ሰውን መውደድ እግዚአብሔርን ከመውደድ ለይቼ አላየውም መርሐቸውም ተግባራቸውም ነው። ለዚህ ደግሞ አስተዳደጋቸው መሰረት እንደሆናቸው ያምናሉ። በተለይ ችግርን እያዩ ማደጋቸው ሌሎችን እንዲመለከቱና ለቁምነገር እንዲያበቁ አግዟቸዋል። መማር ለሰዎች መኖር፣ ከሰዎች ጋር አብሮ ማደግ ነው የሚል ፍልስፍና ስላላቸውም ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ለማገዝ ሰርተዋል። ለእርሳቸው ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች የእምነታቸው መለኪያ፣ የሰው ወዳድነታቸው መሰረትና ወደፊት የመጓዛቸው ምስጢር ናቸው። ስለዚህም ቤተሰባቸውን ትተው ከእነርሱ ጋር እያደሩ፤ የሚበሉትን እየበሉ ጊዜያትን አሳልፈዋል። ይህ ደግሞ ሰው ሰው እንዲሸቱ እንዳገዛቸውም መቼም አይረሱትም።
ከእምነት መሰሎቻቸው ጋር በመሆን ብራይት ስታር ኢትዮጵያን የመሰረቱ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ በሥሩ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒክና መሰል ነገሮችን በመክፈት ለማህበረሰቡ አገልግሎት ጭምር እየሰጡ ይገኛሉ በዋናነት ግን ተጠቃሚዎቹ የጎዳና ልጆች ናቸው። ምክንያቱም መነሻቸውም መድረሻቸውም እነርሱ ስለሆኑ ነው። ለመሆኑ እርሳቸውና ተቋሙ እንዴት ተዋወቁ፤ የእርሳቸውስ ህይወት ምን መልክ ነበረው ስንል ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው። እርሳቸውም ምንም ሳይሸሽጉ እንካችሁ የምትማሩበት ከሆነ በማለት ተሞክሯቸውን አካፍለውናልና እኛም ለዛሬ የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ አድርገን አቀረብንላችሁ፤ የዛሬው እንግዳችን አቶ ግዛቸው አይካ ይባላሉ።
የጎረቤት እንጀራ
የተወለዱት አዲስ አበባ ውስጥ ሽሮሜዳ አካባቢ ነው። ሽሮሜዳ ስትታወስ ደግሞ ሽመና ዋነኛ መለያዋ ነው። የእንግዳችን አባትም ሸማኔ ናቸው። እናታቸው ደግሞ የተለያዩ እቃዎችን ከተለያዩ ክልሎች እያመጡ በጉልት መልክ ተቀምጠው የሚሸጡና ቤቱን ለመደጎም የሚሞክሩ ናቸው። እርሳቸውና ወንድሞቻቸው እንዲሁም እህቶቻቸውም ቢሆኑ የራሳቸው ድርሻ ያላቸውና በሥራ የሚያግዙም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ቤተሰቡ በጣም ብዙ ስለነበር እህቶቻቸው እንጨት ይለቅሙና ይሸጣሉ። ወንድሞቻቸው ደግሞ በሽመናው አባታቸውን ያግዛሉ። የእርሳቸው ድርሻም እንዲሁ ከትምህርት ውጪ ባሉ ጊዜያት ማለትም ቅዳሜና እሁድ ጉልት ሄዶ ወይም እየዞሩ የተሰሩትን ልብሶች መሸጥ፣ አባታቸውን በቤት ውስጥ በተለያዩ ነገሮች ማገዝ፣ ወፍጮቤቱ ሩቅ ስለነበርም እህሉን ተሸክሞ ማድረስና መመለስ በዋናነት የሚጠቀሱ ሥራዎቻቸው ናቸው። በተመሳሳይ ብዙም ባይሆንም ታላላቆቻቸውን ተከትለው ተራራ ላይ ወጥተው እንጨት ለቅመው ያውቃሉ። ከዚያ ውጪ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተልና በቤተክርስቲያን ማገልገል ነበር ሥራቸው።
የማህበረሰቡ ኑሮና ባህል እርሳቸውን እንዳሳ ደጋቸው የሚናገሩት ባለታሪካችን፤ ጎረቤት ባይኖር ኖሮ የእኔም እጣ ፋንታ ጎዳና ይሆን ነበር ይላሉ። ምክንያታቸውም ቁርስ ቤት ከበሉ ምሳና እራት ጎረቤት መመገባቸው እንደሆነ ያነሳሉ። ማካፈልንም የተማርነው ከዚህ ነው ባይ ናቸው። ቤቱ ተያይዞ ያለና የግል ህይወት የማይታወቅበት መሆኑም ህብረት ምን ማለት እንደሆነ እንዲረዱ ማድረጉንም ያስታውሳሉ።
እንግዳችን ብዛት ባለው ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ሲሆን፤ ከ15 ልጆች ውስጥ እርሳቸው ስምንተኛ ልጅ ናቸው። ሁለቱን በማደጎ ሁለቱን ገጠር ለቤተሰብ በመስጠታቸው ቤተሰቡ ቀነሰ እንጂ በነበራቸው ጠባብ የቀበሌ ቤት ውስጥ ለመኖር እጅግ ከባድ ነበር። ይሁን እንጂ አባታቸው ቆጥ ሰርተውላቸው ስለነበር እዚያ ላይ እያደሩ ነው ልጅነታቸውን ያሳለፉት። ክብ ሰርቶ መመገብ በእነርሱ ቤት አይታሰብም። ራት ላይ ብቻ የሽመና ቦታው በመጠኑም ቢሆን ሥራ ስለማይኖረው ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ከዚያ ውጪ ቶሎ የተነሳና የደረሰ ምግብ ካለ ተሰጥቶት ውጣ መባል ልምዳቸው ነው። ስለዚህም የልጅነት አብዛኛው ትዝታቸው የቤት ውስጥ ሳይሆን የውጪ ነበር።
በጣም የሚገርመው የእነ አቶ ግዛቸው ቤት ሦስት በአራት መሆኗ ብቻ ሳይሆን በደባል ሌላ ቤተሰብ የጨመረች መሆኗ ነው። ቆጥ ባይኖር ኖሮ ማንም ለመተኛት ሳይሆን ለመቆምም አይችልባትም። ነገር ግን አባት ከሦስት የሽመና ቦታ በላይ ለሁሉም የሚበቃ ቆጥ ሰርተው እንዲተኙ አመቻችተውላቸዋል። ተለቅ ያሉትና ክብደት ያላቸው ግን መኝታቸው ሁልጊዜ መሬት ላይ ነው። ስለዚህም ማደሪያም የሥራ ቦታቸውም ትንሿ መኖሪያ ቤታቸው መሆናቸውን ሲያስቡ በተአምር እንጂ በሌላ ጉዳይ ኖርን ለማለት እቸገራለሁ ይላሉ።
ቤተሰብ ከመብዛቱና ሥራዎች የሚፈለገውን ያህል ሳይሳኩላቸው ሲቀሩ ቤት ውስጥ ምግብ ጭምር ያጥራል። በዚህም ተለቅ ያሉት ምግብ ሲመጠንላቸውና ይበቃሀል ሲባሉ ያስታውሳሉ። ከዚያም አልፈው እናት ሳይበሉ በልቻለሁ ብለው ቤተሰቡን ሲመግቡ እንደነበርም አይረሳቸውም። እናም የችግርን አስቀያሚነት በመኖር ጭምር ያዩት በመሆናቸው ማንም ሰው ይህ እንዳይገጥመው የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ የሚታትሩ ሆኑ።
በልጅነታቸው በጣም ከሚደሰቱበት ነገር አንዱ ትምህርት ቤትና ቤተክርስቲያን መሄዱን ነው። ምክንያቱም ሁለቱ ጋር ብዙ ነገሮች ደስታቸውን እንጂ ችግራቸውን አያስታውሱም። በተለይም በጨዋታ ብዙ ነገሮችን ስለሚረሱ ደስተኝነታቸው ይበዛል። የሚያባርራቸውና የሚቆጣቸው ስለሌለ በሰፊው ቦታ ላይ የፈለጉትን ጨዋታ ይጫወታሉ። ከጨዋታዎች ሁሉ ደግሞ ችግረኛን መርዳት ላይ የሚያደርጉት ምናባዊ የእቃእቃ ጨዋታ መቼም አይረሳቸውም። ህልማቸውም ያ እንዲሆን ያደረገው ይህ እሳቤና ፍላጎት እንደነበር አጫውተውናል።
በባህሪያቸው ተጫዋች፣ እልኸኛና ያሰቡትን ከማሳካት ወደኋላ የማይሉ ናቸው። በዚህም ሰፈር ውስጥ የሚጣሏቸው ሳይቀር ከእርሳቸው በእድሜ የሚበልጡ መሆናቸውን አይረሱትም። ለዚህ የሚያበቃቸው ደግሞ ምክንያታዊ ሳይሆኑ ስለሚያናድዷቸው ነው።
ማህበራዊነትን በትምህርት
የትምህርት “ሀ ሁ” ን የጀመሩት በቤተክርስቲያን ሲሆን፤ በዚያ ብዙ ተጉዘዋል። ከዚያም ዘመናዊ ትምህርቱን ደግሞ በእንጦጦ አንባ ወይም በዛሬው አጠራር አመሀ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስም በዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ቀጣዩን ትምህርታቸውን የተማሩት ደግሞ በተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለማቋረጥ ትምህርታቸውን መማር ችለዋል። በትምህርታቸውም የደረጃ ተማሪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ የመግባቱ ሁኔታ አልነበራቸውም። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ውጤታቸው ሳይሆን ሌላኛው ፍላጎታቸው ነው። ሰዎችን የመርዳትና ማህበራዊነት ልባቸውን ሰልቦታል። እናም በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን በማገዙ ሥራ ለዓመት ያህል ተጠመዱ።
መማር ለሁሉም ሥራ ውጤታማነት የበለጠ አቅም እንደሚኖረው የተረዱት ባለታሪካችን፤ በዲፕሎማም ቢሆን ቀን እየሰሩ ማታ መማር እንዳለባቸው ወሰኑ። በዚህም ‹‹አድማስ ዩኒቨርሲቲ›› በመግባት በማታው መርሐግብር የማኔጅመንት ትምህርትን አጠኑ። ዲፕሎማቸውንም ለመያዝ ቻሉ። የትምህርት ጥቅሙ የበለጠ ሲገባቸውም አሁንም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በማታው መርሐግብር የትምህርት መስካቸውን ሳይቀይሩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ። ከዚያ ኢንተርናሽናል ሊደርሽፕ የትምህርት መስክን ለመማር ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ጋር በሚሰራው በኢንተርናሽናል ሊደርሽፕ ኢንስቲቲውሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተማሩ። ከዚህ በፊትም ቢሆን ኮሚኒቲ ዴቨሎፕመንት ላይ የመጀመሪያ ዲግሪ መማር የቻሉም ናቸው።
ትምህርት በቃኝ የማይሉት እንግዳችን፤ አሁንም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ይገኛሉ። የመረጡት የትምህርት መስክ ደግሞ ሚኒስትሪ ሊደርሽፕ ይባላል። ለዚህ የሚረዱና ሥራቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፉ የተለያዩ ስልጠናዎችን በአገር ውስጥና በውጪም መውሰድ ችለዋል። አሁን ደግሞ ስልጠና ጭምር እየሰጡም ከሰዎች በሚያገኙት ልምድ ራሳቸውን በትምህርት እያጎለበቱም እንደሆነ አጫውተውናል። በተለይ ግን በልምድ ልውውጥ የሚያገኙት እውቀት የላቀ እንደሆነም ይናገራሉ። በተመሳሳይ ፊሊፒንስ ውስጥ ለአፓረንት ሄደው ያገኙት ልምድም ብዙ አቅም የጨመረላቸውና በአገራቸው የጀመሩትን ሥራ እንዴት ማገዝ፣ መለወጥ እንዳለባቸው ያስተማራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
የህይወት ጥሪን በሥራ
ሥራቸው ከማህበራዊ አገልግሎትና አመራር ያልወጣ ነው። በትምህርት ቤት የጀመሩት ሥራ ህይወታቸው ውስጥ መኖርና እርሳቸውን ማኖር ጀምሯል። ጥሪያቸውንም የተረዱት ከዚህ ውጪ ባለመሆናቸው እንደሆነ ያስባሉ። ሰው የተፈጠረበትን አላማ የሚያውቀው በአስተዳደጉ ጊዜ ነው። አስተዳደጉ በጎነትን ካስተማረውና ከፍ እስኪል ከተከተለው ጥሪውን ለማወቅ ብዙም አይቸገርም ብለው ያምናሉ። ለዚህም ማሳያው ራሳቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። እርሳቸው በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ቤተሰቦች ውስጥ የፈለቁ ቢሆኑም መልካምነትን ተምረውባቸዋል። ያለን መስጠትን፣ ባይኖርም አንተ ቅደም ማለትን ከቤተሰቦቻቸው ኖረውበት ተምረዋል። ከዚያም አለፍ ሲሉ ጎረቤቱ የሁሉንም ቤተሰብ መግቦ እድገት እንዲቀጥል አድርገዋል። አለፍ ሲሉ ደግሞ በእምነቱ ጎራ ‹‹ ሁለት ካለህ አንዱን ስጥ›› ተብለዋል። እናም እነዚህ ነገሮች ሲደመሩ ማህበራዊ ግልጋሎት የእርሳቸው ህይወት እንደሆነ አውቆ መኖርና ሌሎችን ማገዝንም ልምዳቸው አደረጉ።
ስለ ሥራ ስናስብም ብዙ ህይወታቸው የሚያጠ ነጥነው ከዚህ ሳይለይ የመሆኑ ምስጢር ይህ ብቻ ነው። ከ12ኛ ክፍል ጀምረው ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር መጀመሪያ በጓደኝነት ከዚያ በአጋዥነት ቀጥለዋል። ህልማቸው እነርሱን ከጎዳና ወደቤት ማስገባት ቢሆንም ከትንሽ በጎነት ትልቁ ይገኛልና ብቻቸውንም ባይሆን በጋራ ልፋታቸው በተሰራው ተቋም ውስጥ ብዙዎችን እያገለገሉ ፤ ለብዙዎች እየኖሩ አድገዋል። በእርግጥ መጀመሪያ በቅጥር ሲሰሩ የነበረው ራሳቸው ቋንቋ ለመማር ገብተው ትምህርት ቤት ረዳት በመሆን ያገለገሉበት ነው። ነገር ግን ስድስት ወር እንኳን አልቆዩበትም።
በብዛት የሰሩትና ሦስት ዓመታትን ያሳለፉበት ግን ራሳቸው ሸማ እየሰሩ ገቢ ማግኛቸው ላይ ነው። በዚህም ሁልጊዜ በሚሰሩት ሥራ ‹‹ለምን ይህ ብቻ›› የሚል መርህ አላቸውና የሰሩትን ልብስ በሰፈር ብቻ ከመሸጥ አልፎ የማይሄዱበት ቦታ አልነበረም። ሲሻቸው ሆቴል ጭምር እየገቡ መሸጥን ልምዳቸው አደረጉ። ይህ ደግሞ ሌላ እድል ሰጣቸው። ውጪ ድረስ የሚልኩበትን መንገድ አሳያቸው። ለዚህ መንስኤው አንድ ሆቴል ውስጥ ያገኙት የውጭ ዜጋ ነው። ልብሱን በጣም ወዶታል። የገዛበት ዋጋም
በወቅቱ ከሚሸጡበት በጣም ከፍ ያለ ነው። በዚህም አገር ውስጥ ለምን እወሰናለሁ በሚል ሥራቸውን ከፍ ለማድረግ ዓይናቸውን አበራላቸው። ሰፋ ወዳለ የገበያ አማራጭ እንዲገቡም አድርጓቸዋል።
በንግዱ ሲጠመዱ አገልግሎታቸው የቀነሰባቸው የመሰላቸው እንግዳችን፤ ይህንን ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝላቸውን ሥራ በመተው ለእነርሱ መኖር አለብኝ ሲሉ ቋሚ አገልግሎታቸውን ጀመሩ። ሶስት ዓመት ያህልም ያለምንም ገቢና ክፍያ መስራታቸውን ቀጠሉ። የቤተሰብ እጅ ጠባቂም ሆኑ። እንደውም እህታቸው ምግብ ካላመጣችላቸው ደረቅ ዳቦ እየበሉ ያሳለፉት ጊዜ ጥቂት እንዳልነበርም አይረሳቸውም። በተለይ በዚህ ትግላቸው ታናሻቸውንና ታላቅ እህታቸውን መቼም መዘንጋት አይፈልጉም። የህይወቴ ቀያሽ ናት ይሏቸዋል። ወቅቱ ምንም የሚሰሩበት ስላልነበረም ምሳም ፣ ቁርስም ሆነ ራት እርሷን ጠብቀው ነበር። ሁኔታቸውን ያዩና ቆራጥነታቸውን የተረዱ ቤተሰቦች ደግሞ ከመደገፍ ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው አመኑ። በዚህም በቻሉት ሁሉ ያግዟቸው ጀመር።
ሥራቸውን ያዩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና አባቶች እንዲሁም በማደጎ የተወሰደችው እህታቸው ሊያግዟቸው ቃል ገቡላቸው። ፍላጎታቸው እንዲሳካም የበኩላቸውን ረዷቸው። ይህ ደግሞ ገቢያቸው ቢያንስ ምግብ መብላት እንዲችሉ አገዛቸው። ከፍ እያለ ሥራዎቻቸውን እያጠነክሩ እውቅና ኖሯቸው መስራት ሲጀምሩ ደግሞ ከውጭ አገር ጭምር የሚያግዛቸው በዛ። እነርሱም ቋሚ ተከፋይ ሆነው ወደመስራቱ ገቡ። ከዚህ በኋላም ነው ወደ ተረጋጋ ህይወታቸው ዳግም የተመለሱት። በመሰረቱት ተቋም ውስጥም በጸሐፊነት፣ በመሪነት እያሉ ዛሬ ድረስም የደረሱት።
እንግዳችን አሁን ተቋሙን በኃላፊነት የሚመሩ ሲሆኑ፤ በመምራት ብቻ 22 ዓመታትን አገልግለዋል። ዛሬም በዚሁ ሥራ ላይ ይገኛሉ። ሆኖም ከዚህ በተጓዳኝ በተማሩት ትምህርት የተለያዩ ስልጠናዎችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ይሰጣሉ። ፐብሊክ ስፒቾችንም ያደርጋሉ። በቤተክርስቲያን አገልግሎትም ቢሆን እንዲሁ ይሳተፋሉ። እንደውም ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ጉዳይ ላይ መታየት እንዳለበት ይጠቁማሉ። ይህም ማህበራዊነት በአለን ልክ በመዋቅር ሊሰራበት ይገባል የሚለው ነው። አውሮፓ ላይ ለልምምድ በሄዱበት ጊዜ ከቀኑበት አንዱ ማህበረሰቡ በማህበራዊ ግንኙነቱ በጣም ጠንካራና መዋቅር ያለው መሆኑ ነው።
መንግሥትን ጠብቆ የሚደጉም ማንም የለም። በጣም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ጭምር መንግሥት ሳይሆን ማህበረሰቡ (ሶሻል ሰርቪስ) በራሱ ሰንሰለት ፈጥሮ ከዚያ ነገር እንዲላቀቁ ያደርጋል። በተለይም የሲዊዲን ማህበራዊነት በጣም ያስገርማቸው እንደነበር ያወሳሉ። ለምን ብዙ ኢትዮጵያውያን ድሃ ሆኑ የሚለውን ሲያስቡም ማህበራዊነቱ በሚገባ ባለመያዙ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ያለው ትልቅ ሀብት በአደረጃጀትና በመዋቅር አልተያዘም፣ አልተደገፈምም። መንግሥትን ብቻ የመጠበቅ አመልም አለ። በዚህም ሁሉም ለመደጎም እንጂ ለመስጠት አይነሳም።
ሌሎች አገራት መንግስት ባይኖር ይኖራሉ። እኛ ጋር ግን ማህበራዊነታችን የጠነከረ ቢሆንም ይህ አይቻለንም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መንስኤው ማህበራዊ ነገራችንን ከዘመናዊው ጋር በመዋቅር አሰናስለን አለመ ስራታችን ነው። አመራሮችና ማህበረሰቡ የተለያዩና የሚፈራሩ መሆናቸው፤ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ አለመሰራቱም ሌላው ችግር ነው። ነገር ግን ይህ ተቀርፎ ቢሆን ኖሮ ድሆች ጥቂት ሀብታሞች ብዙ ሆነው መተጋገዝ ይሰፋ ነበር። ተደጓሚነታችንም ይቀራል። በዚህም ደስ የሚል ኑሮን ለመኖር ማህበረሰቡ ውስጥ መግባትና ኑሯቸውን መኖር ያስፈልጋልና ይህንንም ለማምጣት ነው በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ላይ ጠንክሬ የምሰራው ባይ ናቸው።
ዊን ሶልስ እና ብራይት ስታር
