
አዲስ አበባ፡- የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ ክለሳ ሥራ ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ፡፡
አቶ ንጉሱ ጥላሁን እየተከለሰ ባለው ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመጨረሻ ምዕራፍ ውይይት ትናንት በተካሄደበት ወቅት እንደገለፁት፤ በትግበራ ላይ ያለው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ በ1997 ዓ.ም የተዘጋጀና በ2003 ዓ.ም በከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር የተከለሰ ነው ። የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ አገራዊ ባለሀብቶችን ለማፍራት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠንና የዕድገት ፍትሃዊነትን ለማስፈን ያለመ ነው።
ስትራቴጂው የትርጓሜ ክፍተት፣ የአካታችነት እና ምሉዕነት ችግር፣ መደበኛ ያልሆነው ዘርፍ መግዘፍ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አነስተኛ መሆን፣ ከድጋፍ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከፍተኛ የማደግ አቅም ላላቸው ኢንተርፕራይዞች የተለየ የድጋፍ አሰራር አለመኖር፣ የብድርና ፋይናንስ አቅርቦት አሰራሩ ክፍተት ያለበት መሆን፣ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ አለመሆን፣ ዘርፉ በተለያየ ተቋማት መመራቱ እና የክትትልና ግምገማ ሥርዓቱ ውስንነት ያለበት በመሆኑ ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ መከለስ አስፈልጓል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ፤ አዲሱ ስትራቴጂ በሥራ ላይ ያሉ ኢንተርፕራይዞች ራሳቸውን በማጠናከር፣ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችም በመመስረትና ወደ ሥራ በመግባት ለአገራዊ ኢኮኖሚው የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ በመጨመር እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የሥራ አጥነት ምጣኔን የመቀነስ ዓላማን ያነገበ ነው።
በተጨማሪም የተሻለ የኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግር እንዲኖርና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ምርታማነታቸው እንዲጨምር፣ የፋይናንስና የገበያ ተደራሽነትን በማሻሻል፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ አቅርቦትና ጥራትን በማሳደግ፣ በኢ-መደበኛ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች ወደ መደበኛ ሥርዓት እንዲገቡ በማድረግ የድጋፍ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
በስትራቴጂው የተጠኑትንና የመፍትሄ ሃሳብ የተቀመጠላቸው አስተዳደራዊ አሠራሮችን የማቅለል፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ተደራሽነትንና የአገልግሎት ጥራትን የማሻሻል፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ትብብርን የመፍጠር፣ የንግድ ልማት አገልግሎቱ ዒላማውን የጠበቀና ጥራት ያለው የማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።
የፋይናንስ አቅርቦት ሥርዓቱን ውጤታማና ቀልጣፋ የማድረግ፣ የብድር ዋስትና አማራጮችን የማስፋፋትና የማሻሻል፣ የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ አስተዳደር አቅም የማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ውጤቶች ተደራሽነትን በተቋማዊ ቅንጅት የማሳለጥ ሥራዎች የዘርፉን መዋቅር በማጠናከርና የፈፃሚና ድጋፍ ሰጭ ተቋማትን አቅም በመገንባት ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡
የስትራቴጂ ክለሳው ከጥር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ሲሆን እስካሁን ድረስ የነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ ጥናት፣ ከዓለም አቀፋዊ ልምዶችና ተሞክሮዎች ማነፃፀሪያ፣ እንዲሁም በዘርፉ እውቀት ካላቸው ባለሙያዎችና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት እንደሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013