
የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ነጫጭ ልብሳቸውን ለብሰው የጸሎተ ሐሙስ በዓልን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ለማክበር ተሰብስበዋል። በዕለቱም እንደ ወትሮው ሁሉ ስግደቱ፣ ጸሎቱ እና ሌላውም ሥነ ሥርዓት ይከናወናል። መቅደሱ ውስጥ የሚጨሰው እጣንም በጣም አስደሳች ነው ።
ፓትርያርኩን ጨምሮ ጳጳሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት እስር በእርሳቸው እንዲሁም የምዕመናኑን እግር የማጠብም ሥነ ሥርዓትም ያከናውናሉ። ይህም የሚሆነው ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የደቀመ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትህትናና ፍቅር ለማመላከት መሆኑን ቤተክርስቲያኗ ትናገራለች። በጸሎተ ሐሙስ በቤተክርስቲያን ይህንን ዓይነት ድባብ ሲኖረው ሁሉም ምዕመን በቤቱ ደግሞ ባቄላና ስንዴን ደባልቆ በመቀቀል (ጉልባን ) በማዘጋጀት ዕለቱን ያከብራል።
የዘንድሮው በዓልም በቤተክርስቲያኗ ሥነ ሥርዓት መሠረት የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተከብሯል። በዚህ ዕለት የሚከናወነው የፍቅርና የትህትና ምልክት የሆነው የህጽበተ እግር ሥነ ሥርዓትም በቤተክርስቲያኗ አባቶች ተፈጽሟል።
የዕለቱን በዓል በማስመልከትም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት፣ ፍቅር አንድነትና ትህትና የክርስቲያናዊ ሕይወት መገለጫዎች ናቸው። ምዕመኑ የክርስቶስ ፍቅር አለኝ ካለ በዚህ መንገድ መሄድ ይገባዋል።
ፍቅር ካለ ሁሉም ነገር አለ ሰላማዊ በሆንን መጠንም የክርስቶስ መሆናችን ይገለጻል ለእኛ የሚጠቅመውም እርሱ ነው ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ እርስ በእርሳችን መፋቀር መዋደድ ከቻልን እግዚአብሔርን በውስጣችን እናነግሳለን፤ ይህ ካልሆነ ግን በአገራችን የምናየውን ዓይነት መጥፎ ድርጊት ውስጥ እንገባለን፣ ድርጊቱ ደግሞ የክርስቲያን መገለጫው አይደለም፤ ክርስቶስም አላዘዘም በመሆኑም ፍቅር በልባችን ሊነግስ ይገባል ብለዋል።
እንደ አገር ሰላማችንንና ፍቅራችንን ጠብቀን ልንኖር ይገባል ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ይህንን ማድረግ ከተሳነን የእግዚአብሔር በረከት ስለሚርቅ ለአገርም ለሕዝብም መልካም እንደማይሆንም አስታውቀዋል።
እንደ ፈጣሪ ትሁት መሆንን ትህትናን ፍቅርን ለሌሎች ወገኖቻችን ማሳየት አለብን ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ እራሳችንን ከፍ ከፍ በማድረግ ሌላውን በተጫንን መጠን ከክርስቶስ አስተምሮ ከመውጣታችንም በላይ ከእግዚአብሔር የምናገኘውን በረከትም የሚያሳጣን መሆኑን አመልክተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ያናገርናቸው መሪጌታ አባተ አሰፋ በበኩላቸው፣ በዓሉ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቀን ለዓለም ሕዝብ ሁሉ ትልቅ ትምህርትና ስጦታ የሆነውን ፍቅርንና ትህትና ያስተማረበት ቀን ነው ብለዋል።
ፈጣሪ ሁሉ በእጁ ሲሆን ለእኛ ለሰው ልጆች ድህነት በረከት እንዲሁም ምን መሆን እንዳለብን ለማስተማር ብሎ ዝቅ በማለት የደቀመዛሙርቶቹን እግር አጥቦ ትህትናን አሳይቶናል እኛም የክርስቶስ ነን የምንል ከሆነ ይህንን ትህትና ለአንድ ጸሎተ ሐሙስ ቀን ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ሁሉ እየተገበርን ማሳየትና በረከቱን ማግኘት እንደሚገባን አመልክተዋል።
ይህንን ትህትና ወደጎን ብለን በወገኖቻችን ላይ ለመጨከን ብሎም ለጥፋትና ለተንኮል ቦታ ከሰጠን የክርስቶስ ሳንሆን ከመቅረታችንም በላይ ለመጥፊያችንም መንገድ እንደማመቻቸት መሆኑን አብራርተዋል።
«በዚህ ቀን ልንመለከተው የሚገባው ትልቁ ነገር እያንዳንዳችን እንፋቀር ዘንድ የታዘዝነው ነው፤ በመሆኑም ተፋቀሩ ተባበሩ አንድ ሁኑ ነው የተባልነው፤ በመሆኑም የቅድስናን የደግነትን የፍቅርና የአንድነት ሥራን መስራት ይገባናል፤ ትውልዱም በዓል ከማክበር ባሻገር የፈጣሪን ትዕዛዝ በአግባቡ በመፈጸም አገርን ከጥፋት መታደግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ናትናኤል ገብረማርያም፣ ዕለቱ ክርስቶስ መላው ክርስቲያን በትህትና እርሱን እንዲመስል የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ተጨባጭ ትምህርት ያስተማረበት ቀን እንደሆነ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ግን በተለይ ኢትዮጵያውያን ክርስቶስ ያዘዘንን እየሆንን ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ? አይደለም አንደበታችንና ተግባራችን ተለያይቷል፤ በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስ ያሳየንን ትህትና እግር መተጣጠብ ቀርቶ እርስ በእርሳችን የምንገዳደል ሆነናል፤ ክርስቶስ ይህንን አላስተማረንም፤ አሁንም የክርስቶስን አስተምሮ እየዘነጋን የዳቢሎስን መንገድ እየተከተልን ነው፤ ከዚህ ተግባር ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013