
አዲስ አበባ፡- ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስቀረት እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡ ለዚህ ተግባር ሲባል የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎች ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን በግዢና በድጋፍ እንዲያሟሉና ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የሰው ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰገድ ሳሙኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ውጭ አገራት ያደርጉት የነበረውን የውጭ ጉዞ ለማስቀረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ዜጎች ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጭ በሚያደርጉት ጉዞ ብዙ ውጣ ውረዶች እንዳሉበት ያመለከቱት አቶ አሰገድ ፣ ለሕክምና የሚወጣውም የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በአብዛኛው ሕክምና ለማግኘት ወደ ባንኮክ፣ ታይላንድ፣ ቱርክና ሕንድ እንደሚጓዙ ገልጸዋል።
በውጭ አገር የሚሰጡ ሕክምናዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦትና በአጠቃቀም ብቁ ባለሙያዎች የሚፈልጉ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ አሰገድ፣ በዚህ ምክንያት ዜጎች ሕክምናውን በአገር ውስጥ ለማግኘት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከአጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የአገር ውስጥ ሕክምናን ለማዘመን፣ የሕክምና ቴክኖሎጂ እውቀትን ለማሳደግና አቅርቦቱን ለማመቻቸት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የሕክምና ቴክኖሎጂ አቅርቦትና የአጠቃቀም ክህሎት ውስንነትን ለመፍታት በቀጣይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡
በውጭ አገር የሚሰጡ ሕክምናዎች በአገር ውስጥ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ጥረት ዜጎች ሳይጉላሉ በአገር ውስጥ ሕክምና ማግኘት እንደሚያስችላቸው የጠቆሙት አቶ አሰገድ፣ ለዚህም በመንግሥትና በግል ሆስፒታሎች የሥልጠና፣ የሕክምና፣ የግብዓት አቅርቦት የማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለልምድ ልውውጥ ከውጭ ይመጡ የነበሩት የበጎ ፈቃደኛ እስፔሻሊስት ሐኪሞች በኮቪድ ምክንያት መቋረጡን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ ከ14 ከፍተኛ የሕክምና ተቋማት ጋር በመተባበር ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት አቅምን የመገንባት ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ተግባር ሲባል የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎች ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን በግዢና በድጋፍ እንዲያሟሉና ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚያስችል የትብብር ደብዳቤ መጻፉን አመልክተዋል፡፡
ሲልክ ሮድና ኮሪያ ሆስፒታል ትብብር ከተደረገላቸው መካከል ለአብነት ጠቅሰው፤ ሆስፒታሎቹ የኮሮናንና ሌሎች ሕክምናዎችን በነፃ በመስጠት ችግሩን እየተጋሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ አሰገድ ማብራሪያ፤ ቀድሞ የጭንቅላት ቀዶ ጥገናና የነርቭ ሕክምናን በአገር ውስጥ የማግኘት ዕድል ዝቅተኛ ነበር። አሁን ላይ ግን ሕክምናው በአገር ውስጥ በስፋት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ሕክምናውን በውጭ አገራት ለማግኘት የነበረውን ውጣ ውረድና የገንዘብ ወጪ ማስቀረት እንዳስቻለ አስታውቀዋል፡፡
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013