በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪና የኢትዮጵያ የድርድር ቡድን የህግ አማካሪ ናቸው። የግብጽ አምባሳደርም በመሆን ለኢትዮጵያ በርካታ ሥራ ከሰሩ መካከል ይጠቀሳሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባገለገሉባቸው ጊዜያት ብዙ አበርክቶን ያደረጉም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። በተለይም የሰላም ማዕከሉን በመመስረትና ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጀመረውን አፈርማቲቭ አክሽን ያስጀመሩ በመሆናቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል።
በፓርላማና በመከላከያ ጭምር አገልግሎት ላይ እንዲውል ያደረጓቸው መጸሐፍቶችም ስማቸውን ከሚያስጠሩት መካከል ናቸው። በሌላ በኩል በአማካሪነት የሰሩባቸው አለማቀፍና አገራዊ ተቋማትም ሁልጊዜ የሚያመሰግኗቸው አይነት ሰው በመሆናቸው ተሞክሯቸው ለብዙዎች ልምድ ያጋራልና ለዛሬ የ‹‹ ህይወት ገጽታ›› ዓምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስን። ስለዚህም ከተሞክሯቸው ተማሩ ስንል ጋበዝናችሁ።
ልጅነት
ተወልደው ያደጉት የሰላም ከተማ፣ ሀይማኖት፣ ብሔር ልዩነት የሌለባት ተብላ በምትጠቀሰው ወሎ ክፍለ አገር ደሴ ፒያሳ ውስጥ ነው። በዚህች የአንድነት ከተማ ውስጥ ልጅነታቸውን ብቻ ሳይሆን ዛሬያቸውን ሰርተዋል። መከባበርና አንዱ አንዱን መርዳትን ተምረዋል። በተለይ በዓላት ሲመጡ ያለውን ድባብ መቼም አይረሱትም። ምክንያቱም መረዳዳቱ ብቻ ሳይሆን አብሮ መጫወቱም አለ። አብሮ መብላትና መጠጣቱም እንዲሁ ልዩ ትዝታ የሚፈጥር ነው። አንዱ የአንዱ ነገርን አክብሮ ብቻ ሳይሆን ኖሮበትም ነው የሚያሳልፈው። እናም እርሳቸውም በክርስቲያኑ ባህል ጭምር ኖረው አድገዋል። እንደውም የማይረሱት በዓል ጭምር እንዳለ ያነሳሉ። ከእነዚህ መካከል የቡሄ ጨዋታ ልዩ ስሜት የሚሰጣቸው ነው። ልመናው እንኳን ሳይቀየር በእስላም ክርስቲያኑ ቤት መሆኑ የሁልጊዜ ትዝታቸው ነው።
ፋሲካም ቢሆን እንዲሁ ልዩ ጣዕም ያለው እንደነበር ያስታውሳሉ። ለክርስቲያን ጓደኞቻቸውም መውሊዱና አረፋው ልዩ ስሜት ሰጥቷቸው ያሳልፉት እንደነበር አይረሱትም። ምክንያቱም ማስተማር ያለበትን ሀይማኖታዊ ትምህርት ከመንገር ውጪማንም እናት አባት እዚያ ቤት አትሂድ፣ የአንተ ሀይማኖት አይደለም አይልም። በዚህም ሁሉም ልጅ ልዩነቱ ሳይሆን አንድነቱ ጎልቶበት ነው ያደገው።
በጓደኛ ደረጃ፣ በቤት አቀማመጥና በቤተሰብ ሁኔታ በደሴ የሚኖር ህዝብ ሙስሊምም ክርስቲያንም ነው። ስለዚህም በሁለቱም ባህል፣ ሀይማኖት እንዲሁም መተሳሰብ ነው የሚታደገው። እንግዳችንም ይህ እየሆነላቸው ነው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት። እንደውም ዛሬ ድረስ ያሏቸው ጓደኞች ከሁለቱም ወገን ያሉ መሆናቸውን አጫውተውናል።
‹‹ደሴ ላይ የሚያድግ ልጅ ቤተሰቡ ጭምር ከክርስቲያን የተጋባ ነው። እናም እኔም ይኸው ልዩነት ያለብኝ ነኝ። ከፍ ብሎ ሲጠራ ብዙ ክርስቲያን ዘመዶች አሉኝ። በዚህም እነርሱ ጋር ስሄድ ሁሉ ነገሬን አክብረው የምፈልገውን እያደረጉልኝ ቆይተው ነው የምመለሰው›› ይላሉም። እናም እስልምና እና ክርስትና ልዩነት ሳይሆን ፍቅር እንደሆነ ነው የሚያውቁት። ደሴ የኢትዮጵያ የንግድ ከተማ ስለነበረችም ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ሰዎች በመሰባሰባቸው ምክንያት የተለያዩ ባህሎችን እንዲያውቁ እንዳገዛቸውም አይረሱትም። ይህ እድል ደግሞ ዛሬ ድረስ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያበረታላቸው እንደሆነም አጫውተውናል።
ልጅነታቸውን ሲያስቡት መጀመሪያ የሚመጣላቸው ሰርግ ቤት የሚሆነው ነገር ነው። መከባበሩና በጋራ መብላቱ ልዩ ትዝታን ይፈጥርላቸዋል። ምክንያቱም በዚህ ቦታ ክርስቲያኑና ሙስሊሙን የሚለየው የምግቡ አይነት ብቻ ነው። ተሰባስቦ በህብረት መብላቱ የተለመደ ነው፤ አብሮ መጨፈሩና ስርዓቱን ማድረጉም እንዲሁ በአንድነት የሚሆን ነው። ይህም ኢትየጵያዊነታቸውን እንዳጠነከረላቸውና የአገር ፍቅር ጉዳይ የማይደራደሩበት እንዲሆንላቸው አስችሏቸዋል።
እንግዳችን በባህሪያቸው የያዙትን ተስፋ ሳይቆርጡ መጨረስ የሚወዱ፣ በጨዋታ ደግሞ ከሁሉም ጋር መጫወት ምርጫቸው የሆነ ናቸው። በተለይ ኳስ መጫወት የተለየ ትኩረታቸውን ይስበው ነበር። ሆኖም ፀሐይ ሲነካቸው ይነስራቸዋልና ብዙም አይዳፈሩም። ከዚያ ይልቅ ብዙ ጥላ ወደሚኖርበት መዝናኛ ቦታ መሄድና በዚያ ማሳለፍ ይመርጣሉ። ስለዚህም ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ዘና የሚያደርጉት ፊልም በማየት ነው። ማንበብ እንዲሁ ያዘወትራሉ።
ቤተሰቦቻቸው ነጋዴ ሲሆኑ፤ እርሳቸውም በዚያ ሙያ እንዲቀጥሉ ይፈልጉ ነበር። ነገር ግን እናታቸው ከዚህ የተለየ አቋም አላቸው። መማር ሰውን ይለውጣል ብለው ያምናሉ። ስለዚህም ከንግዱ ይልቅ ትምህርታቸው ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉ ያግዟቸዋል። በትምህርታቸውም ጎበዝ የመሆናቸው ምስጢር እናታቸው እንደሆኑ ይናገራሉ።
እንግዳችን ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ አየር ሀይል ውስጥ መግባት የሚፈልጉ ሲሆን፤ ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ሁሉም በአካባቢው ያሉ የጸጥታ አካላት በስብዕናቸው፣ በአለባበሳቸውና ተግባራቸው ይመስጧቸው ስለነበረ ነው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ሰባተኛ ክፍል እንደደረሱ መልማዮች ሲመጡ ለመሳተፍ ራሳቸውን አስመዝግበው እንደነበር አይረሱትም። ሆኖም እናትም ሆነ አባት ትምህርትህ መጀመሪያ ይለቅ ስላሏቸው ትተውታል። ከዚያ ጂኦግራፊ መማር ህልማቸው ነበር። ምክንያቱም ተፈጥሮ ወዳድ ናቸው። ጠበቃ መሆንም ፍላጎታቸው እንደነበር ያነሳሉ። ህልማቸው የተቋጨውም በዚህ ነበር።
ከመድረሳ እስከ አዲስ አበባ
ከትምህርት ጋር የተገናኙት የሀይማኖት ትምህርት ቤት በሆነው መድረሳ ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ሲሆን፤ በአማርኛና በዓረብኛ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከዚያ ወደ ዳውዶ ወይም ቅዳሜ ገበያ እየተባለ ወደሚጠራው ትምህርትቤት ተዛወሩ። በዚህም ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ተማሩ። ቀጥለው ትምህርታቸውን የተከታተሉበት ቦታ ወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትና ከፍተኛ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑት ትምህርትቤትም ነው።
