
አዲስ አበባ፡- በበዓላት ወቅት መብራት እንዳይቆራረጥ ግብረኃይል አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ዘንድሮ በስርቆትና በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱን ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ባዩ ለገሰ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በቀጣይ በሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላትና በምርጫ ሂደት ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ እንዲቻል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡
ግብረኃይሉ በዋና ሥራ አስፈፃሚው የሚመራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ባዩ፤ ዲስትሪክቶችንና ማዕከላትን ያቀፈ፣ በእያንዳንዱ አገልግሎት መስጫ በተዋረድ ባሉ አደረጃጀቶች የተዋቀረ ነው ብለዋል፡፡
ለበዓላት ብቻ ሳይሆን በመደበኛው ሁኔታም ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማዳረስ በከተማ ደረጃ የአረጁ መስመሮችን የመቀየር፣ በአየር ላይ የተዘረጉ መስመሮች መሬት ውስጥ የመቅበር፣ የረገቡ ሽቦዎችን የመቀየር፣ የእንጨት ምሰሶ ወደ ኮንክሬት ፖል የመቀየር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ከበዓላት ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዳይፈጠር በሁሉም አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአስቸኳይ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በማሟላት ስምሪት መደረጉንም ጠቁመዋል ፡፡
በከተማ ደረጃ በሚከናወኑ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ቁፋሮ በሚከናወንበት ወቅት በመስመሮች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ በኬብል ላይ የሚፈፀም ስርቆት፣ ፖሎች በተሽከርካሪዎች መገጨትና መሰል ችግሮች ለኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ምክንያት መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
በቦሌ አራብሳና በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በ30 ምሰሶች ላይ የተዘረጋ አንድ ሺ 550 ሜትር ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ኬብል ስርቆት በመፈፀሙ ምክንያት 20 ሺ ቤቶች አገልግሎቱ እንደተቋረጠባቸው ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ በስርቆትና በተለያዩ የኃይል መቆራረጥ ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማጣቱንም ያመለከቱት አቶ ባዩ ፣ ኬብሎቹ በውጭ ምንዛሬ የሚገዙ እንደመሆናቸው በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮቹ በማርጀታቸው ምክንያት በዝናብ ወቅት ኮንታክት የሚፈጠርበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት በመሬት ተቀባሪ መስመሮች የመዘርጋት የእንጨት ምሰሶዎችን ወደኮንክሬት መቀየር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በበዓላት ወቅት ወፍጮ ቤቶችና ኢንዱስትሪዎች አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ፣ ኅብረተሰቡም ጭነት የሚበዛበትን ወቅት ለይተው ከፍያሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ሥራዎችን ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት በመስራት የሚፈጠረውን የኃይል መጨናነቅ በመቀነስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013