ፍትህ የለም ወይ?ኢ ፍትሀዊ ፍርድ እንደተ ፈረደብኝ መንግሥት ይወቅልን፣የኢትዮጵያ ህዝብ ጩኸታችን ይስማ የሚለው እናቱ በጠና ታማው ሆስፒታል በመተኛታቸው እሳቸውን ወክሎ ቅሬታውን ሊያሰማ ወደ ዝግጅት ክፍላችን የመጣው የወይዘሮ የሺ ልጅ አቶ ዳንኤል ፋንቱ ነው።ወይዘሮ የሺ አቶ አየለ መንገሻን አግብተው ሁለት ልጆች ወልደዋል።ከአቶ አየለ የወለዱት የመጀመሪያ ልጃቸው 28 ዓመቱ ሆኖታል።የአሁኗ ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት አየለም ወይዘሮ የሺ ባይወልዷትም እንደ እናት ተንከባክበው እንዳሳደጓት አቶ ዳንኤል ይናገራል።
ሆኖም አቶ አየለ መንገሻ በጠና ታመው የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ህይወታቸው ያልፋል። የእሳቸውን ሞት ተከትሎም ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ አቶ አየለ ከቀድሞ ባለቤታቸው የወለዷት ልጅ ወይዘሮ ወይንሸት ያሳደገቻትን እናቷን ወይዘሮ የሺን በቦታና በቤት ይገባኛል ጥያቄ መክሰሷን ይገልጻል።
የአቶ አየለ መንገሻ ልጅ ወይዘሮ ወይንሸት በ 24/09/10ዓ.ም አባቴ አቶ አየለ መንገሻ በአዳማ ከተማ ደጋጋ ቀበሌ ውስጥ የቀድሞ ይዞታ 363 ነጥብ 75 ካሬ ሜትር የተሰራው ቤት ውስጥ 141 ነጥብ 75 ካሬ ሜትር ላይ ተሰርቶ የሚገኘው ሁለት ክፍል ቤት በ12/06/89ዓ.ም በተጻፈ የስጦታ ውል የቤት ቁጥር 6020 የሆነውን ሰጥተውኝ በ2008 ዓ.ም የአዳማ ከተማ ደጋጋ ቀበሌ የመሬትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ በስሜ ለክቶልኝ የባለቤትነት ማስረጃ ሊሰጠኝ ሲል ተከሳሽ ወይዘሮ የሺ በጉልበት ይዛብኝ እንዳልጠቀምበት ስለከለከለችኝ በሚል ለአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረቧን ያስታውሳል።
ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት ይህን ብላ ክስ ብታቀርብም ሀቁ ሌላ ነው ።ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት ያቀረበችው ክስ በሀሰት መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው ይላል። በተለይ በ 12/06/89 የተጻፈ የመኖሪያ ቤት ስጦታ ውል ተፈጽሞልኛል ብላ ያቀረበችው የሀሰት መረጃ ነው ።በስሜ ግብር ከፍዬበታለሁ ብላ እንደ ማስረጃ ያቀረበችው ካርኒ በቁጥር 57559 በ12/06/79ዓ.ም የተጻፈ መሆኑ የተባለው መኖሪያ ቤት በስጦታ ተሰጥቶኛል ያለችው በ1989ዓ.ም ሲሆን ግብሩን የከፈልኩት ካለችበት ቀንና ዓመተ ምህረት ጋር የዘጠኝ ዓመት ልዩነት ያለው መሆኑ የሀሰት መረጃ መሆኑን ያሳያል ብሏል።
በስሜ ግብር ከፍዬበታለሁ ያለችውና ካርኒ ላይ ከፈልኩት ያለችው ብር በፊደልና በቁጥር የተጻፈው የብር ልዩነት ያለው መሆኑ የሀሰተኛ መረጃ መሆኑን ያረጋግጣል ብሏል።የስጦታ ውል ነው ያለችውም የሀሰትና በወቅቱ የነበሩን ምስክሮች ያልመሰከሩበትና ውሉም ሟች ባለቤታቸው ያልፈረመው መሆኑን ያወሳል። ክስ የቀረበበትን ሁለት ቤቱንም አሁንም ወይዘሮ የሺ 600 ብር አከራይተው ገቢውን የኑሯቸው መደጎሚያ እንደሚጠቀሙበት ነግሮናል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት እናቴ ከባለቤቷና ከሁለት ልጆቿ አባት ጋር በጋራ ያፈራችው 141 ካሬ ሜትር ያረፈውን ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤት በተጣመመ ፍርድ ለወይዘሮ ወይንሸት ሊወሰን ችሏል ።እናቴም በዚህ የተጣመመ ፍርድ ምክንያት በብስጭትና በእንግልት በጠና ታማ ሆስፒታል ናት የሚለው ወጣት ዳንኤል ፋንቱ፤ወይዘሮ የሺ ቤቱን እያከራዩ ኑሯቸውን ይደጉሙበት እንደነበር ይናገራል።
የአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት ያቀረቡትን የቤቱን ይገባኛል ጥያቄ አይቶ ቢወስንም ተከሳሽ ወይዘሮ የሺ ጉዳዩን ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤት ማለታቸውን ያወሳል። ሁለቱም ፍርድ ቤቶች የአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ የህግ ስህተት ሰርቷል በሚል ለወይዘሮ የሺ ውሳኔ ቢወስኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሁለቱን ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመሻር የአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ማጽናቱ ተገቢም፣ትክክለኛ ፍርድም አይደለም ብሏል።
እናቴም ሆነ ምስክሮች ወይዘሮ ወይንሸት የአቶ አየለ መንገሻ ልጅ መሆኗን አይክዱም የሚለው አቶ ዳንኤል ምስክሮቹ ከሳሽ ቤቱ በስጦታ ተሰጥቶኛል ባለችው የውል ሰነድ ላይ እኛ አልፈረምንም ሲሉ ለወረዳ ፍርድ ቤት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የወረዳ ፍርድ ቤት ምንም ተጨባጭ መረጃ ሳይኖረውና ለእሷ የሚያስፈርድ የህግ አንቀጽ እንኳን ሳይጠቅስ ለከሳሽ ፈረደላት ሲል ቅሬታውን ያቀርባል።
ጉዳዩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ እያለ ኮሮና በመከሰቱ በኮሮና ምክንያት የፍርድ ሂደቱ መጓተቱን የሚያስታውሰው አቶ ዳንኤል ፍርድ ቤቱ በጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የቀጠረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ቀጠሮው ተዛውሯል ተባልን ይላል። ከጥቅምት 30 ጀምሮ ለሶስት ወራት ከቆየ በኋላ ጉዳዩ በቀጥታ በኦንላይን ውሳኔ ይሰጠዋል ተብሎ ስንከታተል ከቆየን በኋላ ሲዘገይ የካቲት ወር ላይ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽህፈት ቤት ጉዳዩ ምን ላይ ደረሰ ብዬ ስደውል ፋይሉ ኦንላይን ገብቷል።ለየሺ ጌታነህ ተፈርዶላት ፋይሉ ተዘግቷል ተብሎ በስልክ ተነገረኝ ሲል ይናገራል።
ሆኖም ለየሺ ጌታነህ ተፈረደ ተብሎ በስልክ የተነገረን ተለውጦ ለወይንሸት አየለ የመጀመሪያው ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ ጸድቋል ተብሎ አፈጻጸም ወጣብን ይላል። እናቴም መሬቱንና ቤቱን አስረክቢ ተባለች።የኢትዮጵያ ህዝብ ይፋረደኝ፣በደላችንን ይስማን፣መንግሥት ኢ ፍትሀዊ ፍርዱን ይወቅልን ሲል ቅሬታውን ያሰማል። ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትም የጻፍነው የቅሬታ ደብዳቤ ጭምር መስጠት አትችሉም ተባልን ተከልከልን ተባረርን ሲል ፍርዱ ከጀርባው ሌላ ጉዳይ እንዳለው እንድንጠራጠር አድርጎናል ሲል አቤት ብሏል።
የፍርድ ውሳኔው ትክክል አይደለም። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሶስቱ ፍርድ ቤቶች የወሰኑት ውሳኔ ሽሮ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የወሰነውን እንዴት ያጸናል ፤እንዴት በኦንላይንና በአካል ሁለት አይነት ተቃራኒ ውሳኔ ይሰጣል ሲል ይጠይቃል።በስልክ ለየሺ ጌታነህ ተወስኗል ተብሎ ተነግሮኛል፤አሁን የኦንላይኑን መረጃ አጥፍተውታል።በስልክ ግን ነግረውኛል።ከተባበረን ቴሌ የስልክ ልውውጡን ቢሰጠን እውነቱን መረዳት ይቻላል ሲል የጥርጣሬቸው ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።
አባቴ ለብቻዬ መሬት ሰጥቶኛል ብላ ያቀረበችው ጉዳይ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።ከሳሽ ያቀረበችው የይገባኛል ጥያቄ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ግብር ገብሬበታለሁ ብላ ያቀረበችው ደረሰኝ በ1979-83ዓ.ም ነው።ሁለተኛ አየለ መንገሻ አባቴ በስጦታ ሰጥቶኛል ያለችው የመሰከሩት ምስክሮች ፊርማችን የእኛ አይደለም ብለዋል።ይህን ለወረዳ ፍርድ ቤት አቅርበናል።ፊርማው የአየለ መንገሻ ፊርማም አይደለም፤ካልሆነ በፎሪንሲክ ይመርመርልን ብንልም የእኛን መቃወሚያ ክርክር ወደ ጎን በማለት ለወይዘሮ ወይንሸት ውሳኔ መስጠቱን ይናገራል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰ/መ/ቁጥር181721 ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም ጉዳዩን ማየት መጀመሩን ይገልጻል።በዚህ መሰረትም ከሳሽ በተከሳሽ ላይ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ለክርክሩ መነሻ የሆነው የይዞታ ለእኔ ይገባኛል በማለት ያቀረበችው ክስ ተቀባይነት ቢያገኝም በይገባኛል ሰሚው የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሽሮ ፤በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሜ ችሎት ውሳኔው ሳይለወጥ መቅረቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመ መሆኑን ስህተቱ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ አቤቱታ አቅርበዋል ይላል።ይህን መነሻ አድርጎም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጥቅምት ወር በ 24/2013ዓ.ም ጉዳዩን ማየት መጀመሩን ያወሳል ማስረጃው።
በመጀመሪያ ደረጃ ጉዳዩን ያየው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የምስራቅ ሽዋ ዞን የአዳማ ከተማ ፍርድ ቤትም ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት አየለ በአዳማ ከተማ በደጋጋ ቀበሌ 141 ነጥብ 75 ካሬ ሜትር ሁለት ክፍል ቤት በላዩ ላይ ያረፈውን አዋሳኞቹን በክሱ የተገለጸው በ12/06/1989ዓ.ም በተጻፈ የስጦታ ውል ከሟች አባቴ የተሰጠኝንና እያከራየሁ የምጠቀምበትን ቤት መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ በስሜ ለክቶልኝ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊሰጠኝ ሲል ተከሳሸ ወይዘሮ የሺ ቤቱን ስለያዘች ሊፈጸምልኝ ስላልቻለ ቤቱን ለቃ እንድታስረክብልኝ ውሳኔ እንዲሰጥ ሲሉ መጠየቃቸውን ያትታል።
ተከሳሽም ወይዘሮ የሺ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት መልስ ክርክሩ ምክንያት የሆነውን ቤት ከሳሽ በስጦታ አግኝቼዋለሁ የምትለው በሀሰት ማስረጃ የቀረበ ሲሆን ከክሱ ጋር ተያይዞ የቀረበው ደረሰኝ ስጦታው በ1989ዓ.ም የተሰጠኝ ነው እያለች ደረሰኝ ላይ ያለው ማስረጃ ደግሞ በ1979 ዓ.ም የተቆረጠ መሆኑን የሚገልጽ ነው።የስጦታ ውል ከመደረጉ በፊት በስሟግብር ተከፍሏል በማለት በሀሰት በተቀናጀ በመሆኑ ስጦታ አለ ቢባል እንኳን ከባለቤቴ ጋር በጋራ ያፈራነው ንብረት ብቻውን መስጠት ስለማይችል ክሱ ውድቅ እንዲደረግ መጠየቃቸውን መረጃው በመጥቀስ ያብራራል።
