
ሐዋሳ፦ በሐዋሳ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ሁለገብ የስፖርት ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የከተማ መስተዳድሩ አስታወቀ።
የከተማዋ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካዊሶ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የከተማዋን ወጣቶች በስፖርት ሜዳ ውሎ በየጊዜው በውጤት የታጀበ ቢሆንም ከፍተኛ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት አለ ።
በዚህም የተነሳ ለከተማዋ፣ ለክልሉ ሆነ እንደ አገር ከዘርፉ መገኘት ያለበት ጥቅም አልተገኘም። በዚህም የተነሳ ኪሳራው ውስጥ እንደገባን ይሰማናል ያሉት አቶ ጥላሁን ፣ በተለይ ስፖርት ፍቅር፣ አንድነት እና ሰላም የሚሰበክበት ትልቁ መሳሪያ ሆኖ ሳለ በዚህ ላይ አበክሮ አለመስራት አግባብ አይደለም ብለዋል ።
ከችግሩ የተነሳ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ሊያስጠሩ የሚችሉ ብርቅዬ ወጣቶች አቅም ተደብቋል ያሉት አቶ ጥላሁን፣ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ማዕከሉን መገንባት አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ስፖርት እና ስፖርተኞች በዓለም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን እያንቀሳቀሱ ነው ። ኢትዮጵያ በዚህ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ መሪ ተዋናይ አለመሆኗ አሳዛኝ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በአገር ደረጃ ለስፖርት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ፣መሰል የስፖርት ማዕከላትንና ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባት ያላቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንድምታ ከፍያለ እንደሆነም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የተጀመሩ የስፖርት ማዕከላት ሆኑ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ሆነ አልቀው ስራ ላይ የሚገኙት አገሪቱ በስፖርት ዘርፍ ካላት አቅም አንጻባራቂ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል ። በዘርፉ በጥንካሬ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል ።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ፤ በከተማዋ የሚገነባው ሁለገብ የስፖርት ማዕከሉ በአራት ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው ። የቦታው መረጣና ዲዛይን ሥራውም ተጠናቋል።
ማዕከሉ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የስፖርተኞች መኝታ ክፍሎች፣ የማስተማሪያ ክፍሎች፣ ለተጨማሪ ገቢ ማስገኛ የሚሆኑ የሚከራዩ ሱቆች ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፣ ካፌዎችንና የተለያየ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን የሚያካትት እንደሆነም አመልክተዋል ።
ግንባታው 20 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ ወጪው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን እንደሚሆንም አስታውቀዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት፤ ከዚህ ሁለገብ የስፖርት ማዕከል በተጨማሪ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማከናወን መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ሥራ እንደገባ አስታውቀዋል።
የሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ በስፖርት ያላትን አቅም አሟጣ እንዳትጠቀም መሠረት ልማቶች አለመሟላት ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
በርካታ ስፖርተኞች መፍለቂያ የሆነችው ሐዋሳም የዚሁ ሰላባ በመሆኗ በርካታ ስፖርተኞች ለውጤት የበቁት በራሳቸው ጥረት እንጂ ተገቢው የመንግሥት ድጋፍ ተደርጎላቸው አይደለም ። በመሆኑም መሰል ችግሮች ቀጣይ ሆነው መነሳት ስለሌለባቸው የከተማው መስተዳድር የተቻለውን አቅም አሟጦ ስፖርትና ስፖርተኞችን ያገናኛል ። በቀጣይም መሰል ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በግንባታው ዙሪያ አስተያየቱን የሰጠው ወጣት በጋሻው ታደሰ፤ የማዕከሉ ግንባታ እውን መሆን ለበርካታ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ነው። ለታዳጊዎችም ብዙ እውቀት የሚቀስሙበት ይሆናል። ይሁንና መሠረተ ድንጋይ ከማስቀመጥ በዘለለ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ግንባታው እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም