
አዲስ አበባ፦ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምንፈልግ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ የሥልጣን ሽግግር እና ቅቡል መንግሥት መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምንፈልግ ኃይሎች በተቻለ መጠን አውዱ ለዚያ የሚመች መሆኑን አውቀን በመሥራት ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ የሥልጣን ሽግግር እና ቅቡል መንግሥት መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን አውቆ ከዛሬ ጀምሮ ማንን ለምን እንደሚመርጥ እያሰበ እንዲቆይ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምርጫውን ተከትሎ ድንጋይ የሚወረውር ካለ ኅብረተሰቡ በጋራ በመቆም መከላከል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ከምርጫ በስተቀር የሚሸጋገር፣ የሚደራደር መንግሥት አይፈጠርም። ማንም ሰው ሥልጣን መያዝ የሚችለው በምርጫ ብቻ ነው። ይህን አውቆ የሚፎካከር ኃይል ሃሳብ ካለው፣ አደረጃጀት ካለው፣ ሃሳቡን ሸጦ፣ ሕዝብ አሳምኖ እንዲመረጥ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ሃሳቦች ሁሉ ቅዠቶች ናቸው፤ አይሆኑም ብለዋል፡፡
ሃሳቦቹ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ ያደናቅፉ ይሆናል እንጂ አይሳኩም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ዴሞክራሲ አብቦ እንዲያፈራ፣ ተፎካካሪዎችም፣ ሕዝብም፣ መንግሥትም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርገው ምርጫ ሰላማዊ፣ ሁሉም የሚፎካከሩ ኃይሎች እኩል መድረክ የፈጠረ፣ በሃሳብ የላቀ፣ በተግባር የበቃ፣ በልምድ የተካነ፣ ቃል ከመግባት ሳይሆን ሠርቶ ለማሳየት የቆረጠ፣ ሕዝቡን የሚያደምጥ፣ ሕዝቡን የሚያከብር፣ የማይሰርቅ ኃይል ሥልጣን የሚይዝበት ምርጫ እንዲሆን እንፈልጋለን።
በምርጫው ያሻችሁን ምረጡ ፣ ግን ሰላምን አስቀድሙ፣ በዚህ ምርጫ ያሻችሁን ምረጡ፤ ግን እኩል መድረከ መፈጠሩን አረጋግጡ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲገባ የማይፈለግ ኃይል መኖር የለበትም፤ ለኢትዮጵያ የቀና፣ ኢትዮጵያን አገለግላለሁ የሚል እኩል መብት የሚያገኝበት ምርጫ እንዲሆን ከልባችን እንፈልጋለን፤ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው ሲሉም በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013