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ከሳሽ በክሷ እንዲለቀቅ የጠየቀችው የቤት ቁጥር 6020 አግኝታዋለች ወይ?ወይስ አላገኘችውም? የሚል ጭብጥ በመያዝ የግራና የቀኙን ምስክሮች ሰምቷል ይላል።ሁለቱ ምስክሮች አንደኛው ቤቱ በከሳሽ ስም እንደሆነ አውቃለሁ፣ሁለተኛው ምስክር ደግሞ የከሳሽ አባት በህይወት እያለ አንድ ቤት በከሳሽ ስም አስመዝግቤያለሁ ብሎ ነግሮኛል በማለት መመስከራቸውንም ያስታውሳል።
ለክርክሩ መነሻ የሆነው ንብረት የከሳሽ መሆኑን የደጋጋ ቀበሌ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ተጠይቆ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቦታና ቤት በከሳሽ ስም በቤት ቁጥር 2060 የተመዘገበና ከሳሽ ቤት ጋር የሚዋሰን በመሆኑ መገለጹ እንዲሁም ከቀረበው የግል ማህደር ስጦታ ውል ስምምነት በ 06ቀን 2006ዓ.ም የተመዘገበ ደረሰኝ በደረሰኝ ቁጥር 57559 በ12/06/1979ዓ.ም ከሳሽ ለቦታው ብር ሁለት ሺህ አምስት መቶ( 2500) የከፈለች ስለመሆኑ የተረጋገጠ በፍትሀ ብሄር ቁጥር 1206 መሰረት ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቦታን ሁለት ክፍል ቤት ተከሳሽ ለከሳሽ እንድትለቅ በማለት ወስኗል።
ተከሳሽም ውሳኔው ፍትሀዊነት የጎደለው ነው በማለት ውሳኔውን በመቃወም የይግባኝ ቅሬታቸውን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት በማቅረባቸው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን አስቀርቦና ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በ1979 ግብር ስለመክፈሏ ያቀረበችው ማስረጃ ቅደም ተከተል ይጋጫል? ወይስ አይጋጭም ለክርክሩ መነሻ የሆነው ንብረት በስጦታ መሰጠቱን የከሳሽ ምስክሮች አረጋግጠዋል ወይስ አላረጋገጡም ለአመልካች የተደረገው ውል ህጋዊ ነው? ወይንስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዞ ግራ ቀኙን አከራክሯል።ሆኖም ስጦታ የተሰጠው የተባለው በ1989 ዓ.ም ሲሆን ስጦታ ተቀባይ የገበረችበት ካርኒ የደረሰኝ ቁጥር 75559 በሆነ በ 12/06/1979 ዓ.ም የቀድሞ የእሸት ቦታ በነበረበት መሆኑን፣በአባቷ ተደረገ የተባለው ስጦታ ደግሞ በ 12/06/1989 ዓ.ም. መሆኑን እየገለጸ ከሳሽ ስጦታውን አስቀድሜ ገብሬበታለሁ የምትልበት ሁኔታ ስለሌለና የቀረበው ማስረጃ እርስ በእርሱ የሚጋጭና የሚጣረስ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ውስኗል።
እንዲሁም በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው የምስክር ቃልም ሲመዘንም በ 2/06/1989ዓ.ም በስጦታ ውል ላይ አሉ የተባሉ ምስክሮች ያልፈረሙ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በሌላ በኩል ተከሳሽ የስጦታው ውል ሲደረግ የስጦታው ሰጪ ባለቤት አቶ አያሌው መንገሻ የከሳሽ አባት አለመሆናቸውን ባላስተባበሉበትና ተጠሪ ከንብረቱ መብት እንደሌለ ባልተገለጸበት ሙሉ ንብረት የባል ንብረት ተደርጎ ስጦታ መደረጉ የስጦታን መስፈርት የሚያሟላ አይደለም።እንዲሁም ንብረቱ በከሳሽ ስም ተመዝግቦ በመገኘቱ ብቻ ባለቤት ስለማያደርጋት ከሳሽ( ወይዘሮ ወይንሸት) ለተከሳሽ (ለወይዘሮ የሺ) እንድትለቅ በማለት በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ሊሻር ይገባዋል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህን ውሳኔ በመቃወምም ከሳሽ( ወይዘሮ ወይንሸት) ቅሬታቸውን ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ይግባኛቸው ተቀባይነት ሳያገኘ ቀርቷል። ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም የስር ፍርድ ቤት ሳይለወጥ እንዲጸና መወሰኑን አቶ ዳንኤል ይናገራል።
ሆኖም ካሣሽ ውሳኔውን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደገና ለማየት መወሰኑን ይገልጻል።በዚህ መነሻነትም የከሳሽ አቤቱታ በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ አከራካሪው ቤት ለከሳሽ በስጦታ የተሰጠና ስጦታው ባፈረሰበት ሁኔታና እንዲሁም ቤቱ የባልና ሚስት ነው ብሎ በስር ፍርድ በማስረጃ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ከሳሽ ቤቱ አይገባትም የተባለበት አግባብነት ለማጣራት ሲባል መረጃውን መመርምር መጀመሩን ያወሳል።
በተደረገው የጭብጥ ክርክርም ተከሳሽ ወይዘሮ የሺ ጥቅም 12 ቀን 2012ዓ.ም መልስ አቅርበዋል።በዚህም መሰረት በ 12/06/1989ዓ.ም የተጻፈው የስጦታ ውል ውሉ ከመጻፉ ከ10 ዓመት በፊት በ1979ዓ.ም በስሜ ግብር ገብሬያለሁ ያለችውን ደረሰኝ ዋናውን ወይም ኦርጅናሉን ሊቀርብ ያልቻለ ሰነድ ማስረጃ በመሆኑ ተቃውመው ተከራክረዋል። የስጦታ ውሉም በሟች ባለቤቴ ያልተፈረመ ህጋዊ ውል ባለመሆኑ በፎሪሲንክ እንዲመረመርልኝና የግብር ደረሰኙ በአዳማ ከተማ መሬት ኤጀንሲ ገንዘብ ገቢ የተሰበሰበ ስለመሆኑ እንዲመረመርልኝ። እንዲሁም ውሉ በህግ መስፈርት ያሟላ ቢሆን እንኳን መሬቱና ቦታው የጋራችን በመሆኑ እኔ ሳልፈርም ሊጸድቅ እንደማይችል ክርክር አቅርቤያለሁ ይህን በማለፍ በስጦታ ውሉ መሰረት ይለቀቅ በማለት የሰጠውን ውሳኔ ትክክል አይደለም ብላ አቤት ማለቷን ያብራራል።
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከሳሽ በጹሁፍ ያቀረበችውን የስጦታ ውል ኦርጅናሉን ማቅረብ ባለመቻሏና በውሉ ላይ ያሉ ምስክሮች እኛ ውሉን አናውቅም፤ በውሉ ላይ ያለው ፊርማ የእኛ አይደለም ማለታቸውን ከሰጡት የምስክርነት ቃል አረጋግጦ ውሉ የውል መመዘኛ የማያሟላና ክርክር የተነሳበት ቤት በተከሳሽ ግቢ ያለና አንድ የመግቢያ በር ብቻ ያለው ስለሆነ ከሟች ጋር የጋራ ንብረት እንጂ ለከሳሽ በስጦታ የተላለፈ ስላልሆነ የስር ፍርድ ውሳኔ መሻሩ የተፈጸመ የህግ ስህተት ስለሌለ የሰጡት ውሳኔ ይጽና ሲል ውሳኔ እንዳስተላለፈ ነግሮናል።
የሶስቱን ፍርድ ቤቶችና የከሳሽና የተከሳሽን የግራ ቀኙን ክርክር አየሁት ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሜ ችሎት ደረጃ በጭብጥነት ተይዞ ሊመረመር የሚገባው እያከራከረ ባለው ይዞታ በ1979 ዓ.ም በከሳሽ ስም የተገበረበት እና በ1989 ዓ.ም ሟች ለከሳሽ ስጦታ ማድረጋቸው የሚጋጭ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን መመርምሩን የፍርድ ውሳኔ ባስተላለፈው ሰነድ ላይ ገልጧል።
ከሳሽ የሚያከራክረውን ይዞታና ቤት የአባቴ በህይወት እያለ በ1979 ዓ.ም ሃያ አምስት ብር (25.00.00) ግብር በስሜ ተከፍሏል።በኋላም በ1989 ዓ.ም የስጦታ ውሉን አስመዝግቧል በማለት የምትከራከርና በስር ፍርድ ቤትም የስጦታ ውሉ መቅረቡን ተረድተናል ይላል።እንዲሁም በሰው ምስክሮችም የከሳሽ አባት ይዞታውን በከሳሽ ማስመዝገቡን የነገራቸው ስለመሆኑ አንድ የጋራ ምስክራቸው ቀርበው መመስከራቸውን ፤ የሚያከራክረው ቤትና ቦታም ከሳሽ እያከራየች የምትጠቀምበት መሆኑን ገልጻ የተከራከረች ሲሆን ማህደሩ ቀርቦ እያከራከረ ያለው ይዞታና ቤት በከሳሽ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ቤቱም የተለየ የቤት ቁጥር ያለው ስለመሆኑ ጭምር ተረጋግጧል ይላል በ 22/6/2013ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው የውሳኔ ሰነድ ።
ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ይገባኛል በሚል ሲከራከሩበት የነበረው ይዞታ በአመልካች ስም ግብር መገበሩ በቀረበው የግብር ደረሰኝ ከመረጋገጡም በላይ በስር ፍርድ ቤት የሚያከራክረውን ቤትና ይዞታ ማህደር አስቀርቦ ተመልክቶ አረጋግጧል። ከዚህ በመነሳትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚረዳው በከሳሽና በተከሳሽ በኩል የሚያከራክረው ይዞታና ቤት በ1979ዓ.ም በከሳሽ ስም የተመዘገበና በግብር ካርኒም የተቆረጠለት ሆኖ እያለ የስር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከሳሽ አይገባትም ሲል የወረዳ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ መሻሩና በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶችም የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ስህተትን ሳያርሙ ማለፋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ሆኖ በመገኘቱ ሊሻር ይገባዋል ሲል የውሳኔ ፍርድ ሰጥቷል።
በውሳኔውም በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ሰበር ሰሜ ችሎት በመለያ ቁጥር 311877 በ17/10/2011 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ፣የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣በመ.ቁ 308490 በ12/10/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ እና የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/32658 በ 4/10/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ ተሸሯል ሲል አስፍሯል።በአንጻሩ በአዳማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ11279 በ 02/07/2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ ጸንቷል ሲል ፍርዱን ሰጥቷል።
እኛ ከሳሽ ወይዘሮ ወይንሸት ቤቱና ቦታው አባቴ አቶ አየለ በስጦታ ተሰጥቶኛል ብላ ያቀረበችው መረጃ የሀሰት ነው በሚል በመረጃ የተደገፈ ክርክር ብናቀርብም ይህን ጉዳይ በጥልቀት አጤነው በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ሰበር ሰሜ ችሎት፤የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰኑትን ውሳኔን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሻሩ ፍትህ አዛብቶብናል ሲል የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይፋረደን ሲል ብሶቱን ገልጧል ።
እናቴ የራሷገቢ የላትም በዚያ ላይ በሽተኛ ናት የሚለው አቶ ዳንኤል፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በሀሰተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ፍርድ ነው። የምስክሮችም እኛ አልፈረምንም ብለው ቃላቸውን ለወረዳው ፍርድ ቤት ሰጥተው እያለ ለውሳኔው እነሱን እንደ ውሳኔው ማጠናከሪያ መጠቀሙ ፍትህ ምን ያህል እንደምትነጠቅ ያሳያል ብሏል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013