
ደብረ ብርሃን፦ የአካባቢውን ህብረተሰብ የመልማት ችግር የሚቀርፉ ጥናትና ምርምሮችን በጥራትና በስፋት ለመስራት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራቱን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ ዩኒቨርሲቲው ትናንት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በአፕላይድ ዩኒቨርሲቲነት የተመረጠው በአካባቢው እየመጡ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ እንዲሰራባቸው በተመረጡ ኢንጂነሪንግ፣ ጤና፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ሥራዎችን በመስራት በዙሪያው ለሚገኙት ኢንደስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ሀብት ለማፍራት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የህብረተሰቡን የመልማት ችግር የሚቀርፉ ጥናትና ምርምሮችን ለመስራት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመልክተው፤ የከተማዋን ፈጣን እድገት ከግምት ያስገባና ለ30 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል የተቀናጀ መዋቅራዊ ፕላን ለማዘጋጀት ኃላፊነቱን ወስዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ አካባቢው የኢንደስትሪ መናገሻ ከሚባሉት ዞኖች ቀዳሚው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የኢንደስትሪ ተቋማትን ትስስር ለማጠናከርና አስፈላጊና ጠቃሚ በሚባሉ የጋራ ስራዎች ላይ መሪ ተዋናይ ለመሆን ዝግጁ ነው ።
በሰሜን ሸዋ ዞን ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም ለይቶ በመሰነድ ባለሀብቶች ሊሰማሩና ሀብት ማፍራት የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት አይነቶች ለመለየት እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎች የተማረ የሰው ሃይል በማፍራትና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በመስራት ለአገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲሚያበረክቱ ገልጸዋል።
ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲም የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍና ለከተማዋም እድገት የድርሻውን እያበረከተ ነው። ከተማዋ በፍጥነት እያደገች የምትገኝ በመሆኗ ዩኒቨርሲቲው በዛው ልክ እያደገ መምጣት አለበት ብለዋል፡፡
እየተመዘገበ ያለው እድገት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆንና ለሰዎች የስራና ምቹ የኑሮ ሁኔታን እንዲፈጥር በትጋት መስራት እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ገዱ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
አካባቢው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉበት በመሆኑ ይህንን አደራጅቶ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ደብረ ብርሃን እያሳየች ባለው ፈጣን እድገት ምክንያት ለዓመታት ያገለግላል የተባለውን የተቀናጀ መዋቅራዊ ፕላን ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነቱን ወስዶ ሥራ በመጀመሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም