
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት 51 ሚሊዮን 671 ሺ 617 ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አያሌው ሀብተማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት 9 ወራት 82 ሚሊዮን 164 ሺህ 90 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 51 ሚሊዮን 671 ሺ 617 ብር መሰብሰብ ተችሏል። አፈጻጸሙ የእቅዱን 62 ነጥብ 88 በመቶ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 5 ሚሊዮን ብር ቅናሽ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
አቶ አያሌው እንዳብራሩት፣ በእነዚህ ወራት በበጀት ዓመቱ ሊሰበሰብ የታቀደውን 70 በመቶ መሰብሰብ ነበረበት። የከተማ አስተዳደሩ ከ85 በመቶ በላይ ገቢውን የሰበሰበው በቱሪዝም አገልግሎት በሚሰጡ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች፣ መኪና አከራዮች፣ የሥጦታ ዕቃ አቅራቢዎችና በሌሎችም ከቱሪዝም ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ከሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ነው። ለእነዚህ ተቋማትና ግለሰቦችም በኮቪድ 19 ምክንያት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሥራ በማቆማቸው የሥራ ግብር ገቢ የቀነሰ በመሆኑና የታክስ ገቢም ባለመኖሩ እቅዱን ማሳካት ሳይቻል ቀርቷል፡፡
በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ከ2013 በኋላ ያሉትን ውዝፍ ገቢዎች በቶሎ ኦዲት አድርጎ ለመሰብሰብ፤ የሊዝ ገቢዎችን የመሰብሰብና ከመጪዎቹ በዓላት ጋር ተያይዞ ከስጋ ቤቶች፣ ከሕንፃ መሣሪያዎችና ከመሳሰሉት ተቋማት ጠንከር ያለ የደረሰኝ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ፤ እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢን ከፍ በማድረግ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አቶ አያሌው ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ አያሌው ገለጻ፤ አብዛኞቹ የከተማዋ ሆቴሎች ስሪታቸው ጎብኝዎችን መሰረት ያደረገ ነው። አሁን ላይ ደግሞ የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የአገር ውስጥ ጎብኝዎችንና አካባቢውን መሰረት ያደረገ የሆቴል አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ፣ የሥጦታ ዕቃን ሲሸጡ የነበሩም በሸቀጣ ሸቀጥና በሌሎችም የአካባቢው ማህበረሰብ ሊጠቀምባቸው በሚችልባቸው የንግድ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ለማስቻል ከነጋዴው ማህበረሰብ ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይደረግ ጎብኝዎች ብቻ የሚጠበቁ ከሆነ ገቢያችን ብቻ ሳይሆን የንግድ ድርጅቶች ህልውናና ቀጣይነትም ችግር ውስጥ የሚገባ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ከቱሪዝም ውጭ ባሉ ሌሎች ዘርፎች ላይም እንዲሰማሩ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ኮሮናን በተመለከተ በተለያዩ አገራት ክትባት እየተሰጠ በመሆኑ በቀጣይነት ሁኔታው እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፤ የቱሪስት ፍሰቱ ወደ ላሊበላ እንዲመጣ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ቦታውን የማስተዋወቅ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013