ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ አለሙ ይባላሉ።በአካባቢ ልማትና የትምህርት ጥራት ላይ በሚኖሩበት አካባቢ ሽልማት ያገኙና አሁንም ይህንን ሥራቸውን ለሽልማት ሳይሆን ለውጤት፣ ለለውጥ ብለው የሚያከናውኑ ናቸው።በኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ፣ በኢትዮጵያ ባይሎጂካል ሶሳይቲ ፀሐፊነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ማይክሮ ባዮሎጂ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ሆነው በኃላፊነት ሲሰሩ ብዙ ለውጦችን ያመጡም ናቸው። በመጀመሪያ በቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴርና በተለወጠው ስሙ በቡናና ሻይ ባለስልጣን በስራ በነበሩበት ወቅትም አገር ላይ ለውጥ የመጡ አሻራቸውን አኑረዋል።
አሁን ደግሞ የእውቀት ብርሃን የሚፈነጥቁበት ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር፣ በማማከርና በምርምር በመደገፍ ፍሬያማ እንዲሆኑ እየተጉ ይገኛሉ።እኛም እኒህን የእውቀት ባለሟል ለዛሬ የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ከልምዳቸው ተማሩ ስንል ጋበዝናችሁ።
ራስን ማኖር በልጅነት
ትውልዳቸው በባሌ ጠቅላይ ግዛት በዋቤ አውራጃ በጊኒር ወረዳ ልዩ ቦተዋ ራህመቴ ተብላ በምትጠራው ስፍራ ነው።አካባቢው ሁልጊዜ ዝናብ የማይለየውና ለምለም በመሆኑ ተፈጥሮን ወደው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።በተመሳሳይ አየር ንብረቱ አብዛኛውን ነዋሪ በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማራ ያደረገው በመሆኑም የእነ ተስፋዬ ቤተሰብም ኑሯቸውን በዚሁ ላይ ያደረጉ በመሆናቸው ልጅነታቸውን ከዚሁ ሥራ ጋር አቆራኝተው እንዲያሳልፉ ሆነዋል።ከብት ማገዱም ዋነኛ ሥራቸው ነበር።
ሀብት የሚቆጠረው ባለ ከብት ብዛትና መሬት በመሆኑም ቤተሰቦቻቸው በተለይም አያታቸው ሰፊ ጋሻ መሬት ያላቸው ስለነበሩ ንብረታቸው ያሳሳቸዋልና መማርን ሳይሆን ለእንግዳችን የሚነግሩት ሀብትን ማስተዳደርን ነበር።‹‹አንተ አድገህ ቤቱን ትመራለህ››ም የዘወትር ንግግራቸው እንደነበር አይረሱትም።በባህሉ የመጀመሪያ ልጅ በምንም መንገድ ከተወለደበት ቦታ እንዲርቅ አይፈለግም።በዚህም ለዓመታት በአያታቸው ቤት ሆነው እንዲያሳልፉ ተገደዋል።
ትምህርትን ፍለጋ በራሳቸው ትግልና ጫና እናታቸው ወደ ሚኖሩበት ወደ ጊኒር ቢያቀኑም አስር ዓመት ሳይሞላቸው እናታቸውን በሞት ተነጠቁ።በዚህም በአያታቸው ዘመድ ቤት በመኖር እንዲማሩ ሆኑ።ይህ ደግሞ በሰው ጫንቃ ላይ መደገፍ ነው ብለው ስላመኑ በአልጠና ጉልበታቸው ያልሰሩት ሥራ አልነበረም።
የገበያ ቀን ሲሆን ከሱቆች ሸቀጦችን በመውሰድ ጉሊት በመቀመጥ ይሸጣሉ።ከዚያ ውጪ ባሉ ቀናት ደግሞ በቤት ውስጥ ከብት ማውጣትና ማሰማራት እንዲሁም ወደ በረቱ የመመለስ ተግባር የእርሳቸው ነው።ቡና ማፍላትና ሊጥ ማውካት የመሳሰሉ ሥራዎችንም ይሰራሉ።
እንግዳችን በወቅቱ በባህሪያቸው ታዛዥ፣ ተፈጥሮን በጣም የሚወዱና ያሰቡትን ካላሳኩ ወደኋላ የማይሉ ልጅ ነበሩ ። አስተዳደጋቸው መስጠትን ያስተማራቸው በመሆኑ ሁልጊዜ ከራሳቸው በላይ ሌሎችን ያስቀድማሉ።እንደ ማንኛውም ልጅ ተጫውተው ያደጉበትን ጊዜ ብዙም አያስታውሱትም።
ሬዲዮ ማዳመጥና ችግኞችን መንከባከብ ዋና ሥራቸውና መዝናኛቸው አድርገው ይውላሉ።በተለይም ከጥናት በኋላና ሥራዎችን ካጠናቀቁ በኋላ ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬን በግቢያቸው ውስጥ መንከባከብ ለእርሳቸው የውስጥ ረፍት ማግኘት ነው።
በጣም ጨነቅ ካላቸው ደግሞ የእጅ ኳስ መጫወትና ሩጫ መሮጥን ያዘወትራሉ።እንደውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ጎባ ለመሄድ ጓጉተው ስፖርት መምህራቸውን ሲጠይቁ ‹‹አንተ አትችልም›› ተብለው በቁጭት ያደረጉት ነገር መቼም አይረሳቸውም።
ይህም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለመውጣት ሳምንት ሙሉ ጠዋት ተነስተው መለማመዳቸው ሲሆን፤ በዚህም ከወረዳ በብዙ ዝግጅት ተመርጠው የመጡትን ለዚያውም የመሮጫ መስመር ሳይሰጣቸው ሰፊውንና ዳሩን ይዘው በመሮጥ አንደኛ ወጥተው ስኬታቸውን አረጋግጠዋል።ይህ ሁኔታቸው ደግሞ ካመኑበት ማንም እንደማይመልሳቸውና እንደሚያደርጉት ያዩበት እንደነበር ያስታውሳሉ።አሁንም ቢሆን ይህ አቋማቸው እንዳለና የቀጠለ መሆኑን አጫውተውናል።
ለትምህርት የተከፈለ ዋጋ
እናትና አባታቸው ባለመስማማታቸው የተለያዩባቸው ባለታሪካችን ገና በአምስት አመታቸው ነበር ለአያታቸው ተሰጥተው ወራሽ እንጂ መማር አይቻልምን የቀመሱት።ግን በቀላሉ አልተረቱም ነበር።ይልቁንም መማር እፈልጋለሁ ባይነታቸውን በጫና ጭምር አሳምነው ወደ ትምህርትቤት ተልከዋል።ይህ ግን በቀላሉ የተገኘ እንዳልነበር ያነሳሉ።እናታቸው ሲመጡ ጠብቀው በቀየሱት ዘዴ ነው አሸንፈው መማር የቻሉት።በእርግጥ መማርን እንዲወዱትና እንዲነቃቁ ያደረጓቸው እነርሱ ቤት ወደ ትምህርት ለመሄድ ስንቃቸውን ይዘው የሚመጡና የሚያድሩ ልጆች ናቸው።እናም አንድ ቀን እናታቸው ወደ አያታቸው ጋር በመምጣት ሲቀይሱ የቆዩትንም፡ ዘዴ ሰዓታትን ጠብቀው ተገበሩት።
የመጀመሪያው ዘዴያቸው ከብቶቹን በተኩላ ማስበላት ነበር፤ ስኬታማ አልነበረም።እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ የተገረፉበት ነበር።ከዚያ ወደሁለተኛው ርምጃቸው ገቡ።ይህም ከብቶቹን መልስ ሲባሉ ማሳ ውስጥ ለቀቋቸው።እህሉም ልቅም ተደርጎ ተበላ።በዚህ ጊዜ ሊመታቸው የተቃረበው ብዙ በመሆኑ ቤቱን ጥለው ጠፉ።ፍለጋው ተጧጧፈ።ግን ማንም ሊያገኛቸው አልቻለም።ጥሻ ውስጥ ተደብቀውም ቤት ውስጥ ያለ ሰው ሁሉ ወጥቶ እናታቸው ብቻ መቅረቷን ሲያረጋግጡ ወደ እርሳቸው በመሄድ ሁኔታውን አስረዱ።አልቀበልም ሲሏቸውም ማስፈራሪያ ጭምር አደረጉ።እሞታለሁም አሉ።ይህ ያስፈራቸው እናትም ቤተሰቡ ሲሰባሰብ ሁኔታውን አስረድተው አሳመኑ።በዚህም እንዲማሩ ተመርቀው ተሸኙ።የትምህር ሀሁም የተጀመረው ከዚህ በኋላ ነው።
ዘመናዊ ትምህርታቸውን የጀመሩት መኩሪያ ተሰማ አባ ይላቅ ትምህርት ቤት ነው፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል።ቀጣዩትን ትምህርት ማለትም ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ጊኒር መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።በእርግጥ ከእናታቸው ጋር ወደ ጊኒር ሲመጡ ጊዜው የትምህርት መጠናቀቂያ ላይ በመሆኑ እንዳይማሩ የሚያደርጋቸው ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።ሳይመዘገቡ ከልጆቹ ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ የተከራዩበት ሰው የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ በመሆናቸው አግዘዋቸው ስለነበር ከተማሪዎቹ ጠቅላላ አንደኛ በመውጣታቸው እንዲመዘገቡ ሆነዋል።ጎበዝ በመሆናቸውም ሁኔታውን ድል ነስተውታል።ሁለተኛ ክፍልንም ሙሉ ዓመቱን ከተማሩት እኩል በማለፍ መቀላቀል ችለዋል።
ይህ ዓመት ለእርሳቸው ሁለት ፈተናን ይዞ የመጣ እንደነበር ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ የመጀመሪያው እናታቸውን መነጠቃቸው ነው።ሁለተኛው ደግሞ የት ሆነው መማር እንደሚችሉ ግራ የተጋቡበት ነው ፤ ለጊዜው ትምህርቱን አቋርጠው ለሁለት ወር ያህል ገጠር ቤተሰብ ጋር ቆዩ።ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ ሆነና የአያታቸው ዘመድ እኔ አስተምረዋለሁ ብለው መልሰው ወሰዷቸው ።ጥሩ ውጤትም በማምጣት ሦስተኛ ክፍልን ተቀላቀሉ።ይሁን እንጂ እዚህ ላይም ሆነው ነገሮች አልተመቻቹላቸውም።አያቶቻቸው በመማራቸው ደስተኞች አልነበሩምና እንዲመለሱ ጠየቋቸው።እርሳቸው ግን በእንቢታቸው ጸኑ።ይህ ደግሞ ስንቅ መላካቸውን አቋረጠው።በዚህም የራሳቸውን ወጪ ራሳቸው ለመሸፈን ባልጠነከረ ጉልበታቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ አስገደዳቸው።
በገበያ እየተቀመጡ የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ ራሳቸውን ይደጉሙ እንደነበር የሚያስታውሱት እንግዳችን፤ በተለይ ማክሰኞ ክፍል ውስጥ አለመገኘታቸው ከአንድ መምህራቸው ጋር እንዳጋጫቸውና ከዚያም አልፎ ጊዜውን እየጠበቀ በመፈተን ከ40 ዜሮ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው አይረሱም። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ሳይገባኝ አላልፍም የሚለው ግትርነታቸው እንደነበርም ይናገራሉ።ይሁን እንጂ ከ60ው 56 በማምጣት የእርሱን ትምህርት ጭምር ማለፍ እንደቻሉም ያነሳሉ።
ውጤታቸው በጣም ቆንጆ በመሆኑ የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ውሰድ ተብለው የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ ስጋት ውስጥ በመሆናቸው አሻፈረኝ አሉ።ጊዜያቸው ሲደርስም ተፈትነው ወደ ሰባተኛ ክፍል ተዛወሩ።ይሁንና ሰባተኛ ክፍል ሲደርሱ ስምንተኛ ክፍልን መፈተን ግን ፈለጉ።በብዙ ትግልም ጎበዝ ስለነበሩም ተፈቀደላቸው።በዚህም ሰባትን በትምህርት ስምንትን በፈተና አልፈው በዓመት ውስጥ ዘጠነኛ ክፍልን መቀላቀል ችለዋል።እንዲህ እንዲህ እያሉም በብዙ ችግርና ፈተና ውስጥ ሆነው 12ኛ ክፍልን አጠናቀዋል።
ከነበሩት የአካባቢው ተማሪዎች ያለፉት ከአምስት አይበልጡም ነበርና እርሳቸውም አንዱ በመሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደርሷቸው ነበር።ሆኖም ዩኒቨርሲቲ ላለመግባት ወስነዋል።ምክንያቱም ዩኒቨርስቲ ለመማር የሚያስችላቸው ገንዘብ የላቸውም።የሚረዳቸውም ቢሆን እንዲሁ።ስለዚህም መምህራን ማሰልጠኝ እገባለሁ የሚል ሀሳብ ነበራቸው ።ነገር ግን መምህራኑ በሀሳባቸው አልተስማሙምና እኛ እናግዝሀለን ብለው አደፋፈሯቸው።አዋጥተውም ዩኒቨርሲቲ ላኳቸው።ይሁን እንጂ ቀጣዩን ቆይታቸውን ሲያስቡትና ሲኖሩበት ግን የሚወጡት አይነት አልመሰላቸውም።ስለዚህም የውጪ የትምህርት እድልን እየሞከሩ መስራትና ራሳቸውን ማስተዳደር እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡
