
ቦሌ ዛሬ እንደ ተለመደው በጠዋቱ ዘንጣለች። እስቲ ከናጠጠው መንደሬ ልውጣና “ዎክ” ላድርግ አለች። ተወልዳ ካደገችበት ቀዬ ለመሄድ ሽቅብ አቀበቱን ተያይዛ ከተጓዘች በኋላ መኪናዋን አንድ ቦታ ላይ አቁማ ወረደች። አይስክሬሟን እየላሰች የመኪና ቁልፏን እያሽከረከረች በቀስታ መራመድ ጀመረች።
መሀል ከተማ ብዙ ክፍለ ከተሞች ተሰብስበው ይንጫጫሉ። ቦሌ አንዳንዶቹን በስም ብቻ ነው የምታውቃቸው። ጠጋ ብላ የሚጨቃጨቁትን መስማት ጀመረች። ጭቅጭቁ ቂርቆስ የምትባል ችስታ እቁብ በልታ ስታበቃ በሌሎቹ ተራ አልከፍልም በማለቷ ነው የተቀሰቀሰው። የቂርቆስ የቅርብ ጎረቤት ልደታ እየቀወጠችው ነው።
ቂርቆስዬ ምንም ሳትደናገጥ “የፈለገ ቢሆን አልከፍልም፤ በቃ ቸግሮኛል፤ አትጨቅጭቁኝ” እያለች ወገቧን ይዛ ትውረገረጋለች። ብዙ ጊዜ ይከፋታል፤ ትበሳጫለች። “እንዴት አትከፍይም ባለፈውም የሌላ ሰው እጣ ሁላ በልተሽ የለ እንዴ!? ተይ ቂርቆስ ተይ ሁሉም ይታዘብሻል! አበስኩ ገበርኩ!“ አለቻት ቦሌ። ብድግ ብላ እጇን እያወራጨች ጭምር ትናገር ስለነበር የተቀባችው ሽቶ በቀላሉ ያውዳል፤ የሚገርም ሽቶ ነው።
“አሁን ምንም የለሽም የምር?“ አላት አራዳ። “እውነቴን ነው፤ ቤሳ ቤስቲን የለኝም“ ብላ መዳፉን በመሀል ግጥም አድርጋ መታችው። ቂርቆስ አራዳ ስለሆነች ዝባዝንኬ መሀላ አታበዛም። እውነት ካለች ሁሉም እንደማትዋሽ ያውቃሉ፤ በዛ ላይ አራዳ የቂርቆስ ነገር አይሆንለትም፤ ይዋደዳሉ። አንዳንዴ ብሔራዊ አካባቢ ሲገናኙ ቴአትር አብረው ይመለከታሉ። እናም በአንዴ አመናት። እዳዋንም ከፈለላት።
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ዳር ላይ ቆም ብሎ ሁኔታቸውን በግርምታ ሲከታተል ቆይቶ የቂርቆስ ድርቅና ሲገርመው እየሳቀ ጥሏቸው ሄደ። ቂርቆስ ከአራዳ ፍቅር የያዛት ይመስላል። ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው። ሁለቱም ነቄ ናቸው። ሁለቱም ችስታ ናቸው። ከእቁቡ በኋላ አራዳን ይዛ ለሽርሽር መሄድ አማራት። ምቹ ወደ ሆነው ጉለሌ አቀናች። ጉለሌ በሽርሽር እየሰቀለ ነው። አራዳ ፍንዳታ ነገር ነው። ፊቱ በጸብ ምክንያት ተቦጫጭሯል። የፊት ጥርሱም ወላቃ ነው።
ከግርግርና ሁከታ ተላቀው ዘና ማለት ፈልገዋል። አረፍ የሚሉበት ቦታ ፍለጋ ወደ ላይ የእንጦጦ መውጫን ተከትለው ወጡ። በጨዋታቸው ለአራዳ እንዳወጋቸው ከሆነ፤ ቂርቆስ እድሜዋ ረጅም ነው። ቁመናዋ ግን ትንሽ ነው።
አራዳ የቂርቆስ ሙድ ቢመቸውም እድሜዋና ነገረ ሥራዋ ግን የነገረኛ ባልቴት ሆነበት። ኮንፊደንስ አላት። ዝም ብላ ከጎን ከጎኑ እየሄደች ኃላፊ አግዳሚውን ትገላምጣለች። ትንሽ ሄድ እንዳሉ ጉለሌ ከርቀት አይቷት “ቆይ ጠብቂኝ አንቺ ኩሩሩ አገኝሻለሁ! አራዳ የሚያድንሽ መስሎሻል” አላት ሌባ ጣቱን እያወዛወዘ።
“አሁን ምን አደረግኩህ እስቲ?“ አለች ቂርቆስ ብዙም ፍርሃት ሳይታይባት። “ከዛች ሀብታም ተብዬ ቦሌ ጋር አፍ ለአፍ ገጥመሽ ስታሚኝ ያላየሁሽ ያልሰማሁሽ እንዳይመስልሽ!“ አላት ጉለሌ። “ቆይ ከጎረቤቴ ጋር ቡና መጠጣትም ልትከለክለኝ ነው?“ አለች ቂርቆስ፤ በአንድ በኩል “በፓርክ” ዘንጦ ስታየው የማነው ሸበላ በሚል ጉለሌን ከእግር እስከራሱ እየገረመመች። “አሳይሻለሁ ቀንሽን ጠብቂ!“ አላትና እየተገለማመጡ ተላለፉ።
ቆሞ የሚጠብቃት አራዳ ጋ ለመድረስ ራመድ ራመድ አለች። “አስቆምኩህ አይደል ይቅርታ!“ አለችው እንደደረሰች። “አይ ምንም አይደል“ አለ አራዳ። ምን ባክህ ይሄ ነገረኛ ፍንዳታ ጉለሌ አላሳልፍ አለኝ እኮ። ቁመናው እንኳን አሪፍ ነበር። ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች አሉት፤ ተፈጥሮው ውብ ነው። ነገር ግን ጠባይ ነሳው። ይገርምሀል ሁሌም ዝናብ የሚመጣው በእርሱ በኩል ነው። ከፍታ ቦታ ላይ ስላለ ከሁሉም በላይ መሆን ይመኛል። እያለችው ከአራዳ ጋር ሽርሽሯን ወደ ሌላ አቅጣጫ ቀየረች።
ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ከየካ ጋር ተያያዘች። “ይሄ ደግሞ ምን አደረገሽ?’ አላት አራዳ። “የካ ምን? ያላደረገኝ ነገር አለ? ቆይ እሰራለታለሁ“ አለች። እኔን ከሩቅ እያሽኮረመመኝ ቦሌን ተጠግቶ “ ለሚ ኩራ” የሚባል ልጅ መውለዱን አልሰማህም እንዴ?” …”በእርግጥ ልጅ ጸጋ ነው። እኔ ልጅ በመወለዱ ቅሬታ የለኝም። ነገር ግን እኔን አሽኮርምሞ ከእኔ ጎረቤት መውለዱ ነው ቅናት ያሳደረብኝ ። ገና ለገና ቦሌ የሀብታም ልጅ ስለሆነች እኔን መካድ ነበረበት?” አለችው።
ካፌ እያፈላለጉ ወደ ታች ቁልቁል ሲጓዙ ከአቃቂ ጋር ተገናኙ። ቂርቆስ ሰረቅ አድርጋ አቃቂን አየችው። አቃቂ ፊቱ ልውጥውጥ ብሏል። ለቦክስ የተዘጋጀ በሚመስል አኳኋን፤ እጁ ላይ ያደረገውን ጌጥ አወለቀ። “ምነው ያምርብሀል እኮ አታውልቀው” አለው አራዳ ቂርቆስን እንዳይመታት በአራድኛ ለማስቀየስ በሚል ሁኔታ።
“ምንድነው ይሄ?“ አለው የእጁን ጌጥ እየጠቆመው። የአቃቂ ወንዝ ይባላል አለውና ወንዙን አውልቆ እፊታቸው አስቀመጠው። “እና ለምን ታወልቀዋለህ?” አለችው ቂርቆስ ፈራ ተባ እያለች። “በዚህ ወንዝ ተጠራቅሞ የሚመጣው ቆሻሻ የራሴ አይደለም። የእናንተ ነው።” አላቸው፤ እልህ እየተናነቀው።
“ሁላችሁም ከላይ ሆናችሁ እኔ ላይ የምትልኩትን እጣቢ እኔ አሜን ብዬ ስቀበላችሁ ነበር። አሁን ሰለቸኝ። በተለይ ቂርቆስ፣ ቦሌና ላፍቶ ጎረቤቶቼ ሆናችሁ ሳለ አንድ ቀን እንኳን ብቅ ብላችሁ የሚያቆሽሸኝን እጣቢ መቼ አጸዳችሁልኝ ፤ ይህን ወንዝ ከአሁን በኋላ ተረከቡኝ” አላቸው።
ግልጽነቱን ወደዱለት። ጎዳቱንም አዩለት። ወዲያው ከኪሳቸው ስልክ አውጥተው ለሁሉም ክፍለ ከተሞች መደወል ጀመሩ። ቦሌ ከየካ ጋር እያወራች በእጇ ልጇን ለሚ ኩራን ይዛ መጣች። ንፋስ ስልክ ላፍቶና አዲስ ከተማ በምዕራብ በኩል ሆነው የጦፈ ወሬ እያወሩ ከተፍ አሉ። ጉለሌም ከሰሜኑ እየተንደረደረ ወረደ። ልደታም እስር ቤት ሰው ጠይቃ ስትወጣ ከጉለሌ ጋር ተገናኙና እያወጉ ደረሱ። በቦሌ ቃለ ጉባዔ ያዥነት፤ በአራዳ ፕሮግራም መሪነት፤ በአቃቂ ቃሊቲ ቅሬታ አቅራቢነት በሌሎች ታዳሚነት ውይይቱ ተጀመረ። አዲስ ከተማና ኮልፌ ቀራንዮም ተገኝተዋል።
“ባለፈው ለማይረባ አቁብ ስንጨቃጨቅ ቆይተን እንዲሁ ተበተንን። መቼም ፈጣሪ ያክብረውና አራዳ ነው ከእናንተ ዱላ ያዳነኝ። !አንዳንዴማ የወለድኩት ልጄ ነው የሚመስለኝ። እስካሁን ሳይለይ የሚንከባከበኝ እሱ ነው። እርሱ በሁለት እግሬ ባያቆመኝ መቼ እዚህ እደርስ ነበር። ብቻ ያኑርልኝ” አለችና እንባዋን አበስ አደረገች- ቂርቆስ። “እናም ሁላችንም ተጋግዘን የአቃቂን ችግር ችግራችን ልንል ይገባል ለማለት ነው።“ አለችና ንግግሯን ቋጨች።
የካ ኮቱን አስተካከለና በኩራት ወደ እነርሱ ዘር ብሎ “በዚህ ጉዳይ በመሰባሰባችን ደስ ብሎኛል። እኛ የአዲስ አበባ ውበቶች እርስ በእርስ ካልተጠባበቅን ማን ሊጠብቀን ይችላል፤ ለእንግድነት ከሩቅ የሚመጡት እኮ አንድነታችንን ሲመለከቱ ነው የሚደመሙት። ከእንግዲህ አንዱ ጸድቶ ሌላው የሚቆሽሽበት ሁኔታ መኖር የለበትም። የኛን ውበት ከጠበቅን ሌላውም ይዋባል፤ ያጌጣል። ስለዚህ ከላይ ከእንጦጦ ጀምረን አዲስ ልብስ እንልበስ፤ እንሽቀርቀር የዛኔ ነው አቃቂም ከችግሩ የሚወጣው” ብሎ ሁሉንም አስማማ።
ሁሉም በሀሳቡ ተስማምተው ከአንድ ገበታ ሊመገቡ ተከታትለው ሄዱ። ገበታ ለሸገር የምትባል ቆንጆ ጋ ደረሱ። ከእጇ በልተውና ጠጥተው ሂሳባቸውን አወራረዱ። ሸገርም ተዋበች።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013