ዓለምን ስጋት ውስጥ ከከተቷት ቀውሶች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ነው። ታዲያ ኢትዮጵያም የዚህ ቀውስ ሰለባ እንዳትሆን ከወዲሁ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች። የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዎችን ለመተግበር አራት ዋና ዋና ግቦችን ማለትም የግብርና ልማትና የመሬት አጠቃቀም፣ የደን ልማትና ጥበቃ፣ የተሻሻሉና ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአንዱስትሪ ልማት፣ ለትራንስፖርት አገልግሎትና ለግንባታ ስራ ማዋል፣ እንዲሁም ታዳሽ ሃይልን የማመንጨት ሥራን ተግባራዊ በማድረግ ከተደቀነባት ስጋት ለማምለጥ እየተጋች ትገኛለች።
በተለይም በየዓመቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በሀገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ውጤታማ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። የአረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ከሆኑት የሀገሪቷ ከተሞች መካከልም ሀዋሳ ከተማ አንዷ ነች። በሀዋሳ ከተማ ተገኝተን በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመዳሰስ በዛሬው የአረንጓዴ ልማት አምዳችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በአረንጓዴ ልማትና ጽዳት አስተዳዳር ላይ ድርድር የማያውቅና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን ያስረዱን የሀዋሳ ከተማ ጽዳት አስተዳደርና የአረንጓዴ ልማት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ዘለቀ ናቸው።
በከተማዋ ያለው የአረንጓዴ ልማት ሽፋን በተለያየ መልኩ ያለ ሲሆን የመንገድ አካፋይ፣ የመንገድ ዳርቻና የመንገድ መሀል ናቸው። አረንጓዴ አካባቢ የሚባሉት ደግሞ ሀይቅ ዳርቻ፣ ትራፊክ ደሴት እንዲሁም የተለያዩ አይነት ፓርኮችም በአረንጓዴ ልማት ይሸፈናሉ። በከተማ ግብርናም ለአረንጓዴ ልማት ውበት የሚሆን የከተማ ግብርና ላይ ይሰራል። በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙ ህንጻዎች ላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ይሰራሉ። በከተማዋ ደረጃቸውን የጠበቁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የሚሰሩ ሲሆን ለአብነትም የውበት የጥላና ሌሎች ዛፎችም ይተከላሉ። ይህን መነሻ በማድረግ እንደ የአካባቢው ሁኔታ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ዛፎች ይተከላሉ።
ደረጃ የወጣለት የአረንጓዴ ልማት ሽፋን 30/30/40 ነው። ይህ ማለት ከተማው 40 በመቶ ህንጻዎች፣ 30 በመቶ መንገዶችና 30 በመቶ ደግሞ አረንጓዴ ልማት ይሆናል ማለት ነው። በመሆኑም ባለፈው ዓመት በተሰራው ኦዲት መሰረት በእምነት ቦታዎች ዘላቂ ማረፊያ፣ ተቋማት፣ የግለሰብ ቦታዎች፣ እንዲሁም መንገድ አካፋዮችን አረንጓዴ በማድረግ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያወጣውን ደረጃ 30 በመቶ ማሟላት ተችሏል።
አረንጓዴ ልማት የከተማው ሳንባ ነው የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ አረንጓዴ ልማትን በስታንዳርዱ መሰረት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ሲያስረዱ፤ ሀዋሳ ከተማ እንደ ሀገር የተሻለች አረንጓዴ ልማትን አስቀድማ እየሰራች በመሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ጤና ማረጋገጥ ተችሏል። ለአብነትም ከዚህ ቀደም በከተማዋ ቆሻሻ ይጣልበት የነበረ ቦታ በአሁኑ ወቅት ፓርክ መሆን ችሏል። በከተማዋ የሚገኙ አራት ፓርኮች የአረንጓዴነት ምሳሌ በመሆናቸው የተለያዩ ከተሞች ወደ አረንጓዴነት ለሚያደርጉት ጉዞ አብነት አድርገው በመጥቀስ ይጎበኙታል። እነዚህ አራት ፓርኮች ሚሊኒየም፣ አሞራ ገደል፣ ጉኤና አሞራ ገደል ሚኒ ፓርኮች ናቸው። እነዚህ ፓርኮች ለሀዋሳ ከተማ ወሳኝ ናቸው። ጉኤ ፓርክ አራት ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን አስቀድሞ ቆሼ የነበረና የቆሻሻ ክምር የነበረበት ቦታ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ተቋማትንና ባለሀብቱን በጋራ በማሳተፍ በየተቋማቱና ባለሀብቱ እስከ 50 ሜትር ርቀት ያለውን ዙሪያ አረንጓዴ በማድረግ እንዲሳተፉ ይደረጋል። ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላውን ሁሉ በማሟላት በጋራ ይሰራል። ለአብነትም ሴንትራል ሆቴል አካባቢ በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ባለሀብቱ የሰራው አካባቢ ይጠቀሳል። ይህም በየደረጃው ተከፋፍሎ እየተሰራበት ነው።
ሀዋሳ ከተማ ላይ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ በክልሎች ለማስፋት በተደረገው ጥረትም በርካታ ክልሎች ወደ ሃዋሳ መጥተው ተሞክሮ ወስደዋል። ከአዲስ አበባ ከተማም አስሩም ክፍለ ከተሞች ሃዋሳ ተገኝተው ተሞክሮ ቀስመዋል። ሌሎችም ተሞክሮ ለመቀመር በርከታ ወጪ አውጥተው ወደ ውጭ ሀገራት ይሄዳሉ። ነገር ግን ይህ ተገቢ አይደለም የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ ሃዋሳ ከተማ ላይ ያለው ተሞክሮ በቂ እንደሆነና ለዚህም በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተመሰከረለት ስለመሆኑ አንስተዋል።
የከተማዋ አካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት በጋራ በመሆን መንግስት ያስጀመረው ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ይከናወናል። ሀምሌ 22 አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀንን መነሻ በማድረግ በየክረምቱ ይተከላል። ባለፈው ዓመት በጽዳትና ውበት ብቻ 254 ሺ ችግኞች በሀይቅ ዳርቻዎች ላይ ተተክለዋል። ሀዋሳ ከተማ 30 ቀበሌዎች ያሏት ሲሆን 12 ቀበሌያት የገጠር ክፍለ ከተሞች በሆነው ቱላ ክፍለ ከተማ ውስጥ ይገኛል። የአረንጓዴ ልማት በሰጣቸው ኮታ መሰረት አብዛኛው ችግኝ የተተከለው በእነዚህ ገጠራማ ተፋሰስ፣ ሀይቅና ተራራማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ነው። ነገር ግን በከተማ ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁና ውበት ያላቸውን ችግኞችም ይተከላሉ።
በከተማዋ መሀልና ዳርቻዎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የአረንጓዴ ልማትን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ማስተሳሰር በመቻሉ ውጤት ተመዝግቧል የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ ለዚህም ከዩኒቨርሲቲ የወጡ 130 ማህበራት የተቋቋሙ እንደሆነ አስረድተዋል። እያንዳንዱ ማህበራትም ከአምስት እስከ አስር የሚደርሱ አባላት አሏቸው። ማህበራቱ አስፈላጊውን ሥልጠና ያገኙ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ይገኛሉ።
ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት መሆን የቻለው የሃዋሳ ከተማ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆን የቻለው ከተማ አስተዳደሩና ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ በሰጡት ትኩረት ነው። ባለስልጣናቱ ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል። ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል እያደረጉም ይገኛሉ ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ከሁሉም ነገር በፊት የከተማዋ ጽዳት መቅደም እንዳለበት ያስረዳሉ።
የጸዳ ከተማን በቀላሉ ማልማትና አረንጓዴ ማድረግ ይቻላል። ለዚህም በሃዋሳ ከተማ 20 ሺ የሴፍቲኔት ሰራተኞችና ሁለት ሺ ከተማዋን ጠዋትና ማታ የሚያጸዱ ቋሚ የጽዳት ሰራተኞች አሉ። በሴፍትኔት ስር ያሉት በዘመቻ የሚሰሩ በመሆናቸው ሀይቅ ዳርቻዎችንና ምንጣሮን ይሰራሉ። ሁለት ሺ የከተማዋ መደበኛ የጽዳት ሰራተኞች ደግሞ ዘወትር ከንጋቱ 11፡30 እስከ 1፡30 ድረስ ከተማዋን ሙሉ ያጸዳሉ። ማታም በተመሳሳይ ይጸዳል። በዚህ ልክ የሀዋሳ ከተማ ጽዳት ይጠበቃል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ማሽነሪዎች ማለትም 27 ትራክተሮችና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ማሽነሪዎች አሉ። ቆሻሻውን ቤት ለቤት ተዘዋውረው እንዲሁም ከመንገድ ላይ ይነሳል። በመሆኑም በከተማዋ የሚመነጩ 85 በመቶ የሚደርሰው ቆሻሻ ተሰብስቦ ወደ ተገቢው ቦታ ይወሰዳል። ተዝረክርኮ የሚቀር ቆሻሻ የለም። ኦርጋኒክ የሆነውና ያልሆነውን ቆሻሻን በመለየት ወደ ሀብትነት የመቀየር ተግባርም እየተከናወነ ይገኛል። በከተማዋ የሚመነጨው ቆሻሻ 80 በመቶ የሚሆነው የሚበሰብስ ስለመሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። ስለዚህ 80 በመቶው ኮምፖስት ይሆናል። ሀይላንዶችም እንዲሁ ተሰብስበው ይጨፈለቁና ወደ አዲስ አበባ ይላካሉ። በአጠቃላይ ከከተማዋ የሚመነጨው ቆሻሻ አብዛኛው ወደ ሀብት የሚቀየር ሲሆን ጥቂቶቹ ብቻ የሚወገዱ ይሆናል።
በአረንጓዴ ልማትም ይሁን በሌላ ፕሮግራም የሚተከሉ ችግኞች መጽደቅ እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ ኤልያስ፤ በሀዋሳ ከተማ የሚተከሉ ችግኞች 95 በመቶ የሚጸድቁ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም ከፍተኛ የሆነ ክትትል ይደረጋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀዋሳ ከተማ ላይ የተተከሉ በርካታ ችግኞች ጸድቀው የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ በተለይም ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል። በዚህም ተራራና ሀይቅ ዳርቻዎች ላይ ለተተከሉት ችግኞች ሳይቀር በጀት መድቦ ቦቲ፣ ታንከርና ሌሎች ግብዓቶችን በማሟላት ችግኞቹ እንዲጸድቁ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። እንደ ሀዋሳ ከተማ የማናሳድጋቸውንና የማንከታተላቸውን ችግኞች አንተክልም ብለዋል።
ፓርኮችን በተመለከተም በሀዋሳ ከተማ የተለያዩ ፓርኮች ስለመኖራቸውና ከእነዚህም መካከል በተለይም ሁለቱ ሞዴል የሆኑና ሥራቸው ተጠናቅቆ ለሰርግ፣ ለልደትና ለተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጡ ያሉ ሁለት ፓርኮች ይገኛሉ። አንደኛው ፓርክ በቀደመው ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ ይጣልበት የነበረው ቦታ ሲሆን ጉኤ ፓርክ ይባላል። ሁለተኛው ደግሞ አሞራ ገደል ሚኒ ፓርክ ሲሆን ከእነዚህ ሁለት ፓርኮች በተጨማሪም 49 ሄክታር የሚሸፍን ትልቅ ፓርክ ጥናቱ አልቆ የዲዛይን ሥራው እየተሰራ የሚገኝ ግዙፍ ፓርክ መኖሩንም ገልጸዋል። ፓርኩ ጥቁር ውሃ አካባቢ ሀይቅ ጥግ ያለ ሲሆን ሥራውም በሂደት ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ በሀዋሳ ከተማ አራት ትላልቅ ፓርኮች ሲገኙ ሁለቱ ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው ።
ሀዋሳ ከተማ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚጎበኟት ከተማ እንደመሆኗ አራቱ ፓርኮች ብቻ በቂ ናቸው ወይ ስንል ላነሳነው ጥያቄ አቶ ኤልያስ ሲመልሱ፤ በቅድሚያ የጥያቄውን ትክክለኝነት በማመን ሀዋሳ ከተማ ከተመሰረተች 53 ዓመታት ያስቆጠረችና ጎልማሳ ከተማ ናት። ከተማዋ ከዚህ ቀደም ስትቆረቆር ደረጃውን የጠበቀ የከተማ ይዘትን ያላሟላች ነበረች። በተለይም መሀል ያለው ከተማ አሁን ባለው ደረጃውን በጠበቀ መሰረት የተመሰረተ አልነበረም።
ነገር ግን አስቀድሞ ከነበረው የከተማ አከታተም ቅርብ ጊዜ የተከተሙ ከተሞች ደረጃውን በጠበቀ መሰረት ነው። ለአብነትም በከተማዋ አዳዲስ የሆኑና የማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች አካባቢ በጥናቱ መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ሥራ እየተሰራ ነው። ለአብነትም ከዚህ ቀደም መሀል ከተሞች አካባቢ ያልነበረ በደረጃው መሰረት 500 ነዋሪዎች በሚኖሩበት ስፍራ አንድ የአረንጓዴ ልማት ይኖራል። በዚህ መሰረትም በከተማዋ አዲስ በተመሰረቱ ሁለት ክፍለ ከተሞች ይህን ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል።
ለአብነት የቀረቡት ሁለት ክፍለ ከተሞችም ታቦር እና መናኸሪያ ክፍለ ከተማ ሲሆኑ፤ በአካባቢው 78 የአረንጓዴ ልማት ተግባራዊ ሆኗል። እንዲህ ያሉ የአረንጓዴ ልማት አካባቢዎችን በመፍጠር በከተማዋ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ መሆን ያልቻሉትን ፓርኮች መሸፈን ይችላል በሚል ጭምር እየሰሩ እንደሆነ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል። ለጊዜው በየመንገዱ መሀል ያሉትን ክፍት ቦታዎችን በማልማትና አረንጓዴ በማድረግ እየተሰራ ነው።
ለሀዋሳ ከተማ አንዱ ውበቷ ሀይቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ኤልያስ፤ ሀይቁንና ከተማዋን መለየት የሚያስችል የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየተሰራ ነው። ይሁንና ከተማዋን ይበልጥ ጽዱና አረንጓዴ ከተማ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች ይጠበቃሉ። ስትራቴጂክ እቅዶች የከተማውን ሽፋን ሙሉ ለሙሉ አረንጓዴ ማድረግ በመሆኑም በቀጣይ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ መንገዶች በሙሉ በደን የተሸፈኑ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ተጀምሯል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013