ታሪክንና አረንጓዴ ስፍራን ( መናፈሻ) አጣምሮ በያዘው የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ብቅ አልኩ።በፓርኩ ውስጥ በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በ1970ዓ.ም ወራሪው የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን በኃይል ለመያዝ ሞክሮ ነገር ግን በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ድል ተደርጎ መመለሱን የሚያስታውስ ሐውልት ይገኛል። ሐውልቱ ከመንገድ ገባ ብሎ መሰራቱና በአረንጓዴ ልማት የታጀበ በመሆኑ የጎብኝዎችን ቀልብ ይስባል። ውድ አንባቢያን ስለሐውሉቱ ታሪክና ከሐውልቱ ጋር የተያያዘውን በሌላኛው የማስተናገጃ አምዳችን ወይንም ዝግጅታችን ላይ የምንመለስበት ይሆናል። ለዛሬ በአረንጓዴው መናፈሻ ላይ አተኩራለሁ።
የግቢውን የስፋት መጠን በመረጃ ማስደገፍ ባልችልም እንዳየሁት ከሆነ ግን እጅግ ሰፊ ነው። በመሆኑም ትርምስ አይበዛበትም። በውስጡ ለመቆየት ምቹ ነው። ድባቡ ደስ ይላል። በሥፍራው ረፋድ ላይ በደረስኩበት ወቅት አንዱ ሲገባ፣ ሌላኛው ደግሞ ሲወጣ፣ አንዳንዶችም በሐውልቱ ሥፍራ የማስታወሻ ፎቶግራፍ ሲነሱ፣ሻይ ቡናም የሚሉ፣ በአረንጓዴው መናፈሻ ውስጥ ሆነው መጽሐፍ የሚያነቡ፣ ጥንድ ሆነው የግል ጨዋታቸውን የሚጫወቱ፣ብቻቸውንም ሆነው የሚዝናኑ ሰዎችን ነበር ያየሁት።
ሻይ ቡና የሚያስተናግዱ ሁለት አነስተኛ ተቋማትና ግልጽ በሆነ ቦታ የንባብ አገልግሎት ከሚሰጥ አነስተኛ ቤተመጽሐፍት በስተቀር ሁካታ ያለው መስተንግዶ አይታይመ፣ አይደመጥመ።አእመሮና አካልን ዘና ለማድረግ ወደ ፓርኩ ለሚገባው ሰው ምቹ ነው።ከክፍያ ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ተገልጋዩ የፍላጎቱን ያህል ቆይቶ ይወጣል።የቅጥረ ግቢውን ልማት የሚንከባከቡ አትክልተኞችም ያለእረፍት አትክልቶቹን በመንከባከብ፣ቁጥጥር፣ክትትልና ድጋፍ የሚያደርገው ባለሙያም በመዟዟር የእንክብካቤውን ሥራ በማገዝ ሥራቸውን እየተወጡ ነበር።በሌላኛው ወገን ደግሞ የግቢውን ጽዳት የሚጠብቁ ሰራተኞች የጽዳት ሥራውን ተያይዘውታል።እኔም በእግረኛ መንገድ በመጠቀም በፓርኩ ውስጥ እየተዘዋወርኩ ጉብኝቴን ቀጠልኩ።
በፓርኩ ውስጥ በትላልቅ ዛፎች መካከል የተለያየ ቀለማት ያላቸው እጽዋቶች በመደብ ተተክለዋል።የአትክልቶቹ ተንከባካቢ ወይዘሮ ንጹህ ዘሪሁን፤የእጽዋቱን ስም ጭምር በመግለጽ እንዲህ ስለእንክብካቤ ሥራዋ አጫወተችኝ።እርስዋ ተንከባክባ ባለማችው አረንጓዴ መናፈሻ ውስጥ ከሚዝናናው ተገልጋይ በላይ ደስተኛ ናት።ችግኝ ተተክሎ እስኪጸድቅ ድረስ ያለውን ሂደት ስለምትከታተል ሥራውንም ጥቅሙንም ከማንም በላይ እንድትረዳው አድርጓታል።በውበታቸው ትማረካለች።እንደሰውም የማነጋገር ኃይል አላቸው ትላለች።ስሜቷም ከአትክልቶቹ ጋር በመሆኑ እጽዋቱ ሲጸድቅ ትደሰታለች።
