
አዲስ አበባ፡- የዘንድሮ የፋሲካ በዓል የገበያ ሁኔታ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱን በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃና አራት ኪሎ የበዓል ወቅት ገበያዎች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ።
ዝግጅት ክፍሉ ቅኝት ባደረገባቸው በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃና አራት ኪሎ አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎችና ሸማቾች እንደተናገሩት፣ የበዓል ወቅት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የገበያ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ አሳይቷል ሲሉ በአራት ኪሎ ያገኘናቸው በግ፣ ዶሮና ፍየል ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ አሻግር ሸዋታጠቅ ሰሜን ማዘጋጃ ያነጋገርናቸው ነጋዴ ጋሻው በላይ ተናግረዋል፡፡ በሁለቱም አካባቢዎች ተመሳሳይ ዋጋ መኖሩንም ዝግጅት ክፍሉ ለመገንዘብ ችሏል፡፡
እንደ ነጋዴዎቹ ገለጻ፤ የሸኮ ዶሮ ዝቅተኛው ዋጋ 500 ከፍተኛ 600 ብር፣ የአበሻ ዶሮ እንደ መጠናቸው ከ350 እስከ 450 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ፍየል ከሰባት ሺህ እስከ 13 ሺህ ብር ሲሆን፤ የበግ ዋጋ ደግሞ ከአራት ሺህ እስከ ሰባት ሺህ 500 መግባቱን ነው አቶ አሻግርና አቶ ጋሻው ያረጋገጡልን፡፡
ይህም ካምናው የበዓል ገበያ ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ማሳየቱን ያስታወሱት ነጋዴዎቹ፤ በ2012 ዓ.ም የፋሲካ በዓል የሸኮ ዶሮ ዝቅተኛ ዋጋ 300 ትልቁ 450 ብር፣ የሃበሻ ዶሮ ከ250 እስከ 300 ብር መሸጡን አስታውሰዋል፡፡ ፍየል ከአምስት ሺህ እስከ 10 ሺህ፣ በግ ከሦስት ሺህ 500 እስከ ሰባት ሺህ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡
የበግ ግብይት ሲያካሂዱ ያገኘናቸው አቶ ሙሉነህ አምሳሉ ዘንድሮ የፋሲካ ገበያ ዋጋ መጨመሩ በግና ፍየል በግለሰብ ለመግዛት አዳጋች እንደሆነባቸው ጠቁመዋል። በመሆኑም አንድ የደብረብርሃን ሙክት በግ በሰባት ሺህ አምስት መቶ ብር በጋራ ከጓደኛቸው ጋር ለመካፈል ወስነው መግዛታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች የሃበሻ ዶሮ እንቁላል ከአምስት ብር ከ50 ሳንቲም እስከ ስድስት ብር፣ የፈረንጅ ዶሮ እንቁላል ከአምስት ብር ከ75 ሳንቲም እስከ ስድስት ብር እየተሸጠ መሆኑን ወ/ሮ ነኢማ አብዱና ነገዴ ሰላም ብሩ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የቅቤን ዋጋ በወተት ቤት መሸጫ መደብሮች የገበታ ቅቤ በኪሎ እስከ አምስት መቶ ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የዓመት በዓል የባዛር ገበያዎች ለጋ ቅቤ ከአራት መቶ እስከ 380 ብር እየተሸጠ መሆኑን ወ/ሮ ሮዛ ወርቁ ጠቁመዋል፡፡
ቅቤም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውሰው፤ በ2012ዓ.ም የፋሲካ በዓል የበሰለ ቅቤ 280፣ ለጋ ቅቤ 290 እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ አራት ኪሎና ፒያሳ አካባቢዎች በባዛር ገበያዎች የጤና ዘይት በሊትር አንድ መቶ አስር ብርና የአምስት ሊትሩ ዋጋ ደግሞ አምስት መቶ 35 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013