የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ የጠብታ አንቡላንስ ባለቤትና ዋናሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ ዳይሬክተር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎች ኮሚሽን የአማካሪዎች ቦርድ አባል ሆነው ይሰራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የድንገተኛ ህክምና ስታንዳርድን ያወጡ፣ የተገበሩና ለብዙዎች መድረስ የቻሉም ናቸው። በእርሳቸው እያንዳንዱ ጉዞ ሰርቶ ማሰራት እንጂ አይቻልም ብሎ መግፋት አይደለም። ለዚህም ማሳያው በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፈው ጠብታን መስርተው ዛሬ ብዙዎችን መታደግና የስራ እድል መፍጠር መቻላቸው ነው።
አቶ ክብረት አቤቤ ነጻ፤ አዲስ ሀሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱና ለብዙዎች ከስልጠና ጀምሮ ሀሳባቸውን የሚያካፍሉም ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። እናም ከዚህ ሁሉ ተሞክሯቸው ያቋድሱን ዘንድ ለዛሬ ‹‹ የህይወት ገጽታ ›› አምድ እንግዳ አድርገናቸዋልና መልካም ቃርሚያ ተመኘን።
ልጅነት
ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ጃንሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። 12 ልጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ አድገዋል። አባታቸው ሁሉን ነገር በአቅማቸው አሟልተውላቸው ነው ያሳደጓቸው። በቤት ውስጥ ቤተሰቡን ለማገዝ የሚደረገውን ውጣ ውረድ ትንሹ ክብረት በዚያ ጨቅላ አዕምሮው ይረዳ እንደነበር ያስታውሳል። ይሁን እንጂ ማንም ምንም እንዲያደርግ አይፈቅድለትም። ያው ገንዘብ ማምጣት ላይ ማለቴ ነው። ስለዚህም የትናንቱ ልጅ የዛሬው ጎልማሳ አባታቸው የሚሉትን እያደረጉ እንዲያድጉ ሆነዋል። በቤት ውስጥ ሥራ ግን ማንም አያክላቸውም። እናታቸውን ሊጥ እስከማቡካት ድረስ የሚደርስ ሥራ ያግዛሉ። አልፎ አልፎም ክረምት ላይ የመስከረም ወጪያቸውን ለመሸፈን ማንኛውም የሰፈር ልጅ እንደሚያደርገው ራሳቸውን ለመቻል እንጨት ለቅመው በመሸጥ ቤተሰቡን ከተጨማሪ ወጪ ይታደጋሉ። ግን ከዚህም አለፍ ብለው እንደነበር አይረሱትም። ይህም ለአባታቸው ምንም ሳይሉ የሰፈር ልጆችን ተከትለው ሊስትሮ ለመጥረግ ያደረጉት እንቅስቃሴ ነው። እቃዎቹን ለመገዛዛት መርካቶ በሄዱበት ወቅት የሰፈር ሰው አግኝቷቸው ለቤተሰቡ በመናገራቸው የማይረሱትን ግርፍ ተገርፈዋል። ከዚያ በኋላ ግን ምንም እንዳልሞከሩም አጫውተውናል።
አባታቸው ሻምበል ሲሆኑ፤ በግቢያቸው ውስጥ የማይሰሩት ስራ የለም። ከብት ማርባት፤ ወይን መትከል ብሎም ንብ ማነብ የዘወትር ሥራቸው ነበር። የራሳቸውን ቤት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዳቸውን ልጆቻቸውን ቤት ሳይቀር ራሳቸውም የሰሩ ናቸው። ከዚያም በተጨማሪ የሰፈሩ ሽማግሌ፤ ተጨዋች ፤ አንባቢና የእውቀት ሰውም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። እርሳቸውም በዚህ የአባታቸው ባህሪ እንደተዘወሩም ያስረዳሉ። ቁጭ አቤቤን ነው የሚሏቸውም እንዳሉ ይናገራሉ።
በእነ አቶ ክብረት ቤት የቤተሰቡ ብዛት ሳይበቃ ከክፍለ አገር ለህክምና ተብሎ የሚመጣው ሰው ቁጥር ስፍር የለውም። ከዚህ አንጻርም የሰፈር ልጆች ለቤታቸው ቅጽል ስም አውጥተውለታል። ይህም የካቲት 13 የሚል ሲሆን፤ ከየካቲት 12 ሆስፒታል ቀጥሎ ሪፈር የሚባልበት ቤት እንደማለት አስበው ያወጡለት እንደሆነም ያነሳሉ። ይህም ቢሆን እነርሱ ቤት ሁሌ በተድላ ይኖራል፤ ደስታና ፍቅር ሙሉ ነው። እነርሱ ቤት የመጣ እንግዳም ቢሆን ደስታውን ሸምቶ ይመለሳል፤ ተርቦም፣ ተጠምቶም አያውቅም። ቤቱ የበረከት ቤት መሆኑም ሁልጊዜ ያስደንቃቸዋል። እንደውም ደሃ ነን የሚለውን ትተው ሀብታም ነን ማለት የጀመሩትና ሰው የመውደዳቸው ምስጢር የተገለጠላቸው ይህንን ከአዩ በኋላ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንግዳችን በጣም ነጭናጫና ሁሉን ነገር መቆጣጠር የሚፈልግ አይነት ልጅ ነበሩ። ለራሳቸው እውነተኛ መሆን የሚፈልጉና መቼ ምን መሆን እንዳለባቸው አሁንም ያለዩም ናቸው። ለዚህ ደግሞ ነጻነት ትልቁን ቦታ እንደያዘ ያስረዳሉ። ድህነት በጣም የሚጎዳው ስላልበላን ሳይሆን በስነልቦና ቀውስ ስለምንመታ ነው። የድሀ ድሀ መባል በራሱ ትልቅ የአዕምሮ ጫና ይፈጥራል። ይህ እንዳይሆንብን ደግሞ አባቴ ብዙ እንደለፋብኝ ዛሬ አይቻለሁ። ምክንያቱም ምንም ያልቀረብኝ ልጅ ሆኜ ነው ያደኩት። በዚህም መሆን የምፈልገውን አይቼ እንድወስን አግዞኛል ይላሉ።
ከአዲስ አበባ እስከ ዓለም ጫፍ
አቶ ክብረት ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት በህብረት ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል በዚህ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከዚያ ቀጣዩን ክፍል ለመከታተል በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ገቡ። እስከ 12ኛ ክፍልም በትምህርት ቤቱ ቆይታቸውን አደረጉ። እንደውም ትምህርት ቤቱን ልዩ ትዝታ ያየሁበት ነው ይላሉ። ከጨዋታ ርቀው የትምህርት ፍላጎታቸውም የጨመረው በዚህ ትምህርት ቤት እንደሆነ ያስታውሳሉ። በተለይም ዘጠነኛ ክፍል ሲገቡ ትልቅ ወንድማቸው ዩኒቨርስቲ ገብቶ ስለነበር ለእርሱ የሚሰጠውን ክብርና ሞገስን ሲያዩ መንፈሳዊ ቅናት ይዟቸው ስለነበር ተወዳዳሪና የደረጃ ተማሪ መሆንን ተያያዙት። ይሁን እንጂ 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ለዲፕሎማ የሚያስገባ ውጤት ነበር ያመጡት። በዚህም ጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅን እንዲቀላቀሉ ሆነዋል።
ከዩኒቨርስቲው በነርሲግ ሙያ የተመረቁት እንግዳችን፤ ባሌ ለሥራ በሄዱበት ከሌሎች ጓደኞቻቸው ማነሳቸው አንገብግቧቸው ነበርና ማትሪክ ድጋሚ ወሰዱ። 3 ነጥብ 8 በማምጣትም በሥራ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል እንደመጡ በውጤታቸው ተወዳድረው ቀን እየሰሩ በማታው ክፍለጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ በማኔጅመንት የትምህርት መስክ መማራቸውን ቀጠሉ። ሦስት ዓመታትንም እንዳሳለፉ ትምህርቱ የሚፈጀው ሰባት ዓመት በመሆኑ በቀን በአንስቴዢያ ትምህርት መስክ የመማር እድል አግኝተው ነበርና ማኔጅመንቱን ዊዝድሮ ሞልተው አንስቴዥያ ሙያን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ተማሩ። በከፍተኛ ዲፕሎማም በከፍተኛ ውጤት ተመረቁ።
በትምህርት ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እልህ ያለባቸው ባለታሪካችን፤ ቀደም ሲል የጀመሩትን የማኔጅመንት ትምህርትንም ቢሆን አጠናቀዋል። ሁለተኛ ድግሪያቸውንም ቢሆን በሥራ አመራር የትምህርት መስክ ተከታትለዋል። ይህ የትምህርት እድልም የተገኘው በዩኤስ ኤድ እና በዲኤፍ አይ ዲ በኩል በጤናው ዘርፍ ላይ አዲስ ሃሳብ ባመጡ የኢትዮጵያና የኬንያ ስራ ፈጣሪዎች በናይሮቢ በተደረገው ውድድር 200 ሺህ ዶላር በማሸነፋቸውና በሥራቸው የተገረሙት ክርስቲን የሚባሉ የውጪ ሃገር ዜጋ በስራቸው መደሰታቸውን ገልጸው «አኩመን ፌሎሽብ» በተባለ የስልጠና እንዲወዳደሩ በመጋበዟ ነው።
በእርግጥ መጀመሪያ ይህ የትምህርት እድል ለኢትዮጵያዊያን አይሰጥም ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ እንጂ በአፍሪካ ምስራቁ ክፍል የምትገኝ አይደለችም በሚል እንዳይጠቀሙት አድርገዋቸዋል። እርሳቸውም ከመላው አፍሪካ ብዙዎች ተመዝግበው 20 ሰዎች ብቻ ተመልምለው የሚሳተፉበትም ስለሆነ እልህ ውስጥ ገብተው ኒዎርክ ለሚገኝው የአኩመን ዋን መስሪያ ቤት ደብዳቤ ጻፉ። የደብዳቤውም ጭብጥ ኢትዮጵያ እዚህ ፕሮግራም ላይ እንዳትሳተፍ የተደረገው የምስራቅ አፍሪካ ሃገር ስላልሆነች ሳይሆን ቅኝ ስላልተገዛች ነው የሚል ነበር። ይህን የተረዱት የድርጅቱ መስራች ጃኩሊን ኖቮግራትዝ ደብዳቤው ሲደርሳቸው እኛ እንዲህ አይነት አፍሪካዊያንን ነው የምንፈልገው በማለት ለኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2015 ለሚደረገው ፕሮግራም እንድትሳተፍ ፈቀዱ።
አቶ ክብረትም በዚህ ውድድር ተሳትፈው ሁለት ሴት ኢትዮጵያውያን አልፈው ወደ ስልጠናው ገቡ። ይህ የአኩመን ሊደርሺፕ ስልጠና ህይወታቸውን የለወጠላቸውና የማህበራዊ ስራ ፈጣሪነታቸውን ያጠናከሩበት ስልጠና እንደሆነም ይናገራሉ። ከዚያም በኋላ ከ44 ሃገራት በላይ በመጓዝ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል። ራሳቸውም በሚሰጡት ስልጠናም ቢሆን ሁልጊዜ ተማሪ እንደሆኑም ያምናሉ።
ቦታ ያልገደበው ሥራ
‹‹ሥራዬ ማንነቴ ነው፤ ክብሬና የደስታዬ ምንጭም ነው። በዚህም ችግር አለ ማለት በየጊዜው ለምሰራው ሥራ እድል አለኝ እንደማለት አድርጌ እወስደዋለሁ። እኔ ችግርን ሳይሆን አለመስራትን ነው የምጠላው። ከመንግስት እንደ ፈጣሪ ምንም አልጠብቅም። አልፎ ተርፎ መንግስትን ማገዝ የእኔ ድርሻ ነው ብዬ አምናለሁ›› የሚሉት እንግዳችን፤ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት፤ የጠብታ አንቡላንስ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። የአዲስ አበባ ቻንበር ኦፍ ኮሜርስ ቦርድ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎች ኮሚሽን የአማካሪዎች ቦርድ አባል ሆነውም ይሰራሉ። የኢትዮጵያ የድንገተኛ ህክምና ስታንዳርድር ያወጡም ናቸው። ራስን መኮፈስ ሌላ መስራት ሌላ እንደሆነም ያምናሉ። ሰርቶ ማሰራት ግን ፈውስ ነውና ዝም ብሎ ከመኮፈስ ራስን ማራቅ ነው ባይ ናቸው።
ህይወት ወደምድር የመጡበትን ምክንያት ማወቅ ነው። የመጡበትን ምክንያት ማወቅና ወደ ተግባሩ መግባት እንጂ ትልቅ መኪናና ትልቅ ቤት አይደለም የሚሉት እንግዳችን፤ ሰው ከራሱ ሲያልፍ መኖር ይጀምራል። ለዚህ ደግሞ ወሳኝና በችግር ውስጥ ማለፍ ካለበት ማለፍ ይኖርበታል። መወዳደርም ያለበት ከራሱ ጋር ነው። ከራስ ሲታለፍ ነው ስኬታማ የሚኮነው ባይ ናቸው።
የሥራ ጅማሮዋቸው ከዲፕሎማ ምርቃት በኋላ በባሌ ክፍለአገር ጊኒር ወረዳ ላይ ተመድበው የሰሩበት ነው። አምስት ዓመታትን በጊኒር ጤና ጣቢያ በነርስነት ሙያ በመስራት አሳልፈዋል። ይህ ጊዜ ግን ከአዲስ አበባ ወጥቶ ለማያውቅ ልጅ እጅግ ፈታኝ ይሆን ነበር። ሆኖም የወዳጃቸውንና ህይወታቸውን ያቀለለላቸውን አቶ ልዑል ተክለመድህን የሚባል ወንድም በማግኘታቸው ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አልፏል። ዛሬ ድረስ ወዳጅነታቸውን ያጠነከሩበትም ሆኖላቸዋል። ከዚያ በዘመቻ የሰሩበት ቦታ ብላቴ ሲሆን፤ ለሦስት ወራት አገልግለውበታል። ቀጥለው ደግሞ የመንግስት ለውጥ በመደረጉ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተዛውረው ሀኪሞችን በማገዝ ይሰሩ ጀመር። አንስቴዥያውን ከተመረቁ በኋላ ደግሞ አንስቴቲስት ሆነው መስራታቸውን ተያያዙት። 17 ዓመታትንም በሥራው ላይ አስቆጥረዋል።
ጎን ለጎንም በዚሁ ሙያ በስድስት የግል ህክምና ተቋማት ውስጥ በትርፍ ሰዓታቸው ይሰሩ ነበር። : ይሁንና አንድ አጋጣሚ ይህንን ሥራቸውን ወደ ግል “እንዲያዞሩት አደረጋቸው። ይህም እንግሊዝ አገር ድረስ እንዲሄዱና አንድ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ህመምተኛን ህክምና እየሰጡ እንዲያደርሱ የተሰጣቸው እድል ነው። በወቅቱ ብቃታቸው በሁሉም ዘንድ ተመስክሮላቸዋል፤ እዚያ ሲደርሱም ህመምተኛውን የተቀበላቸው የድንገተኛ ህክምና ስርአት አዲስ ነገር እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ጓደኞቻቸው ወደ ሃገር አይመለሱም ቢሏቸውም እርሳቸው ግን ተመልሰው ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመልቀቅ አዲሱን ስራ ለመጀመር ቆርጠው ተነሱ።
የመንግስት ስራቸውን ሲለቁ ህልማቸው ላይ ወዲያው መድረስ ስለሚያስቸግር የቢሮ ስራን ለመልመድ እንዲችሉ የተቀናጀ የቤተሰብ አገልግሎት በሚባል ሃገር በቀል ድርጅት ውስጥ ለሶስት ዓመታት ሰርተዋል። በእርሳቸው እሳቤ ህልም እውነት ነውና በኢትዮጵያ የተማረውም ሆነ ያልተማረው ሰው ከስም በፊት ማንጠልጠያ ማዕረግ ቢፈልግም እርሳቸው ግን ይህ ሳይኖራቸው ፈተና ቢበዛባቸውም ሀሳባቸውን እውን አድርገዋል። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን ጠብታ አንቡላንስን መመስረት ነው።
ጠብታ አንቡላንስ ሥራው የተጀመረው በሶስት አምቡላንስ ሲሆን፤ አንዱን ራሳቸው እያሽከረከሩ ለሁለቱ ደግሞ ሹፌሮችን በመቅጠር ነው “ሀ” ብለው ስራውን የጀመሩት። አሁን 15 ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ አምቡላንሶች ባለቤት አድርጓቸዋል። 67 ቋሚና 27 ጊዜያዊ ሰራተኞችም አሏቸው። 8035 በሚባል የአጭር ስልክ ቁጥር የጥሪ ማዕከል ከፍተው በእያንዳንዱ አምቡላስ ጂፒኤስ በመትከል አገልግሎቱን አቀላጥፈው በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተሽከርካሪ ብቻ የተወሰነው የአምቡላንስ አገልግሎት ወደ አየር የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ከፍ ለማድረግም እየሰሩ ናቸው። በቀጣይ ደግሞ የእኛ ጠብታ ብዙ ነገር ይቀይራል ብለው ስለሚያምኑ ወር ሲገባ የሚታየውን የነዳጅ ሰልፍ ለማስቀረት የሞባይል ጋዝ ስቴሽን ለመክፈት አስበዋል። በተመሳሳይ የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ እንዲም የድንገተኛ ህክምና ማዕከል ሴንተር ማቋቋም ይፈልጋሉና ለዚህም እየተጉ ይገኛሉ።
‹‹የኢትዮጵያን ወጣቶች ሩዋንዳ ይዤ መሄድ እፈልጋለሁ። በዚያው ልክ ዱባይንም እንዲያዩ ማድረግ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ሰው ሲደማመጥ ምን አይነት ተአምር እንደሚሰራ ሳይደማመጥ ደግሞ መአትን እንደሚያወርድ እንዲገነዘቡ ማድረግን አምናለሁና›› የሚሉት አቶ ክብረት፤ ሳንጠፋፋ እንዴት መዳን እንደምንችል ከንግግር ያለፈ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ይህቺ አገር የደቡብን ሙዚቃ ብቻ ሸጣ ከበለጸጉት ጋር መቀላቀል ትችል ነበር። ሆኖም ግን ብሔሩ ወይም ሃይማኖቱ እስከሚነካበት ድረስ መልካም የሚናገር ሰው የጠፋበት ሃገር በመሆንዋ እየተቸገረች ነው። ወደፊት ግን እንደሚቀለበስ አምናለሁና እኔም ሃገር የማዳን ጠብታዬን አጠናክረዋለሁ ብለውናል።
የእኔ ጠብታ
ጠብታ ማለት የእኔ የታለ ብሎ የመጠየቅ ፍልስፍና ነው። ምንድነው ችግሩ ብሎ ማየትና ለዚያ ብቁነትን ማሳየትም ነው። ስለዚህም እኔ በተፈጥሮዬ ሥራ ፈጣሪ ነኝ የሚል እምነታቸውን ለማሳየት በዚህ ፍልስፍና ተመርተው ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ምክንያታዊ ያልሆኑ ምክንያቶች ለእርሳቸው ቦታ የላቸውም። ሁሉም ችግሮች በሥራ ፈጣሪነት ይፈታሉ ብለው ያምናሉ። እናም አንድ ሰው ስንት ነው በሚል ፍልስፍና ተነሱ። ዋጋ የማይወጣለት ሰው መዳን የሚችለው በአንድ ሰው ጠብታ ነው ሲሉም ቤታቸውንና መኪናቸውን ሸጠው ህልማቸውን ዳዴ እንዲል አደረጉት።
ድህነት መገታት ያለበት በሥራ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁልጊዜ ማሰብ፣ የራስ ሰው መሆንና የራስን ጠብታ ማየት ያስፈልጋል። የራስን አዳዲስ እድሎች መፍጠር መጠቀምም ይገባል አቋማቸው ነው። ሕይወት የውሳኔ ጉዳይ ነው። በችግር ውስጥ አልፌ የተሻለ ነገዬን እሰራለሁ ካልኩ የሚያስቆመኝ አይኖርም። ራሱ ሳይቆምም ሌላ ሰው ያቆመ የለም። ስለሆነም ራስን ለማቆም መልፋት ዋነኛ ተግባራቸው እንደሆነ አምነው ስለተጓዙም ጠብታ ለሌሎች ጠብታ ሆኗል ባይ ናቸው።
“ሁሉ ችግር ሰው ሲኖር ይፈታል። ሁሉ ነገር ሰው ሲኖር ይተርፋል” የሚሉት ባለታሪካችን፤ በአብሮነት የማይበቃ ነገር እንደሌለ ያስባሉ። በዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እጦት በርካቶች ማለቃቸው የሁልጊዜ የእርሳቸው ጭንቀት ነበር። በተለይም ያለበቂ ምክንያት የሚሞተው ሰው ራስምታትን ይፈጥርባቸዋል። ከ20 ዓመት በፊት የነበረው የአምቡላስ አገልግሎት ሁኔታም እጅግ አሳዛኝ ሆኖባቸው ነው የቆየው። ስለዚህ የእኔ ጠብታ የታል ማለትን ጀመሩ።
አደጋ የደረሰበትን ሰው ለማዳን አገልግሎቱን ከፍ ማድረግ የውዴታ ግዴታም መሆኑን ሲረዱና እንግሊዛዊውን ታማሚ ይዘው ሄደው ያዩትን ሲያስታውሱ መቼም መተኛት እንደሌለባቸው ቆርጠዋል። ያ እሳቸው በእንግሊዝ ሃገር ያዩት የድንገተኛ የህክምና አገልግሎት ለሰለጠነ ሃገር ብቻ መሆን የለበትም ብለውም ሃሳቡን ለመጋፈጥ ቆርጠዋል። ስለዚህም ይህ ነገር ለአገሬ ይገባታል ሲሉ ቀልጣፋና የዘመነ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎትን በአገራቸው ላይ አስጀመሩ። ጠብታዬን ለአገሬም አሉ።
ሥራ ፈጣሪነትና ፈተናው
የጠብታ አንቡላንስን ለመጀመር ስታንዳርድ የለም ተብለው ነበር። እንደውም ወቅቱን ሲያስቡ «ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብ ያለው ሰው አይከበርም፤ አብዛኛው ሰው ማሰብን ይፈራል፤ እኔ እቅዴን ያጫወትኳቸው አብዛኞቹ ሰዎች አይደለም ሃሳቤን ሊደግፉት ቀርቶ ማሰቤን ራሱ ተቃውመውታል፤ በርታ ብለው የደገፉኝም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ድሮም ለሰነፍ ሰው እንደ አይቻልምን የመሰለ ጥሩ ምላሽ የለም። ግን ያልፈራ ወሳኝ ያሰበበት ላይ እንደሚደርስ አረጋግጦልኛል›› እንዲህ ነበር ያሉት።
ስራቸውን ለቀው በሰሩት ሥራና ቤታቸውን ሸጠው ባገኙት 350 ሺህ ብርም ዱባይ ሄደው ሶስት አሮጌ አምቡላንሶችን የገዙት አቶ ክብረት፤ አምቡላንሶቹን ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት ለትራንስፖርት ሚኒስቴርና ለጉምሩክ የሚከፈለውን አምስት በመቶ ክፍያ ለመክፈል ተቸግረው እንደነበርና አብዛኞቹ የፋይናንስ ተቋማትም ሃሳብ ካለው ሰው ይልቅ ተጭበርብሮ ለሚመጣ ገንዘብ ቦታ ይሰጣሉና ሊያበድሯቸው ባለመቻላቸው መኪናቸውን እንደሸጡ አይረሱትም። ግን ይህም አለፈ ስኬቴም የመጀመሪያው ላይ ደረሰ ይላሉ የጠብታ አንቡላንስ ምስረታን ውጣውረድ ሲያስታውሱ።
በሌላ በኩል ይህ ዘርፍ የህብተረተሰቡ የአምቡላንስ አገልግሎት የመጠቀም ባህል ያልዳበረበት በመሆኑም ኑሯቸው በብዙ መንገድ መፈተኑን የሚናገሩት ባለታሪካችን፤ ባጋጠማቸው ችግሮች መቼም ተስፋ እንደማይቆርጡ ይበልጡንም እንደሚጠነክሩ ያነሳሉ። በዚህም ሌት ተቀን ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ በማበጀት ሥራቸውን አጠናከሩ። የስራው አስፈላጊነትም ከጊዜ ወደጊዜ መከፈት ሲጀምር ዛሬ ያሉበትን እድል ሰጣቸው። በተለይም ይህንን ስራ ለመስራት ያሰቡበት ምክንያት በአገሪቱ ያለው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በመሆኑ ክፍተቶቹን በጠብታቸው በጥቂቱም መድፈን መቻላቸው የሁልጊዜ ደስታቸው እንደሆነ አጫውተውናል።
የህይወት ፍልስፍና
የህይወት መጨረሻው ስኬት ብዙ ዝና፣ ብዙ ገንዘብና ብዙ ስልጣን ሳይሆን ብዙ ደስታ ነው። ደስተኛ ነህ ወይ ብሎ ራስን መጠየቅ ህይወትን ያሳምራል። ለእያንዳንዱ ስኬትም መሰላል ይሆናል። ምክንያቱም ከዚህ ደስታ ውስጥ መፍትሄ እንጂ ችግር አይኖርም። የደስታ ሁሉ ዋና ምንጩ ማንነትን መቀበል ነው። ማንነት ወዶ የሚሰጥ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ጸጋ ነው። ብሔር የትውልድ ቦታና እና ቀለም ወደን የምንቸራቸው ነገሮች አይደሉም። ስለዚህም የተሰጠንን አምኖ በመቀበል በምንለውጣቸው ነገሮች ላይ ለተሻለ ነገር መትጋት ዛሬ ከሚያስፈልጉን ነገሮች የመጀመሪያዎቹ ነገሮች ናቸው እምነታቸው ነው።
በር ከፋቹ ገጠመኝ
በሚከሰቱ የድንገተኛ አደጋዎች ሁሉ ፈጥኖ መድረስ ልምዳቸው ነው። ደሃ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሲያገለግሉ ደግሞ ከገንዘብ በላይ ሰውነታቸውን አይተው ነው። ለዚህ ደግሞ ዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት በኮልፌ አካባቢ ተከስቶ በነበረው አሰቃቂ የመኪና አደጋ ላይ በ 20 ደቂቃ ውስጥ በመድረስ በርካታ ተጎጂዎችን ከሞት መታደጋቸውን ነው። ያ ጊዜ ለእርሳቸው እድልም መልካምነትም እንደነበር አይረሱትም። እድሉ የለጋሾች ልብ የራራበት ሲሆን፤ አደጋው በተከሰተበት ወቅት እንደአጋጣሚ ሆኖ የካናዳው አምባሳደር በቦታው ተገኝተው ነበርና በሹፌራቸው አማካኝነት ስለ ጠብታ አምቡላንስ ስራ አወቁ። በስራውም ተማረኩ። በዚህም እራት አዘጋጅተው ጋበዟቸው። 30ሺህ ዶላርም አበረከቱላቸው። ይህ ብርም በከንቱ እንዳይፈስ በአምስት ክልሎች የሚገኙ ትራፊክ ፖሊሶችን በድንገተኛ አደጋ ህክምና ዙሪያ ስልጠና ሰጡበት። ተግባሩ ይበልጥ ለአምባሳደሩ ግርምትን ፈጠረባቸው። ለአንድ ወር ካናዳ ሄዶ ተጨማሪ ስልጠና እንዲያገኙም አመቻቹላቸው። በዚህም ሳያበቁ 50ሺህ ዶላር ድጋፍ እንዲደረግላቸው አደረጉ። ይህ ደግሞ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲሰጡ አገዛቸው።
ሁሌም በሚባል ደረጃ አገራትን እንዲዘዋወሩም ያገዛቸው ይህንን መሰል ቅን ተግባራቸው እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም በተዘዋወሩበት ሁሉ ልምድ ከመቅሰም ባለፈ ያሰለጥናሉ። ንግግርም ያደርጋሉ። ንግግራቸውም « አፍሪካ የእናንተን የገንዘብ ድጋፍ የምትሻው ሁሌ ተረጂ ለመሆን መሆን የለበትም፤ ይልቁንም በራሷ እንድትቆም ለማገዝና ቀጣይነት ላለው መፍትሔ መሆን አለበት ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ስራ ፈጣሪዎችዋን በማገዝ ነው » የሚል ነው። በዚህም በተለያዩ ሃገራት በመጓዝ አፍሪካን ወክለው ተከራካሪ ሆነዋል። ከሚጠቀሱት ውስጥም በ 2016 ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በብራስልስ ያደረጉት ትልቁ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
ቤተሰብ
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት በብላቴ ዘመቻ ወቅት ነው። በህክምና ቦታው ላይ ሲያገለግሉ ታማ መጥታም ነው የተገናኙት። ለሦስት ወር ያህል ክትትል አድርገውላታል። ትውውቃቸውም በዚያው ጠነከረና ስልክ ተለዋውጠው ተለያዩ። አዲስ አበባ ተገናኝተው ግንኙነታቸውን አጠናከሩ። አንስትኤዢያና ማኔጅመንት ሲማሩም የእርሷ እገዛ ነበረበት። ጠብታን ከመሰረቱ በኋላ ደግሞ በህግ ትምህርት ተመርቃ በጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ ውስጥ በማገልገል ላይ ትገኛለች። አሁን በትዳር 23 ዓመታቸው ላይ ደርሰዋል። የአንድ ልጅ አባትና እናትም ሆነዋል። ፍቅርና ደስታንም በአሰቡት ልክ እያጣጣሙት ይገኛሉ።
መልዕክት
ሰው መስጠትን ሲያስብ የሚገኘው ገንዘብ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ነገር ግን ከዚያ በላይ መስጠት በእጁ እንዳለ አያስብም። ለምሳሌ ፍቅርና ጊዜን ምንም አይገዛቸውም። ከገንዘብ የላቁ ናቸውና። እናም ገንዘብን የሚያመጡ ነገሮች ላይ መስጠት እንጂ ገንዘብ ሰጥቶ ተቀላቢ ማድረግ ከመግደል አይተናነስም። ስለዚህም ለሰዎች የምንሰጠው ከስጦታዎች ሁሉ የላቁትን መሆን አለበት። ምክንያቱም ይህ ስጦታ ትውልድንም ያሻግራል። ሰዎች ቀድመው ሲሰጡን እኛ ደግሞ ወደፊት ላሉት መስጠት የምንችለው ነው። የሰጠናቸውም ለሌላ ያስተላልፉታል። ስለሆነም ዛሬ መሰጠት ያለበት እኔን አያጎለኝም፤ አገሬንና ህዝቤን ወደፊት ያሳድግልኛል የሚባልለት መሆን ይኖርበታል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ስሰጥ እንደሚጨመርልኝ ከሰው ሳይሆን ከራሴ ተምሬያለሁ። በዚህም ገንዘብና ሥራን አስተያይቼ አላውቅም የሚሉት አቶ ክብረት፤ ሁለቱን ሳላስተያይ መሞት እፈልጋለሁ ባይ ናቸው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሚመጥኑ መሪዎች፤ የሚያሰሩ ሰዎች ሲኖሩ ነው። አዲስ ሀሳብን እንዴት ላኮላሸው ሳይሆን እንዴት ይጉላ የሚሉ መሪዎች ያስፈልጉናል። ወንድምን የሚያስገድል እዚህ ምድር ላይ ምንም ሳይኖር ለመጣላት መሞከርም መውረድ ነው። እናም የፖለቲካው አስተሳሰብ ጭምር በኢንተርፕሬነር ሽፕ ይፈታልና ይህንን እንጠቀምበት ሲሉም ይመክራሉ።
‹‹አገሬ አባቴ በሰራብኝ ሥራ እኔ ውስጥ ዘላለም ትኖራለች። ሁልጊዜ በብርሃን እንጂ በሟርት እንዳያት አልተደረኩምና ይህንንም አስቀጥላለሁ። ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ይህንን ቢያድጉ እመርጣለሁ። የቀደሙ አባቶቻቸው ልጅ መሆን ለዛሬ አገር ፈውስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። በማንም ብሔርና ሃይማኖት ሳይሆን በአገር መደገፍና መመካት ነው የሚያዋጣው። ምክንያቱም መነጋገር አገር ሲኖር፤ ችግርን በመፍትሄ መቀየርም አገር ስትኖር ብቻ የሚሆን ነው። እናም በውጪ ቱሪስት እንጂ ተሰዳጅ ሳንሆን አገራችንን ወደንና አክብረን እንኑር ሌላው መልዕክታቸው ነው።
ሰዎች ሥራን ለመስራት ሲያስቡ ሶስት ነገሮችን ጠይቀው ለነሱ በሚያገኙት መልስ ላይ ተመስርተው ስራውን ቢጀምሩ መልካ ነው፤ እኔ ይህን ስራ በመስራቴ ሌሎች ምን ይሉኛል ከሚል ወጥተውም ስኬትን ሊያጣጥሙ ይችላሉ። የመጀመሪያው የሚሰሩት ሥራ ህጋዊ ነው ወይ? ሁለተኛው ደግሞ ሞራሌ ትክክል ነው ወይ? በሶስተኛ ደረጃ ያስደስተኛል ወይ? የሚለውን መመለስ ነው።
ጊዜውን ስመለከተው የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን የት አሉ ያስብለኛል። ሰው የሚመዘነው በሚናገረውና በሚኖረው መካከል ባለ ልዩነት ነው። የሚናገረውን የሚኖር የታለ? እኛም በእርሳቸው ሀሳብ ተሰናበትን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም