
አዲስ አበባ፦ ባለፉት አምስት ዓመታት የቀነሰውን የቁም እንስሳት የውጪ ንግድ ገቢ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ ።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቁም እንስሳት ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሥነት በላይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት 462 ሺ የቁም እንስሳት ወደ ውጪ በመላክ በየዓመቱ በአማካኝ 75 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ተችሏል።
ገቢው ከቀደሙት ዓመታት ይገኝ ከነበረው የውጪ ምንዛሪ ገቢ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል ያሉት አቶ ደሥነት፣ ገቢው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ በዓመት በ13 በመቶ፤ በመጠን በሰባት በመቶ ቀንሷል ብለዋል። በ 2012 ዓ.ም ለውጭ ገበያ የቀረበው የቁም እንስሳት ቁጥር ከ 2008 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ30 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ዋና ዋና የቁም እንስሳት በግ፤ ፍየል፤ ግመልና የዳልጋ ከብቶች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደሥነት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካኝ በየዓመቱ 300 ሺ በግ መላኩን አስታውቀዋል።
ወደ ውጪ የሚላከው የዳልጋ ከብት ቁጥር በተለይ ከዓመት ዓመት ቅናሽ እያሳየ መምጣቱን ያመለከቱ አቶ ደሥነት ፣ በ2012 ዓ.ም ወደ ውጪ የተላከው የዳልጋ ከብት ቁጥር ከ2008 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ 70 በመቶ ቅናሽ እንዳለው ገልፀዋል።
ግመል እና ፍየል የውጪ ንግድ በተመሳሳይ መልኩ ቅናሽ ማሳየታቸውን ፤ በ 2012 ዓ.ም በአማካይ አንድ ግመል በ609 ዶላር መሸጡን፣ ይህም በ 2008 ዓ.ም ከተሸጠበት ሲነፃፀር በ16 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የጋማ ከብት ዋጋም የ 12 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
ለችግሩ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ከነዚህ መካከል ዋነኞዎቹ እየተስፋፋ የመጣው የኮንትሮ ባንድ ንግድ፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የቁም እንስሳት አቅርቦት እጥረት እና እንደ ዘመናዊ የእንስሳት ማቆያ ያለ ያልዳበረ መሰረተ ልማት መኖር፣በቂ የእንስሳት ጤና አገልግሎት አለመኖር እንዲሁም የገበያ መዳረሻ ሀገራት ውስን መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ውጭ ንግድ እንቅስቃሴ ዋና ዋና መዳረሻ ሀገራት ሳውዲ አረቢያ፣ የመን፣ ጂቡቲ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ ሲሆኑ ከነዚሁ አገራት ጋር የሚደረገው የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በተለያዩ ችግሮችና ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆሉ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።
የቁም እንስሳት የውጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦትንና የእንስሳት ጤናን ማሻሻል፣ የአገር ውስጥ የእንስሳት ግብይትን ማጠናከር፣የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ ኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥ ንግድን በተጠናከረ መንገድ መታገል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የገበያ መዳረሻዎችን በበቂ ሁኔታ ማስፋት፣የሎጂስቲክ አገልግሎት ውስንነት መፍታት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ደሥነት፣ የቅንጅታዊ አሠራርን በየደረጃው ማጠናከር፣ የግብይት ተዋንያን አቅም መገንባት፣ የግብይት ሥርዓትን ማዘመንና ሰንሰለቱን ማሳጠር እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013