“መንግስት በሰጠኝ ቤት እንደዜጋ በነጻነት እንዳልኖር ተደርጌ ፣ የዜግነት መብቴ ተገፎና ህይወቴ የደህንነት ስጋት ውስጥ ከገባ ድፍን ሦስት ዓመት ከአምስት ወር በላይ ሆኖታል። ከሶስት ዓመት በላይ ፍትህ ለማግኘት ተከራክሬ ፍርድ ቤት ቢወስንልኝም የወረዳው አመራሮች በማናለብኝነት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በአግባቡ ሊፈጽሙልኝ አልቻሉም። ዛሬም የዜግነት መብቴና ነጻነቴ ተገፎ ህይወቴ በስጋት ቋፍ ውስጥ እገኛለሁ። እስካአሁኗ ጊዜ ድረስ እያለቀስሁ ነው። ይህን ብሶቴንና እንባዬን ህዝብና መንግስት ሰምቶ ይፍረደኝ” የሚሉት ወይዘሮ ጸጋነሽ ዓለሙ ናቸው።
ወይዘሮ ጸጋነሽ ዓለሙ በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በቀድሞው 01 ቀበሌ የቤት ቁጥር 1501 ነዋሪ ናቸው። ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከመሄዳቸው በፊት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ደጃች ውቤ ሰፈር ሰሜን ሆቴል አካባቢ ይኖሩ ነበር። ሆኖም አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ደጃች ውቤ ሰፈር ሰሜን ሆቴል አካባቢ አራት ክፍል የቀበሌ ቤት ውስጥ እየኖሩ እያለ አንድ አልሚ ቦታውን ለልማት እፈልገዋለሁ ማለቱን ተከትሎ አልሚው ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ እሳቸውን ጨምሮ ለሁሉም የልማት ተነሽዎች በራሱ ወጪ አዲስ ቤት ገንብቶ መስጠቱን ያስታውሳሉ።
እርሳቸውም ቀድሞ ይኖሩበት ከነበረው ቤታቸው በልማት ተነሽነት ተነስተው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በቀድሞው 01 ቀበሌ የቤት ቁጥር 1501 የሆነውን ቤት በምትክነት በ1991 ዓ.ም እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ በልማት ተነሽነት ተሰርቶ የተሰጣቸው ቤት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ይጎሉት ነበር። ስለዚህ የሚጎሉትን አንዳንድ መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ማንኛውም የልማት ተነሺዎች ማዕድቤት፣ ሽንት ቤት እና ሰርቪስ ቤቶች እንደሰሩት ሁሉ እርሳቸውም መስራታቸውን ይናገራሉ።
በዚህ መልኩ ይዞታቸውን አስፋፍተውና አስከብረው ከ20 ዓመታት በላይ ይዘው እያስተዳደሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት ወይዘሮ ጸጋነሽ፤ ከጊዜ ብዛት የተነሳ አጥራቸው አርጅቶ መውደቁን ተከትሎ አካባቢው አረቄና የተለያዩ መጠጦች የሚሸጥበት ስለሆነ በተለይ ሲመሽ ለደህንነታቸው ስለሚያሰጋቸው እንደ ዶሮ ጀንበር ስታዘቀዝቅ ቤታቸውን በጊዜ ዘግተው ኩርምት ብለው እንደሚቀመጡ ይገልጻሉ፤
እንዲሁም ቤታቸው ጣሪያው አርጅቶ ዝናብ ሲጥል እንደሚያፈስና በተለይ ክረምት ወቅት ኑሯቸውን አስቸጋሪ ስላደረገው በ2009 ዓ.ም አጥራቸውን፣ ቤታቸውንና ማዕድቤታቸውን ለማደስ ወረዳውን ፈቃድ ጠይቀው የወረዳው ካቢኔ ችግሩን ቤታቸው ድረስ ወርዶ አይቶ ቤታቸውን እንዲያድሱ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
ቅሬታ አቅራቢዋ በተፈቀደላቸው መሰረት ቤታቸውን እና አጥራቸውን ለማደስ ወደ ግንባታ ሲገቡ አጎራባቾቻቸው የጎርፍ ውሃ መፋሰሻ እንዲሁም የጋራ መውጫና መግቢያ መንገድ ተዘጋብን በሚል ለወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በሃሰት ውንጀላ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያወሳሉ።
ነገር ግን የእርሳቸውም ሆነ የአጎራባቾቻቸው መውጫ መግቢያ መንገድ ለየብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ አጎራባቾቻቸው እርሳቸው ላይ ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት በወቅቱ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ አክሊሉ የቀረበውን ቅሬታ ወርደው መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ቢያዩም፤ ኃላፊው በሌሎች ሰዎች ጫና ተገፋፍተው እያከናወኑት ያለውን ግንባታ እንዲያቆሙ ዛቻና ማስፈራሪያ አድርሶብኛል ይላሉ። እንዲሁም “ ቤቱ ከዚህ ቀደም በተሰራበት ተመሳሳይ ቁሳቁስና በነበረበት ቦታ ላይ እንዲገነቡ ቢፈቀድለወትም በጭቃ የነበረውን ሰርቪስ ቤት በብሎኬት ስለሰሩ” በሚል ሁለት ሺህ ብር ቅጣት እንድከፍል አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ጸጋነሽ ሰርቪስ ቤታቸውን ሲያድሱ አንድ አቅጣጫ በኩል ቤቱን ወጨፎ ስለሚመታው ጭቃው እየተናደ ስላስቸገራቸው በጭቃ ተሰርቶ የነበረውን ሲያድሱ አንዱን የቤቱ አቅጣጫ በብሎኬት ማደሳቸውን አምነው የተጣለባቸውን ቅጣት በወቅቱ መክፈላቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን በወቅቱ የወረዳው ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት የጀመሩትን ግንባታ እንዳያገባድዱ ዛቻና ማስፈራሪያ ከማድረስ ባለፈ 15 የቤት አፍራሽ ግብረ ኃይል ይዞ ቤታቸውን ሊያፈርስ ሲመጣ የጊቢያቸውን በር ዘግተው “የመንግስት ያለህ”፤ “ኡኡ” ብለው ህዝብ ሲሰበሰብ ግብረ ኃይሉ ቤቱን ሳያፈርስ ትተዋቸው እንደሄዱ ያወሳሉ።
እርሳቸውም ቤታቸውን ሊያፈርስ የመጣው ግብረ ኃይል የጊቢያቸውን በር ለቆ ዘወር እንዳለ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት ሄደው ሁከት ይወገድልኝ ብለው ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም አመልክተው በአራተኛው ቀን ሁከት ይወገድላቸው የሚል እገድ አምጥተው ሲከራከሩ፤ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ፍርድ ቤቱም የገነቡት ግንባታ ህገወጥ ነው ወይስ አይደለም? የአጎራባች ድንበር ገፍቷል አልገፋም? የጋራ የጎርፍ ውሃ መፋሰሻ እንዲሁም መውጫና መግቢያ ዘግቷል አልዘጋም የሚሉትን ጭብጥ ይዞ የግራ ቀኙን ማስረጃ ከመመርመር ባለፈ ቦታው ድረስ ወርዶ አይቶ በመሃንዲስ እንዲለካ ማድረጉን ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቱም እርሳቸው ባቀረቡት የሁከት ይወገድልኝ ክስ በመመስረት ጉዳዩን የግራቀኙን ማስረጃ በመመርመር እና ቦታው ድረስ ወርዶ በማየት የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 08408 በቀን 26/04/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ፤ እርሳቸው ህጋዊ የእድሳት ፈቃድ ወስደው ቤታቸውን ማደሳቸው ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንደሆነና ዕድሳት ሲያከናውኑም የማንንም ድንበር እንዳልገፉና የጋራ መግቢያ መውጫ እንዳልዘጉ ማረጋገጡንና ውሳኔ መስጠቱን ነግረውናል፤
እድሳቱን ሲያከናውኑ በተመሳሳይ ቁሳቁስና በነበረበት ቦታ ላይ ማከናወን እንደሚገባቸው በእድሳት ፈቃዳቸው ውል የገቡ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ከዚህ ቀደም በጭቃ የነበረውን ሰርቪስ ቤታቸውን በብሎኬት ገንብተዋል ለተባለው ሁለት ሺህ ብር መቀጮ በመቀጣታቸው በአንድ ወንጀል ላይ ተደጋጋሚ ቅጣት ሊሰጥ እንደማይገባ፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት አዲስ ባወጣው መመሪያ የመንግስት ቤቶችን ይዘው የሚያስተዳድሩ ባለ ይዞታዎች በፈለጉት ቁሳቁስ ቤታቸውን የማደስ መብት እንዳላቸው ስለታወጀ ቤታቸውን በፈለጉት ቁሳቁስ ማደስ መብታቸው በመሆኑ ቤታቸውን በብሎኬት ማደሳቸው ህገወጥ ግንባታ ገንብተዋል ሊያስብላቸው ስለማይችል የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በእርሳቸው ላይ የሚያደርገውን የሁከት ተግባሩን፣ ዛቻና ማስፈራሪያውን እንዲያቆም ፍርድ ቤቱ መወሰኑን ይናገራሉ።
ፍርድ ቤቱ የማንንም ደንበር አልገፋችም። ህገወጥ ግንባታም አላከናወነችም ብሎ ቢወስንላቸውም ወረዳው የጀመሩትን የአጥር እና የቤት እድሳት እንዳያከናውኑ እስካሁን ድረስ እንዳገዳቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ጸጋነሽ፤ በዚህ የተነሳም አጥራቸው ወድቆ ለማደስ እንዳፈረሱት መልሶ ሳይገነባ በመቅረቱ ምክንያት ደህንነታቸው አደጋ ላይ ከመውደቁ ባለፈ ቤታቸው በጋ ላይ በጸሃይ እየተቃጠሉ ክረምት ላይ ላያቸው ላይ ዝናብ እየወረደባቸው ህይወታቸው ከሞቱት በላይ በህይወት ካሉት በታች እንደሆነባቸው በምሬት ይናገራሉ።
እንዲሁም ወረዳው እንደአጎራባቾቻቸው ይዞታቸውን እንዳያጥሩ ስለከለከላቸው በግራና በቀኝ ያሉ አጎራባቾቻቸው ይዞታቸውን ከመግፋት ባለፈ የቤት ቁጥር 1480 የሆነው አጎራባቻቸው አንድ ሜትር ከግማሽ (1 ነጥብ 5 ካሬ ሜትር) ሕጋዊ ይዞታቸውን በማለፍ የእርሳቸውን የቤት ቁጥር 1501 የሆነውን ሰርቪስ ቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ በፈረሰው ቤታቸው ላይ አስደግፎ በህገወጥ መንገድ በ2011 ዓ.ም ሰርቪስ ቤት እንደሰሩበት ይናገራሉ።
እርሳቸውም የቤት ቁጥር 1480 የሆነው አጎራባቻቸው ሕጋዊ ይዞታቸውንና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው በህገወጥ መንገድ ግንባታውን ሲጀምር ወዲያውኑ ለወረዳው ሄደው ህገወጥ ግንባታ በይዞታቸው ላይ እየተከናወነባቸው እንደሆነ ሲያመለክቱ ወረዳው ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እልባት አልሰጣቸው ሲል ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ማመልከታቸውን ያወሳሉ።
ክፍለ ከተማውም በተመሳሳይ ለቅሬታቸው ምላሽ አልሰጣቸው ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በበታች ጽህፈት ቤቶች ሰሚ አጥቻለሁና ጩኸቴ ይደመጥ ብለው በቀን 24/10/2011 ዓ.ም በጽሁፍም በቃልም ማመልከታቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ኮርፖሬሽኑ ጉዳዩን ቦታው ድረስ ወርዶ አይቶና በመሃንዲስ አስለክቶ የቤት ቁጥር 1480 የገነባው ሰርቪስ ቤት ወደ ቤት ቁጥር 1501 ይዞታ በመግፋትና ከፊል ግድግዳውን በማለፍ የተሰራ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም መሰረት የቤት ቁጥር 1480 በህገወጥ መንገድ የቅሬታ አቅራቢዋን ይዞታ በማለፍ የሰራውን ሰርቪስ ቤት እንድታፈርሱ ሲል ለወረዳውና ክፍለ ከተማው በቀን 01/12/2011 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ቤ/ል/ኮ/47/0274/ በተጻፈ ደብዳቤ ማሳሰቡን አውስተዋል።
ወይዘሮ ጸጋነሽ ለወረዳው በተደጋጋሚ ህገወጥ ግንባታ በይዞታቸው ላይ እንደተገነባባቸው ቅሬታ ሲያቀርቡ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የነበረ ቢሆንም ከተጠያቂነት ለመዳን ሲል ለግለሰቡ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፏል ይላሉ። የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኮርፖሬሽኑ በቀን 21/12/2011 ዓ.ም በቁጥር ጉ/ቤ/አስ/0096/2011 ለወረዳው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የቤት ቁጥር 1480 በህገወጥ መንገድ የቅሬታ አቅራቢዋን ይዞታ በማለፍ የተሰራ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ በአካል ወርዶ ያረጋገጠ ስለሆነ እርምጃ ወስዳችሁ እንድታሳውቁኝ በሚል በሰጠው ማስጠንቀቂያ መነሻ አድርጎ ወረዳው እየተናነቀውም ቢሆን ከተጠያቂነት ለመዳን የቤት ቁጥር 1480 የገነባውን ሰርቪስ ቤት እንዲያፈርስ ሲል በቀን 12/01/2012 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ/ይ/አስ/892/2012 በተጻፈ ደብዳቤ ለግለሰቡ ማስጠንቂያ መስጠቱን ይናገራሉ።
ወረዳው ግለሰቡ በህገወጥ መንገድ ወደ ቤት ቁጥር 1480 ይዞታ ገብቶ የገነባውን ሰርቪስ ቤት እንዲያፈርስ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የቤት ቁጥር 1480 ባለቤት አቶ ሚኒሊክ ተፈራ ሁከት ይወደግልኝ በሚል በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት በቀን 13/01/2012 ዓ.ም በወረዳው ላይ ክስ መመስረታቸውን ጠቅሰዋል።
ከሳሽም የእርሳቸውን ይዞታ ገፍቶ ከቤታቸው ግድግዳ አልፎ ቤታቸው ጋር ለጥፈው በ2011 ዓ.ም የሰሩትን ሰርቪስ ቤት በሃሰት ለማብሰያና መጸዳጃ ቤት አገልግሎት የሚውል ከ20 ዓመት በፊት የሰሩትን ቤት ወረዳው ወይም ተከሳሽ ለሌላ አጎራባች /ጣልቃ ገብ/ የሰሩትን ህገወጥ ግንባታ ለማጽደቅ በማሰብ መጸዳጃ ቤታቸውንና ማብሰያ ቤታቸውን አፍርሱ በማለት ወረዳው ሁከት ፈጥሮብናል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ይናገራሉ።
ቅሬታ አቅራቢዋ ይዞታው የሚመለከተው እርሳቸውን በመሆኑ በጣልቃ ገብነት ገብተው መከራከራቸውን ወይዘሮ ጸጋነሽ ገልጸው፤ በተጨማሪም ከሳሽ ጣልቃ ገብ (ወይዘሮ ጸጋነሽ) ከዚህ ቀደም የሰሩት ህገወጥ ግንባታ መውጫና መግቢያቸውን ዘግቶ የነበረና እንዲያፈርሱ ለወረዳው ወይም ለተከሳሽ ቅሬታ አቅርበው ቅሬታቸው ታይቶ በደብዳቤ እልባት እንደተሰጠ ለፍርድ ቤቱ ጠቅሰው ወረዳው ይሄንን ሳያረጋግጥ በሶስት ቀን ውስጥ በጣልቃ ገብ ቤት ላይ ተለጥፎ የተሰራው ቤት ይነሳ በሚል የተሰጠው ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር በመሆኑ ሁከቱ ይወገድልኝ ሲሉ መክሰሳቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ጸጋነሽ ገለጻ፤ ፍርድ ቤቱም ከሳሽ የገነቡት ግንባታ ሰርቪስ ቤት ሲሆን ህጋዊ ፈቃድ ላይ መሰረት ያላደረገ መሆኑ፤ እንዲሁም ወደ ጣልቃ ገብ ይዞታ ውስጥ በተወሰነ መልኩ ገብቶ የተገነባ መሆኑ መረጋገጡን፤ ወረዳው ከሳሽ ያከናወኑትን ህገወጥ ግንባታ እንዲያፈርሱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ መመሪያ ቁጥር 5/2011 አንቀጽ 48/1/ ስር በተቀመጠው መሰረት የተከለከለ ህገ ወጥ ግንባታን ለመከልከል አስተዳደራዊ ግዴታውን ከመወጣቱ ባለፈ የሁከት ተግባር ፈጽሟል ሊያስብለው እንደማይችል ውሳኔ አሳልፏል።
ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 23456 በቀን 07/05/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከሳሽ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የቤት ቁጥር 1480 ጋር በተያያዘ የሰሩትን ሰርቪስ ቤት እንዲያፈርሱ፤ ተከሳሽ (ወረዳው) ጉ/ክ/ስ/ወ/8/አስ/892/2012 ዓ.ም መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም የሰጡት ማስጠንቀቂያ የሁከት ተግባር አለመሆኑ ስላልተረጋገጠ የከሳሽ ክስ ወድቅ ነው በማለት ወስኗል። እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ በተከሳሽ የመከራከሪያ ሃሳብና ጥያቄ መሰረት ከሳሽ የሰሩት ሰርቪስ ቤት ሕገ ወጥ መሆኑ ስለተረጋገጠ እንዲፈርስ በማለት መወሰኑን ቅሬታ አቅራቢዋ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከሳሽ ጣልቃ ገብ (ወይዘሮ ጸጋነሽ) የሰሩት ህገወጥ ግንባታ መውጫና መግቢያቸውን ዘግቶ የነበረና እንዲያፈርሱ ለወረዳው ወይም ለተከሳሽ ቅሬታ አቅርበው ነበር። ወረዳው ቅሬታቸውን አይቶ በደብዳቤ እልባት እንደተሰጠ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ውንጀላ፤ ጣልቃ ገብ የወረዳው አስተዳደር ያስተላለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ለፍርድ ቤት ሁከት ይወገድልኝ በሚል ቀደም ሲል በመሰረቱት ክስ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 08408 በቀን 26/04/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ያከናወኑት ግንባታ ህጋዊ በመሆኑ የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሁከት ተግባሩን እንዲያቆም ውሳኔ አሳልፏል፤
እንዲሁም ጣልቃ ገብ ያከናወኑት ግንባታ የጋራ መግቢያ መውጫ በመዝጋቱ በመልካም አስተዳደር ውሳኔ እንዲያፈርሱና ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ ውል እስከማቋረጥ ደረጃ ድረስ እንደሚደርስ የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ጽፏል በሚል ከሳሽ ማስረጃ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ይህ ማስረጃም የወረዳው ሎጎና ማህተም ቢኖረውም ቀንና የደብዳቤ ቁጥር ሳይኖረው የመስሪያ ቤት ፕሮቶኮል ሳያሟላ ሆን ተብሎ እርሳቸውን ለመጉዳት ተብሎ በአመራሮች እንደተጻፈ ይናገራሉ።
ችሎቱም ከሳሽ በእርሳቸው ላይ ያቀረበውን ማስረጃ መዝኖ እንደተመለከተው ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የወጣ መሆኑን የሚያሳይ ቢሆንም፤ ህጋዊ ሰውነት ካለው የመንግስት መስሪያ ቤት መረጃው ቢወጣም አንድ ደብዳቤ ሊያሟላ የሚገባውን መስፈርት ያላሟላ ማለትም የተጻፈበት ቀን እና የተመዘገበበት የደብዳቤ ቁጥር የሌለው መሆኑን ያሳያል።
ይህ ደግሞ ከወረዳው የወጣው ደብዳቤ ሊያስከትል የሚችለውን ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን ባላረጋገጠ ሁኔታ የተሰጠ ደብዳቤ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ደብዳቤው ህጋዊ ለመሆኑ ጥያቄን የሚያስነሳና ከተያዘው ጉዳይ ጋርም ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያለው መሆኑን በይዘቱ ውስጥ የሚያረጋግጠው ነገር የለም በሚል ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዳደረገው ይናገራሉ።
ከዚህ ባሻገር የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቀን 20/01/2012 ዓ.ም በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ/8/ቤ/ አስ/91/2011 በጉዳዩ ላይ በፍርድ ቤት ለነበረው ክርክር ለክፍለ ከተማው ለህግ ጉዳዮች ክርክር ዳይሬክቶሬት በግብዓትነት በጻፈው ደብዳቤ፤ ከሳሽ እንደማስረጃነት የመልካም አስተዳደር ውሳኔ ብለው ያቀረቡት ማስረጃ የአስተዳደሩ ሎጎና ማህተም ቢኖርም ቀንና ወጭ የተደረገበት የደብዳቤ ቁጥር የሌለው ወረቀት ስለሆነ በአስተዳደሩ እውቅና የሌለው ደብዳቤ መሆኑን ማስታወቁን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 23456 በቀን 07/05/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ ከሳሽ የገነቡት ሰርቪስ ቤት ህጋዊ ፈቃድ ላይ መሰረት ያላደረገ እና ወደ ጣልቃ ገብ ይዞታ አልፎ የተገነባ መሆኑ በመረጋገጡ እንዲፈርስ ሲል መወሰኑን ይናገራሉ።
የቤት ቁጥር 1480 የሆነው አጎራባቻቸው አንድ ሜትር ከግማሽ (1 ነጥብ 5 ካሬ ሜትር) ሕጋዊ ይዞታቸውን ከመግፋት ባለፈ የእርሳቸውን የቤት ቁጥር 1501 የሆነውን ሰርቪስ ቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ ቤታቸው ላይ ለጥፎ በህገወጥ መንገድ የሰራውን ሰርቪስ ቤት ፍርድ ቤት እንዲያፈርስ ውሳኔ ሰጥቷል። ነገር ግን ይህን የፍርድ ቤት ውሳኔ ወረዳው እንዲያስፈጸም በተደጋጋሚ ብጠይቅም የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብሎ እስካሁን ድረስ ሊያስፈጸምልኝ እንዳልቻለም ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።
የቤት ቁጥር 1480 የሆነው አጎራባቻቸው ይዞታቸውንና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ አልፎ በህገወጥ መንገድ እንደሰራ ፍርድ ቤት አረጋግጦ ይፈረስ ብሎ የወሰነው ቦታ የእርሳቸው ቀደምት ይዞታ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት በቀን 29/07/2013 ዓ.ም በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ/8/ቤ/ አስ/447/2013 ለወይዘሮ ጸጋነሽ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ “የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ሁለቱም የመንግስት ቤቶች ስለሆኑ በውሳኔው መሰረት ምን ያህል መፍረስ እንዳለበት ስላልተገለጸ እና ለመንግስት ቤቶች ካርታ እያሰራን ስለሆነ ግራና ቀኙ በመሬት ላይ ያላቸውን የይዞታ መጠን ለይተን ስናውቅ ውሳኔውን ተፈጻሚ የምናደርግ ይሆናል ሲል ምላሽ መስጠቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላለማስፈጸም ሆነ ተብሎ የተሰራ ደባ ነው ብለዋል።
እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ ፤ወረዳው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አላስፈጽምም አሻፈረኝ ብሎ እንቢ ሲል ቅሬታቸውን ለክፍለ ከተማው አመልክተዋል። ክፍለ ከተማው ቦታው ድረስ መሃንዲስ ይዞ መጥቶ ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት ለክቶ በተለካው ልኬት መሰረት የፍርድ ባለዕዳን እንዲያፈርሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ባለሙያ በሌለበት የፍርድ ባለእዳ እራሳቸው ቤቱን አፍርሰዋል።ሆኖም ያፈረሱት ፍርድ ቤቱ በወሰነው ልኬት ልክ አይደለም። በዚያ ቦታ ላይም መልሰው ቤት ሰርተውበታል።
ወይዘሮ ጸጋነሽ ክፍለ ከተማው ባደረገው ጥረት የቤት ቁጥር 1480 የሆነው አጎራባቻቸው ይዞታቸውንና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ አልፈው ቤታቸው ላይ ለጥፎ በህገወጥ መንገድ የሰራውን ሰርቪስ ቤት ፍርድ ቤቱ በወሰነው ውሳኔ መሰረት በመጠኑም ቢሆን አፍርሰው እርቀታቸውን ጠብቀው መልሰው ቤት ቢሰሩም አሁንም በይዞታው ላይ የተለያዩ እቃዎችና እንጨት እንደከመሩበት ገልጸው፤ ነገር ግን አጎራባቻቸው አቶ ሚኒሊክ ተፈራና ወንድሞቹ የእርሳቸውን ይዞታ አልፈው ሰርተውት የነበረውን ሰርቪስ ቤት ማፍረሳቸውን ተከትሎ እርሳቸውም አጎራባቾቻቸው ይዞታቸውን አጥረው እንዳስከበሩት ሁሉ ይህን ይዞታቸውን እንዲያጥሩ እንዲፈቀድላቸው ወረዳውን መጠየቃቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ለወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ይዞታውን በስራቸው አድርገው አጥረው እንዲያስተዳድሩ ፈቃድ ሲጠይቁ ይዞታው ላይ የፍርድ ባለዕዳ የይገባኛል ጥያቄ እያነሱ ስለሆነ የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋጋጫ እየተሰራላቸው በመሆኑ የይዞታ ካርታ ሲሰራላቸው ይዞታው በማን ስር መተዳደር እስኪታወቅ ድረስ እስከዚያው ግን ይዞታው ክፍት ሆኖ ይቀመጣል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ነግረውናል።
