
አዲስ አበባ:- በምርጫው መንግሥት ሆነን የምንመረጥ ከሆነ የዜጎችን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቅና የኢትዮጵያን ክብር የሚመጥን የውጭ ግንኙነትን በመገንባት የአገር ብልጽግናን እናሰፍናለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለጹ።
ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች የተሳተፉበት “ወጣትነቴን ለኢትዮጵያ ሀገሬ፤ ካርዴን ለብልፅግና!” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ስታዲየም ትናንት ለብልፅግና ፓርቲ የድጋፍ ትዕይንት በተካሄደበት ወቅት ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት፤ ብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ክብርና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የውስጥና የውጭ ግንኙነት ሥራ ይሠራል።
ፓርቲው በሚያካሂደው እያንዳንዱ ተግባር፣ በሚቀረጹ ፖሊሲዎች እንዲሁም በዕየለቱ እየተጠናከሩ በመጡት ተቋሞች አማካኝነት የሚያንፀባርቀው ቀዳሚ ጉዳይ ሀገራዊ ክብርንና የዜጎችን ጥቅም ማስከበር ነው ብለዋል፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት በማስቀጠልና ጠንካራ የውጭ ግንኙነት በመገንባት ረገድ በርካታ ክፍተቶች የነበሩበት ዘርፍ እንደነበር አስታውሰው፤ ብልፅግና ይህን ክፍተት በመቅረፍ በቀጣይ የዜጎችን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
በለውጡ ማግስት የብልጽግና ፓርቲ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች በውጭ ግንኙነት ዘርፉ የነበሩ ጉድለቶችን፣ የአፈጻጸም ክፍተቶችንና የተልዕኮ ችግሮችን መፍታት ማስቻሉን ጠቁመዋል።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የሀገር ሉዓላዊነትና የዜጎች ደህንነትንና ክብርን የሚያስጠብቅ ብቁ ቁመና ያለው ጠንካራ የመከላከያ አቅምና የደህንነት ተቋማት ግንባታ ላይም አያሌ ለውጦች ፓርቲው አስመዝግቧል።
ብልፅግና የኢኮኖሚ ፍላጎት ማሟላት ላይ ብቻ የሚያተኩር ሳይሆን የዜጎችና የሀገር ክብርን የማስጠበቅ ሥራን ጭምር የሚሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የሀገር ክብርንና ፍቅርን አጣምሮ በመስራት ሁለቱንም ግቦች ለማሳካት የሚታትር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ብልፅግና የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር፣ ሀገራዊ ክብርን የሚያስቀድም፣ የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት የሚያረጋግጥ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልፅግና የማሳካት ግንኙነት የረጅም ጊዜ ሉዓላዊት ሀገርን፣ ነፃ የመንግሥት ታሪክን፣ መቻቻል ያለበት ብዝኃነትን፣ መልካም መስተጋብሮችን፣ መወራረሶችንና የአብሮነት ባለቤት ሀገር ውስጥ የፌዴራሊዝም ጅማሮዎች መኖርን እንደ እሴት የሚያገናዝብ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው፤ ‹‹ብልፅግናን የወለዳችሁት እናንተ ወጣቶች ናችሁ፣ ባለቤቶቹም እናንተው በመሆናችሁ ክብር ይገባችኋል፣ ፓርቲው ኢትዮጵያውያንን ለማገልገል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው›› ነው ብለዋል።
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም