በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በሁሉም ቦታዎች እየተቀጣጠለ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት ወጣቱ ግንባር ቀደም ነው።መንግስትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩት በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው።ይህም እንቅስቃሴ በዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ነው።የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛል።በተለይ የህብረተሰቡን ችግር ከስሩ ለመፍታት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።በኢትዮጵያ ታድያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስ በርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል።በአገሪቱ የሚሰራ ስራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ።በመንግስትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ስራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፍያና ቅምያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል።ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት።ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው።የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ የሚሉ በርካታ በወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር።አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
ሰው ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት በርካታ አስገራሚ የሆኑ ስራዎችን እንዲያከናውን አድርጎታል።ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ድጋፍ ነው። በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው። በበዓላት ወቅት ከመንግስት ጀምሮ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ድጋፍ ሲደረግ ይስተዋላል።ለዚህ ደግሞ ያለፈውን የትንሳኤ በዓል ማንሳት በቂ ነው።የመንግስት ተቋማት ይሁን ሌሎች ግለሰቦች በዓላትን ብቻ በመጠበቅ ስጦታ መስጠትን እንደ ባህል ይዘውታል።ድጋፍ ማድረጉ ጥሩ ተግባር ቢሆንም ሁልጊዜ አለመቀጠሉ ተረጂውን የከፋ ችግር ውስጥ ይከተዋል።ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት አሁን አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ በሌላ ጊዜ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
የኮቪድ 19 ወረርሽን ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ሁኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አቅም የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳትና ለመደገፍ ብዙ በጎ አድራጎት ማህበራት ተመስርተዋል።ማህበራቱ የእለት የምግብ ድጋፍ ከማቅረብ በተጨማሪ በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እስከማድረስ ተሻግረዋል።ማህበራቱ በወጣቶች የተደራጀ በመሆኑ የደም ልገሳ፣ የከተማ ፅዳት እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ የአቅመ ደካሞችን በስራ እያገዙ ይገኛሉ።በሁሉም ክልሎች በዓላትን ጠብቆ ቤት የማደስ፣ ማዕድ ማጋራት እንዲሁም በዘላቂነት ድጋፍ የሚፈልጉትን በመደገፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ ስራ ሰርቷል።ይህም ስራ ብዙ ወጣቶችን አበረታቶ በአሁን ወቅት ብዛት ያላቸው ማህበራት ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙት የበጎ አድራጎት ማህበራት ድገፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ባላቸው አቅም እርዳታ ቢያደርጉም ከህብረተሰቡ ግን የሚፈለገውን ያክል ተቀባይነት እያገኙ አይደሉም።ህብረተሰቡ ያለውን በአቅሙ እንዲያዋጣ ሲጠየቅ ከመሳደብ እስከ መማታት የደረሰ ሁኔታ እንደሚፈጠር ብዙ ማህበራት እንደ ችግር ያቀርባሉ።ህብረተሰቡም አጭበርባሪዎች በመብዛታቸው ህጋዊውን ማህበር ለመለየት ተቸግረናል የሚል መማረር ያሰማል።ለዚህ ደግሞ መፍትሄው የበጎ አድራጎት ማህበራትና ህብረተሰቡ ተጋግዞ የሚሰራበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
ለዛሬ የመረጥነው በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች በመደገፍ የሚታወቀው በእናት መንገድ በጎ አድራጎት ማህበርን ነው።ማህበሩ የተመሰረተው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም በቻለው መጠን አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች እየደገፈ ይገኛል።ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን እንቅፋቶች ቢያጋጥሙትም ሁሉን ተቋቁሞ ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል።ስለማህበሩ አጠቃላይ የስራ እንቅስቀሴ ከማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት በላይ ደመቀ ጋር ቆይታ አድርገናል።መልካም ንባብ፡፡
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ የተመሰረተው ከአራት ዓመት በፊት ሲሆን ህጋዊ ሰውነት ማግኘት የቻለው ግን በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ነበር።ማህበሩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በችግር ላይ የሚገኙ ህፃናት ላይ ነው።ህፃናቱ ቤተሰቦቻቸው አቅም የሌላቸው ሆነው ነገር ግን በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙ ነው።ተማሪዎቹ ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን የመማሪያ ቁሳቁስ በመግዛት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮችም በየጊዜው እንዲሟሉ ይደረጋል።
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ በ2010 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ስራውን የጀመረው ለአስራ ስድስት ህፃናት ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ ነበር።ለልጆቹ የመማርያ ደብተርና ቁሳቁስ አሟልቶላቸው ነበር።በ2012 ዓ.ም ላይ ደግሞ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ልጆች ወደ 26 በማሳደግ የመማርያ ቁሳቁስ አሟልቶላቸዋል።በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ስራ በመፍታት የተቸገሩትን ህፃናት የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።በተጨማሪም የደብተርና የእስክርቢቶ ድጋፍ ተከናውኗል። በሌላ በኩል በጎዳና ላይ ወድቀው የሚገኙ ህፃናትን ለመደገፍ ከህብረተሰቡ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመጠየቅ ድጋፍ ተደርጓል።
የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ማህበሩ ህብረተሰቡ ግንዛቤ ኖሮት ከበሽታው እንዲጠበቅ የሚያደርጉ ስራዎች ተከናውነዋል።ስራውን ከሌሎች በጎ አድራጎት ማህበራት ጋር በመተባበር እየተሰራም ነው።በሌላ በኩልም የደም ልገሳ እንዲደረግ ስራዎች ተሰርተዋል።ማህበሩ ከአባላት ከሚያገኘው መዋጮ በተጨማሪ ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ገንዘብ የሚያገኝ ሲሆን ከሚኖሩበት ሰፈርም ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመዘዋወር ድጋፍ ይሰበስባሉ።
በጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናት ላይ ማህበሩ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ነበር።በቀጣይ ማህበሩ ወደ ማዕከል መቀየር ሲቻል ልጆቹን በቋሚነት የመርዳት ሀሳብ አለ።አሁን ግን ወደ ጎዳና የወጡበትን ምክንያት በመጠየቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።ሌላው ደግሞ የሚያስፈልጋቸው የአልባሳትና የምግብ ሁኔታን በማመቻቸት ድጋፍ እየተደረገ ነው።ልጆቹን ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በማህበሩ ድጋፍ የሚያገኙ ልጆች ቅድሚያ በአካባቢያቸው ሶስት ምስክር ሲያገኙ በድጋፍ ይታቀፋሉ።በየአካባቢው ችግረኛ ማነው ማነውስ መረዳት ያለበት የሚለውን ሶስት ሰዎች መመስከር ሲችሉ ድጋፍ ይደረጋል።ለተማሪዎቹ ከመማርያ ቁሳቁስ ውጪ የምግብ አገልግሎት የሚያገኙ የተወሰኑ ልጆች አሉ።
የህብረተሰቡ አቀባበል
በአካባቢው የሚገኘው ህብረተሰብ በጣም በደስታ ለማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።የማህበሩ መስራችና አባላት ተማሪዎች በመሆናቸው አሁን ባሉበት እድሜ የበጎ ስራ በማሰባቸው ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እያደረገላቸው ይገኛል።በዚህም የማህበሩ አባላት ባላቸው አቅም እየሰሩ ይገኛሉ።አብዛኛው የማህበሩ አባላት ቤተሰቦች በደስታ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።ሰውን ማገዝ የሁሉም ሰው ፍላጎት በመሆኑ ከቤተሰብ ምንም አይነት ጫናዎች እስካሁን አልመጡም።ማህበሩ አሁን ያለበት ቦታ ለመድረስ ቤተሰብ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉ አስተዋፅኦ አድርጓል።ቤተሰቦቻቸው ለእያንዳንዱ ነገር ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ተመስርቶ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ከገጠሙ ችግሮች ውስጥ ማህበሩ እውቅና ያገኘው ከፌዴራል ሲቪክ ማህበራት ኤጀንሲ በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ችግር አጋጥሟል።በአዳማ ከተማ የበጎ ተግባር ለማከናወን የግድ ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ ተገልፆላቸዋል።በዚህም በክልል ውስጥ መንቀሳቀስ አይቻልም ተብለዋል።ይህ ሁኔታ ችግር እየፈጠረባቸው ሲሆን በክልሉ ውስጥ ፈቃድ ለማውጣት ከፍተኛ ገቢ ያስፈልጋል፡፡
የማህበሩ አባላት ተማሪዎች በመሆናቸው ቋሚ ገቢ የማግኘት እድሉ የላቸውም።አብዛኛው ገቢ ሁሉም አባል ከቤተሰብ ተቀብለው በሚያመጡት የሚሸፈን ነው።ድጋፍ ለሚደረግላቸው ተማሪዎች የሚሆን እንጂ ቋሚ የሆነ ገቢ ማግኘት አልተቻለም።ከህብረተሰቡ ገንዘብ ለመሰብሰብም ይህ ሁኔታ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል።ወጥቶ ከመስራትና ከመንቀሳቀስ መገደብ ውጪ ሌሎች ችግሮች አላጋጠሙም።የማህበሩ የራሱ የሆነ የሚሰራበት ቢሮ የሌለው በመሆኑ ፈቃድ ለማውጣትም ችግር ፈጥሮበታል።አባላቱ በራሳቸው ተነሳሽነት ከፌዴራል ሲቪክ ማህበራት ኤጀንሲ ባገኘው ፈቃድ በተወሰነ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ነው።የቢሮ አለመኖር ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች መጥተው ችግራቸው የሚታይበት ሁኔታ እንዳይኖር አድርጎታል።ቢሮ ተከራይቶ ለመስራት የገቢ አናሳነት ስላለና ባሉት ገቢዎች ድጋፍ ቢደረግ ይሻላል በሚል ትተውታል።
የማህበሩ አባላት ተማሪዎች ቢሆኑም ስራዎችን ለማከናወን የተወሰኑ ችግሮች አሉ።ነገር ግን ስራዎችን ለመስራት አባላቱ አቅም ያላቸው ሲሆኑ በፈቃዱ ጉዳይ መንቀሳቀስ ቢከብድም አሁን ካለው በላይ መስራት ይቻል ነበር።በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሚከብዱ ነገሮች አይጠፉም።የማህበሩ አባላት ያላቸውን አቅም ሙሉ ለሙሉ ተጠቅመውበታል ተብሎ አይታሰብም።
የማህበሩ ቀጣይ እቅዶች
በቀጣይ ማህበሩ ካሰባቸው ስራዎች ውስጥ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ልጆች ቁጥር ማሳደግ ነው።ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም ማህበሩን ወደ ማዕከል በማሳደግ ሙሉ ድጋፍ የሚፈልጉ ልጆችን ለማስገባት እቅድ አለው።ልጆቹ አንድ ላይ ከተሰበሰቡ በስርዓት እንዲማሩ በማድረግ ውጤታማ ስራ ለማከናወን አስቧል።ይህን ለማድረግ ማህበሩ የራሱ የሆነ ቋሚ ገቢ ማግኘት አለበት።እንዲሁም የራሱ የሆነ ቢሮ ኖሮት እራሱን ማደራጀት ሲችል ነው።የተለያዩ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ለቢሮ ኪራይ የሚሆን ገንዘብ በመጠየቅ ላይ ይገኛል።ይህ ከተስተካከለ ሀሳቦችን ማሳካት ይቻላል።ከከተማ አስተዳደሩና ከሚኖሩበት አካባቢ ምንም አይነት ድጋፍ እስካሁን አልተደረገላቸውም።ነገር ግን ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም