
ነቀምት:- ህዝባዊ ወንድማማችነትና የጋራ የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ህዝቡን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።
በአራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በፌዴራል መንግሥት በጀት የሚገነባውና 160 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የነቀምት-ሶጌ-ካማሽ-ቆንጮ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ከትናንት በስቲያ ባስጀመሩበት ወቅት አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፤ ህዝቦችን በልማት በማስተሳሰር ወንድማማችነትን ለማጠናከርና ፍትሃዊነትን ለማስፈን የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የኦሮሚያንና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት ለማጠናከር በመንገድ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል
ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት በፍቅር የኖሩና በደም የተሳሰሩ ቢሆንም ባለፉት 27 ዓመታት በተጠነሰሰው ሴራ በጥርጣሬ እንዲተያዩ መደረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ሽመልስ ፣ የተጠነሰሱ የግጭት ድግሶች እንዲከሽፉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኘሬዚዳንት አቶ አሻድሌ ሀሰንን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በህዝቦች መካከል መቀራረብና መተሳሰብ በይበልጥ እንዲጠናከር በተለይ የመንገድ መሠረተ ልማት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚመረቱ ሰፊ የግብርና ምርቶችና ማዕድናት በቀላሉ ለውስጥና ለውጭ አገራት ገበያ በማቅረብ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ኘሬዚዳንት አቶ አሻድሌ ሀሰን በበኩላቸው፤ ‹‹በጋብቻ የተገመደ በደም የተሳሰረ የህዝቦችን አንድነት በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ሥራ ተጠናክሮ ከቀጠለ የተፈለገው አንድነትና የታለመው ብልጽግና ሩቅ አይሆንም›› ብለዋል።
የኦሮሞና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ለዘመናት በፍቅር የኖሩ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ አሻድሌ ፣ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት በይበልጥ ለማጎልበት በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር የተጀመረው ሥራ ከሌሎች ክልሎችም ጋርም በጋራ ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ምርትን ወደ ገበያ ወስደው በአማራጭ ዋጋ ሸጦ የተሻለ ገቢ ለማግኘት፣ በተለይ ወላድ እናቶችን ወደጤና ተቋማት በጊዜ ለማድረስ የመንገዱ ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል ፡፡ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በመሆኑ በታቀደለት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን በበኩላቸዉ፤ ኦሮሚያን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ጋር በመንገድ ማገናኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንገዱ የሁለቱን ክልሎች ህዝብ የሚታወቁባቸውን እንደ ቡና ያሉ የግብርና ምርቶችንና ወርቅና ሌሎች ማዕድናትን ለገበያ በማቅረብ የአካባቢውና የከተማውን ብሎም የአገር ኢኮኖሚ እድገት ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም