የቀድሞው ቤንች ማጂ ዞን በከፍተኛ የማዕድን ሃብት ክምችቱ ይታወቃል፡፡ ዞኑ ምዕራብ ኦሞና ቤንች ሸካ ዞን ተብሎ ከተከፈለ ወዲህ በተለይ አዲሱ የቤንች ሸካ ዞን የተፈጥሮ ሀብቱ አሁንም እንዳለ ነው ፡፡ ወርቅን ጨምሮ በርካታ ለኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ የመአድን ክምችት በስፋት ከሚገኙባቸው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥም በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በዞኑ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት እንዳለ በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም በጥናቱ ልክ ወደ ስራ እንዳልተገባ ይነገራል፡፡
የቤንች ሸካ ዞን ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዮርዳኖስ በየነ እንደሚናገሩት ዞኑ ከዚህ በፊት በቤንች ማጂ ስር እያለ ወርቅ በቤሮና ማጂ ወረዳዎች ላይ በባህላዊ መንገድ ይመረት ነበር፡፡ በአዲሱ የቤንች ሸካ ዞን ስድስት ወረዳዎች ላይ ደግሞ ፅህፈት ቤቱ በማዕድን ፍለጋ ዙሪያ የአቅሙን ያህል ጥናቶችን አካሂዷል፡፡ ባካሄደው ጥናት መሰረትም በጉራፈርዳ ወረዳ ወርቅ ያለባቸው ቦታዎችን መለየት ተችሏል፡፡ የክልልና የፌደራል የማዕድን ዘርፍ ባለሞያዎችም ቦታው ላይ በመገኘት የወርቅ ክምችት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ይሁንና በታቀደው ልክ ስራዎች ባለመሰራታቸው ወደ ስራ ገብቶ ወርቅ ከማምረት አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡ በዚሁ አዲሱ ወረዳ ወርቅ ከማምረት አኳያ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባም ሁኔታዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይም በጀት ሲሟላ ተጨማሪ የማስፋፊያ ጥናቶች ተደርገው የማምረቱ ስራ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ ማዕድናትም በዞኑ የሚገኙ ሲሆን ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም ባለው ግዜ ውስጥ ጥናቶች ተካሂደው አስራ አራት የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ማዕድናት በዞኑ እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ የማዕድናቱ ናሙና ተወስዶም የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተሰርቷል፡፡
በክምችት ደረጃ ግራናይት፣ ክሮማይትና ኳርትዝ ማዕድናት በዞኑ እንደሚገኙ በጥናቱ ተለይቷል፡፡ በነዚህ ማዕድናት ላይ ለመስራት ያመለከቱ ኩባንያዎችም አሉ፡፡ ይሁንና ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል፡፡ ከሶስቱ ማዕድናት ውጪም ሌሎች ማዕድናትም በዞኑ እንደሚገኙ ይገመታል፡፡ የማርብል ማዕድንም በሳይት ደረጃ ናሙና የተወሰደ ቢሆንም ማርብል ስለመሆኑ ገና የጂኦሎጂካል ሰርቬይ አልተደረገበትም፡፡
እንደ ሃላፊው ገለፃ ከከበሩ ማዕድናት አኳያ ከወርቅ ውጪ በዞኑ አማታይስት የተሰኘ ማዕድንም እንዳለ አንድ ኩባንያ ጥናት አድርጎ ከፍተኛ ክምችት እንዳለው አረጋግጧል ይላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጥናት ከተደረገባቸው በከፊል ከከበሩ ማዕድናት ውስጥ ፍሎራይትና ጋርኔት ማዕድናትም ይገኙበታል፡፡
በተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ማዕድናትም ድንጋይና አሸዋ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን በስፋትም አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው። በሰሜን ቤንች፣ ሸካና ሼ ቤንች ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ማዕድን ክምችት አለ፡፡ በደቡብ ቤንች አንድ ወረዳ ላይም ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ማዕድን ክምችት እንዳለ በጥናት ታውቋል፡፡
በዞኑ በኮንስትራክሽን ማዕድናት ማምረት ስራ በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ወጣቶችም በአሸዋና በድንጋይ ማምረት ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዞን ደረጃ በዚሁ የኮንስትራክሽን ማዕድን ማምረት ስራ 642 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡
ወጣቶቹ በዚህ የስራ ዘርፍ ለስድስት ወራቶች ከሰሩ በኋላ ለሌሎች ወጣቶች በመልቀቅ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል፡፡ በአነስተኛ ደረጃ የሚመረቱ የግራናይትና የማርብል ምርቶች አነስተኛ ማሽኖችን የሚጠይቁ በመሆናቸው በቀጣይ በነዚህ ማዕድናት ወደ ማምረት ስራ ሲገባ ተጨማሪ የስራ እድል ለወጣቶች ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሃላፊው እንደሚገልፁት ከዞኑ የማዕድን ዘርፍ ጋር በተያያዘ ዋነኛ ማነቆዎች ስትራቴጂክና ትኩረት የሚሰጥ አመራር ያለመኖር፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማነስና የበጀት እጥረት ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያም የዞኑ የማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ማዕድናትን ያጠናው በራሱ ውስን ሀብትና የሰው ሃይል ነው፡፡ ሰፊ ጥናቶችን ለማከናወንም ፅህፈት ቤቱ የካፒታል እጥረት አለበት፡፡ ከክልል ወደ ዞኑ እየወረደ ያለው ካፒታልም ለጥናቱ እንዲውል የመጣ በጀት አይደለም፡፡ ከዚህ ውጪ ከሰው ሃይል አኳያ የማዕድን እውቀት ያለው ባለሞያ ታችኛው መዋቅር ድረስ ባለመኖሩ ባለሞያዎች ከዞን ወርደው ለመስራት ተገደዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያም ፅህፈት ቤቱ ባለው የሰው አቅም ከአመራር ጀምሮ ታች ወርዶ ለመስራት ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ከበጀት እጥረት አኳያም ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተገኘው በጀት አንዳንድ ግዜ በባዶም ጭምር ያለሎጀስቲክ በቁርጠኝነት ባለሞያዎች ታች ወርደው ይሰራሉ፡፡
የፅህፈት ቤቱ ጥረት እንዳለ ሆኖ ከበጀት፣ ከሰው ሃይል አደረጃጀትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልን ከማሟላት አኳያ የሚታዩ ችግሮች በፌደራልና በክልል ቅንጅት የሚፈቱ ከሆነ የዞኑን ማዕድን ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ የማዋል እድል ይኖራል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013