ኢትዮጵያን በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስክ በማበልጸግ ከድህነት አዙሪት በማውጣት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ማሰለፍ…..”አገራችን በአሥር ዓመት የብልጽግና ዕቅድ ከያዘቻቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው ።በዚህ ምዕራፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ሁለት የተለያዩ ተልዕኮዎች ይኖሩታል ተብሎ ተቀምጧል። የመጀመሪያው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ በኢንዱስትሪው ፍላጎት ላይ በመመስረት በመካከለኛ ደረጃ የበቃ በሙያው የሚተማመን የሰው ኃይል በጥራትና በመጠን ማፍራት።ሁለተኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሥራችንን ውጤታማ ማድረግ ነው። ለዚህ እቅድ መሬት መውረድና በተግባር መገለጥ ለቴክኖሎጂ ያለው አተያይና ትኩረት ትልቁን ቦታ የሚይዝ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት በተለይ ቴክኖሎጂን የመቅዳትና የማሸጋገር አቅማቸው እና ብቃታቸው ጥሩ ቁመና ሊኖረው እንደሚገባ ይታመናል ።ገበያው የሚፈልገውን የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና ስትራቴጅ እንዲሁም በአሰራር ስርዓቱ ላይ የማሻሻያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ከዚህ ባሻገር በአሰልጣኞች፤ በሰልጣኞች እና አንቀሳቃሾች መካከል የክህሎት ውድድር ማካሄድ ይገባል።ይህም የስራ ተነሳሽነታቸውንና ክህሎታቸውን በማጎልበት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸውን ማሳደግ እንዲቻል በማድረግ ረገድ ትልቅ ውጤት ያመጣል ።በዚህ ረገድ ያለውን እውነታ ደግሞ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ይነግረናል።የሀገራችንን ቁመና ስንመለከት እስከ አሁን ሰፊ ሥራ ቢሰራም፤ በተሰራው ስራ ቴክኖሎጂን የመቅዳትና የማሸጋገር አቅም በሚፈለገው ደረጃ ማድረስ አልተቻለም የሚሉ ትችት አዘል አስተያየቶች ይሰማሉ ።ይሄም የአሥር ዓመት የብልጽግና ዕቅዱን ለማሳካት ትልቅ ፈተና ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ይፈጥራል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ የ2013 ዓ.ም የቴክኖሎጂ፣ ክህሎት፣ ካይዘን እና ተግባር ተኮር ጥናትና ምርምር ውድድርና ሲምፖዝየምን ለማስፈጸም በተዘጋጀ አንድ የጋራ ዕቅድ ላይ እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን በዝርዝር በማቅረብ ስጋቱ ተገቢነት ያለው ስለመሆኑ ያረጋግጥልናል። በእቅዱ እንደተብራራው፤በሀገራችን የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂውን የመፍጠርና ማሻሻል የሚችል የሰው ሀይል ማፍራት ይገባል ።በዚህ አቅጣጫ መሰረት በ2011 ዓ.ም ውድድር መድረክ የቀረቡና በ2012 ዓ.ም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የተቀዱ ቴክኖሎጂዎች የሚያበረታቱ ቢሆኑም ሀገራችንን ከችግር ሊያወጣ የሚችል ቴክኖሎጂ በታሰበው ልክ መቅዳት አልተቻለም፡፡ቴክኖሎጂን መቶ በመቶ መቅዳት ያልተቻለባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።
˝በዋነኝነት የሚጠቀሱት ችግሮች፤ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት፣ ለቴክኖሎጂስቶች ግልጽ የሆነ የማበረታቻ ስርዓት አለመኖሩ፣ የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው በታቀደና በተደራጀ ሁኔታ አለመስራት። የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ለህዝብ ይፋ ማድረጊያ መድረኮች አለመመቻቸታቸው። ባለሙያዎች ለሰሩት ስራና ለአበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት አለመቻሉና የተቀዱ ቴክኖሎጂዎችን ለምርትና አገልግሎት የሚውሉበት ስርዓት አለመኖር ናቸው ሲል ሰነዱ ያትታል። ቴክኖሎጂን መሰረት አድርጎ የተቀመጠውን ሀገር አቀፍ እቅድ ወደ ስኬት መለወጥ የሚቻለው በቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላቱን ሰቅዞ ከያዙት ችግሮቹ ማላቀቅ ከተቻለ እንደሆነ እሙን ነው።
በዚህ ረገድ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንዳመላከቱት ፤የተጠቀሱትን ጉድለቶች ለማሻሻል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣ ልዩ ክህሎት ያላቸውንና ቴክኖሎጅስቶችን በማበረታታት ቴክኖሎጂ የመቅዳት አቅማቸውን ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው።በተጨማሪም የተቀዱ ቴክኖሎጂዎችን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ለአብዥዎች ለማስተዋወቅና ወደ ምርት ለመቀየር በየደረጃው የቴክኖሎጂ ውድድርና ሲምፖዚየም ማካሄድ አስፈላጊነት በመነሻነት መወሰዱን ያመላክታሉ፡፡ከሚያዝያ 12 እስከ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለ ሁለተኛ ጊዜ ሀገር አቀፍን የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር እና ሲንፖዚየም ይሄንኑ መሰረት ያደረገ መሆኑን ያመለክታሉ ።
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ ፤በአሰልጣኙ፣ በሰልጣኙና በአንቀሳቃሾች መካከል ጤነኛ የውድድር መንፈስ በመፍጠር ቴክኖሎጂ የመቅዳት አቅምን ማሳደግ የውድድሩ ዓላማ መሆኑን ነው ። ይህም በመላው ህብረተሰብ ዘንድ ስለሙያ ተገቢው ግንዛቤ እንዲያዝ እና በዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት መካከል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እንዲፈጠር ያግዛል ።በተጨማሪም ስራዎቻችንን በህዝብ ንቅናቄ አጅበን ከተጓዝን የቀጣይ አሥር ዓመት እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል አቅም መኖሩን አመላካች ነው ። ቴክኒክና ሙያ ቁልፍ የልማት መሳሪያና የኢንዱስትሪ መሰረት ነው የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራር ይጠይቃል̋̋̋˝ያሉት ዳይሬክተሩ ፤ስለዚህ የኢኖቬሽን እና የምርምር ስርዓቱ ተዋናዮች በመመጋገብ ስራዎችን ማከናወን ከተቻለ የተቀመጠው ግብ የማይሳካበት ምክንያት ይኖራል ብሎ ለማመን አዳጋች መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
“ሀገራዊ ራዕያችንን ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ራዕይና ተልዕኮ ጋር አሰናስሎ ለዕቅዱ ስኬት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ብቁና በቂ የሰው ሃይል ማፍራት ከቴክኒክ ትምህርት ሥልጠናው ዘርፍ ይጠበቃል” ያሉት ደግሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስተር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ናቸው ።ዘርፉ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘርፉን በልዩ ትኩረት ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ መሆኑንም ያስታውቃሉ። ስለዚህ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ከምርምርና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውጤታማ ትብብርና ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ ልዩ ትኩረት በተሰጣቸው የሙያ መስኮች ቢያንስ 75 በመቶ የተግባር ሰጪ የልህቀት ማዕከላትን እየገነባ የሚገኝም መሆኑንም ነው ያብራሩት።
በአጠቃላይ የኢኖቬሽን እና የምርምር ስርዓቱ ተዋናዮች ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ በማላመድና በመጠቀም ረገድ ተቋማቱ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላት የሚገባቸውን ድጋፍ አለማድረጋቸው ክፍተቶች የተፈጠሩ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።ሚኒስቴሩ የስርዓቱ ተዋናይ ከሆኑት ተቋማት ጋር ውጤታማ ትብብርና ትስስር መፍጠር የሚያስችል ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እቅድ መያዙ በአንድ በኩል በኢኖቬሽን እና የምርምር ስርዓቱ ተዋናዮች የተቀናጀ አሰራር መፍጠር የሚያስችላቸው ይሆናል።በሌላ በኩል ደግሞ ተቋማቱ በጥናት፤ በዲዛይን እንዲሁም አዋጭ ቴክኖሎጂ በመምረጥና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለተጠቃሚዋች ማሸጋገር ያስችላል የሚል እምነት ያሳደረ ሆኗል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013