ሳይጸድቁ ሲቀሩና ሲጠወልጉ ደግሞ ትናደዳለች።በፓርኩ ውስጥ ተቀጥራ ሥትሰራ ገና አንድ አመቷ ነው።ቀደም ሲል ልምድ ስለነበራትና ስልጠናም በመውሰዷየእንክብካቤ ሥራው ለእርሷ አዲስ አይደለም።የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ መኖሩም በተሻለ እንድትሰራ አግዟታል።በመሆኑም ስለአፈርና ማዳበሪያ አጠቃቀም፣አትክልቶቹ ሲያድጉና ውበት እንዲኖራቸው እንዴ መከርከም እንዳለባቸውና ሌሎችንም ነገሮች ሳይንሳዊ በሆነው የአሰራር ዘዴ ትንከባከባለች።እያንዳንዱ ተንከባካቢ የየራሱ መደብ ሥላለው የተሰጠውን ቦታ ተንከባክቦ የማልማት ኃላፊነቱን ይወጣል።በሥራ ቀናት ከጠዋት ሁለት ሰአት ተኩል እስከ እስከ ምሽት አስራአንድ ሰአት ድረስ ከዕጽዋቶቹ አትለይም።በእርሷ ቦታ ላይ ዱራታ፣ጅራኔ፣ዘባባ፣በስከስ፣ኢበስከስ፣ጽጌረዳ፣አስቴር፣ሲጋሬት የተባሉን ሌሎችም ዝርያዎች ይገኛሉ።ንጹህ ከሥራ ቦታዋ ውችም በምትኖርበት ቤት አከራዮችዋ በደጃፋቸው የተለያዩ እጽዋት እንዲተክሉ በማበረታተም ሙያዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት ጥረት እንደምታደርግና አረንጓዴ ልማት ቢስፋፋ እንደምትመርጥ ሀሳብ ሰጥታለች።
በፓርኩ ውስጥ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንዲሰሩ የተመደቡት በልደታ ክፍለከተማ ተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ጽህፈትቤት የቁጥጥር ባለሙያ አቶ ቢሊሱማ ግርማ ናቸው። ወተር ሪሶርስ ኢንጂነሪንግ ነው የተማሩት። በሥራ ላይ ገና አመት እንኳን ባይሞላቸውም ስለአትክልትና እጽዋት እንክብካቤ በመማራቸው ለሙያው ቅርበት አላቸው። በመሆኑም እጽዋት ተንከባካቢዎቹን በማገዝ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ከችግኝ ተከላ ጀምሮ ጸድቆና ውበቱ ተጠብቆ ለጎብኝዎች ማራኪ እስኪሆን ድረስ ያለውን ሂደት በመከታተል ሙያዊ እገዛ የሚያደርጉት አቶ ቢሊሱማ በፓርኩ ውስጥ ስላሉት የተክል አይነቶችም እንዳስረዱት በፓርኩ ውስጥ ሀገር በቀል ኮርች፣ ወይራ፣ ግራዋ፣ ግራር፣ ዝግባ ባህርዛፍ፣ የሀበሻና የፈረንጅ ጥድ፣ ከውጭ ዝርያዎችም ዋጋቸው ውድ የተባሉ እንደ አሮካራ፣ ቦትልብሪሽ፣ግራቭል ይጠቀሳሉ።የአበባ ዝርያ ካላቸው መካከል ደግሞ ዱራታ፣አ ተርናታ፣ በርነር፣ ምንጣፍና ፈርጥ አበባ፣ ከፍራፍሬ ደግሞ ዘይቱና፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ወይን፣አፕል ጥቂቶቹ ናቸው። እንደ አቶ ቢሊሱማ ማብራሪያ እነዚህ እጽዋቶች በባለሙያ የታገዘ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጥረት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን መረዳት የተቻለው በቂ አፈርና ማዳበሪያ ተደርጎ ጥልቀት ባለው ሁኔታ አልተከናወነም። ይህ ደግሞ አንዳንድ እጽዋቶች እንዲደርቁ ምክንያት ሆኗል። በጥናት ባለመደገፉም ከፍራፍሬዎቹ መካከል በአሁኑ ጊዜ አፕል እያፈራ አይደለም።ጥላ ቦታ የሚፈልጉና የማይፈልጉ እጽዋቶች ተቀያይረው በመተከላቸው ቢቀያየሩ የተሻለ ነው። የደረቁ እጽዋቶችም መተካት ይኖርባቸዋል። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ክረምትን ጠብቆ ችግኝ በማቅረብ ብቻ መከናወን የለበትም። እጽዋት ስላደገ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው የሚከረከመው። በመሆኑም ሙያዊ እገዛ ወሳኝ ነው።
