
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሰባት ሺ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከ26 መንግሥታዊ ካልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተፈራረመ፡፡
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ትናንት በተከናወነበት ወቅት የቢሮው የሴፍቲኔት ቀጥታ ድጋፍና ኑሮ ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው አበራ እንዳታወቁት፤ ቢሮው ሰባት ሺ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከ26 መንግሥታዊ ካልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱ 590 ሚሊዮን ብር የተመደበለትና በ21 ወራት ጊዜ ውስጥ የሚከናወን መሆኑን ያስታወቁት አቶ እንዳሻው፣ ከጎዳና ይነሳሉ ተብለው የታሰቡት ሰዎች ምንም ዓይነት ድጋፍና አድራሻም የሌላቸው እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡
በሴፍቲኔት ፕሮግራም አማካኝነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ተረጂዎቹ በአራት የተመደቡ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ እንደሻው፤ የመጀመሪያዎቹ ምድቦች ዕድሜያቸው እስከ 18 ዓመት የሚደርሱ 669 ሕፃናት፣ ሁለተኛዎቹ ሕፃናት የያዙ ሦስት ሺህ 530 እናቶች ናቸው ብለዋል።
በሦስተኛ ምድብ የሚገኙት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 59 ዓመት ድረስ የሆኑ ሁለት ሺ 394 ዜጎች፣ እንዲሁም አራተኛ ምድቦች ከስልሳ ዓመት በላይ የሆኑ 428 አረጋውያን እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከዓለም ባንክ በተገኘው ድጋፍ በተከናወነው የሴፍቲኔት ፕሮግራም 179 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ 66 ሺህ ያህሉ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል፡፡
የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎች ምንም ዓይነት ሥራ መስራት የማይችሉና በየወሩ ለኑሯቸው መሻሻል በቀጥታ ገንዘብ እየተከፈቸው የሚደጎሙ ናቸው ያሉት አቶ ተፈራ፣ በዚህ ዓመት ብቻ በከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛና ማህበራዊ ቢሮ አማካኝነት ስምንት ሺ 826 ዜጎችን ከጎዳና የማንሳት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ አማካኝነትም የዕለት ምግብ ማግኘት ለማይችሉ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሚሆኑ በአምስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ ቋሚ የምገባ ማዕከላት ተገንብተዋል፤ ዜጎች በነዚህ ማዕከላት ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013