አረንጓዴ ልማት
የጂኦስፓሻል መረጃዎች በምድር ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበትን ደረጃ በመለየት ለዘላቂ ጥቅም ለማዋል የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ በየጊዜው የሚሰበሰቡ የጂኦስፓሻል መረጃዎች በባለሙያዎች እጅ ገብተው ከተተነተኑ በኋላ መሬት ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ከጉዳት ለመታደግ አልያም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ያስችላሉ።
በኢትዮጵያም በምድር ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን መረጃ በመያዝ ሀብቶቹ እንዲጠበቁ የሚሠራ የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተሰኘ መስሪያ ቤት ተቋቁሞ መሥራት ከጀመረ ረጅም ጊዜያትን አስቆጥሯል። ከሰሞኑም መቀመጫውን ኬኒያ ያደረገ ‹‹ሪጅናል ሴንተር ፎር ማፒንግ ኦፍ ሪሶርስስ›› የተሰኘ ተቋም ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመሆን ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ጋር በተያያዘ በጂኦስፓሻል መረጃዎች አስፈላጊነት ዙሪያ የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ እንደሚገልጹት በምሥራቅና ደቡባዊ የአፍሪካ አካባቢዎች ያሉ ሀገራትን የጂኦስፓሻል መረጃ ለማረጋገጥ መቀመጫውን ኬንያ ያደረገውና ‹‹ሪጅናል ሴንተር ፎር ማፒንግ ኦፍ ሪሶርስስ›› የተሰኘው ተቋም 20 አባል ሀገራትን በማቀፍ እ.ኤ.አ በ1975 ተመስርቷል። ኢትዮጵያም ከሃያዎቹ አባል ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት። የተቋሙ ዋነኛ ዓላማም የዚህ ቀጠና ሀገራትን የጂኦስፓሻል መረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የአፍሪካን እድገት እውን ለማድረግ ብሎም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚያመቹ ከተፈጥሮ ሀብትና ከሰላም ጋር ተያይዞ ያሉ የተለያዩ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን ማምረት ነው።
ተቋሙ የሚያመርታቸው የተለያዩ የጂኦስፓሻል መረጃዎች የአካባቢ ስነምህዳርን ለመንከባከብ በተለይ ደግሞ ከመሬት መራቆት ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ደረጃና በቀጠናው አባል ሀገራት አካባቢ የመሬቱ ሁኔታ ምን እንደሚመስልና መሬቱ መራቆቱን አልያም ደግሞ መልሶ የማልማቱ ሥራ በትክክል እየተሠራ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለአባላቱ ተደራሽ ያደርጋል። በተመሳሳይ በእርጥበት አዘልና በሳር የተሸፈኑ መሬቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለው ለውጥ ምን እንደሚመስልም መረጃዎችን በማጠናከር በተለይ ለአርብቶ አደሩ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ መረጃዎችን ያመርታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ በኢትዮጵያ፣ በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ ያሉ የተፈጥሮ የውሃ ሀብቶች ምን እንደሚመስሉና የውሃ ሀብቶቹ የት አካባቢዎችና በምን ያህል መጠን እንደሚገኙ እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ተፅእኖዎች የውሃ ሀብቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለም በቀጠና ደረጃ ያጠናል። የቀጠናው አባል ሀገራት ባሉበት የአግሮ ኢኮሎጂካል ዞን ለቀጠናው የምግብ ዋስትና የሚሆኑ ምን ዓይነት የሰብል ምርቶች የት አካባቢዎች ላይ መመረት እንደሚችሉም መረጃዎችን ይሰጣል።
ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞም ተቋሙ በቀጠናው ያለው የመሬት አጠቃቀም ምን እንደሚመስልና ምን ያህሉን ለግብርና፣ ለከተማ ልማት፣ ለደን ሀብት እንክብካቤና ለመልሶ ማልማት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ ለአባል ሀገራት የጂኦስፓሻል መረጃዎች እንዲደርሳቸው በማድረግ በመረጃው መሰረት ሥራዎችን እንዲሠሩ ያደርጋል።
በዋናነት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር ተቋሙ ለቀጠናው አባል ሀገራት የጂኦስፓሻል መረጃዎችን እያመረተ ያቀርባል። ኢትዮጵያም እንደ አንድ አባል ሀገር በምድሯ ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በዘላቂነት ለመጠቀም ተቋሙ የሚያመርታቸውን የጂኦስፓሻል መረጃዎችን እየተጠቀመችና አብራ እየሠራች ትገኛለች።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የበረሃማነት መስፋፋት አዝማሚያዎች ይታያሉ። እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ ከመከላከል አንፃር በአንድ ሀገር ብቻ የሚሠራ ሥራ ባለመሆኑ ቀጠናዊ ትብበር የሚፈልጉ ጉዳዮች በመሆናቸው አብሮ ለመሥራት የቀጠናው አባል ሀገራት ተባብረዋል። ለኢጋድም ሆነ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለውሳኔ አሰጣጥና የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚጠቅሙ መረጃዎችም በተቋሙ በኩል እየተመረቱ ይገኛሉ።
