ክረምቱ ሲቃረብ ለእርሻ ሥራ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተለያዩ የዕፅዋት ችግኞችን ለመትከል ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጀምሯል። ምድር አረንጓዴ በሚለብስበት የክረምቱ ወራቶች መሬቱ ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎችና እንስሳትም ጭምር አናት ከሚበሳው የበጋ ፀሐይና አስጨናቂ ሙቀት ወጥተው ቀዝቃዛና ነፋሻማ አየር ያገኛሉ። እንስሳትም የሚጠጡት ውሃና የሳር ግጦሽ እንደልብ ያገኛሉ። በውሃ አቅርቦት እጥረት እየተቸገረ ያለው ማህበረሰብም የውሃ ችግር ይቃለላል። ይሄ የክረምቱ ወቅት ይዞልን የሚመጣ ገጸ በረከት ነው። ይሄንን ተጠቅሞ ታዲያ ዘላቂነት ያለውን አረንጓዴ ልማት ማልማት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ጉዳይ ይሆናል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከመደበኛው የእርሻ ሥራና የአትክልት ልማት ጎን ለጎን በክረምቱ የተለያየ ዝርያ ያላቸው አገርበቀል የዕፅዋት ችግኝ ተከላ መርሃግብር ላይ ተሳተፊ መሆን አለበት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በማቅረብና ሰፊ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ በማሳተፍ የተጠናከረ ሥራ መሰራቱ ይታወሳል። ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ ይኸው መርሀግብር ይካሄዳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከአገርም ውስጥ አልፎ ከጎረቤቶች አገሮች ጋር አብሮ በመልማት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነትንም ለማጠናከር ‹‹ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ›› በሚል ሦስተኛው የአረንጓዴ ልማት መርሃግብር የማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል።
የሦስተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አጠቃላይ እንቅስቃሴና በሁለቱ ዓመታት የተገኙ ተሞክሮዎችና ክፍተቶችንም በማረም በቀጣይ በተሻለ ለመፈጸም ስላለው ቅድመ ዝግጅት በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው ጋር ቆይታ አድርገናል። ለአራት ተከታታይ ዓመታት ለማከናወን የታቀደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ኢትዮጵያን በደን የመሸፈን ዓላማን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ እስካሁን በተከናወነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል። በቅርቡ በተከናወነው ሳይንሳዊ የሳተላይት ቆጠራ 15ነጥብ5 በመቶ የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 17ነጥብ ሁለት በመቶ ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል። እ.ኤ.ኣ በ2030 ዘላቂ የልማት ግብ ደግሞ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ሲሆን፣ በአራት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም 20 ቢሊዮን ችግኞች በመትከል የልማት ግብ ዕቅዱን ለመሳካት ነው የታቀደው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በመላ ሀገሪቱ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዘጠኝ ቢሊዮን አገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል። በያዝነው ወር በተጀመረው መርሃግብር ደግሞ አምስት ቢሊዮን ችግኞች በፌዴራል መንግሥት፣ በክልሎች፣ በፕሮጀክቶችና በማህበረሰብ ተሳትፎ እየተዘጋጀ ይገኛል።
በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ እንደ ቡና፣ ሙዝ የመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የተካተተ ሲሆን፣ ተከላውም እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ለማከናወን ነው የታቀደው። የደን ልማት ሥራው የአጠቃላይ አገራዊ ስትራቴጂካዊ ግብ አካል በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ችግኞችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ስላለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ አቶ ተስፋዬ እንዳስረዱት ክልሎች፣ ከልማቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የግብርና፣ የውሃ መስኖ፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሌሎችም የዘርፍ መስሪያቤቶች ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ተፋሰሶችን በደን የመሸፈን ሥራ በማከናወን ለአዝርዕት ዝርያ ጠቀሜታ ያላቸውን ዝርያዎች በማልማት፣ አካባቢና ደንንም ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ሁሉም የየድርሻውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ዝግጅት በማድረግ እንቅስቃሴው ተጠናክሯል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት ሲጀመር፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየመ ከሰባት ሚኒስቴር ተቋማት የተውጣጡ ሰባት ሚኒስትሮች የሚገኙበት ኮሚቴ ተዋቅሯል። የተመረጡት ተቋማት ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሁሉም የሚወጡት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። ኮሚቴውን የሚመራም ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሯል።
የቴክኒክ ኮሚቴው ተግባርም ችግኞች እና ሌሎችም ለመርሃግብሩ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዲሟሉ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ያመቻቻል። ለውሳኔ የሚያስፈልግ ነገር ሲኖር ደግሞ ተጠሪ ለሆነው በሚኒስትሮች ለተዋቀረው ኮሚቴ በማቅረብ ያስፈጽማል። የችግኝ ተከላና የልማት ሥራው በዚህ መልኩ በክትትልና ቁጥጥር ሪፖርት ይደረጋል። እያንዳንዱ የተከናወነው የሥራ መረጃ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ይላካል።
የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርሃግብር ቀደም ሲል በሁለት ዙር ከነበሩት ቀድሞ ነው የተጀመረው። ምክንያቱንም አቶ ተስፋዬ ሲገልጹ፤ ለዘመናት የተለመደው ሐምሌና ነሐሴ ወራትን ተጠብቆ ነው ችግኞች የሚተከሉት። ይሄ ባህል ወይንም ልማድ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ሆኖ ተገኝቷል። ምክንያቱ ደግሞ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ እኩል በሆነ ጊዜ አይዘንብም። ዝናቡ ሲቆምም እንዲሁ እኩል አይደለም። አንዱ አካባቢ ከሌላው ይለያያል። ሌላው ደግሞ ችግኝ ለመትከል የዝናብ ወቅትን መጠበቅ ግድ አይደለም። ትኩረት መደረግ ያለበት እንክብካቤው ካለ በማንኛውም ጊዜ ችግኝ ይጸድቃል። ለአብነትም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በደቡብና በከፊል ኦሮሚያ ክረምቱ ቀድሞ በመግባቱ እየዘነበ ነው። ኦሮሚያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ካላቸው መካከል አንድ ቢሊዮን የቡና ችግኞች ተከላ በማካሄድ መርሃግብሩን ጀምሯል። በደቡብ ክልልም የሙዝ ልማት በተመሳሳይ ተከናውኗል።
ልማቱ ቀድሞ መከናወኑ ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስም የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። በአካባቢዎቹ በተጓዳኝ የዛፍ ችግኞች ተከላም እየተከናወነ ነው። እንዲህ ዝናብ ቀድሞ በጀመረባቸው አካባቢዎች የችግኝ ተከላ መርሃግብሩን ማስጀመር ጥቅሙን ከፍ ያደርገዋል። በአንጻሩ ደግሞ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዝናቡ ገና አልጀመረም። ዝናቡ ዘግይቶ ጀምሮ ዘግይቶ ሊያቆም ይችላል። ስለዚህ ሁሉንም አጋጣሚዎች በወቅቱ መጠቀም ያስፈልጋል። ሐምሌና ነሐሴ ወራትን አስገዳጅ አድርጎ ከመጠበቅ እንደየአካባቢው ሥነምህዳራዊ ነባራዊ ሁኔታ መጠቀሙ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። ዘንድሮም ይህን ስትራቴጂ የመከተል ግብ ተይዞ ነው በመከናወን ላይ ያለው።
ኢትዮጵያ በምቹ የመሬት አቀማመጥ የምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ ተብላ እንድትጠራ ተፈጥሮ ያደላት አገር መሆኗን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ የአረንጓዴ አሻራ ርብርቡ በተፈጥሮ ያገኘችውን ፀጋ የበለጠ በማጎልበት ተጠቃሚነቷን ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የጎረቤት አገራትን ያካተተው የችግኝ ተከላ መርሃግብርም በውሃ እጥረት በተፈጥሮ ድርቅ የሚጠቁ የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም የቱርፋቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ በጎ ከመመኘት የመነጨ እንደሆነ ያስረዳሉ። በአጠቃላይ መርሃግብሩ ለአየርንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልትን የተከተለ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ስልቱም አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸው እንደሆነም አመልክተዋል።
በተለይም አረንጓዴ ልማቱ በፖለቲካዊ ዘርፉ ስለሚኖረው ፋይዳ አቶ ተስፋዬ እንዳብራሩት፣ በውሃ እጥረት ለድርቅ አደጋ የሚጋለጡት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በግጦሽ እና በድንበር ለተደጋጋሚ ግጭቶች መንስኤ ሲሆን ይስተዋላል። በመሆኑም ጎረቤት አገሮችን ማዕከል ያደረገ የአረንጓዴ ልማት መከናወኑ የውሃ ግኝታቸው እንዲያድግና ለከብቶቻቸው የሚያጋጥማቸው የሳር ግጦሽ ችግርም እንዲቃለል ያግዛል። ለግጭት መንስኤ የሆኑትን በልማቱ ለማስቀረት ያግዛል።
ከግጭት ይልቅ በመካከላቸው የሚኖረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይዳብራል። በአጠቃላይ አብሮ የመልማትና የማደግ ስትራቴጂ የአገራቱን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ተነሳሽነቱ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ጋር ተያይዞ የመልማት ፍላጎትንም የሚያሳይ በመሆኑ በበጎ ይወሰዳል። በዚሁ መሠረትም አንድ ቢሊዮን ችግኝ በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ጎረቤት አገሮች ውስጥ ለማከናወን በሦስተኛው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ውስጥ ተካትቷል። አፈፃፀሙ በብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ የሚወሰን ሲሆን፣ ችግኞችን ከማድረስ ባለፈ በቦታው ተገኝቶ የመትከል ሚና አይጠበቅም። ምክንያቱም የአካባቢውን ማህበረሰብ ማዕከል አድርገው የተከላ ቦታን ከማዘጋጀት ጀምሮ በራሳቸው ቢያከናውኑ ይመረጣል። ግንኙነቱም ምንም እንኳን የመንግሥት ለመንግሥት ቢሆንም በመርሃግብሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ምኞት ይተላለፋል።
ለጎረቤት አገራት የሚውለውን ችግኝ የማፍላቱ ሥራ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የገንዘብና ቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ በአምስት አካባቢዎች የማደራጀት ሥራ ቀድሞ ተከናውኗል። ችግኝ የማፍላቱ ሥራም ችግኞቹ በቀላሉ እንዲላመዱ የየአገሮቹን ሥነምህዳር ማዕከል ባደረገ ሁኔታ የሚከናወን ሲሆን፣ የችግኝ ጣቢያዎቹም ለአገራቱ አቅራቢያ በሆኑ አካባቢዎች ነው የተቋቋሙት። ለአብነትም ወደ ሱዳንና ከፊል ኤርትራ አገራት የሚላኩ ችግኞች ሁመራ፣ ወደኬንያ የሚላከው ሆለታ ላይ ሶማሌና ከፊል ጅቡቲ የሚላከው ሰመራ እና በድሬዳዋና ሐረር መካከል በሚገኝ ደንገጎ አካባቢ ተደራጅቷል።
ጎረቤት አገሮችን ታሳቢ ያደረገ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ከዚህ ቀደም ስለመኖሩ አቶ ተስፋዬ ላቀርብኩላቸው ጥያቄ መረጃው እንደሌላቸው ነው ምላሽ የሰጡት።
እርሳቸው እንዳሉት የአሁኑ እርምጃም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስልት ነው የምትከተለው። የዓለምአቀፍ የአየር ንብረት ድርድር ጉባኤዎች ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ 40 አገራትን ጉባኤ ለሁለት ዓመታት ስትመራ ቆይታለች። በአየርንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚደርስባቸውን አገራትን የያዘ ማህበርም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላበረከተችው አስተዋጽኦ ሞዴል አድርጎ በመውሰዱ ወይንም በመምረጡ ማህበሩን ለሁለት ዓመታት መርታለች። በአየርንብረት ተጽዕኖ ቅነሳ ያላትን የመሪነት አስተዋጽኦ በጎረቤት ሀገሮች በአርአያነት ለማሳየትም ጭምር ነው አገራቱ በአረንጓዴ ችግኝ ተከላ መርሃግብሩ እንዲካተቱ የተደረገው። ኢትዮጵያ የኃይልና የትራንስፖርት ምንጮቿን አረንጓዴ ለማድረግ ስትነሳ ለጎረበት አገሮችም ምሳሌ ለመሆን ነው።
የአረንጓዴ ልማት ሥራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ለአየርንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እንደ እኤአ 2011 ደርባን ላይ በነበረው የአየርንብረት ለውጥ ድርድር ጉባኤ ከተካሄደ ጀምሮ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት በተዘጋጀው ብሔራዊ የልማት ዕቅድ አረንጓዴ ልማት አንዱ አጀንዳ ነው። በመሆኑም አረንጓዴ የኢትዮጵያ የልማት አማራጭ ተደርጎ ሲወሰድ በመርህ ላይ የተመሰረተና ሳይንሳዊ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የነበሩ ጥንካሬና ክፍተቶች ላይም አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ በመጀመሪያው ዙር አራት ቢሊዮን፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዘጠኝ ቢሊዮን ችግኞች በላይ ለመትከል ተችሏል። ለዚህ ስኬት ሕዝቡ ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። ችግኝ መትከል አስፈላጊነቱን ተገንዝቧል። የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠንም 80 ከመቶ ላይ እንደሆነ ሳይንሳዊ በሆነ የጥናት ዳሰሳ ተረጋግጧል። ይሄ ትልቅ ስኬት ቢሆንም በራሱ ግን በቂ አይደለም። ችግኞቹ እስኪጎለብቱ እንክብካቤ ሊለያቸው አይገባም። የአረንጓዴ አሻራ እንደ አንድ ማስጀመሪያ መርሃግብር እንጂ ሕዝቡ የራሱ አድርጉ ከዘመቻ ባለፈ ሊሰራና ሊያስቀጥል ይገባል።
በችግኝ መረጣ ላይም ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዳስረዱት የአካባቢን ሥነምህዳር ታሳቢ ያደረገ ተስማሚ ችግኝ ፈልቶ እንዲተከል ነው የሚደረገው። ጎን ለጎን የሚከናወነው የቦታ ልየታ ሥራ ነው። በምን ያህል ሄክታር መሬት ላይ፣ ምን ያህል ችግኝ ያስፈልጋል የሚለው ቀድሞ ነው የሚዘጋጀው። በከተማና በገጠር የሚከናወነው የችግኝ ተከላም ይለያያል። በከተማ ሥነውበትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ በገጠሩ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ላይ ትኩረት ያደርጋል።
የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያግዙ ተግባራት ናቸው የሚከናወኑት። የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ክልሎችም የሰሯቸውን ዕቅድ የሚያካትቱ በመሆናቸው ከዕቅዱ በላይ ሊከናወን እንደሚችል ይጠበቃል። እስካሁን ባለውም በዚህ መልኩ ነው የተከናወነው። የክልሎች የቆዳ ስፋት አንዱ ከሌላው የተለያየ በመሆኑም የሚተከለው የችግኝ መጠን አንዱ ከሌላው ሊበልጥ ይችላል።
ማህበረሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያገኝም ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ። እስካሁን ባለው ተሞክሮ ዛፍ እንዳይነካ መከላከሉ ላይ ትኩረት ይደረጋል። በችግኝ ዝግጅት ለብዙ ዜጎች በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩም መርሃግብሩን የጎላ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
አቶ ተስፋዬ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ ላይ ለሚሳተፈው ሁሉ በሁለት ዙሮች ከታየው ክፍተት በመነሳት መልዕክት አስተላልፈዋል። ችግኞችን ከላስቲክ ውስጥ በማውጣት ለተከላ ዝግጁ በሚደረግበት ወቅት በስለት ነገር ላስቲኩን ለመቅደድ በሚደረግ ጥረት የችግኝ ስሮችን መጉዳት፣ ችግኞችን ቆልምሞ መትከል፣ ያልደረሱ ችግኞችን መትከል፣ የችግኝ ዘሮች ቀድሞ አለማዘጋጀት፣ ችግኞችን በማጓጓዝ ወቅት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት በቀጣይ መስተካከል ይኖርባቸዋል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013