እስከ 12ኛ ክፍል በትምህርት ላይ ሳሉ የደረጃ ተማሪ ሲሆኑ፤ በዚህም የሙያ ትምህርቶችን በመተው ቀለሙን መርጠው እንዲማሩ ሆነዋል። ይህ አቅም ባይኖራቸው ኖሮ በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ መግባትን እንደማያስቡትም ያስታውሳሉ። ስለዚህም ጉብዝናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል። በበፕራይቬት ኢንተርናሽናል ሎውም ትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሰሩም ሆነዋል። ከዚያ በኋላ ያለው የትምህርት ጉዟቸው በምርምር ስራ ላይ የቀጠለ ሲሆን፤ በምርምር ስራቸው ብዙ ልምዶችን እንደቀሰሙ ይናገራሉ። የምርምር ሥራው የተለያዩ የስልጠና እድሎችን ስለሚሰጥም ሁልጊዜ ተማሪ እንደሆኑበትም ያወሳሉ። ለዚህም በአብነት የሚያነሱት ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘም የውጪ እድል አግኝተው በአሜሪካ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት አንዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
20፤ 20ን በሥራ
ከምረቃ በኋላ መጀመሪያ መስራት የጀመሩት በመንግሥት እርሻ በአዋሽ እርሻ ኮርፖሬሽን ውስጥ በአማካሪነት ሲሆን፤ ቀጥለው ወደ ምዕራብ እርሻ ኮርፖሬሽን በመዘዋወር መስራት ችለዋል። በዚህም አማካሪነታቸውን ሳይለቁ በቦታውም ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ ከገንዘብ በላይ እውቀቱ የተለየ ነገር እንደሆነ በማመናቸው ሥራውን ትተው በዚያው በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ደሞዛቸውን ቀንሰው ለማስተማር ገቡ። የመጀመሪያው 20 ዓመትም የጀመረው በዚህ ዩኒቨርሲቲ ነው። እናም በዩኒቨርሲቲው መጀመሪያ በማስተማር፤ ከዚያ በመመራመርና በማማከር ሥራ ቀጠሉ።
ረዳት ፕሮፌሰርነት ሲሰጣቸው ደግሞ የበለጠ ሥራቸውን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለማቀፍ ደረጃም በውጤታማነት አሳይተዋል። ከእነዚህ መካከልም በዓለም ደረጃ ምንም አይነት ስብሰባ ካለና ኢትዮጵያ ትወክል ከተባለ እርሳቸው ተመርጠው እንዲሄዱ መሆኑ አንዱ ነው። በተመሰሳይ ሄደው መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ወረቀት እስከማቅረብ የሚደርሱ ሥራዎችን ይሰራሉ። በተለይ በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልዩ ሥራዎችን በማቅረብ ብዙዎች ያደንቋቸዋል። እነዚህም የጦርነት ህግ፣ ሰብዓዊ መብትና በስነዜጋና ስነምግባር ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። የግል አለማቀፍ ህግ ላይም ጥሩ የሚባሉ ሥራዎችን ያቀርቡ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲ ስራቸውን እንደቀጠሉ ጎን ለጎን በኢንተርናሽናል ሬድ ክሮስ ሙቭመንት ውስጥ ለ16 ዓመት ያህል ማገልገል ችለዋል። ከዓለማቀፍ ቀይመስቀል ጋር በመሆን የጦርነት ህጎችን ከማውጣት ጀምሮ የደረሱ ሥራዎችንም ሰርተዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ዋና የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከተው በመሆን ነው። በዚህም በዓለማቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚመለከት ጉዳይ ላይ የሚሳተፉ አድርጓቸዋል።
በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተጋበዙ በግለሰቦችና በአገራት መካከል ፣ በአገራትና በአገራት መካከል የሚደረጉ ክርክሮችን በጠበቃነት ሲያግዙም ነበር። በስራው ከአምስት ዓመታት ካሳለፉ በኋላም በዚያው በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ሆነው ወደማገልገሉ ገቡ። ከአራት ዓመት በላይም በቦታው እንዳገለገሉ ሥራቸው እየላቀ በመምጣቱ የዩኒቨርሲቲው የህግ አማካሪ በመሆን እንዲሰሩ ተደረጉ። የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባል፣ ዋና ሥራአስፈጻሚም አባልና የፕሬስ ክፍሉ የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋልም።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከሰሩት ሥራ ያረካኛል የሚሉት ሥራቸው ብዙ ቢሆንም ጥቂቶቹን አንስተውልናል። ከእነዚህ መካከልም የሰላም ማዕከል ማቋቋማቸው አንዱ ነው። ሌላው በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማሰባሰብም መምህራን ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ምርምሩ የሚጠናከርበትን እንዲሁም የህግ ትምህርት ክፍሉ በመጽሐፍት የሚደራጅበትን ሁኔታ ፈጥረዋል።
እንደውም የህግ ክፍሉ ቤተመጽሐፍት የተደራጀውና ወደ 12ሺህ መጽሐፍት የገባበት እርሳቸው በነበሩበት ጊዜ መሆኑ ያስደስታቸዋል።
ቶይፕ የሚባል ድርጅትም አቋቁመውም እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ማለት ትሪያል ኦብዘርቬዥን ኤኒ ኢንፎርሜሽን ፕሮጀክት ሲሆን፤ ዋና አላማውም ፍትሀዊ ዳኝነትን ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ያነሳሳቸው በደርግ ጊዜ የነበሩ አባላት በኢህአዴግ መንግሥት ታስረው ስለነበር ብዙ ፍትህ እየተጓደለባቸው ስለነበር ትክክለኛ ፍትህ እየተሰጠ ነወይ የሚለውን ለማጥናት የሚሰራ አካል በመፈለጉ የተቋቋመ ነው። ከፕሮፌሰር እንድርያስ ጋር በመሆን ተማሪዎችን እየያዙ መስራት ጀመሩ። ወደ አምስት ዓመት የፈጀ ፕሮጀክትም እንደነበር ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ አፈርማቲቭ አክሽን ፕሮግራም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲጀመርም ያደረጉ ናቸው። አካባቢውን በአካባቢው ተማሪ ማገዝ ካልተቻለ ከሌላው ማህበረሰብ እኩል በልማት ማሳተፍ አዳጋች በመሆኑ ዋና አላማውን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በተለይ ታዳጊ ክልሎች የሚባሉት ላይ የትምህርት ሁኔታውን ማስፋፋት አድርጎ መስራት ጀመረ። ስለዚህም ከቦታዎቹ ላይ ተማሪዎችን በማምጣትና ተጨማሪ በማስተማር ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተምረው ለአካባቢያቸው እንዲበቁ ማድረግም ነው። የመጨረሻው የትምህርት ደረጃ 10ኛ ክፍል ስለነበር ከዚህ ክፍል መልምለውም ከሁሉም ታዳጊ ክልሎች 100 ተማሪዎችን በመምረጥ ትምህርት እንዲሰጥ አደረጉ። ይህም የወደዱት ሥራቸው እንደሆነ አጫውተውናል።
በዓለም ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች አስቸጋሪ እንደሆኑ ሲታሰብ ሁሉንም አንድ የሚያደርገው ባህላዊ ህጎች ቢሰባሰቡ እንደሆነ ታመነበት። በዚህም አለማቀፉ ቀይመስቀል ባህላዊ የጦርነት ህጎች ይሰባሰቡ ብሎ ውሳኔ አሳለፈ። ይህንን እውን ያደርጉታል ተብሎ የታመነባቸው 56 ሰዎች ከሁሉም አገራት ሲሰባሰቡ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት እንግዳችን ነበሩ። በዚህም ሥራ ስድስት ዓመታትን አሳልፈዋል። ወደ 10 ሺህ ገጽ የያዘ መጸሐፉን በጋራ አዘጋጅተውም በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥበት ካደረጉ መካከል መሆናቸውም የተደሰቱበት ሥራቸው ነበር።
በተመሳሳይ በ1975 ዓ.ም መንግሥት የኢትዮጵያ ህጎችና መጽሐፍቶች መቀየር አለባቸው ባለው መሰረትም እርሳቸው አንዱ ሆነው ተሳትፈዋል። በተመራማሪነት ስለነበር የሚያገለግሉት ግማሽ ፍታብሔር ህጉን እንዲሻሻል ካደረጉ መካከል ሆነዋል። ይህ ሥራም አራት ዓመታትን አንደፈጀ ያስታውሳሉ። ፕራይቬትና ናሽናል ሎ የሚባል አዲስ ህግ አዘጋጁ ተብለውም አዘጋጅተዋል። የማስረጃና ውል ጉዳይን የሚመለከት አዋጅም ካዘጋጁት ውስጥ ይገኙበታል። ከእነዚህ ስራዎች ጎን ለጎን በአማካሪነትም ይሰሩ ነበር። ይህ የሚሆነው ደግሞ በአገር ውስጥም በውጪ አገርም ሲሆን፤ ለዓለም አቀፍ መንግሥታቶች ጭምር ያማክራሉ። ለአብነትም ለካናዳና ለኦስትሪያ መንግሥት እንዲሁም ለዓለምአቀፉ ቀይመስቀል አማክረዋል። እንደ አውራጎዳና አይነት የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ክርክር ሲኖራቸውም የህግ ጉዳዩን በመያዝ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አማካሪነታቸው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በነጻም ጭምር ነው። ለዚህም ማሳያው ሁለት የመንግሥት ተቋማት የህግ አማካሪ ስላልነበራቸው እርሳቸው ሲያማክሯቸው እንደቆዩና ጥሩ የሚባል ሥራ እንደሰሩባቸውም ይናገራሉ። እነዚህ ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴርና ፓርላማው ናቸው። ለተቋማቱ የሰሩትን ዋና ዋናዎቹን ብናነሳ ለፓርላማው ከኦስትሪያ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ የህግ መጽሐፍትን በማዘጋጀት አሁን ድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል። ለትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ኮሌጆቹ ወደ ዩኒቨርሲቲነት እንዲያድጉ ያደረጉበት በዋናነት ይጠቀሳል። ለዚህ መነሻ የሆናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የነበሩ ኮሌጆች ሲሆኑ፤ ለእነርሱ የህግ ማዕቀፍ እንዲያወጡ ታዘዙ። ይሁንና እርሳቸው ይህንን አላደረጉም። ከዚያ ይልቅ በረቂቅ አዋጅ አቋቁመዋቸው መጡ። ይህ እንዲሆን አልፈለግንም ሲሏቸውም ኮሌጆቹ ነገ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ዳግም ፓርላማ ማየት አለበት። አዋጅ ከሆነ ግን አንድ ጊዜ ብቻ ስለሚታይ አያስቸግርም በማለት አሳምነዋቸው ሀሳባቸው እንደጸደቀ አይረሱትም። በዚህም ለጅማ ለመቀሌ፣ ለባህርዳርና ሀዋሳ የሚሆን ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያድጉበትን መንገድ አመቻችተዋል።
ሌላው ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ሳይለቁ የሰሩት ሥራ አፈርማቲቭ አክሽን በጀመሩበት ወቅት የስራውን ውጤታማነት የተመለከቱ የመንግሥት አካላት ከሁሉም ክልል ተማሪዎች ተመልምለው እርሳቸው ህግ አስተምረው እንዲያስመርቁላቸው የጠየቋቸውና ሀሳቡ እንዲቀየር ያደረጉበት ነው። በግል አስተምሮ ከሰርተፍኬት እስከ ዲግሪ ድረስ መስጠት አይቻልም። ይህንን የምትፈልጉ ከሆነ እንደ ሌሎች አገራት የአስተዳደር ኮሌጅ እንዲከፈት አድርጉ አሏቸው። ይህ አማራጭ መልካም መሆኑን የተረዱትም የመንግሥት አካላት ሀሳቡን መነሻ አድርገው የአሁኑ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ እንዲቋቋም አደረጉ። እርሳቸውም በብዙ ነገር አገዟቸው። መጀመሪያ ትምህርቱ የሚሰጠው በህግና ምህንድስና ስለነበርም ከመጽሐፍት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን እንዲያገኙ አድርገዋል።
ዓለማቀፍ መጽሄቶች ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያሳተሙ ሲሆን፤ አምስት አካባቢ እንደሚደርሱ ይናገራሉ። ህትመቶቹም በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትምህርት እንደሚሰጥባቸው ያነሳሉ። ከዚህ በተጓዳኝ መጽሐፍትም ለንባብ አብቅተዋል። በአብዛኛው ግን ለማስተማሪያነት የሚያገለግሉ ናቸው። ለአብነትም አሁን የምንጠቀምበትን የጦርነት ህግ ማለትም አራቱ የጄኒቫ የጦርነት ህጎች የሚባሉትንና ሁለት ፕሮቶኮሎችን ወደ አማሪኛ በመተርጎም አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጉት እርሳቸው ናቸው።
ሁለተኛው 20 ዓመት የጀመረው በጣም ትልልቅ ችግሮች አገሪቱ ላይ በመደቀናቸው እርሳቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ በተዛወሩበት የውጪ ጉዳይ ነው። በቦታው ሲገቡ ብዙ ተደራራቢና አዳዲስ እንዲሁም ከባድ ጉዳዮች እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እነዚህም የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ችግር፤ ከኤርትራ ጋር ያለው የፍትሐብሔር ክርክሮች ፤ በግብጽ፣ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው የናይል የውሃ ጉዳይ፤ የድንበር ጉዳዮችና የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ ይውጣ ክርክሮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ስለዚህም እነዚህን እውን ለማድረግ ብዙ ስራዎችን ይጠይቅ ነበርና ጠንካራ ትግል እንዳደረጉ ይናገራሉ።
በውጪ ጉዳይ መጀመሪያ ሲገቡ እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን የሚያስችላቸው ቦታ ላይ ነበር የተቀመጡት። ስለዚህም የዓለማቀፍ ህግ ዳይሬክተር ጀነራል በመሆን ሲሆን፤ የህግ ዳይሬክቶሬት ጀነራሉን በማደራጀትና የሰው ኃይሉን በማጠናከር የተሻለ ሥራ እንዲሰራ አድርገዋል። ሌሎች ሥራዎቻቸውን ጭምር እየሰሩም በቦታው ለአራት ዓመት ያህል አገልግለዋል። የዓባይና ሌሎች የኢትዮጵያ ወንዞች የሚኒስትሩ አማካሪም ነበሩ። ከዚያ አምባሳደር ሆነው ወደ ግብጽ ያመሩ ሲሆን፤ በዚያም ከአምስት ዓመት ያላነሰ ጊዜ አሳልፈዋል። ይህ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የፈተና ወቅት እንደነበር አይረሱትም። ምክንያቱም ሌሊት ሳይቀር በሥራ ያሳልፋሉ። መስራታቸው ቢያስደስታቸውም አንዳንዴ ውስጡ አያስደስታቸውም። በተለይም ትክክለኛ ቪዛ አግኝተው የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በየጊዜው ንትርክ የበዛበት ነው።
ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸውና ዳግም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ ያንገበግባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ግብጾች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥላቻ በብዙ መንገድ ስለሚገልጹት እርሱም ፈተና ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያና የግብጽ የንግድ ግንኙነት እንዲጠናከር ቢያደርጉም ቀንድ ከብት ንግዱ ላይ የተፈጠረውን ደባ ግን መቼም ቢሆን አይረሱትም። ምክንያቱም እነርሱ የሚፈልጉትን ለማድረግ የኢትዮጵያን ስም አጥፍተዋል። ይህ የሆነውም በጋዜጣ ጭምር አውጥተው የኢትዮጵያን ከብትም ሆነ ሥጋ የግብጻውያኑን ከብት እየመረዘ ነው ብለው ማውጣታቸው ነው። በዚህ ሳያበቁም የኢትዮጵያ የቀንድ ከብትም ሆነ ሥጋ እንዳይገባ ተብሎ ከስምምነት ውጪ መወሰኑም አሳዛኝ ነበር።
በዚህ ውሳኔ ምክንያት በሜድሮክ አማካኝነት የገባ ወደ 32 ሺህ ኪሎግራም የሚደርስ ሥጋ እንዳይገባና እንዲበላሽ ሆኗል። ማጣሪያቸው ግን የተሳሳተ ቢሆንም ሊያምኑ አልፈለጉምና ስምምነታቸውን አፈረሱ። ነገር ግን ሥጋው በጣም ተፈላጊ ስለሆነ ነጋዴዎቻቸውን በጎን እየላኩ ያሰሩ ጀመር። ይህንን ያዩት እንግዳችንም ከዚህ በኋላ የግብጽ የቀንድ ከብት ነጋዴዎችና አስመጪዎች በኢትዮጵያ እንዳይገቡ ለሁለት ዓመት ቪዛ እንዳያገኙ አደረጉ። ይህ ደግሞ ግብጽአዊያኑን አስቆጣቸው። ገበሬውም ሆነ ነጋዴው ተነሳ። በዚህም ስምምነቱ ዳግም እንዲታይ ሆኖ መፍትሄ ተሰጠው።
ሌላው ፈተናቸው ከናይል ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ተደራዳሪ መሆናቸውና የተከዜ ወንዝ ሥራ መጀመሩን ተገን አድርጎ የገጠማቸው ሲሆን፤ በእርሳቸው ላይ ክትትል የሚያደርግ ሀይል እስከመመደብ የደረሰ ነበር። ግን እያንዳንዱን ሴራቸውን ቀድመው ስለሚረዱትና ቋንቋቸውን ስለሚችሉት ምንም አይነት የአካል ጉዳት አላደረሱባቸውም። እናም ይህንን የአምስት ዓመት የፈተና ጊዜ አጠናቀው ሲመለሱ ዳግም በውጪ ጉዳይ ነበር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች ጉዳይ የሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን የገቡት። በተጨማሪ የህዳሴ ግድቡ የህግ አማካሪም ናቸው። የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን ኮሚሽን አባል በመሆንም እየሰሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ታይላንድን በቀድሞ ጊዜ አግዛ ስለነበር ታይላንድም ውለታዋን ለመመለስ መልዕክተኛ ስትልክ የህክምና ሴንተር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ፤ የንግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩም ያሳመኑና ኢምባሲ እንዲከፈት የመሩ ናቸውም። ከእነዚህ የሥራ ጊዜያት ተደስቼበታለሁ የሚሉት በብዛት በአማካሪነት የሰሩባቸው ቦታዎች ላይ ውጤታማ መሆናቸውን ነው። በተለይም በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሉት መሻሻሎች የእኔን ውጤታማነት ያሳዩኛል ይላሉ።
የህይወት ፍልስፍና
መልካም ማድረግ፣ በጎ ብቻ አሳቢ መሆንና በሌሎች ደስታ መደሰት መቻል ታላቅነት እንደሆነ ማመን እምነታቸው ነው። ሌላው መስራት፣ ተስፋ ያለመቁረጥና የፊቱን ማየት ለስኬት ያበቃል ብለው ማሰባቸው ሲሆን፤ ነገ ጥሩ ነገር ያመጣልን ይዞ ያለመሰልቸት መስራትም የእርሳቸው አቋምም ፍልስፍናም ነው።
የቤተሰብ ምርጫ የራስም ነው
አብዛኛውን ጊዜያቸውን በማስተማርና በምርምር ጊዜያቸውን በማሳለፋቸው ቶሎ አግብተው ለመውለድ አልቻሉም ነበር። ይሁንና ቤተሰባቸው በጣም ይጨነቅ ስለነበር ብዙ ነገሯ ከእርሳቸው ጋር ይዛመዳል ያሉትን መረጡላቸው። እንዲያገቡም አሳመኗቸው። እርሳቸውም ቢሆኑ በቤተሰቡ ምርጫ እጅጉን ነው የተደሰቱት። ምክንያቱም ገና ሲያዩዋት ወደዋታል። በዚያ ላይ ከዚያው አካባቢ የነበረች ስለሆነ ማንነቷን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህም ተቀብለዋት ባለቤታቸው፤ የኑሮ ጎጇቸው አሟቂ አደረጓት።
ጊዜው ሳይረፍድባቸውም መልካሟን ሚስታቸውን፣ ቤተሰባቸውና ራሳቸውን ለማስደሰትም የሚያስችል እቅድ ዘረጉ። ሁለት ልጆችም ወለዱ። አሁን ሁለቱም ልጆቻቸው ዩኒቨርሲቲ ገብተው እየተማሩ ይገኛሉ። 30 ዓመታትንም በትዳር ሲያሳልፉ በደስታ እንጂ ጸብ እንደማያውቁ አጫውተውናል። ልጆቻቸውም ይህንን ባህሪያቸውን እንደያዙና ከሁሉም ጋር በሰላም ለመኖር እንደሚጥሩም ይናገራሉ።
በቤት ውስጥ በሚያሳልፉበት ወቅት ተማሪም ሆነው፣ አማካሪ፣ አምባሳደርም ሆነው መምህር የኑሮ ስልታቸው አንድ አይነት እንደነበር የሚያወሱት ባለታሪካችን፤ ብዙ ጊዜ መሬት ላይ ተቀምጠው ነገሮችን ማድረግ ይመቻቸዋል። ከቤተሰብ ጋር መሰባሰብም በዚህ አይነት መልኩ የሚመርጡት ነው። በተለይም ባለቤታቸው ልክ እንደእርሳቸው የትምህርት ሰው ስለሆነች ሁለቱም ቤት ውስጥ ሳይቀር ሥራዎችን ይሰራሉ፤ ይመካከራሉም። ለልጆቻቸው መስጠት ያለባቸውንም ጊዜ አይነፍጉም። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ በጣም ጠንካራ የሚባሉ አይነት ናቸው። ምክንያቱም የአደጉበት አካባቢ ይህንን አስተምሯቸዋል። ስለዚህም አዲስ አበባም ቢሆን ያንን ለመተግበር ይጥራሉ። ቤተሰብን በማገዝም ቢሆን በወር ውስጥ ክፍለአገር በመሄድ እንደ አንድ የቤተሰብ ኃላፊ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ያደርጋሉም።
መልዕክት
ኢትዮጵያ ሀብታም አገር ነች። ከድሮው ይልቅ አሁን ሀብታም እንደሆነችም እየተረዳን የመጣንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ማየቱን በሚገባ ከቻልንበት እንዴት ተስማምተን በጋራ መጠቀም እንደምንችል እንረዳለን። ወደተግባሩ ለመግባትም የሚያግደን አለ ብዬ አላስብም። እናም ባለን ሀብት ልክ በመዋደዳችን ተካፍለን አገራችንን እናሳድጋት። አገራችን ላይ በምንሰራው ሥራ ሁላችንም እንከበራለን። መለያየታችን በብዙ ነገር እንድንዋረድ የሚያደርገን መሆኑን ዛሬ መገንዘብ ይገባናል የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ኢትዮጵያ ሌሎች አገራትን ስትረዳ እንደነበር ብዙዎች ምስክር ናቸው። ያንን ሁኔታዋን የምንመልሰው ደግሞ ዘወትር ለማኝ በመሆን አይደለም። በመስራትና በመዋደድ አንድ ሆኖ ለአገር በማሰብ ነው። እናም የኢትዮጵያ የቀደመ ክብር መመለስ በእኛ በጎ ፈቃድና መተባበር ላይ ይመሰረታል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። ስለዚህም ሁላችንም ፈቃደኛ ሆነን በአገራችን ያለው ዋና ችግር ቁጭ ብሎ በመደማመጥ የሚፈታ ነውና ይህንን እናድርግ። በእኛ መካከል መሰረታዊ ልዩነት ሳይሆን አርቴፊሻል ልዩነት ነው ያለው። ይህ ደግሞ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ይፈታል። እናም ሀሳብ እንጂ ጉልበት እንዲበልጥ እድል አንስጥ። አንዱ አንዱን አክብሮ ሀሳቡን ማዳመጥ መቻል ላይ እንስራ ሲሉም ይመክራሉ።
ለሌሎች ማሰብ ሲመጣ የራስም ደህንነት ይጠበቃል። ከዚህ በተጓዳኝ ሀይማኖት የግል እንደሆነ ማመንና በጋራ መስራትን ይህ ነገር እንደማይከለክል ማመንም ያስፈልጋል። እኛ የምንኖረው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር እንደሆነ መገንዘብም ተገቢ ነው። አሁንም የቀደመውን የመተሳሰብ ባህል ተግባራዊ ስናደርግ አንድነታችን እንደሚጠናከር፣ ሰላማችን እንዲመለስ በሚያደርግ መልኩ ያደረግነው መሆን አለበት የማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም