ኢትዮጵያ ተነግረው የማይሰለቹ ተወርተው የማያልቁ ድንቅ ባህል ያላቸው ህዝቦች መገኛና በብዝኃነት የተዋበች ሀገር ናት፡፡ ይበልጥ ስናውቃትና ቀርበን ስንመረምራት በባህል ማህደርነቷ የምንደመምባት ድንቅ ምድር፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በደቡባዊ ክፍልዋ ተገኝተን የማሾሌ ብሄረሰብን ባህላዊ የአኗኗር ሥርዓት፣ የአስተዳደርና የብሄረሰቡ ልዩ መገለጫዎች ለማሳየት የወደድነው፡፡ የሚማርክ ጥበብ ከምትመስለው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አንድ ውብ ክር የሚመሰሉት ማሾሌዎች ድርሳን በዛሬው ገፃችን ላይ ይገለጣል፡፡ አቶ ገንዘበ ገዛኸኝ የዴራሼ ወረዳ ባህል ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡
የማሾሌ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴት ላይ ይመራመራሉም፡፡ የማህበረሰቡን ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ኀዘን ደስታውን፤ ወግ ልማዱን በጥልቀት አጥንተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የዚያው አካባቢ ተወላጅ መሆናቸው በእርሳቸው ብሌን ማሾለቁን ምርጫችን እንድናደርግ አስገድዶናል፡፡ የማሾሌ ብሔረሰብ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰብና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በዴራሼ ወረዳ ከጊዶሌ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡ ፡ ብሄረሰቡ ዘጠኝ የተለያዩ ጎሳዎች ያሉት ሲሆን፤ መግባቢያ ቋንቋው «አፋ ማሾሌ» በመባል ይታወቃል፡፡ ግብርናና ከፊል አርብቶ አደርነት የማህበረሰቡ መተዳደሪያ ነው፡፡
የተለያዩ ሰብሎችና ጥራጥሬዎች ያመርታሉ፡ ፡ መልካአምድሩ ተራራማ ነው፡፡ ቆላ፣ደጋና ወይናደጋ ደግሞ የአካባቢው የአየር ንብረት መገለጫ ነው፡፡ ባህሉ ባጎናጸፋቸው ልዩ ጥበብ በተለያዩ ቁሳቁስ የሚሰሩት «ማና» የተባለ መኖሪያ ቤታቸው የሚኖሩት ማሾሌዎች፤ በህብረት በመሥራትና ችግሮችን በጋራ መጋፈጥ ተለምዶዓዊ ተግባራቸው ነው፡፡ በደቦ የሚሠሩት ባህላዊ ቤታቸው የተለያየ አገልግሎት መስጠት የሚችልና ልዩ የአሰራር ጥበብ የተካኑ ለመሆናቸው ማሳያ ነው፡፡ የሳር ክዳን ያለውና በተለምዶ ጎጆ ቤት ብለን የምንጠራው ቅርጽ ያለው የማሾሌዎች ቤት በተለያየ ቅርጽና መጠን የታነጸ ነው፡፡
ለብሄረሰቡ ንጉስ (ዳማ) የሚያንጹት ቤት በቅርጽና ስፋቱ የተለየ ሲሆን፤ ሰፋ ያለ ግቢና ብዙ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከሌሎች ቤቶች የሚለየው የሰጎን እንቁላል በቤቱ ምሶሶ ላይ ይቀመጣል፡ ፡ ይህ የንጉሡን ታላቅነትና ክብር መግለጫ መሆኑን የአካባቢው ተወላጆችና የብሄረሰቡ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ባህላዊ ልብስ በብሄረሰቡ በሽመና የሚዘጋጅ ከጥጥ የሚሠራ «ኮንቦራ» ወንዶች የሚለብሱት ነው፡ ፡ የሚያምር ‹‹ቱቡጎታ›› ደግሞ የሴቶች የባህል ልብስ ሲሆን፤ በእረፍትና በበዓላት ማሾሌዎች የሚደምቁበት የሚዋቡበት ባህላዊ ልብሳቸው ነው፡፡ ባህላዊ ምግብና መጠጥ ብሔረሰቡ ‹‹ካፖናካላታ›› የተሰኘ ባህላዊ ምግብ አላቸው። በብሄረሰቡ ዘንድ በጣም የተለመደ የሰርክ ምግብ ነው፡፡ ካፖናካላታ በልተው የሚጎነጩት እጅግ ተወዳጅ መጠጥ ደግሞ ‹‹ጨቃ›› ይባላል። በብሄረሰቡ ባለሙያ ሴቶች በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ጨቃ ከአንድ ወር በላይ በዝግጅት ሂደት የሚያልፍ በብሄረሰቡ ዘንድ እጅግ የሚወደድ ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት በሀገራችን የማዕከላዊው መንግሥት ተጠናክሮ በአንድ አስተዳደር ሥርዓት ከመተዳደርዋ በፊት የማሾሌ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ነበረው፡፡ ይህንን ባህላዊ ሥርዓት ማህበረሰቡ ለዘመናት የማህበራዊ ግንኙነቱን አጠንክሮበታል። የፍትህ ሥርዓቱን ማስተግበሪያና የአስተዳደር ወሰኑን መጠበቂያ አድርጎትም ቆይቷል፡፡ የማሾሌዎች ንጉስ (ዳማ) (dhama) በብሄረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሚከበርና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የብሄረሰቡ ንጉሥ ‹‹ዳማ›› ይባላል፡፡ ዳማ የብሄረሰቡ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ነው፡፡ ሰዎች ከፍተኛ ወንጀል ሠርተው የሚዳኙትና የጎሳዎች ግጭት መፍትሄ የሚያገኘው በዳማ ነው፡ ፡ ዳማ ለማህበረሰቡ ጥላና መከታ ነው ተብሎ
ይታሰባል፡፡ ከብሄረሰቡ የሆነ አንድ ወገን ወይም ግለሰብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከባድ ጥፋት ቢያጠፋ ጥፋቱ ታይቶ እስኪወሰንበት ድረስ ዳማ ቤት ገብቶ ይጠለላል፡፡ በዚህ ወቅት ማንም ሰው በደል ፈጻሚው ላይ ምንም አይነት ጥቃት አይፈጸምበትም፡፡ በደል ፈጻሚው ላይ አንዳች ነገር ለማድረስ ቢሞክር የሚጠየቀውም በንጉሡ ዳማ ነው፡፡ ተግባሩም ዳማን የመድፈር ያህል ይቆጠራል፡፡ ዳማ ብሄረሰቡን በበላይነት ይመራል፣ ህግና ደንቦችን ያወጣል ፤ያውጃል፡፡ ከሱ ቀጥሎ ያለውን ‹‹ቱሪዓ›› የተባለውን የሥልጣን ክፍል ይሾማል። ልዩ ልዩ ተግባራትን እንዲያስፈጽሙ ያዛል፡፡ ሁለተኛው የአስተዳደር እርከን (ቱሪዓ) ቱሪዓ ህዝብና ዳማ የሚያገናኙ ማዕከላዊ አስተዳደሮች ናቸው፡፡ ከዳማ የሚመጡ ትዕዛዞችን ህዝብ ድርስ ወርዶ እንዲተገበር ማድረግ፣ አጠቃላይ አካባቢያዊ ሁኔታን ለዳማዎች እየተከታተሉ ማሳወቅና መቆጣጠር ተግባራቸው ነው። የንጉሡ ዘር ሀረጎችና በንጉሡ ዳማ የሚሾሙም ናቸው፡፡ የግለሰቦች አለፍ ሲልም የቤተሰብና አካባቢያዊ ግጭቶችን ያያሉ፤ ይዳኛሉም ቱሪዓዎች፡፡ ከዚህ አልፎ የሚከሰት ማንኛውም ከፋ ያለ ጉዳይ ወደ ዳማ ተልኮ በዳማ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ሦስተኛው የአስተዳደር ሥልጣን (ማቃ) ማቃ ሦስተኛው የአስተዳደር ሥልጣን ሲሆን፤ ከቱሪዓ ያነሰ ሥልጣንና ተግባር አለው፡ ፡ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የማስተዳደር፣ ዳማና ቱሪዓን የመታዘዝ፣ ከእነሱ የመጣን ትዕዛዝ በህዝቡ እንዲተገበር የማድረግ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በማህበረሰቡ የእርስ በእርስ ጥብቅ ትስስር ምክንያት ግጭቶች ብዙም መመልከት ያልተለመደ ቢሆንም አልፎ አልፎ ሲከሰት የተጋጩትን ወገኖች መዳኛ የራሳቸው የሆነ ስርዓት አላቸው፡፡
በዳዩ ቀርቦ የተከሰሰበትን ጉዳይ የማይቀበለው መሆኑን ከገለጸ ወደ ‹‹አራሜ›› (ማህላ አስፈጻሚ) ጋር ይላካል፡፡ እዚያም ምሎ ተገዝቶ ጉዳዩን አለመፈጸሙን ይናገራል፡፡ በብሄረሰቡ እምነት መሰረት አራሜ ቤት ሄዶ ‹‹አላደረኩም! እኔ አልፈጸምኩም!›› ያለ የሚታመን ሲሆን፤ ነገር ግን ዋሽቶ ያስተባበለ ትልቅ መዘዝ ይመጣበታል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ጥብቅ እምነት ስላለ ማንኛውም ሰው የሠራውን ወንጀል አስተባብሎ አራሜ ቤት ሄዶ አልፈጸምኩም በማለት አያስተባብልም፡፡ የጋብቻ ሥርዓት የጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ለማሾሌ ብሔረሰብ ሠርግ መደገሻ የፍስሀ ጊዜ ነው፡፡ የጋብቻ ወቅት እህል ደርሶ ከአዝመራ ታጭዶና ተወቅቶ የሚሰበሰብበት ሰማዩ ጥርት ብሎ ምድሩ የሚፈካበት መሆኑ ወሩን አስመርጦታል፡፡ አራሽ ገበሬው ያኔ ያርፋል፡፡ የደረሰ ልጅ ያለው ልጁን ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት ወገቡን ታጥቆ ከዘመድ አዝማዱ ጋር ይዘጋጃል፤ ይደግሳል፡፡ ለጊዜው ታይቶ የሚጠፋ በዘመን ሂደት የሚከዳው ቁንጅና ለጋብቻ መስፈርት አይደለም፡ ፡ ቁመተ ሎጋ፣ አፍንጫ ሰልካካ፣ ተረከዘ ሎሚ፣ ፀጉርዋ የተዘናፈለ እያሉ ማማረጥና ሙሽራን ማጨት በማሾሌዎች ለጋብቻ ምርጫም መለኪያም አይደለም፡፡ ዘላለማዊ ስብዕና አብሮ የሚዘልቅ ጨዋነትና ለመልካም ሰው መለኪያ የሆነው ፀባይ እንጂ፡፡
በልጅቷ ወገን ያሉ ወላጆች ልጃቸውን ለመስጠት ሙሽራው ጎበዝ አራሽ መሆን፣ በአካባቢው ጥሩ ስብዕና የተላበሰና ለእነሱ ጥሩ ከሚሉት ቤተሰብ መገኘት ቀዳሚ መስፈርት ሲሆን፤ ለሴትዋ ደግሞ በምግብ ዝግጅት ጎበዝ እጅ የሚያስቆረጥም ባህላዊ ምግብ ማዘጋጀት የምትችል መሆን ይጠበቅባታል፡፡የጋብቻ ምርጫ የሚወሰነው በአግቢው ወይም ሙሽራው ቤተሰብ ነው፡፡ ወላጆች ለጋብቻ የደረሰ ልጃቸው ማግባት እንዳለበት ሲወስኑ ለእሱ ትሆነዋለች የሚሏትን ኮረዳ መርጠው ልጃችሁን ለልጃችን ብለው ቤተሰቦቿ ጋር ሽማግሌዎችን ይልካሉ፡፡ ወንዱ የሚያገባት ልጅ ከሌላ ጎሳ መሆን ይኖርባታል:: ምክንያቱም በማሾሌዎች ባህል መሰረት ተመሳሳይ ጎሳ አይጋባም፡፡ በብሄረሰቡ ዘንድ የእርስ በእርስ መከባበር የጎለበተ ባህል ነው፡፡ የአካባቢው ሴቶችን መጠበቅ የሁሉም የአካባቢው ብሄረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ በመሆኑም ሴቶች ለጋብቻ እስኪደርሱ ድረስ በማህበረሰቡ ይጠበቃሉ፤ በነፃነት ያድጋሉ፡ ፡
ልጅቷ ቤተሰቦች የጋብቻ ጥያቄ ከተቀበሉ ለልጅቷ የሚነግሯት ቀጥታ ሳይሆን በአክስቷ በኩል ነው፡፡ ይሄም ነጻ ሆና የቀረበላትን ባል ወይም ሙሽራ መውደድ መጥላቷን እንድትናገር ያግዛታል ብለው ስለሚያምኑ ነው። ቤተሰቧ በጥንቃቄ ባል የሚሆናትን ሰው አይተው መርምረው መቀበላቸው ለልጅቷ ዋስትና ስለሚሆን ብዙውን ጊዜ የቤተሰቧን ምርጫ አክብራ መቀበል የተለመደ ነው፡፡ እንደ ባህሉ ከሦስት ጊዜ በላይ ለጥየቃ የመጣን ሽምግልና በአዎንታ ተቀብሎና ጥሎሽ ተጥሎ እንደ አቅም ተደግሶ ሙሽሪት ተዘጋጅታና ተቆነጃጅታ ለሙሽራው በክብር ትሰጣለች፡፡ ጋብቻው በወግ በሥርዓቱ መሰረት ይፈጸማል፡፡ ነገር ግን በብሄረሰቡ አንድ የተለመደና ከሌላው ማህበረሰብ የሚለይ ልማድ አለ፡፡ ሙሽራ አገባሁ ብሎ የያዛትን ሙሽራ ይዞ ወደተዘጋጀለት ጫጉላ ቤት አያመራም፡፡ በብሄረሰቡ ልምድ አንዲት ሙሽራ አግብታ ከባሏ ጋር ምንም አይነት የግብረ ስጋ ግንኙነት ሳታደርግና ከባሏ ጋር ሳትገናኝ ሦስት ወር ትቆያለች፡፡ ለልጅቷ ክብር ከልጁ ቤተሰብ ጋር መላመጃና የእሷን ክብር ያስጠብቃል የሚል እምነት አለው ብሄረሰቡ፡፡ ከሙሽራው ቤተሰብ ጋር አካባቢውን እየተላመደች በእንክብካቤ የምትቆየው ሙሽሪት ሦስት ወር ሳይሞላት ሙሽራው በዓይን እንኳን እንዲያያት አይፈቀድም፡፡ ሙሽራው ለሥራ መስክ ሄዶ ሲመለስ አጋጣሚ ልመለከታት የሚችል ቦታ ላይ ከተገኘች ‹‹ላሎ ባኤ›› (አሞራው ደረሰ) ተብሎ ይነገራትና ወደ ጓዳ ገብታ ትደበቃለች፡፡
የማሾሌዎች ባህል፣ ወግ እና ሥነ ሥርዓት በዚህ አርበ ጠባብ ፅሁፍ ተገልፆ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የበዛ የባህል ሀብት አላቸው፡፡ እግር ጥሏችሁ በእንግድነት ብትገኙ ግን የዛሬው የባህል ገፃችን መረጃ ጥሩ ስንቅ ይሆናችኋል፡፡ ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ተገኝ ብሩ