እነዚህ መረጃዎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች በተለይ ‹‹The Global Monitoring for Enviroment and Security and Africa›› በሚለው ፕሮግራም ከላይ በተጠቀሱት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሠራበት ይገኛል። ኢትዮጵያም በኢንስቲትዩቱ በኩል በፕሮጀክቱ የምርምር ሥራዎች ላይ ተሳትፋ ለቀጠናው የሚጠቅሙ የተለያዩ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን ለተጠቃሚ አካላት ተደራሽ እንዲሆኑ የጂኦፖርታል ልማት ሠርታለች።
መረጃ ማምረቱ አንድ ሂደት ሆኖ እነዚህን መረጃዎች በቀጣይ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳኪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ ደረጃም የአረንጓዴ ልማትን ለማስቀጠል ጥቅም ላይ ይውላሉ። ይህም የደን ሀብቱ በለማ ቁጥር የውሃ ሀብት ክምችቱ እንዲጨምር ያደርገዋል። ስነምህዳሩም እየለማና እያዳበረ ይሄዳል። የጂኦስፓሻል መረጃዎቹም ይህንኑ እውን ለማድረግ ያስችላሉ።
የጂኦፖርታሉ መልማት የቀጠናው አባል ሀገራት ሳይቸገሩ መረጃዎችን በቀላሉ ከቀጠናው ማእከል በኢንተርኔት አማካኝነት ማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ ተሠርቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ተቋማትም በኢንስቲትዩቱ በኩል እነዚህን መረጃዎች በመጠየቅ ከቀጠናው ማዕከል ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም መረጃዎቹን ለማየትና ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል።
መረጃዎቹን በመጠቀም አዳዲስ የመረጃ ምርቶችንም እሴት ጨምሮ ማምረት ይቻላል። የግሉም ዘርፍ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገባ ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ካሉት ምርቶች ላይ በመነሳት አዳዲስ ምርቶችን እንዲያመርቱ፤ መሰረታዊ የሆነ ዳታ ለሌሎች ተጨማሪ አዳዲስ መረጃዎች እንዲለሙ ይረዳል። በመረጃዎቹ አማካኝነት የቀጠናው ሀገራትም ከልማት፣ ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና የተፈጥሮ ሀብቱን ለዘላቂ ልማት ከመጠቀም አንፃር ጉልህ ሚና እንዲኖረው በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ‹‹ The Global Monitoring for Enviroment and Security and Africa›› በተሰኘው ፕሮግራም ኢትዮጵያ በሦስት አበይት ምርምሮች ላይ ከሌሎች የቀጠናው አባል ሀገራት ጋር በተለይም ኬኒያ ከሚገኘው የቀጠናው ማዕከልና ኡጋንዳ ከሚገኘው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የተሠሩ ሥራዎች አሉ። በተለይ ደግሞ የመሬት መራቆት፣ የእርጥበት አዘልና በሳር የተሸፈኑ መሬቶች፣ የውሃ ሀብቶችና የአግሮ ኢኮሎጂካል ግምገማና ቁጥጥር መረጃዎች የለሙትም በዚህ ፕሮግራም ነው።
በዚህ ፕሮግራምም መሰረታዊ የሚባሉ መረጃዎች ለምተዋል። መረጃውን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ጂኦፖርታል እንዲለማም ተደርጓል። በቀጣይም ይህ መረጃ ለሁሉም የመንግሥት ተቋማት፣ ለግሉ ዘርፍና ተመራማሪዎችም ጭምር የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ለዚህ ፕሮግራም እውን መሆንም ኢትዮጵያ የራሷን አስተዋፅኦ ስታደርግ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የመሬት መራቆት አዝማሚያዎች በሳተላይት ምስልም ሆነ በመሬት ላይ ምልከታ ባለሞያዎች ከኬኒያና ከኢትዮጵያ ተውጣተው ብዙ መረጃዎችን በማሰባሰብ ብዙ ዓይነት የመረጃ ምርቶች እንዲመረቱ ተደርጓል። ይህን ምርት በቀጣይ የመንግሥት ተቋማት እንዲያውቁትም የጂኦፖርታሉ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል። በቀጣይም የጂኦፖርታሉን የማስተዋወቅ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራበታል።
አንድ የጂኦስፓሻል መረጃ ሲመረት በብዙ ተቋማት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ይፈለጋል። ለአብነትም መረጃውን የግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ፣ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና ሌሎችም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሳተፉ የመንግሥት ቁልፍ ተቋማት የከተማ ዘርፉን ጨምሮ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እነዚህን መረጃዎች ይዘው የት አካባቢ የስነ ምህዳር ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ለመለየትም ያስችላቸዋል። መልሶ ማልማት የሚያስፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች የት እንዳሉና ስነ ምህዳሩን ከማጎልበት አንፃር በቀጣይ በስትራቴጂክ ልማት መንግሥት እንዲሠራ እንደመነሻ የሚጠቅሙ መረጃዎች ናቸው። ለውጥ የመጣባቸውንና ከዚህ በፊት ያልታዩና የተጎዱ ቦታዎችን በማየትም እነዚህ መረጃዎች በየጊዜው እንዲታደሱ ይደረጋል።
ኬኒያ ናይሮቢ በሚገኘው ‹‹ሪጅናል ሴንተር ፎር ማፒንግ ኦፍ ሪሶርስስ ፎር ዴቨሎፕመንት›› የጂ ኤም ኢ ኤስ ኤንድ አፍሪካ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ደገሎ ሰንዳቦ በበኩላቸው እንዳሉት ፤ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን ‹‹ The Global Monitoring for Enviroment and Security and Africa›› ፕሮግራም በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እ.ኤ.አ በ2018 በቀጠናው አባል ሀገራት ውስጥ ተጀምሯል። ሆኖም በ2020 ማለቅ የነበረበት ቢሆንም በኮቪድ19 ምክንያት ወደ 2021 ተሸጋግሯል። የፕሮግራሙ ሁለተኛ ክፍልም በቀጣይ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሮግራሙ ሳተላይቶች የሚያመርቱትን የመረጃ ምርት የመጨረሻው ተጠቃሚ ጋር እንዴት ማድረስ እንደሚቻል መነሻ በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፤ ፕሮግራሙን በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ውስጥ የሚገኘው የአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ ተቋም ይዞታል።
የተለያዩ ሳተላይቶች የሚያነሷቸው መረጃዎች ቢኖሩም ጥቅም ላይ ሲውሉ አይታይም። በተለያየ መልኩ የሚሠራ የጂኦኢንፎርሜሽን መረጃና የመሬት ምልከታ ዳታ ቢኖርም የመጨረሻ ተጠቃሚዎች የሆኑት በተለይ አርሶና አርብቶ አደሮች አያገኙትም። የዚህ ፕሮግራም ዓላማም የሳተላይት መረጃዎችንና የመሬት ምልከታ ዳታዎችን በመጠቀም ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ማረጋገጥ ነው።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ የቀጠናው ሀገራት እርጥበት አዘል መሬቶች በግጦሽና በእርሻ አማካኝነት በመገፋታቸው ሊጎዱ የቻሉትም እነዚህን የሳተላይትና የመሬት ምልከታ መረጃዎችን ታች ድረስ በማውረድ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ውሳኔ ሰጪው አካል የዚህን መረጃ አስፈላጊነት በመረዳት ጥቅም ላይ ለመዋል መቸገሩ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
በመሆኑም ከአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጋር በተያያዘ የሚያሰጉ በርካታ ነገሮች በመኖራቸው ውሳኔ ሰጪውና የመጨረሻው ተጠቃሚው የጆኦ ኢንፎርሜሽንና የመሬት ምልከታ መረጃዎችን እንዲያውቁና ጥቅም ላይ እንዲያውሉ በማድረግ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ይጠይቃል። የሳተላይት መረጃ በአብዛኛው በነፃ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያም መረጃው ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ያስፈልጋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ፕሮግራሙ በሦስት አበይት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን፤ እነዚህም በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ያሉ ጨፊያማ ቦታዎች እየጠፉ መምጣት፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተራቆቱ ቦታዎች መብዛትና በየቦታውና በየመስሪያ ቤቱ ያሉ የጂኦንፎርሜሽን መረጃዎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በተዋረድ ማድረስ አለመቻል ናቸው።
በዚሁ መሰረትም ፕሮግራሙን በቀጠናው ባሉ ሀገራት ተግባራዊ በማድረግና በተለይ ደግሞ የሳተላይትና የመሬት ምልከታ መረጃዎች ውሳኔ ሰጪው አካል ጋር እንዲደርሱ እና የመጨረሻ ተጠቃሚ የሆኑት አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲጠቀሙባቸው በማድረግ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውሉና ልማቱን እንዲያረጋግጡ እየተሠራ ይገኛል። ይህንኑ መረጃ በሀገር፣በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግም አመቺ ከመሆኑ አኳያም በዚህ ረገድ በቀጣናው ብሎም በኢትዮጵያ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ይሁንና መረጃው እስካለ ድረስ ደግሞ መረጃውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከሁሉም አካላት ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013