ ይደርጋል ። ምርምሩን ማድረግ የሚያስችል በቂ የበጀት ድጎማ ይደረግላቸዋል ። የፒኤች ዲ ተማሪዎች ከሌሎች ትልልቅ ልምድ ካላቸው ተመራማሪዎች ጋር በማሰራት የአቅምና ልምድ ልውውጥ እንዲቀስሙ ይመቻቻል።
መሰል ትስስሮችም ዩኒቨርሲቲው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ትልልቅ የምርምር ስራዎችን እንዲሰራ ያስችሉታል ያሉት ዶክተር ቢኒያም ፣ በአገር አቀፍ ደረጃም በጣም ጠቃሚ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ የተለያዩ ምርምሮችን በመስራት አገሪቱ ወደምትፈልገው አቅጣጫ እንድትጓዝ አቅም ይፈጠራል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው ከተለዩ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቢኒያም፣ ፤ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ብዙ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ700 በላይ የሚሆኑ ምርምሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳተሙን የጠቆሙት ዶክተር ቢኒያም፣ይሕም ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ከሚገኙ 1 ሺህ 250 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች 20ኛ ደረጃን፣ ከኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ እንዳደረገው አመልክተዋል።
‹‹የምርምር ቡድኖች አዋቅሮ ወደተግባር ሲሸጋገር አሁን ካለበት ደረጃ ወደላቀ ከፍታ መድረስ ይቻለዋል ያሉት ዶክተር ቢኒያም፣ ዩኒቨርሲቲው በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም