
አዲስ አበባ፡- በዓላትና ምርጫ መቃረባቸውን ተከትሎ የፀጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡ ፡ከበዓላትና ከመደበኛ እንቅስቃሴዎች ጋር በተገናኘ ለሚገጥሙ የጸጥታ ስጋቶች ኅብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቀረበ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሁሉም አካባቢ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን መጪው የትንሳኤ በዓልና ምርጫ በሰላም እንዲከናወኑ ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየሰራ ነው ፡፡
6ኛው አገራዊ ምርጫ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዝግጁነት እንዲኖር ለማስቻል ለሁሉም የፖሊስ አካላት በሦስት ዙር ሥልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ሥልጠናው ባለፉት ምርጫዎች የፖሊስ ሚና ምን ነበረ? በጊዜው የነበሩ ችግሮችስ ምን ነበሩ? ቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች ኮሚሽኑ ምን መስራት አለበት? ምንስ መስራት የለበትም የሚለውን መሠረት ያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል። ሁሉም የጸጥታ አካላት በዚህ ልክ ዝግጁ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአገር ደረጃ እያንዳንዱ የፖሊስ አካል በቂ ሥልጠና ሳይወስድ በምርጫ የጸጥታ ማስከበር ሥራ ላይ መሳተፍ የለበትም በሚል ጥብቅ መርህ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ በምርጫ የሚሳተፉ የፖሊስ አካላት ምርጫ ጣቢያ የሚሰራቸውን ሥራዎች የሚገልፅና ማድረግ የሚገባውንና የማይገባውን የሚያብራራ መመሪያ ለሁሉም የፖሊስ አካላት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። መመሪያው በህትመት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ከህትመት በኋላም ለሁሉም የፖሊስ አካላት እንደሚሰራጭ ገልጸዋል፡፡
እንደ ኮማንደር ፋሲካው ማብራሪያ ከትንሳኤ በዓል ጋር በተያያዘ አስቀድሞ በየአካባቢው፣ በንግድ ትርዒት ስፍራዎች፣ ሰዎች በብዛት በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎችና በዕምነት ስፍራዎች ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡በተለይ የገበያን ግርግር ተጠቅመው ወንጀል እንዳይፈጸም ፖሊስ በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል ፡፡
ከአንድ ወር በፊት የኅብረተሰቡ የፀጥታ ስጋት ከፍተኛ እንደነበር ያመለከቱት ኮማንደር ፋሲካው፣ ይህን የሕዝብ ስጋት ለማስወገድ ጠንካራ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ከማረሚያ ቤት የወጡና በሌሉበት ውሳኔ ተወስኖባቸው የነበሩ ግለሰቦች፤ በግድያ፣ በዝርፊያ፣ በመኪና ስርቆትና በሌሎች ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩት ወንጀለኞችን በመያዝ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም የሕዝቡ ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ መሆኑን ያመለከቱት ኮማንደር ፋሲካው፣ ባሳለፍነው አንድ ወር ውስጥ በመዲናችን የተፈጸሙ የመኪና ስርቆትና የግድያ ወንጀል አለመኖሩ ወንጀሎች ለመቀነሳቸው ምስክር ነው ብለዋል፡፡
ወንጀሎች ስለቀነሱ አንዘናጋም፤ ይበልጥ በማጠናከር ሕዝቡ ያለምንም ስጋት በነፃነት እንዲንቀሳቀስ፣ ሲወጣ ሲገባ ምን ያጋጥመኛል እንዳይል ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በስፋት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡
ፀጥታውን ለማስፈን በቀጣይ ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ፖሊስ ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት ኮማንደሩ፤ ከበዓላትና ከመደበኛ እንቅስቃሴዎች ጋር በተገናኘ ለሚገጥሙ የጸጥታ ስጋቶች ኅብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት መተባበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
991ን ነጻ የጥሪ አገልግሎት በመጠቀም ጥቆማ ቢሰጥ በሁሉም ክፍለ ከተማዎች ላይ የሚገኙ የፖሊስ አካላት አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት ይችላሉ፡፡ መጪው የትንሳኤ በዓል የሰላም፣ የደስታ፣ ወንጀል የሌለበትና ሰላም የሆነ በዓል እንዲሆን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013