ጽህፈት ቤቱ ይሄን ምላሽ ሲሰጣቸው አጎራባቻቸው አቶ ሚኒሊክ ተፈራ በይዞታቸው ላይ የሰራው ህገወጥ ግንባታ በፍርድ ቤት እንዲፈርስ በመደረጉ ይህንን ይዞታቸውን አጥረው አስከብረው እንዲይዙ ይፈቀድልኝ በሚል ለወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ በ04/09/2013 ዓ.ም በጽሁፍ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ዋና ስራ አስፈጻሚውም ይዞታው የመንግስት ቤቶች በመሆኑ ከዚህ በፊት የይዞታ ማረጋገጫ ስላልነበረው የመንግስት ቤቶች የይዞታ ካርታ እየተሰራላቸውና በይዞታው ላይ የግራ ቀኙን የይገባኛል ጥያቄ እያነሱ ስለሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ተሰርቶ ሲጠናቀቅ በይዞታው ላይ አጥርም ሆነ ግንባታ ለማከናወን ፈቃድ የሚሰጥ ይሆናል የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ቅሬታ አቅራቢዋ ይናገራሉ።
ነገር ግን የፍርድ ባለዕዳ የወይዘሮ ጸጋነሽን ይዞታ ገፍቶ መስራቱ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ቤቱን እንዲያፈርስ ከመወሰኑ ባለፈ ይዞታው የሚመለከተው ጣልቃ ገብን በመሆኑ ፍርድ ቤት ፈቅዶላቸው በጣልቃ ገብ ገብተው ተከራክረው ይዞታቸው ላይ ህገወጥ ግንባታ መገንባቱ ተረጋግጦ ይፍረስ ተብሎ መወሰኑን ነግረውናል። ሆኖም የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰራላቸው የሚያደርገው ይዞታው ባለበት እንዲከበር እንጂ የአንዱን ይዞታ ለሌላው ነጥቆ ለመስጠት ስላልሆነ ይዞታው በተለያዩ የበላይ አስተዳደሮችና ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በፍርድ ቤት ጭምር የወይዘሮ ጸጋነሽ መሆኑን የተረጋገጠ ይዞታን በምን አግባብ ነው ሌሎች የይገባኛል ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉት? በሚል ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት ልኬቱ ተለክቶ ይዞታቸውን ለምን አታስረክቡኝም በሚል ዋና ስራ አስፈጻሚውን ሲጠይቁ በህገወጥ የተሰራውን ቤት አፍርሱ ነው እንጂ ይዞታውን አስረክቡ አልተባልንም በሚል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሊያስፈጸሙላቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ለአጎራባቾቻቸው በመወገን አጎራባቾቻቸው የእርሳቸውን ይዞታና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ ቤታቸው ላይ ለጥፈው የሰሩትን ሰርቪስ ቤት እስኪ የሚያፈርሰውን እናያለን በሚል ሲዝቱና ሲያስፈራሯቸው እንደነበር ቅሬታ አቅራቢዋ ጠቁመው፤ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት ይዞታቸውን አጥረው አስከብረው እንዲይዙ በተደጋጋሚ የወረዳውን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲጠይቁ አርፈሽ የማትቀመጭ ከሆነ እቃሽን አውጥቼ ነው የምጥለው በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ከማድረስ ባለፈ ስብዕናቸውን የሚነካ ንግግር እንደሚናገሯቸው ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ጸጋነሽ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ ለፍርድ ባለዕዳ ወገንተኛ በመሆኑ ይዞታው የማን እንደሆነ የሚወሰነው የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ተሰርቶ ሲመጣ ነው የሚሉት እርሳቸው ከፍርድ ባለዕዳ በፍርድ ቤት በክርክር በነበሩበት ወቅት ካርታ ለመስራት ጥናት ሲደረግ ስለነበር የመንግስት ቤቶች ይዞታ ካርታው ሲሰራ ይዞታውን በፍርድ ባለዕዳ ስር ይተዳደር እንደነበር አድርገው አስጠንተው መልሰው ለፍርድ ባለዕዳ ይዞታውን ለመስጠት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ መብታቸውን ገፎ ስብዕናቸውን አጉድፎ ከሰው በታች እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ በአጠቃላይ ወረዳው ቤታቸውንና አጥራቸውን እንዳያድሱ የዜግነት መብታቸውን በመንፈጉ አጥራቸው ወድቆ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ከመሆኑ ባለፈ ቤታቸውን ለማደስ እንዳፈረሱት መልሶ ሳይገነባ በመቅረቱ በጋ ላይ በጸሃይ እየተቆሉ ክረምት ላይ ላያቸው ላይ ዝናብ እየወረደባቸው በመልካም አስተዳደር እጦት ሳቢያ ህይወታቸው ከሞቱት በላይ በህይወት ካሉት በታች ከሆነባቸው ድፍን ሶስት ዓመት ከመንፈቅ እንደሞላቸው ይናገራሉ።
እንዲሁም ወረዳው በፍርድ ቤት የተወሰነላቸውን ይዞታቸውን መልሶ ለፍርድ ባለዳ ለማስረከብ የመንግስት ቤቶች የይዞታ ካርታ ተሰርቶ ይምጣ በሚል ቀን እየቆጠረ እንደሚገኝ ቅሬታ አቅራቢዋ ጠቅሰው፤ “የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ እኔ ድሃዋን ማንም ዘመድና ረዳት የላትም በሚል በመልካም አስተዳደር እጦት ከማሰቃየት ባለፈ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመፈጸም አሻፈረኝ ስላለ የወረዳው ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባገነን መሆኑን ህዝብና መንግስት አውቆት የሚመለከተው አካል እልባት እንዲሰጠኝ” ሲሉ ወይዘሮ ጸጋነሽ ይጠይቃሉ።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 አስተዳደር ጽህፈት ቤት ምላሽ
የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ እዮብኤል ጣፋ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ በፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት የቤት ቁጥር 1480 በህገወጥ መንገድ የሰራው ሰርቪስ ቤት ወደ ወይዘሮ ጸጋነሽ ይዞታና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ ቤታቸው ላይ ለጥፎ የሰራውን ቤት እንዲፈርስ በወሰነው መሰረት ቤቱን በማፍረስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማስፈጸማቸውን ተናግረዋል።
የቤት ቁጥር 1480 በህገወጥ መንገድ ሰርቶት የነበረው ሰርቪስ ቤት ፈርሶ ይዞታው አሁን ላይ ክፍት ሆኖ እንደተቀመጠ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰው ፤ ይህንን ክፍት የሆነውን ይዞታ የፍርድ ባለዕዳ እንዲሁም ጣልቃ ገብ ይዞታው ይገባናል የሚል ጥያቄ እያነሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በተለይ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማክበር በህገወጥ የተሰራውን ሰርቪስ ቤት ወረዳው ካፈረሰ በኋላ ቅሬታ አቅራቢዋ በደብዳቤ ጭምር ክፍት የሆነውን ይዞታ ወደ ይዞታቸው አካተው ግንባታ እንዲያከናውኑበት ፈቃድ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገልጸው፤ ይዞታው የመንግስት ቤቶች በመሆኑ የቤት ቁጥር 1480 ይሁን 1501 ይሄነው ይዞታችሁ ተብሎ ተከልሎ የተሰጣቸው ቦታ ስለሌለ ይገባኛል የሚለው ጥያቄ የሚስተናገደው የመንግስት ቤቶች የይዞታ ካርታ ተሰርቶ ሲመጣ ነው። ነገር ግን ካርታና ይዞታ በሌለበት ይሄ ያንተነው ያ ያንቺነው ልንል አንችልም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል ።
የፍርድ ባለዕዳ በህገወጥ መንገድ የሰሩት ሰርቪስ ቤት ፍርድ ቤቱ እንዲፈርስ ወስኗል። ወረዳውም ፍርድ ቤቱ በወሰነው መሰረት እንዲፈርስ አድርጓል። ከዛ በዘለለ ይዞታውን ለቅሬታ አቅራቢዋ የእርሷ ይዞታ ነው ብሎ ለመስጠት የሚያስችል ምንም ህጋዊ መሰረት የለም። ቅሬታ አቅራቢዋም ይዞታው የእርሳቸው መሆኑን የሚያሳይ የይዞታ ማረጋገጫ የላቸውም። ነገር ግን ይዞታው ይገባኛል በሚል ግራቀኙ የሚያቀርቡት ማስረጃ ካለ ባቀረቡት ማስረጃ መሰረት የሚሰጣቸው ይሆናል የሚል ምላሽ አቶ እዮብኤል ሰጥተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ይሄንን ምላሽ ሲሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቦታው ድረስ ወርዶ ባየው መሰረት ለወረዳውና ክፍለ ከተማው በቀን 01/12/2011 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ቤ/ል/ኮ/47/0274/ በጻፈው ደብዳቤ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 23456 በቀን 07/05/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ የቤት ቁጥር 1480 ወደ ቅሬታ አቅራቢዋ ይዞታ እና የቤታቸውን ከፊል ግድግዳ በማለፍ ቤታቸው ላይ ለጥፎ የሰራውን ሰርቪስ ቤት እንድታፈርሱ በሚል የሰጡት ትዕዛዝ በቅሬታ አቅራቢው ይዞታ ላይ ህገወጥ ግንባታ መሰራቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህም በተዘዋዋሪ ህገወጥ ግንባታው የተገነባበት ይዞታ የቅሬታ አቅራቢው መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ እና ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ህገወጥ ግንባታው ሲፈርስ ለምን ክፍት የሆነው ይዞታ ለቅሬታ አቅራቢዋ አይመለስም? ለምን የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰርቶ እስኪመጣ መጠበቅ አስፈለገ የሚሉ ጥያቄዎችን የዝግጅት ክፍላችን ለአቶ እዮብኤል አንስቷል።
አቶ እዮብኤል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ኮርፖሬሽኑ የጻፈውን ደብዳቤ ተቀብሎ ከማስፈጸም በፊት ምን ህጋዊ መሰረት ይዞ ነው ደብዳቤ የጻፈው ብሎ ማጣራት ያስፈልጋል። ይሄ ይዞታ ስላላቸው በዚህ ይዞታ መሰረት የቅሬታ አቅራቢው ነው የሚል ማስረጃ ከቀረበ በቀረበው ማስረጃ መሰረት ተፈጻሚ የማናደርግበት ምንም ምክንያት የለም። ነገር ግን ያለምንም ህጋዊ መሰረት አንድ ከላይ ያለ አካል ስለጻፈ ብቻ ወረዳው ስህተት ውስጥ አይገባም። ስለዚህ ኮርፖሬሽኑ ህጋዊ መሰረት ይዞ አይደለም ተገፍቷል አልተገፋም ብሎ ደብዳቤ የጻፈው። አንድ ባለሙያ የጻፈው ደብዳቤ ሁሉ ትክክል ነው ሊባል አይችልም። ትክክል ካልሆነ ደግሞ ስህተቱን ተከራክሮ የማረም ስልጣኑ አለን። በመሆኑም ወረዳው ይዞታ ሊሰጥ የሚችልበት የራሱ የሆነ ህግና መመሪያ አለው ብለዋል።
በሌላ በኩል የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምንም ይሁን ምንም ወረዳው የማስፈጸም ግዴታ ስላለበት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት ህገወጥ የሆነውን ግንባታ አስፈርሶ ይዞታውን ክፍት አድርጓል። ስለዚህ ክፍት የሆነው ይዞታ በይዞታዬ ስር ተካቶ ግንባታ ላከናውን የሚለው ጥያቄ ወረዳው ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ የተገነባው ግንባታ ህገወጥ ነው አፍርሱ ብሏል ባለው መሰረት እንዲፈርስ ተድርጓል። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ይዞታው የሚገባው የዚህ ነው የዚያ የሚል ውሳኔ ስልላሰጠ ይዞታው የዚህ አካል ነው ተብሎ ሊሰጥበት የሚችል የመመሪያም፣ የማስረጃም፣ የህግም መሰረት እንደሌለ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳዊት በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ በቅርቡ ወደዚህ ኃላፊነት እንደመጡ ጠቁመው እርሳቸው ወደ ኃላፊነት በመጡበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቅሬታ አቅራቢዋ ተበድያለሁ የሚል ቅሬታ እንዳቀረቡ ይናገራሉ።
እርሳቸውም በቀረበላቸው ቅሬታ መሰረት የቅሬታ አቅራቢዋን አቤቱታ ትኩረት ሰጥተው እልባት ለመስጠት ሲሰሩ ባገኙት መረጃ ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ከዚህ በፊት ጽህፈት ቤቱን የእድሳት ፈቃድ ጠይቀው ፈቃድ እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም የተሰጣቸው ፈቃድ መመሪያን ያገናዘበ ነው። ምክንያቱም በመመሪያ ቁጥር 2/2010 በአየር ካርታ በ1988 ወይም በ1997 ዓ.ም የሚታይ ቤት የእድሳት ፈቃድ ይወስዳል የሚል ሆኖ እያለ ቅሬታ አቅራቢዋ ለማደስ የእድሳት ፈቃድ የጠየቁት ቤት በመመሪያው ላይ በተጠቀሰው ዓመተምህረት እንደማያሳይ እየታወቀ የተሰጣቸው ፈቃድ ስለሆነ ቤቱን እንዳያድሱና ባለበት እንዲቆም ተደርጓል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር የአጥር እድሳት በተመለከተ ይዞታው የመንግስት ቤቶች በመሆኑ ሁሉም ይዞታ አንድ ላይ የነበረ ስለሆነ ተከራዮች በራሳቸው በጎ ፈቃድ ተስማምተው አጥረው መያዛቸውን ኃላፊው ጠቁመው፤ በመሆኑም ሁሉም ተከራዮች ከወደ ፊት ለፊት ያለውን አጥራቸውን በመመሪያው መሰረት እንዲያጥሩ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን ቅሬታ አቅራቢዋ አጥራቸው ወድቆባቸው ማደስ አይችሉም ተብሎ የተከለከሉት 12 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በአጎራባቾች መካከል ያለ ነው። ስለዚህ ለዚህ አጥር የእድሳት ፈቃድ ለመስጠት ከመመሪያ አኳያ ስለማይፈቅድ በመልካም አስተዳደር ውሳኔ አኳያ ይፈቀድላት የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ይናገራሉ።
ነገር ግን ይህንን አጥር በመልካም አስተዳደር የእድሳት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ከአጎራባቾች ጋር ተስማምተው እንዲያጥሩ ለማስማማት የተሞከረ ቢሆንም ከአጎራባቾቻቸው ሊስማሙ ባለመቻላቸው የእድሳት ፈቃዱ በመልካም አስተዳደርም ሊሰጣቸው አለመቻሉን ተናግረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013