ተቋሙ የተመሰረተው ከዛሬ 23 ዓመት በፊት ነው። መስራቾቹ የእንጦጦ መካነ ኢየሱስ የሰንበት ተማሪዎች ሲሆኑ፤ በትምህርት ቤቱ እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ የሚነገራቸው በጎ የማድረግ ተግባር አዕምሯቸው ውስጥ በመጸነሱ የገቡበትም ነው። እንግዳችንም የዚህ አካል አንዱ በመሆናቸው በጎ ምንድነው የሚለውን በደንብ አውቀውበት በህይወት እንዲኖሩ አሳይቷቸዋል። በተለይም ሁለት ያለው አንዱን ይስጥ የሚለው ትምህርት ውስጣቸው ገብቷል። በዚህም በዚያ በልጅነት አዕምሯቸው ሌላ ሰው ከምንጠብቅ ለምን እኛ ማካፈል አንጀምርም ወደሚለው ገቡ። ሰዎችን ለማገዝም ማማከርም ልገሳ ነው ብለው እጃቸውን ዘረጉ።
መጀመሪያ የሀሳብ ስምምነት ላይ ለመድረስ ማንን እናግዝ በሚል ተፋጩ። ሃሳብ በሃሳብ ተሸናነፉናም በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ላይ የሁሉም እምነት ወደቀ። ከዚያ በፊት ግን ይህንን ለማድረግ የሚያግዛቸውን ተግባር ይከውኑ ነበር። ይህም ሰዎች ቤት በመሄድ ቤታቸውን ማጽዳት፣ ልብሳቸውን ማጠብና ለታረዙ ማልበስ እንዲሁም ለተራቡት ማብላትን ተግባራቸው አደረጉ። ይህ ደግሞ ሌሎችን የሚያዩበት ዓይናቸውን ከፈተላቸው። ከዚያ የባሱ ሰዎችን እንዲመለከቱም ሆኑ። ቤት ያለው ይሻላልን ያዩትም በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ህይወትን ሲያስቡት ነው። ይህንን ደግሞ አይተው ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው ጎዳና ላይ ጭምር በማደር እንደነበር አይረሱትም።
መጀመሪያ አካባቢ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ለመቅረብ የተጠቀሙት ዘዴ ማውራት ሲሆን፤ አስተሳሰባቸው በጣም የላቀ እንደነበር ተረዱ። ቢታገዙ ራሳቸውን ብሎም ሌሎችን ለውጠው አገርን እስከመምራት እንደሚደርሱ አሳሰባቸው። እናም ጊዜ ሳይፈጁ ሥራቸውን ለማጠንከር ጓደኛ ወደማድረጉ ገቡ። በእርግጥ ይህም ቢሆን ለሁሉም በሁሉም መንገድ ፈተና የበዛበት ነበር። የጎዳና ተዳዳሪው ድብቅ ምስጢር፣ የትምህርታቸው ጉዳይ፣ የቤተሰብ አይሆንም ባይነት፣ የገንዘብ እጦት ወዘተ ሊታለፍ የማይችል ይመስል ነበር። ሆኖም ፈተናው ከባድ ቢሆንም ማገዝ፤ የሰው ፍቅር አሸንፎ ዛሬን እንዲያዩ አድርጓቸዋል።
ቸርቸር ጎዳና ላይ ያደሩበት ቀን ቤት የሚለውን እንዳሳሰባቸው የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ ብርዱና ውርጩ ምን እንደሚመስል መቅመሳችን በቤተክርስቲያን ላይ ጭምር እስከማመጽና ለምን እዚያ አይጠለሉም እስከማለት አድርሶን ነበር። ሆኖም ሁኔታውን ሲያስረዱን ተውነው። ቀጥሎ አማራጩ ቤት መከራየት ነበርና ገንዘብ ብናሰባስብም ሊበቃን አልቻለም። እናም አንድ ሰው ፈቃደኛ ሆኖልን መጀመሪያ አርባ ሰው ለማንሳት አቅደን በሁኔታው ያልተደሰተው ገንዘብ ከፋዩ አምስት እንዲሆኑ ተስማማንና ራሳቸው በወሰኑት ሰው ሥራው ተጀመረ። እዚህ ላይም ቢሆን ጎዳናም ያለ ለደከመው ጎዳና ተዳዳሪ ሲያስብ ያየንበትን ሁኔታ የፈጠረ ነበርና መተሳሰባቸው እስከህይወት ፍጻሜ እንድንሰራላቸው ያስገደደን ነበር ይላሉ ሂደቱን ሲያስታውሱ።
ተቋሙ በመመስረቱ በሺዎች የሚቆጠሩ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ከጎዳና ወጥተው ራሳቸውን ለውጠዋል። ለዚህ ደግሞ በትምህርት ሲወሰድ ሦስት ትምህርት ቤቶችን መገንባት በመቻላችን በዚያ የሚማሩበትን እድል ፈጥረናል። እየተማሩ ያሉትን ጭምር ብንጠቅስ በሺዎች ይቆጠራሉ። በሶስቱ ትምህርት ቤትም ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለን በማስተማር ላይ እንገኛለን። በየዓመቱም ትምህርት ቤቶቻችን ከመቶ በላይ ልጆችን ይቀበላሉ። ሲጀመር በ15 ነበር። ከዚያ 30 ሆኑ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 27ቱ በዩኒቨርስቲ ገብተው ተመርቀዋል። ከዚህ በተመሳሳይ በተለያየ ሙያ የሚሰለጥኑ ከጎዳና ላይ የተነሱ ልጆችም አሉን።
በዓመት ከ200 እስከ 300 ልጆች ከጎዳና አንስተን ትምህርት እንዲማሩ ድጋፍ እንሰጣለን። ቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉም የማድረግ አማራጭን እናመቻቻለን። በዚህም ብዙ ልጆች ትልቅ የሚባለው ደረጃ ላይ የደረሱ ልጆች አሉ። የምንገነባቸውን ህንጻዎች ሳይቀር የሚያማክሩንም ከእኛው የወጡ ናቸው። ከ80 እስከ 90 በመቶ የገቡትም ውጤታማ ለውጥ ያመጡ መሆናቸውን በሥራቸው እንደገመገሙ ይናገራሉ።
ዛሬ ላይ በዓመት እስከ 15ሺህ የሚሆን ተጠቃሚ መኖሩን የሚያወሱት ባለታሪካችን፤ በጤናም ቢሆን የህክምና ማዕከል መመስረታቸውን ፤ የወጣቶች ማዕከልም እንዲሁ መገንባታቸውን አጫውተውናል። አሁን ደግሞ የወጣቶች የአዕምሮ ልህቀት ማዕከል ለመክፈት ግንባታ ላይ እንደሆኑም ያነሳሉ። በቀጣይም ቢሆን የሚፈልጉት እነርሱ የሚችሉትን እየሰሩ አገራዊ ራዕይን የሚያስፈጽም ተቋም እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፤ የማይችሉትን ደግሞ ሀሳቡን በመንገር በአገር ደረጃ የሚሰራውን ማበርታት ላይ መታተር ነው።
የህይወት ፍልስፍና
የህይወት ፍልስፍናቸው ከአስተዳደጋቸው የሚርቅ አይደለም። ሰው ሁሉ እኩል ነው ፤ እኩልም ሊታይ ይገባል ብለው ያምናሉ። ኃላፊነት ለቀጣይ ትውልድ ብቻ ሳይሆን በዙሪያ ላለ ሁሉ የሚሰጥ ነው የሚል አቋምም አላቸው። ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውም ናቸው። ነገሮች ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይሄዱም። ከኋላ ያሉት ለጥሩ ነገር ይበጁናል። ትናንትን ስናይ ነገን የተሻለ እንድናደርግ መንገድ ይጠርጉልናል። እነርሱ የጀመሩትን እኔ ለልጆቼ አስተላልፈዋለሁ ብለው ያስባሉ።
በጎነት ያስተሳሰረው ትዳር
የባልና ሚስቱ ትውውቅ የጀመረው በቤተክርስቲያን ሲሆን፤ ወንድምና እህትነት እንጂ በፍቅር መተሳሰብን በጭራሽ አላሰቡትም። ሆኖም የፍላጎታቸው መመሳሰልና ለችግረኞች መድረስ ውስጣቸው እንዲግባባ አደረጋቸው። በተለይም በራይት ስታር ኢትዮጵያ ተጀምሮ ከፍተኛ ፈተና ውስጥ በገቡበት ወቅት አገልግሎቱን ከተቀላቀሉት መካከል ስለነበረች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ሰጪነታቸው ውስጣቸውን ሁልጊዜ ይገዛው ነበር። አሳቢነቷና እንክብካቤዋም እንዲሁ የልባቸው ተጋሪ እንድትሆን እንዲመኝዋት አረገቻቸው።
ከተጋቡ 16ተኛ ዓመታቸውን ጨርሰው 17 ዓመታቸውን ለመቀበል የተዘጋጁት እነዚህ በጎ አድራጊዎች ልጆቻቸው ጭምር እነርሱን እንዲመስሉ የማይሰሩት ሥራ የለም። ከወለዷቸው ልጆች በተጨማሪ ችግረኞችን አይተው ማለፍ አለመቻላቸው ቤታቸው ብዙ ሰው እንዲኖር አድርገዋል። የወንድምና ቤተሰብ ልጆችም አሉ። ግን መቼም አይበቃቸውም። ሁልጊዜ እነርሱ የበሉትን እየበሉ እንዲኖሩ ሌሎችንም ማምጣት ይፈልጋሉ። ይህም ሆኖ አሁን ቤቱ ውስጥ 16 ቤተሰብ ይኖራል። ግቢ ውስጥም እንዲሁ እንዲኖሩ የፈቀዱላቸው አሉ። ይህ ደግሞ ደስተኝነትን በበጎነት ገዝቶ መኖር እንዲቻል አድርጓቸዋል።
በቤት ውስጥ ያለ ልጅ ሁሉ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ከልብሳቸው ከጫማቸው ውስጥ ብዙዎቹ እንደሚወሰዱና ለችግረኞች እንደሚሰጡ ያውቃሉ። እነርሱም ቢሆኑ ይህ ይሻላቸዋል ባይ ከሆኑ ውለው አድረዋል። ይህ ደግሞ በጎነት በልጆቹ ላይ ጭምር ኖሮ እንዲያድግ የተደረገበት ሁኔታ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ስለዚህም በቤት ውስጥ ደስታ፣ መስጠት እንጂ መሰብሰብ አይታሰብም። ይህ ደግሞ የበረከት ቤት እንዲሆን አምላክ እድሉን እንዳመቻቸላቸውም አጫውተውናል።
መልዕክት
ሰዎች ለሌላው ማካፈል በረከት እንጂ እንደማያሳጣ ቀምሰው ቢያዩት ደስ ይለኛል። ምንም ማካፈል የሚችሉት ነገር ባይኖራቸውም ሰላምታን ቢሰጡ ብዬ እመኛለሁ። ምክንያቱም ለአገራችን ህዝብ ምግቡ እንደምን አደርክ በመሆኑ በሰላምታው ሰላምን ያሰፋል። ፍቅርን ያጠነክራል። ለሌሎች መኖርን ያላምዳል። ሰውን መውደድን ያላብሳል። ሰውን ሁሉ በእኩልነት ለማየትም መንገድ ይጠርጋል።
እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን ለሰዎች መገልገያ ፈጥሯል። ሲፈጥራቸውም ይሁን ይደረግ በማለት ነው። ሰውን ግን ሲፈጥረው ከዚህ በተለየ መልኩ ነው። በአርአያውና በአምሳሉ ራሱን አስመስሎ ነው። ይህ ደግሞ በምክንያት በመሆኑ የእግዚአብሄርን መልክ የያዘን ሰው ውጣልኝ፣ አታስፈልገኝም ማለት አይገባም። ይህንን ስናደርግ የእርሱን መኖር የምናስብበትን ትልቁን ፈጣሪ እየገፋን መሆኑን ማመን ይኖርብናል። ስለዚህም እንደ አገርም ሆነ እንደ አማኝ ማሰብ ያለብን አምላክን መውደድ ሰውን ሳይለዩ መውደድ እንደሆነ ነው። እምነታችን ለሰው ሁሉ ማሳየት ያስፈልገናል። የዓለም ጨው ናችሁ ተብለናልናም ለሰው ሁሉ እኩል ጨው መሆንም አለብን። ተራራውን ብንቆፍረው አምላካችን አይከፋም። ሰውን ብንገለው ግን ያዝንብናል። ምክንያቱም እርሱ እንጂ እኛ በዚያ ሰው ላይ ስልጣን የለንም። በመሆኑም ሰውን ላለማስከፋትና ከአምላክ ላለመጣላት እንሞክር መልዕክታቸው ነው።
የትኛውም ዘር ይሁን የትኛውም ሀይማኖት እንደ አገር የሚታሰብበት ሲሆን ብቻ ነው አሸናፊ የሚሆነው። ሳይሸነፍ ያሸነፈ ማንም አይኖርም። ስለዚህም መሸናነፍ በፍቅርና በውይይት በመተማመን መሆን አለበት። የምንፈልገውን ልክ መርጠው ሲያሸንፉ በእነርሱ ልክ ሁሉም ይሸነፋልና ያንን እድል መስጠትም ያስፈልጋል። ሰውን በእንግድነት እንደምንቀበልበት መጠን ኑሯችንን ማድረግ ላይም መስራት ይኖርብናል። ምክንያቱም ይህ የደስታ ምንጭ ነው። ለሌሎች መደሰት ደስታን ዘላለማዊ ማድረግ ስለሆነ። እናም ሰዎች ይህንን ልምድ ቢያደርጉ ሲሉም ይመክራሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013