ማስታወቂያ ተከታትለውም ለወራት ያህል በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ገብተው ከተማሩ በኋላ ትምርታቸውን አቋርጠው ሥራ ተቀጠሩ። የጠበቁት የትምህርት እድልም ሲመጣ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ሄዱ።በታሽከንት ግብርና ኢንስቲትዩት በመግባትም በእጽዋት በሽታ መከላከል በተለይም በሞቃታማ ግብርናው ዙሪያ ስድስት ዓመታትን ትምህርቱን አጥንተው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመያዝ ወደ አገራቸው ተመለሱ ። በዚህ ቆይታቸው በቲማቲም ላይ ምርምር ማድረግና ጽሁፋቸውን በኢንተርናሽናል ጆርናል ላይ ማሳተም የቻሉ እንደነበሩም ያስታውሳሉ።ሥራቸው ደግሞ ተጨማሪ የትምህርት ክፍያ እንዳስገኘላቸውና መጥተው ችግር ውስጥ እንዳይገቡ እንዳገዛቸውም ይናገራሉ።
ከዓመታት ሥራ በኋላ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ሕንድ/ኒውደይሊ/ ያቀኑት ባለታሪካችን፤ የትምህርት እድሉን ሲያገኙ የሁለት ዩኒቨርሲቲዎችን ፈቃድ አግኝተው ነበር።በዚህም የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በአርያሃና የግብርና ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ወር ያህል ተከታትለዋል።ነገር ግን ሙቀቱ ሊያስቀምጣቸው ባለመቻሉ አምባሳደሩን በመጠየቅ ወደ ኢንዲያን ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተዛውረው ቀጣዩን ትምህርት መማር ችለዋል።በከፍተኛ ውጤት ለማጠናቀቅም በቅተዋል።
በትምህርት ቆይታቸው ያልገቡባቸው የቤተሙከራ አይነቶች እንዳልነበሩ የሚያነሱት እንግዳችን፤ ከምርምር አማካሪያቸው ጋር የትምህርት መስኩን ለመምረጥ ለሁለት ወር ያህል ተከራክረዋል።ሆኖም በመጨረሻ ተሸናፊ ሆነው ለአገራቸው የሚበጀውን መስክ እንዲማሩ ሆነዋል።በዚህም ያመሰግኗቸዋል።ምክንያቱም ለነገ አገራቸው ላይ የሚሰሩትን ለማድረግ ብዙ እንዲቆፍሩ አድርጓቸዋል።እንደውም 45 ኮርስ መውሰድ ሲገባቸው 67 አድርገው እንደተመረቁ ያስታውሳሉ።ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ ከራሳቸው ትምህርት ውጪ ባሉ ቤተሙከራው ውስጥ እንዳይገቡ የታገዱበትን ሁኔታም መቼም አይረሱትም።
በመደበኛነት ከተማሩት ውጪ በስልጠና ያዳበሩት እውቀትም መተኪያ የሌለው እንደሆነና አሁንም ሁሌ ተማሪ እንደሆኑ እንደሚሰማቸው አጫውተውናል።እንደውም ትምህርት በማስተማር ስራ ውስጥ የማይቋረጥ ነው ይላሉም።
ሙያ ትልቁ ፖለቲካ ነው
በቅጥር ከስራ ጋር የተተዋወቁት ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ነበር።ይህም ራሳቸውን ለማኖር ሲሉ በዩኒሴፍ አማካኝነት 260 ብር የተቀጠሩት ነው።ለሦስት ወር ያህል ባሌ ክፍለአገር ውስጥ ሰርተዋል።ከዚያ ደግሞ የመንግስት እርሻ ሥራ ድርጅት ውስጥ ገቡ።ስድስት ወር ያህል እንዳገለገሉም የውጪ ትምህርት እድል ሞክረው ስለነበረ ሥራቸውን በማቆም ወደ መማሩ ገቡ።ከምረቃ በኋላ ደግሞ የተማሩት የትምህርት መስክ በወቅቱ አስፈላጊ ነበርና በቀድሞ ቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር በአሁኑ ቡናና ሻይ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በእጽዋት በሽታ መከላከል ባለሙያ በመሆን ተቀጠሩ።
መኖሪያቸውን ድሬዳዋ አድርገው በሀረርጌ የቡና ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ውስጥ የቡድን መሪ በመሆን ሲሰሩ ቆዩ።በዚህ ደግሞ ስድስት አውራጃዎችን ይሸፍኑ ነበር።በተለይም በእጽዋት በሽታ መከላከሉ ዙሪያ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በማሰልጠንና በሥራው ውስጥ ገብተው በማገዝ እንደእርሳቸው ሁሉም ወረዳ ላይ እንዲሰሩ ያደረጉት ስራ ዛሬ ድረስ ያስመሰግናቸዋል።
እንግዳችን ለአገር ከመጣው ሁሉ መቋደስ አለበት የሚል እምነት ያላቸው ናቸው።በዚህም አርሲ ላይ ያለው የገበሬ ጉዳይ ያሳስባቸው ነበርና የቡና በሽታ መከላከያ መድሃኒት በመስጠት አርሶአደሩን ምርታማ የሚያደርጉበትን መንገድ መቀየስ ችለዋል።አምስት ሰዓት ሙሉ ዝናብ እየወረደባቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ነገር አመቻችተዋልም።በዚህም አጀብ የሚያሰኝ ሥራ መስራት ቻሉ።ወደ አዲስ አበባ ለመቀየራቸው መንስኤውና ጥሩ እድልን ያስገኘላቸውም ይህ ሥራ እንደነበር ያወሳሉ።
ከገበሬዎቹም ቢሆን ልዩ ምስጋና ያገኙበት ነበር።ምክንያቱም በብዙ ትግልም ቢሆን የአርሲ ቡና በሀረርጌ ዋጋ እንዲሸጥ ብዙ ጥረው ተሳክቶላቸዋል።ይህንን ሲያደርጉ የገበሬውን እምነት በጥልቀት ያዩበት እንደነበር ያነሳሉ።እንደውም ዛሬ ድረስ ቃላቸው እምነታቸው ነው ይሏቸዋል።
መልካም መስራት ሁልጊዜ እድገት ነው የሚሉት ባለታሪካችን፤ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት በእድገት ሀረርጌ ወደ አራት ሲከፈል ምዕራብ ሀረርጌ አሰበ ተፈሪ ቡድን መሪ በመሆን እንዲሰሩ ተመድበው ነበር።በዚህም ለዓመት ያህል ሲሰሩ ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰርተዋል።እንደውም ከሥራቸውና ከተወዳጅነታቸው አኳያ ወደ አዲስ አበባ መቀየራቸውን አለቃቸው ሊነግራቸው አልወደዱም። ምክትል ስራስኪያጁ መጥተው በራሳቸው መኪና ጭነው ወስደዋቸው ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋቸዋል።
በባለስልጣኑ ውስጥ የተባይ መከላከል ባለሙያ በመሆን ሰርተዋል፤ ሁለት ዓመታትን በስራው ላይ አሳልፈዋል።የውጪ የትምህር እድል በማግኘታቸው ነበር ሥራውን ያቆሙት።በእርግጥ የሄዱት ተቋሙ በሰጣቸው እድል ስለሆነም ሲመለሱም እንደማይቸገሩ ያውቃሉ።እናም እንዳሰቡትም ከትምህርት መልስ አንዳንድ ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም መስሪያቤቱን ዳግም ተቀላቅለዋል።
ችግር የገጠማቸው በሦስት ዓመት ውስጥ ትምህርቱን አጠናቀው እንደሚመለሱ ቃል ገብተው ቢሄዱም ምርምራቸው አንድ ዓመት አስጨመራቸው።በዚህም በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ወጣባቸው።ተባረሀልም ተባሉ።ነገር ግን እርሳቸው ምክንያቸውን እዚያ ሆነው ጭምር በደብዳቤ አሳውቀዋል።ነገር ግን ሀላፊው እኛ ስናዘው ቆይተን እሱ ሊያዘን አይችልም በሚል ተራ ቅናት አልቀበልም አለ።እያንዳንዱ ቦታ ቢጠይቁም መፍትሄ አጡ።በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሄደው ከሰው ቦታቸውን አገኙ።
በቡና ተባይ መከላከያ ስም የቡና በሽታ መከላከል ባለሙያ በመሆን መስራት ጀመሩ።ይህም ቢሆን ያልተዋጠለት ሀላፊው የተለያዩ ክሶችን ያደርግባቸው ነበር።እንደውም ከሙያቸው ውጪ መድቧቸው የሻይ ባለሙያ አድርጓቸው እንደነበር አይዘነጉትም።በዚህም ሥራቸውን ሳያጓድሉ በትርፍ ጊዜያቸው ሙያቸውን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች በዘርፉ ከተሰማሩ ነጋዴዎች፣ አስመጪና ላኪዎች ጋር በማማከር መስራት ጀመሩ።ይህ ደግሞ ለአለቃቸውም ይደርሳቸው ስለነበረ ብቃታቸው ሀያልነቱን ወደማሳየቱ ገባ።ፍላጎታቸው ሥልጣን ሳይሆን ሥራ መሆኑንም እንዲገነዘቡ አደረጋቸው።በሥራቸው እንዳሸነፉት አምኖም ይቅርታ ጠየቀ።
ሙያዬ ትልቁ ፖለቲካዬና ሁሉንም ድል መንሻዬ መሆኑን ስለማውቅ ከአለቃቸው ጋር ጥሩ ነገር ቢኖረንም በዚያ መቀጠሉ ከሙያዬ የሚያርቀኝ መስሎ ተሰምቶኛል።በዚህም ባለስልጣኑን ትቼ ወጣሁ የሚሉት እንግዳችን፤ ሙያቸውን በደንብ የሚያዳብሩበት ሥራ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማውጣቱ ተወዳድረው በተሻለ ደመወዝ ለመቀጠር ችለዋል።አሁን በሙያቸው እየሰሩ 18ተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
ዩኒቨርሲቲውን ሲቀላቀሉ የሥነህይወት ትምህርት ክፍል ውስጥ የሰሩ ሲሆን፤ ትምህርት ክፍሉ በአራት ተከፍሎ መስራት ሲጀምር ደግሞ በማይክሮቢያን፣ ሴሉራል፣ ሞሎኪውላር ባዩሎጂ ትምህርት ክፍል ውስጥ አፕላይድ ማይክሮ ባዩሎጂን በመያዝ አስተባባሪ በመሆን ጭምር ሰርተዋል።የተመራቂዎች ኮሚቴ ውስጥ አባል በመሆንም ለሁለት ዓመታት ሰሩ።ይህ ሲሆንም ከመቶ በላይ የመጀመሪያ ዲግሪ የባይሎጂ ተማሪዎችን በማማከር ነበር።ለሁለት ዓመታት ደግሞ ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።በተመሳሳይ ለሦስት ዓመታት ደግሞ የአካዳሚው ኮሚቴ አባል በመሆን ሰርተዋል።የጄኔራል ባዮሎጂ የፕሮግራም ዩኒቲ የአካዳሚክ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆነው መስራታቸውን ቀጠሉ።በእነዚህና መሰል ስራዎቻቸው ደግሞ ከ11 ዓመት በፊት ረዳት ፕሮፌሰር መሆን ችለዋል።
ሥራዎቻቸው የሚታዩ መሆን ሲጀምሩም ከሰባት ዓመት በፊት ተባባሪ ፕሮፌሰርነትን አግኝተዋል።አሁንም ቢሆን ሙሉ ፕሮፌሰርነትን ለማግኘት የሚያግዳቸው ስለሌለ ለመጠየቅ ዝግጁ ናቸው።በዚህ የሥራ ጉዟቸው 43 የሁለተኛ ዲግሪና ስድስት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አማክረው አስመርቀዋል።አሁንም ሁለት ሁለተኛ ዲግሪና 15 ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን እያማከሩ ይገኛሉ።ከዚህ በተጓዳኝ ከ80 በላይ ሥራዎችን በአለም አቀፉ የምርምር መጽሔት ላይ አሳትመዋል።ይህ ደግሞ ብቻቸውን የሰሩት ቢሆንም ከተማሪዎቻቸውና ከሥራ አጋሮቻቸው ጋር የሰሯቸው በርከት እንደሚሉ አጫውተውናል።
ከማስተማሩ ማማከሩና ምርምሩ ውጪም ቢሆን በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሰርተዋል።ከእነዚህ መካከልም የኢትዮጵያ ባይሎጂካል ሶሳይቲ ፀሐፊ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል ፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች በአሁኑ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ኮሚቴ በመሆንም ለ12 ዓመታት አገልግለዋል ፤ የኢትዮጵያ ማይክሮ ባዮሎጂ ትምህርት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል።በብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ውስጥ አጋር አካል በመሆናቸው በሙያቸው ማገልገላቸው፤ በሰፈራቸውም ቢሆን በልማቱም ሆነ በድጋፉ ዙሪያ በተለያዩ ኮሚቴዎች የሰሯቸው ስራዎች አንቱታን ያተረፉላቸው ናቸው።
አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይም እንዲሁ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩን በተመለከተ ካጠኑ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው።እርሳቸው ብቻ የሚመሯቸው ከአምስት በላይ ፕሮጀክቶችን ይዘዋል።እንደውም ከዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በእጽዋት በሽታ መከላከል ዙሪያ የሰሩት ፕሮጀክት በአንደኝነት አልፎ ድጋፍ የተሰጠው በመሆኑ ፋብሪካ ለመክፈትና ገበሬውን ከችግር ለማላቀቅ እየሰሩ ናቸው።ወደፊትም ከ10 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር እየሰሩ ይገኛሉ።
የህይወት ፍልስፍና
የሰዎች ህይወት በአስተሳሰባቸውና ህይወትን እንደሚይዙበት ሁኔታ የሚወሰን ነው።በተፈጥሮና ማህበራዊ ህግ የሚመራ ሰው ኑሮውን ደስተኛና መጠን ያለው ያደርገዋል የሚል እምነት አላቸው።ሰዎች እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ማለት የለባቸውም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ተመሳሳይ ነገር ሲነገራቸው ራሳቸውን መመርመር መልመድ አለባቸው።ሰዎችን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ከምንም በላይ ማንነትን ለማየት ይጠቅማልና ይህንን ተገንዝቦ በተግባር ማዋል ፤ ሳይሳሳቱ እንኳን ተሳስቻለሁ ብሎ መቀበል ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ።ምክንያቱም እውነቱ ሲወጣ ተሸናፊው ማን እንደሆነ ይረጋገጣል ባይ ናቸው።
መኖር ያለብኝ እንደጎረቤቴ ሳይሆን ቤተሰቤን እንደሚመጥን ነው።የበታችነት እንዳይሰማቸው ማድረግ ያለብኝን ግን አደርጋለሁ።ይህ ሲሆን ደግሞ ተመጥኖ መጥኖ መኖር ያስችላል ብለው ያስባሉ።ግጭት በማንኛውም ቅጽበት ውስጥ አስፈላጊ ነው።ነገር ግን ያንን ለማርገብ መግባባትና መነጋገር ያስፈልጋል።ምክንያቱም ይህ ሲሆን ልዩነቶችን ያሳያል፤ እድገትን ያመጣል፤ አንድነትንም ያጠናክራል እምነታቸውም ፍልስፍናቸውም ነው።
ሌላው የህይወት ፍልስፍናቸው ራስን መወሰን ኑሮንም ራስንም ያስተካክላል የሚለው ነው።አስተሳሰባችንን ለመግራትና የምንሰራውን ስራ ቦታ እንዳይዝብን ለማድረግም ራስን መወሰን ወሳኝ ነው ይላሉ።የወደፊት ጥቅሜ ምንድነው የምለውን ሳለካ ሥራዎችን መስራት አልፈልግምም ፍልስፍናቸው ነው።የሰው ልጅ የመጀመሪያ ስህተቱ የመጣበትን መርሳቱ ነው።የቀደመ ነገሩን ካልረሳ በባህሉና በወጉ ከተራመደ በሥራው ስኬታማ ይሆናል እምነታቸው ነው።
ውሃ አጣጭን በፍለጋ
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተመርቀው ሲመጡ ሁለት ነገር አላማን አድርገው ነበር።የመጀመሪያው በሙያቸው አገራቸውን ሳይሰለቹ ማገልገል ነው።ሁለተኛው ደግሞ ማግባትና ቤተሰብ መመስረት ነበር ፤ ለሥራ ወደ ድሬዳዋ ተመድበው ከሄዱበት ጀምሮ ነው ውሃ አጣጫቸውን ማፈላለግ የጀመሩት።ይሁንና ማንም ልባቸውን ያስደነገጠው አልነበረም።አሰበ ተፈሪ ሲመደቡ ነው የዛሬዋን ባለቤታቸውን ያዩት።
በዚህም ጊዜ ሳይፈጁ የትዳር አጋራቸው ትሆን ዘንድ ጠየቋት።ነገር ግን እርሷ ፈቃዷን ልሰጣቸው አልቻለችም።ዓመት ያህል ጠብቀውም ነበር ፈቃደኛ መሆኗን የገለጸችላቸው።ይሁን እንጂ እርሳቸው ወደ አዲስ አበባ ተቀይረው ሊሄዱ እየተዘጋጁ በመሆኑ እንዴት ተራርቆ ይሆናል አሉ።እርሷም ችግር እንደሌለው አስረዳቻቸው።ተማምነውም ቀለበት አደረጉ።ጋብቻቸው ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ሲመጡ ተፈጸመ።ዛሬ ባለቤታቸው ሚስት ብቻ ሳትሆን እናት ፣ አባት፣ የሥራ አጋርና ጓደኛቸው ጭምር እንደሆነችላቸው ይናገራሉ።ቤታቸው በፍቅር ተሞልቶ የመኖራቸው ምስጢርም እርሷ መሆኗን ያወሳሉ፡፡
አንድ ልጅ አላቸው።የወንድማቸውን ልጅ አሳድገው ሥራ አስይዘዋል።ከዚያ ባሻገር ቤት ውስጥ በዛ ብሎ መኖርና አብሮ መብላትን ስለሚወዱ አሁንም የወድማቸውን ልጅ አምጥተው ለልጃቸውም ሆነ ለእነርሱ ደስታን ሰጪ አድርገው አብረው እየኖሩ ይገኛሉ።ብዙ ጊዜያቸው በሥራ ስለሚያልፍም በቤት ውስጥ የመቆየታቸው ሁኔታ አይሰፋም።ይሁን እንጂ ወጣ ብለው መዝናናት ባለባቸው ጊዜ ያደርጉታል።ምንም አይነት ሱስ ስለሌለባቸውም አመሻሽ ላይ ከቤተሰቡ ጋር የማሳለፍ እድል አላቸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ሰዎችን በተቸገሩበት ጊዜ ላይ ብቻ መርዳት ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑ ናቸው።በዚህም በሰፈሩ አንቱታን ያተረፉና ለተቸገሩ ሁሉ በቻሉት መጠን የሚደርሱ፤ በተጠሩት ሁሉ አቤት የሚሉ ናቸው።ለዚህም በአብነት የሚጠቀሰው በሚኖሩበት አስኮ ወረዳ 14 የወላጆች ኮሚቴ በመሆን ልጆችን ፣ ሰራተኞችንና ቤተሰብን ከመበተን የታደጉበት ሥራ አንዱ ነው።በዚህ ሥራቸው ወረዳው በትምህርት ጥራት ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል ብሎ ሸልሟቸዋል።በተመሳሳይ ክፍለከተማውም ቢሆን የልማት አርበኛ ሲል በሰሩት የልማት ሥራዎች ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
መልዕክት
ብዙ ምሁራ ያልታዩ የተደበቁ እውቀቶች ባለቤት ናቸው።በዚህም መንግስት፣ ባለሀብቱና ራሳቸው ምሁራኑ በጥምረት በመስራት ለአገር የሚበጀውን ቢያደርጉ ጥገኝነት በማንም ላይ አይሆንም።ከራሳችን አልፈን ቀደም ሲል ነጮችን የመገብንበትን ሁኔታ ዛሬም እንደግመዋለን።ለዚህ ደግሞ ሥራችን የአጭርና ዛሬ ብቻ ተጠቅመነው የሚያልቅ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ አገር አሳዳጊ የሚሆንበትን መንገድ የምናይበት ቢሆን የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሬ እኔ ምን ላድርግ ብሎ ራሱን መጠየቅ መቻል አለበት።በተለይ ምሁሩ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ሲያይ አገሩን የሚለውጥበትን መንገድ መቀየስ ላይ ትልቅ ሃላፊነት አለበትና ይህንን የቤትስራውን ቢሰራ ይላሉ።ከራሳችን ለራሳችን የሚበቃ ሀይል እንዳለን ሁሉም መገንዘብ አለበት።ከውጪ በሚመጣ ቴክኖሎጂ ላይና ርዳታ ጥገኛ መሆን አይገባንም።እናም መደበኛ ሳይንሱን ወደ ተፈጥሮ በመቀየርና በትግበራ በማረጋገጥ ውጤቱን ማየትና ያንን እያሰቡ መስራት ያስፈልጋል።ምክንያቱም ሥራችን እንደ ጅረት ውሃ ተጠቅመን የምናፈስበትን መንገድ ያሳየናል፤ ለመስራትም ያነሳሳናል መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013