እጽዋቶቹ አሁን ካለው በላይ አብበውና አምረው እንዲታዩ ባለሙያው ለሥራ የሚያስፈልጉ ግብአቶችና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ያስፈልገዋል ያሉት አቶ ቢሊሱማ፣‹‹ማዳበሪያ ከውጭ ማምጣት አያስፈልግም፡: በፓርኩ ውስጥ ጉድጓድ በማዘጋጀት የሚረግፉትን አበቦችና ቅጠሎች በጉድጓዱ ውስጥ በማጠራቀም መጠቀም ይቻላል። ክፍለከተማው ፈቃድና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን ካደረገልን እኛ የተማርነውን ትምህርት በተግባር ማዋል እንችላለን››ሲሉ አስረድተዋል። በክፍለከተማው አመራሮች በኩል ፈጣን ምላሽ አለመኖሩ ግን መነቃቃታቸውን ወደኃላ እንደጎተተባቸው ገልጸዋል። ሥራዎች ከንድፍ ባለፈ ቢተገበሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ተናግረዋል። የተማሩት ትምህርት ገና ከአዕምሮአቸው የወጣ ባለመሆኑ በዘርፉ ብዙ ሙያዊ እገዛ ለማድረግም እርሳቸውን ጨምሮ በተመሳሳይ ሙያ ላይ የሚገኙት ዝግጁ እንደሆኑ ያስረዳሉ።
እነዚህን የሚንከባከቡ በፓርኩ ውስጥ 15 ተንከባካቢዎች፣ ዘጠኝ የጥበቃ ሰራተኛችን ጨምሮ የተለያየ ሥራ የሚሰሩ ሰራተኞች በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ። የጥበቃ ሰራተኞቹ በፓርኩ ውስጥ ጉዳት እንዳይደርስና የንጽህና መጓደል እንዳይኖር በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ይሁን እንጂ በጥበቃ ሥራው ላይ የክትትል ሥራውን አስቸጋሪ ካደረጉት አንዱ የፓርኩ ጥበቃ በመንግሥትና በኤጀንሲ የተቀጠሩ ሰራተኞች መኖራቸው ሲሆን፣ በተለይም በኤጀንሲ የተቀጠሩትን ለመቆጣጠር ችግር ፈጥሯል። ለጥበቃዎች የሚሆን ማደሪያም የለም። እጽዋት ተንከባካቢዎቹ ለሥራ የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች የሚያስቀምጡበት መጋዘን(ስቶር) አለመኖሩ ንብረቶችን ለመጠበቅም አልተቻለም። ለሰርግና ለተለያየ ዝግጅት ከፍሎ ከሚገባው ውጭ ፓርኩ ገቢ የለውም። ፕሮግራም ያላቸው ሰዎችም ክፍያ የሚጠየቁት 1500ብር ብቻ በመሆኑ አነስተኛ ነው። ሐውልቱንና የአረንጓዴ ልማቱን የሚያስተዳድረው አካልም የተለያየ በመሆኑ ወደ ፓርኩ ለሚመጣው የተሟላ ምላሽ ወይንም መረጃ ለመስጠትም ክፍተቶች መኖራቸው አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡ ፡ስለሐውልቱ ገለጻ የማድረግ ኃላፊነት ባይኖራቸውም ለብልሽት እንዳይዳረግ ግን የጥበቃውን ሥራ ይሰራሉ።
በፓርኩ ውስጥ ቆይታ የሚያደርጉ ጎብኝዎችስ ምን ይላሉ? ከእይታ ሰወር ባለ ቦታ በፓርኩ ውስጥ ከተዘጋጀው የድንጋይ ወንበር በአንዱ ጥግ ላይ ተቀምጦ መጽሐፍ ሲያነብ ወደነበረ ወጣት አመራሁ። ሚካኤል ሽፈራው ይባላል።ኮልፌ አጠና ተራ አካባቢ ነዋሪ ነው። ወጣቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውሎውን በኩባ ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ በማድረግ መጽሐፍ ማንበቡን እንደ ልምድ ይዞታል። በግሉም በመንግሥት ተቋምም ተቀጥሮ ለተወሰነ ጊዜ ሥራ ሰርቷል። በተለያየ ምክንያት አሁን በሥራ ላይ ባለመሆኑ አልባሌ ቦታ ከመዋል ከአካባቢው ርቆ መዋልን መርጧል።ምርጫው ደግሞ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ሆኗል።ፀጥታው ነፋሻማ አየሩ ስቦታል።ስሜቱ እንዲረጋጋም አግዞታል።ሀሳቡን ሰብስቦ በእጁ የያዘውን ‹‹ስሜትና አዕምሮ››የሚል ርዕስ ያለውን መጽሀፍ እያነበበ ነበር ተዋውቀን የተጨዋወትነው።መጽሐፉ ሰዎች እንዴት ስሜታዊ እንደሚሆኑና እራሳቸውንም እንዴት መምራት እንዳለባቸው የሚያስተምር በመሆኑ ወጣቱ ራሱን የሚገራበትን መንገድ የሚጠቅመውን ዕውቀት እያገኘ ነበር የሚዝናናው።በፓርኩ ውስጥ ስላለው ሀውልት ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠውና ከሀውልቱ ይልቅ አረንጓዴው እንደሳበው ከጭውውታችን ለመረዳት ችያለሁ።
ውሃ በእጁ ይዞ ብቻውን ከሐውልቱ ፊትለፊት ተቀምጦ ያገኘሁት ወጣት ደግሞ አያና ዘለቀ ይባላል። የሚኖረው አቃቂ ቃሊቲ ክፍከተማ ሲሆን፣ የሥራው ቦታ ደግሞ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ በሚገኝበት አካባቢ የሚገኝ አዋሽ ባንክ ቅርጫፍ ውስጥ ነው። የሻይ እረፍት ሲያደርግ በፓርኩ ውስጥ ማሳለፍን ይመርጣል። ወጣት አያና እንዳለው ሌሎች መዝናኛዎች በሰው ሁካታና ግርግር የተሞሉ ናቸው። የመኪናው ድምጽና ከመኪናው የሚወጣው ጭስም ይረብሻል። ፓርኩ ከዚህ ሁሉ የሚጠብቅ በመሆኑ ደስ ብሎትና አዕምሮውን አድሶ ወደ ሥራው ይመለሳል። ወጣቱ ተወልዶ ያደገው ገጠር በመሆኑ የአረንጓዴ ስፍራን አስፈላጊነት ጠንቅቆ ይገነዘባል። በመሆኑም ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። ከተማ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚታዘበው ነገር ግን አብዛኛው ነዋሪ ለአረንጓዴ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ሆኖ ነው ያገኘው። ፓርኩም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ትኩረት አግኝቶ በንጽህና መያዝ የጀመረውና የሚናፈሱ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ የመጣው። እንክብካቤው መጠናከር እንዳለበትና እርሱን ጨምሮ ለአረንጓዴ ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ ቢመቻች የበኩልን አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ዜጎች እውቀት እንዲገበዩ በማድረግ መጠነኛ ገቢ በማግኘት የንባብ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው አቶ ንዋይ አንዳርጌ በፓርኩ ውስጥ ከታዘባቸው ነገሮች አንዱ ከማህበረሰቡ ባህል ያፈነገጠ ያልተገባ ነገር የሚፈጽሙ ሰዎች መኖራቸውን ነው። እርሱ እንዳለው ከህፃን እስከ አዋቂ ወደ ፓርኩ ይመጣሉ። በመሆኑም የፓርኩን ገጽታ የሚያበላሽ ግንዛቤ ይዘው እንዳይሄዱ መጠንቀቅ እና የፓርኩን ዓላማ መረዳት እንደሚገባ መክሯል።
በፓርኩ ውስጥ በነበረኝ አጭር ቆይታ የፓርኩን ገጽታ የሚያበላሹ ሌሎች ክፍተቶችንም አስተውያለሁ። ትዝብቴን የጀመርኩት ከመግቢያው በር ጀምሮ ነበር። በፓርኩ ውስጥ ሐውልትና አረንጓዴ መናፈሻ ብቻ ሳይሆን፣ ትኩረትን በሚስቡ በተለያየ ቀለማት በኤሌክትሪክ ኃይል ታግዞ ወደላይ እየወጣ የሚመለስ ውሃ ወይንም ፋውንቴንም ይገኛል። ፋውንቴኑ ይሰራ በነበረበት ወቅት በፓርኩ ውስጥ ከሚገኘው አረንጓዴ ጋር ልዩ ድምቀት ነበረው። በተለይም ምሽት ላይ ልዩ ውበት እንደነበረውና በቅርቡም ለተወሰነ ጊዜ ማየታቸውን አንዳንዶች ያስታውሳሉ። በበሩ መግቢያ ላይ የሚገኘው ይህ ፋውንቴን ለፓርኩ ድምቀቱን እየሰጠ አይደለም። ምክንያቱን የሚነግረኝ ሰው አላገኘሁም። ፋውንቴኑ በሚገኝበት ሥፍራ የተጠራቀመው ውሃ ወደ ሽታ የሚያመጣ ወደ አረንጓዴ ቀለም ተለውጧል። ንጽህናው የተጓደለው ውሃ ለአካባቢ ብክለትና እንደ ወባ ላለ የጤና ችግር የሚያጋልጥ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ የቁሳቁሶች ክምርም በሐውልቱ ጀርባ ተከልለዋል። ቆሻሻው የተከለለ ይመስላል እንጂ በአረንጓዴ ሥፍራው ውስጥ ከሚናፈሰው እይታ ውስጥ አይደሉም። የሻይ ቡና መሥተንግዶ የሚሰጡት ተቋማትም ለማብሰያ የሚውሉ እንደከሰልና ሌሎችም የሚጠቀሙባቸውንና የሚያመነጯቸው ቆሻሻዎች ከእይታ ውጭ አይደሉም።
ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታልን ጨምሮ በፓርኩ በስተጀርባ የሚገኙት የተለያዩ ተቋማት በአካባቢያቸው አረንጓዴ ሥፍራ በመኖሩ ተጠቃሚዎች ናቸው። በአካባቢው ብዙ ተሽከርካሪዎች የሚያልፉ በመሆናቸው ከመኪኖቹ የሚወጣውን በካይ ጭስ ለመከላከልም የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ ነው። የእግረኛ ፍሰቱም ሰፊ በመሆኑ ጎራ ብሎ ንጹህ አየር ለመቀበል ምቹ ፓርኩ የሚገኝበት ቦታ ምቹ ነው። በፓርኩ ፊትለፊት በስፋት በተሰራው የእግርኛ መንገድ በአካፋዮች ላይ የተለለያዩ ችግኞች ተተክለው ተጨማሪ ውበት ሆነዋል። ውበቱ በመልካም የሚገለጽ ቢሆንም የመኪና ማቆሚያ በአካባቢው ባለመኖሩ ፓርኩን መጎብኘት ለሚፈልጉ የመኪና ባለቤቶችን ማዕከል ያደረገ እንዳልሆነ ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎችም አጋጥመውኛል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2013