
አዲስ አበባ፡- ባለፈው ስርዓት ሰውን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን ከመስራት አንጻር ሰፊ ውስንነቶች እንደነበሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ አስታወቁ፡፡ ብዙኃኑን ከመጥቀም ይልቅ በአብዛኛው የግልና የቡድን ጥቅሞች ብቻ የሚስተናገዱበት አገዛዝ እንደነበር አመለከቱ ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ጥራቱ የጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር ለህሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለማሰራት ከከተማ አስተዳደሩ በተሰጠው የ3000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የቀደመው ስርዓት ብዙኃኑን ከመጥቀም ይልቅ በአብዛኛው የግልና የቡድን ጥቅሞች ብቻ የሚስተናገዱበት አገዛዝ ነበር፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት የሆነውን በተፈጥሮ የተሰጠንን መሬት እንኳን የተወሰኑ አካላትና ባለሀብቶች ተጨማሪ ሀብት ማካበቻ አድርገውት መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡
የተማረ፣ ጤነኛ፣ ሀብት ያለው ወይም የተወሰነ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከተማዋ የህሙማን ጭምር ናት ያሉት አቶ ጥራቱ፤ 3000 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታው የማህበሩ የራሱ እንጂ በእርዳታ፣ በድጋፍ ወይም በችሮታ የተሰጠው አይደለም ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ሰውን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን ከመስራት አንጻር ሰፊ ውስንነቶች ነበሩ፣ በጎ አሳቢ ኢትዮጵያዊያን በቁጥር ጥቂት ቢጨምሩ ብዙ ችግሮቻችንን መፍታት የምንችልበት እድል እንደነበረን አመልክተዋል፡፡ የነበረው ስርዓት ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ባለመቻሉ ምርታማ የሚሆኑ ወጣቶች የብዙ ችግሮች ገፈት ቀማሾች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለሚወጡ ግለሰቦችና ተቋማት የከተማ አስተዳደሩ እገዛ ይቀጥላል ያሉት ኃላፊው፤ ከአንድ ወር በፊት ከተማ አስተዳደሩ በጎ ሥራ እየሠሩ ላሉ ማህበራት 10 የሚሆኑ ቦታዎች ውሳኔ በማስተላለፍ እንዲረከቡ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ማህበራቱ እየሠሩ ያሉት የመንግሥት ሥራን በመሆኑ ከመሬት ስጦታ ጀምሮ ሌሎች ስጦታዎችን ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ ነው፡፡ ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበርም በቀጣይ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል ብለዋል፡፡
ሀብት እያለን ባለመርዳታችንና ፍቅር ባለመስጠታችን ሊድኑ የሚችሉ የአእምሮ ህሙማን የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል፡፡ ጌርጌሴኖን የህሙማን መርጃ ማህበር በዘር፣ በሀይማኖትና በጾታ ሳይለይ ሰዎችን መርዳት መቻሉ መባረክ ነው፣ እንደ ሀገር ደግሞ የሚያኮራ ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር በ1998 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ 1000 የሚጠጉ የአእምሮ ህሙማንን ያለልዩነት በማዕከሉ በማስገባት በማስታመምና በመንከባከብ ላይ ይገኛል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም