
አዲስ አበባ፡- የድሬዳዋ ከተማ በሁለንተናዊ መነቃቃት ላይ እንደምትገኝ የድሬዳዋ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ዘርፍ አደረጃጀትና የከንቲባው አማካሪ አቶ ሮቤል ጌታቸው ገለፁ፡፡ ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመለከቱ ፡፡
አቶ ሮቤል በተለይ ለወጋሕታ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ ድሬዳዋ ከኢንዱስትሪ ጋር የቆየ ትስስር ያላት ከተማ ናት፣ ኅብረተሰቡም የዚህ ባህልና ልምድ ያለው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የብዙ ኢንቨስመንቶች መዳረሻ እየሆነች ነው።
የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ተከትሎ ብዛት ያላቸው ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ እየተገነቡ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፣ ይህም ለከተማዋ ወጣቶች ሥራ በመፍጠር ረገድ ከፍያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለከተማዋም መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ኮቪድ 19 ፈተና ከሆኑባት አንዷ ድሬዳዋ ከተማ እንደሆነችና ይህን ተከትሎ ብዙ የህክምና ማእከላትና የማቆያ ስፍራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሆነ የጠቆሙት አማካሪው፤ ኮቪድ 19 በድሬዳዋ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል። ጫናውን ለመቀነስም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደተሰሩ አስታውቀዋል፡፡
የኮቪድ 19ን ወረርሽኝ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ በመከላከል ምርታማነት ማስቀጠል ይቻላል በሚል ወደ ሥራ መገባቱን ያመለከቱት አቶ ሮቤል፣ እስካሁን ባለው አፈጻጸምም ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከባብረው በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ያመለከቱት አቶ ሮቤል፣ በቀድሞ የፖለቲካ ሁኔታ በሃይማኖትና በብሔር ግጭቶች በመቀስቀስ ሰፊ የሚባል የሰላም መደፍረስ እየተስተዋለ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ፀጥታን በሚመለከት ሰፊ ሥራ መሰራቱን ያስታወቁት አቶ ሮቤል፤ በዚህ ሂደት ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላት በመለየት የተሻለ የጸጥታ መዋቅር በመገንባትና ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይቶች በማድረግ ውጤት የተገኘበት ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡
ምርጫን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ብዙ ምርጫዎች ተደርገዋል፤ ይሁን እንጂ ነፃ፣ ፍትሃዊና በብዙሃኑ የታማኝነት ችግር እንደነበረባቸው የገለፁት አቶ ሮቤል፤ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ድሬዳዋ ላይ ብልፅግናን ጨምሮ ዘጠኝ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ ያስታወቁት አቶ ሮቤል፣ መራጩ ሕዝብ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ካርድ በስፋት እየወሰደ እንደሚገኝና ከዚህ በፊት ከነበረው እንቅስቃሴ አሁን የተሻለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ከተማዋ ከለውጡ በኋላ የምትተዳደርበትን ቻርተር ለመቀየር ከሕዝብ ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመው፣ የከተማዋን እድገት በሚያፋጥን መልኩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሬዳዋ ከለውጡ በፊት በሁለት ፓርቲ ስትመራ የቆየች ከተማ እንደሆነች ፣ ከለውጡ በኋላ ግን አንድ ውህድ ፓርቲ ስለተፈጠረ የከተማችን ጉዳይ በሚመለከት በአንድነት የምንወስንበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል። ይህም በከተማዋ ላይ መነቃቃት መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡
ትርሓስ ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013